Tuesday, December 17, 2024
ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ነው!
ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው!
ከዚህ በላይ የሚታየው ስእል የጣኦት አምላኪዎች እንጂ የሌላ የማንም ስእል አይደለም። በጣኦት አምላኪዎቹ ልብ ሰይጣን ያስቀመጠው ትርጉም እንደምንገምተው ልጅ እግሩ ሰው የኢየሱስ፣ ሽማግሌው ደግሞ የአብ መሆኑ ነው። በእግዚአብሔር መንግስት ሦስት ምስሎች በአኀዝ የሚቀመጡበት ወይም በወጣትና በሽማግሌ የሚመሰልበት መለኮታዊ ማንነት የለም። ከእግዚአብሔር ያልሆነ የሰው ልብ ያመነጨው ስእል ሁሉ ከተመለከ፣ ከተወደሰ እሱ ጣኦት ነው የሚባለው። “እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥”
(ዘዳግም 4፥16)
አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ምሕረትና ይቅርታ የአዳም ልጆች እንዲያገኙ ለማንም ኪዳን አልሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጆች የምሕረትን ኪዳን ሞታችንን ከሞተልን ከኢየሱስ በቀር ለፍጡራን እንደሰጡ አንድም ቦታ ተጽፎ አናገኝም። “ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።” ነው የተባለው።
(ይሁዳ 1፥25) እውነቱ ይህ ከሆነ የመዳን ኪዳን ያገኘነው እንዴት ነው?
ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ፣ የሥርየት ቃል ድምዳሜ ወይም ፍጻሜ ማለት ነው። ምሕረት የማይገባው ጥፋተኛ፣ በምሕረት አድራጊው እቅድ ከእዳ፣ ከበደል፣ ከወንጀል ነጻ አድርጌሃለሁና የነጻነትህን አዋጅ በዚህ ደብዳቤ አረጋግጬልሃለሁ ብሎ የሚሰጠው የአርነት ሰነድ ነው። የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ወደሆነው ዝርዝር ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ራሱ "ኪዳን" የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል የሚለውን ለመመልከት እንሞክር!
ውል በሁለት ተዋዋይ ወገኖች መካከል በቃል ወይም በፅሑፍ የሚደረግ አሳሪ ሕግ ነው። በውሉ ላይ ተዋዋይ ወገኖችን መብትና ጥቅም በማካተት የሚደርሱበት ስምምነት ሲሆን መሠረታዊው የውል አስፈላጊነት ጥቅምንና መብትን ለማስከበር መርህ አድርጎ የሚነሳ ቢሆንም ውል ሁልጊዜ አዋጭ ወይም ዘላቂ ላይሆን ይችላል። ውል በዓለማችን ላይ እየተሠራበት ያለው የተዋዋይ ወገኖች አሳሪ ስምምነት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ኪዳን በጣም የተለየ ነው። የእግዚአብሔር ኪዳን ወይም (Covenant) በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የሚደረግ የአቻ ስምምነት አይደለም። ኪዳን ማለት በጥሬ ትርጉሙ ውል:ስምምነት ቢሆንም ኪዳኑ በምድር ላይ ሰዎች እንደሚያደርጉት በሁለት እኩል ተዋዋይ ወገኖች መካከል እንደተደረገው አይደለም። በውል ሰጪ(በእግዚአብሔር) እና በውል ተቀባይ (በሰው ልጆች) መካከል የተደረገው ኪዳን እግዚአብሔር መብትና ጥቅሙን ለማስከበር ወይም ከሰው ልጆች የሚያገኘው የተለየ መብት እንዲጠበቅለት የተደረገ ኪዳን ሳይሆን እግዚአብሔር በባህርይው ፍቅር ስለሆነ የጠፋውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ በክንዱ ተጠብቆ እንዲኖር ሲል እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለፀበት መንገድ ነው። ሌላውን ወገን የሚጠቅም ኪዳን ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚገባው ኪዳን አምላክነቱን አስገድዶ ለመጫን ሳይሆን ጌትነቱን ለተቀበሉት ሁሉ ከአምላክነቱ በረከት እንዲትረፈረፍላቸው ከፍቅሩ የተነሣ የሚደረግ ኪዳን ነው።
“በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።” (ኢሳ 63፥9)
