ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።
(ክፍል ሦስት) ጳጉሜን 2/2005 ዓ/ም1/ የኢንዱስትሪው አብዮት በሚፈልገው የሰው አቅምና በሚወስደው ረጅም የሥራ ጊዜ ሳቢያ የክርስቲያኖች አእምሮ ያለእረፍት መባከኑ፤
ይህ ዕረፍት የለሽ ረጅም የሥራ ጊዜና የአእምሮ መባከን በአውሮፓውያን ዘንድ የነበረውን
የአማኝነት መንፈስ እየሸረሸረና ከእምነቱ ጋር የነበረውን ቀረቤታ በርቀት ይመለከት ዘንድ እንዳቃረበው ሁሉ በኢትዮጵያችን ውስጥ
እየተስተዋለ ይገኛል። በ1942 ዓ/ም ገደማ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ወደ 18 ሚሊዮን አካባቢ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚያን ዘመን በአንድ ካሬ ኪሎሜትር ውስጥ በማእከላዊ ስሌት 7 ሰው ሲኖር
ዛሬ በተመሳሳይ ስፋት ውስጥ 82 ሰው መኖሩ የሚያመላክተው ሰባት ሰው ይካፈል የነበረውን ፍጆታ 75 ትርፍ ሰው እየተሻማ በመገኘቱ
ማንም እንደጥንቱ ዛፍ ስር ቁጭ ብሎ ጠላ በዋንጫ እየሞላ፤ የጨዋና የባሪያ ዘር እየቆጠረ፤ የድንጋይ ዳቦ ነበር ዘመንን ተረት እየተረተ
መቀጠል እንደማይቻል የሚታየው ለውጣዊ ተግዳሮት አስረጂያችን ነው።
የወር በዓላትን እየቆጠሩ ዛሬ ልደታ፤ በዓታ፤ ዮሐንስ፤
አቦ፤ ግዝረት፤ ሥላሴ፤ ዐርባእቱ እንስሳ፤ ስምኦን፤ መስቀል ፤ ሚካኤል፤ እስጢፋኖስ፤ ኪዳነምህረት፤ ገብርኤል፤ ማርያም፤ ደቅስዮስ፤
ኡራኤል፤ ጊዮርጊስ፤ ተ/ሃይማኖት፤ ሀብተማርያም፤ ገብረ ማርያም፤ አመተማርያም፤ ክርስቶስ ሰምራ ፤ አማኑኤል፤ በዓለወልድ ወልደነጎድጓድ፤
አባ ገሪማ፤ አባ መከራ፤ አባ ጭንቅ፤ አባ እግዚእ ኀረዮ፤ አባ ባሕር አልቅም………….. በማለት እጁንና እግሩን ኮርትሞ ራሱን ለድህነት
የሚሰጥበት እድል ሊኖር እንደማይችል ስለተረዳ በእነዚህ በአንዳንዶቹ
የግዝት በዓላት ቀን ጭምር ሊሰራ ተገዷል። የእመቤታችንን 33ቱን በዓላት እንደእሁድ ሰንበት ያላከበረ በማይፈታ ጽኑ ሥልጣን አወገዝን
እየተባለ የሚወርድበትን የእርግማን ሰይፍ የሚሰማበት ጊዜ ዛሬ የለውም። ኑሮው ሩጫን የሚጠይቅ በመሆኑ በዓል እያከበረ ለወግ ጥረቃ
ጊዜ ስለማያገኝ ክርስቲያኑ በተንዛዛና ለልክ የለሽ የበዓል ውግዘት ጆሮውን የሚሰጥበት ዘመን አብቅቷል። ለዳቦ መግዢያ ድንጋይ መፍለጥ
በሚገደድበት ሁኔታ ውስጥ መጾም አለብህ የሚለውን አስገዳጅ ሕግ እንዴት
ሊተገብር ይችላል? 18 ሚሊዮን ሕዝብ በነበራት ኢትዮጵያችን ውስጥ
ይከበር የነበረውን በዓል በ90 ሚሊዮን ሕዝብ ዘንድ ይከበር ዘንድ መጠበቅ የዋህነት ነው። ከላይ የሰዎችን የቁጥር ልኬታ
ለማሳየት እንደሞከርነው በአንድ ካሬ ኪሎሜትር ውስጥ ድሮ ካልነበሩ 75 ሰዎች ጋር የሚደረገው ኑሮን የማሸነፍ ትንቅንቅ እንዲህ
በበዓላት ቀን ተጎልተው በቀላሉ የሚወጡት ነገር አይደለምና ነው።
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጥንት የነበራትን ቀኖና ለማሻሻል የተገደደችው ጥንታዊውን
የቀኖና ሥርዓት ጫና መፈጸም ባለመቻል የተነሳ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት እስከነአካቴው ትቶ አማኙ ወደሞት መንገድ በክህደት
እንዳይኮበልል ለመታደግ መሆኑን ስናስተውል ለውጥ የሚያመጣውን አስገዳጅ ሁኔታ በጥበብ ለመቀበል የመፈለጓን ሁኔታ የት ድረስ እንደሆነ