እግዚአብሔር አዳምን የፈጠረው ማንንም ሳያማክር ከአምላካዊ ክብሩ ሕያውነት እንዲካፈልና በዘላለማዊ ፍቅሩ እንዲኖር ነው።
“ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። (1ኛ ዮሐ 4፥10)
ለአዳም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያሟላለት በአዳም ጥያቄ አልነበረም። እንዲያውም አዳም የተፈጠረው የአምላክን ባሕርይ ተካፋይ እንዲሆን፣ ክብሩ በሱ እንዲታይ በአርአያውና በምሳሌው ነው። እግዚአብሔር ከፈጠረውና ገዢ እንዲሆን በፍጥረቱ ላይ ካሰለጠነው ከአዳም ጋር የገባው ኪዳን ከሰጠሁህ እልፍ አእላፍ ፍጥረት መካከል ይሄን አንዱ ከበላህ ሞትን ትሞታለህና እንዳትበላው የሚል ትእዛዝ ነበር። አዳም ሞትን የሞተው ባልተነገረውና በማያውቀው ነገር ሳይሆን ራሱ ሞትን በመምረጡና የእግዚአብሔርን ድምጽ በመጣሱ የተነሳ ነው። ይህ የመጀመሪያ ኪዳን የፈረሰው ውል ተቀባዩ ውሉን በማፍረሱ ስለሆነ ውሉ የሚያስከትለው ቅጣት በአፍራሹና በልጆቹ ላይ ሞት ተግባራዊ ሆኗል።
ከአዳም ውል አፍራሽነት በኋላ እግዚአብሔር ከአዳም ልጆች ጋር የገባው ሌላኛው ኪዳን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በኮሬብ ተራራ ነው። ልቅሷችሁንና ጩኸታችሁን ሰምቻለሁ ከባርነት አወጣችኋለሁ፣ ወተትና ማር የምታፈስ ሀገር አወርሳችኋለሁ ብሎ በታላቅ ድንቅና ተአምራት ከግብጽ ከወጡት እስራኤላውያን ጋር ያደረገው ኪዳን ኮሬብ ላይ ተገልጿል።
(ዘጸ19፣4—5) ❝በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤❞ ብሏል። ይህ ኪዳን ዘላለማዊው ኪዳን እስኪፈጸም ድረስ በምድራዊ ርስት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከሌሎች ለይቶ የሚያቆይበት የኪዳን ሕግ ተሰጥቶ ነበር።
እግዚአብሔር ከመረጠው፣ ራሱ ከሚመራው፣ የተሻለ ሀገር አወርስሃለሁ ካለው ከዚህ ሕዝብ ጋር ኪዳን አደረገ። ይህ ኪዳን እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ከአህዛብ የሚለይበት፣ ደግሞም ከእግዚአብሔር ጋር በድምፅና በመልእክት የሚገናኝበት የሕግ ኪዳን ነበር። በአድርግና አታድርግ የተሠጠው የኪዳኑ ስምምነት በተጻፈው የጽሌ ሠሌዳ ላይ እንዲህ የሚል ተፅፎበት እንመለከታለን።
1/ ከኔ በስተቀር ሌሎች አማልክት አታምልክ፣ 2/ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ፣
3/ የሰንበትን ቀን አክብር፣ 4/ እናትና አባትህን አክብር፣ 5/ አትግደል፣ 6/ አታመንዝር፣
7/ አትስረቅ፣ 8/ በሀሰት አትመስክር፣
9/ የባልንጀራህን ገንዘብ አትመኝ፣
10/ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚል የኪዳን ሕግ ነበረ። ይህ ኪዳን ይጠበቅ ዘንድ የሚከናወንበት መንገድ የኃጢአት፣ የደኅንነት፣ የሚቃጠል መስዋዕት በማቅረብና ትዕዛዛትን በመጠበቅ ነበር።
“እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤”
( ዘዳግ 7፥12)
ይህ ሕግና ትዕዛዛቱ ምድራዊ ሥርየትን ያስገኝለታል እንጂ አዳም ትቶ ወደወጣበት ገነት መልሶ የሚያስገባ አልነበረም። ይህንን በእግዚአብሔር ቁጣ የተዘጋውን የገነት በር መልሶ በመክፈት አዳምንና ልጆቹን ማስገባት የሚችል ከሰው ልጆች አንድም ሰው ስላልነበረ በሌዊ ወገን በሚሾሙ ካህናት በኩል ደም በመርጨት ጊዜያዊ ሥርየትን እያገኙ እስከአማናዊ የተሻለ ኪዳን ድረስ ለመቆየት ችለዋል። ምክንያቱም ሰው በጥፋት ሥራው የተረገመ በመሆኑና ምድርም በተረገመው ሰው ምክንያት የተረገመች በመሆኗ ከሰው ልጆች መካከል ከእርግማን ነጻ የሆነ ሰው ስላልነበረ ዘላለማዊ ድነት ማስገኘት የሚችል አንድም ጻድቅ አልነበረምና ነው።
“አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤”
(ዘፍ 3፥1)
እግዚአብሔር ሌሎች ንዑሳን ኪዳናት ከወደዳቸው ጋር ኪዳን አድርጓል። ከኖኅ ጋር በቀስተ ደመና (ዘፍ9፣11-12)፣ ከሙሴ ጋር (ዘጸ34፣27)፣ ከአብርሃም ርስቱን ሲሰጠው(ዘፍ15፣28)፣ የቁልፈታቸው ግርዛት እንዲወድቅ (17፣11)፣ ከይስሐቅ (ዘፍ17፣19)፣ ከያዕቆብ (ዘፍ35፣10-15)፣ ከዳዊት ጋር (ኤር33፣17) ኪዳን አድርጓል። ይህ ኪዳን በዘመናቸው እግዚአብሔርን ለታዘዙበትና ለፈፀሙበት ፍቅር የተነገረላቸው የመኖር ኪዳን እንጂ የአዳምን በደል የሚሽር ወይም ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ ኪዳን አልነበረም።
“የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።” (ዘዳ 28፥9)
እግዚአብሔር የምወደው ልጄ... ያለው ከሰማይ ከወረደው በስተቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የተባለለት ባለሙሉ ሥልጣን ዘላለማዊ ሊቀካህን፣ በደሙ በሰማያዊቷ መቅደስ የገባ ኢየሱስ ብቻ ነው። ሞትን አሸንፎ በሞት የተሸነፉትን ሁሉ ከምርኮ ነፃ ማውጣት የቻለ ከኢየሱስ በቀር ማንም የለም። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ እንዲህ ሲል አስረግጦ ይነግረናል።
(ኤፌሶን 4፣8-10) ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።
ይህ ኪዳን፣ አዲስ ኪዳን፣ የሕይወት ኪዳን ይባላል። አብ በአዳም ልጆች ላይ የነበረውን ቁጣ ያበረደበት፣ የተወደደ መስዋዕት፣ በደሙ በኩል ዘላለማዊ የማዳን ሥርየት የተፈፀመበት ኪዳን ይህ ነው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”
( ዮሐ 6፥47 )
ከዚህ ኪዳን ውጪ እግዚአብሔር ሌላ ኪዳን የለውም።
“ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤” (ሮሜ 5፥10)
ከዚህ የምሕረትና የይቅርታ ኪዳን ውጪ እግዚአብሔር የተቀበለውና ደስ የተሰኘበት ሌላ ኪዳን የለም ብቻ ሳይሆን ይሄንን ኪዳን ማሟላት የሚችል ከሰው ልጆች መካከል አንድም ሰው አልነበረም። ቢኖርማ ኖሮ ኢየሱስ ሰው ሆኖ መወለድ ባላስፈለገው ነበር። ስለዚህ ለሰው ልጆች የተሰጠ የምሕረት ኪዳን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ኪዳነ ምሕረት የለም! ይህንን ኪዳን የሚተካ፣ ማዳን የሚችል፣ አብ የወደደው መስዋእትና የምወደው ልጄ ያለው ከኢየሱስ በቀር ማንም ስለሌለ ኪዳነምሕረት በማለት በቅድስት ማርያም በኩል ዘላለማዊ ድነት አገኛለሁ በሚል ተስፋ ወደ ማርያም የሚለምን ሁሉ ከሕይወት ኪዳን የጎደለ፣ እግዚአብሔር የሰጠውን የመዳን ኪዳን ያቃለለ ሰው ነው። ድንግል ማርያም ቅድስትና ብፅእት እንጂ እግዚአብሔር አብ የምሕረቴን ኪዳን በሷ በኩል አድርጌአለሁ ብሎ ኪዳን የሰጠበት ሁኔታ የለም።አንዳንዶች በማርያም ጉዳይ ስለጥንተ አብሶ (የቀደመ በደል) እያነሱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲያደርጉ ይታያሉ። ይሄ የማይረባ ክርክር ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ድረስ ለሰው ልጆች ሁሉ ገነት ተዘግታበት ይኖር ነበር። በገነት የሌለ ሰው ሁሉ በደለኛ ነው። በሕይወት አኗኗሩ ጻድቅና ንፁህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከገነት ውጪ ስላለ በደለኛ ነው። በአጭሩ በኪሩብ የምትጠበቀው ገነት የተዘጋበት የሰው ልጅ ሁሉ በደለኛ ነው።
እንዲያውም ብፅእት ማርያም ራሷ ነፍሷ ጌታን እንደምታከብር፣ መድኃኒቷም እንደሆነ እንደዚህ በማለት መስክራለች። “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” (ሉቃስ 1፥47)
እግዚአብሔር የብሉይን (አሮጌውን) ኪዳን ከተመረጡት ከእስራኤላውያን ጋር፣ አዲሱን ኪዳን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ካመኑት ጋር የሕይወትን ኪዳን አድርጓል። ሌላ ከማንም ጋር የማዳን፣ የሕይወት ኪዳን አላደረገም።
“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”
(ዮሐ 14፥6) ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ነው!