እንረዳለን።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ነኝ የሚል ነገር ግን ከጾሙም፤ ከበዓል
አከባበሩም፤ ከምኑም የሌለበት በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታይ አለ። አምናለሁ የሚል ደግሞም ከቀኖናው መጠን የለሽነት የተነሳ መፈጸም
እያቃተው ራሱን እየወቀሰ በዚያው የቀረ ብዙ ነው። ከኃጢአት ሞት እንደመዳኛ መንገድ በመቁጠር በርቀት ሆኖ የመስቀል ምልክት ብቻ
በማማተብ የቀረ እልፍ አእላፍ ነው። ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው የለውጥ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሰው በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት
ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያስችል አስተምህሮ ካልተፈጠረ በስተቀር ቤተ ክርስቲያን ለቄሶችና ትርፍ ጊዜ ላላቸው ሰዎች ብቻ የተመደበች
ተቋም አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። ለምሳሌ የገናን ጾም የማይጾሙ አብዛኛዎቹ አማኞች የቄስ ጾም ነው ብለው ራሳቸውን
ከዚያ ውጭ አድርገው እንደሚቆጥሩ ይታወቃል። ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መሆናቸውን በአፋቸው የሚናገሩ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ከጫነችባቸው
ቀኖና ራሳቸውን ያገለሉ ቁጥራቸውን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው። በአካባቢያችን እንደምንመለከተው ከሆነ እንኳን ምእመናኑ ካህናቱና
ጳጳሳቱ ሳይቀሩ ስለቀኖናው እወጃና ውግዘት በወረቀት ያለውን ከሚናገሩ በስተቀር ገቢራዊ ማድረጉን ከተዉት ዓመታት ተቆጥረዋል።
ጾም ለክርስቲያኖች አስፈላጊና ራሳቸውን ለክርስቲያናዊ ተግባር የሚያዘጋጁበት ትልቅ
መንፈሳዊ መሣሪያ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ነው። ክርስቲያናዊ
ጾም ማለት፤ እንዴትና መቼ መጾም እንዳለብን የጋራ ግንዛቤ እንደሌለ ቢታወቅም ሥጋውን ያለልክ እየጨቆነ በሚያስጨንቅ ቀንበር ሥር
አማኙን በመጣል ያይደለ ለሥራ፤ ለአገልግሎትና ለፈቃደ ነፍስ ራሱን ማስገዛት እንዲችል በልክ ማድረጉ ግን ጠቃሚም የሚበጅም ይሆናል
ብለን እናምናለን። ነገር ግን ጥንታዊዋ ነነዌ የዛሬዋ የኢራቅ ሰሜናዊ ሞሱል ከተማ በአንድ ወቅት የፈጸመችውንና የዳነችበትን ጾም እንደሕግ በመውሰድ የማይሻር፤ የማይለወጥ የጾም ሕግ ማድረግ
ግን ከታሪካዊነቱና ከአስተማሪነቱ ባሻገር ለክርስትና የጾም ሕግ ከመሆን ግዴታ ጋር አንዳችም ትስስር የለውም። የነነዌ ጾም ቅድመ
ክርስትና የተደረገ እንደመሆኑ መጠን የነበሩትን የብሉይ ኪዳና አጽዋማት ሁሉ ወደአዲስ ኪዳን ጎትቶ ማምጣት አስቸጋሪ ነው። ይህንንም
በማየት የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በነነዌ ይሁን የፍልሰታ ጾም በሚባለው የጾም ወቅት ሥርዓተ ቅዳሴውን ለምእመናን የምትሰጠው በጥዋት
ክፍለ ጊዜ ነው። ቤተ ክርስቲያን መምጣት ያልቻለ ቅዳሴውን በቀጥታ
ስርጭት ቤቱ ሆኖ ይከታተላል። እግሩ ሳይሆን ልቡ ከአምልኮው ጋር ኅብረት ያደርጋል። ይህንን በማድረጓ አምልኮተ እግዚአብሔርን እንደሻረች
ያስቆጥራት ይሆን? በፍጹም!! እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠው የጾምን ፈቃድ እንጂ የጾምን ሕግ አይደለም። ሕግ ምን ጊዜም የፈራጅነትን
ሥልጣን በሰው ላይ ይወስዳልና እግዚአብሔር በሕግ ቀንበር ስር እንድንወድቅ አላደረገንም። ያሉን የጾም ሕጎች የእግዚአብሔር ሕጎች
አይደሉም። ራሳችንን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት ብለን የሰራናቸው ሕጎች ናቸው። ሕጎቹን አለመፈጸም የሕግ ባሪያዎች ያደርገናል። የሕግ
ባሪያ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛት አይችልም። ያለው ምርጫ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጽበትን ጾም መጾም አለበለዚያም የራሳችንን
የሕግ ጾም ባለመቻል በፍርድ ቀንበር ሥር መውደቅ ነው።
« እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ
እኔም ሞትሁ» ሮሜ 7፤9 እንዳለው።
በአንድ ወቅት አንድ ጳጳስ ቅዳሴ በኢንተርኔት ይሁን ብለዋል ተብሎ በአዲስ አበባ አላዋቂዎች
ቡራ ከረዩ ሲሉ እንደነበር እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ ሂደትና ለውጥ በሰዓቱ እንደሚያደርገው ብንገምት ከእውነታው የራቅን አይደለንም።
በድምጽ ማጉያ ሌሉቱን ሙሉ እያደነቆሩ ከስራ ያረፈውን ሰው እንቅልፍ ከመከልከል በቴሌቪዥን መስኮት እንደምርጫው እንዲከታተል ማድረጉ
ይሻል ነበር። በድምጽ ማጉያ ማደንቆር ጥፋት ካልሆነ በኢንተርኔት ይሁን በቴሌቪዥን ቅዳሴ መከታተል በደል የሚሆነው በምን ስሌት
ይሆን?
ስናጠቃልል የትኛውም ክርስቲያን ኑሮውን ለማሸነፍ በሚያደርገው ትግል ሳቢያ ቀደም ሲል
የነበሩትን ቁጥር አልባ ሥርዓተ ቀኖናት መፈጸም ወደማይችልበት ደረጃ መድረሱ አያጠራጥርም። ቀኖናት የእምነት ሕግጋት ስላይደሉ ሊቀነሱም፤
ሊጨመሩም ይችላሉ። ጭማሪው ይለፈንና በቅነሳው ላይ ሳንወድ በግድ የምንነጋገርበት የለውጥ ጊዜ ደርሷል። መነጋገር ባንፈልግ ደግሞ
የለውጥ ተግዳሮት በአማኙ ዘንድ ቀስ በቀስ እንዲሻሩ ያደርጋቸዋል። አሁንም ያለአዋጅ በተናጠል በብዙዎቹ ዘንድ ተሽረዋል። ለውጥ የሂደት ክስተት እንደመሆኑ መጠን ቤተ ክህነቷ መመለስ የማትፈልጋቸውንና
የማትችላቸውን ጥያቄዎች ተሸክማለች። አሉታዊውን እያስወገዱ፤ አዎንታዊውን እያጎለበቱ መጓዝ ለተግዳሮቶች ያለውን ዝግጁነት ያሳያል
እንጂ ምንፍቅና ወይም ክሂዶተ እግዚአብሔርን እንደመፈጸም አያስቆጥርም። ሕጉ በሁሉም ዘንድ ከወረቀት ባለፈ አለመፈጸሙ የለውጡ ሂደት
መንደርደሪያ መሆኑን ያመላክታል።
ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ሕጉን የመፈጸም ግዴታ ያለበት አብዛኛው ምእመን ከሕጉ ግዴታ
ራሱን አግልሎ የወረቀት ላይ ሕግ እንዳይጣስ የሚያደርገው ጥብቅና ነው። በጾመ አርባ ሽንጥ ከተዳቢት ሲበላ የባጀ ስመ ክርስቲያን
በጾመ ፍቺ ላይ ዋነኛው ጾም ፈቺ ሆኖ የመገኘቱ ነገር አስገራሚ ነው። በክርስትና ሕይወት ባዶ የሆነ አማኝ መሳይ ቅቤ አንጓች የጾም
ሕግ ይሻሻል የሚል የሃሳብ ፍጭት ሲቀርብ ጥብቅና በመቆም ለምን ተነክቶ? እያለ ሲንጨረጨር በየሥፍራው ያጋጥመናል። ጥንትም አይሁዶች
ሕጋቸውን ሳይጠብቁ ለሕጉ ንባብ ሲጨነቁ ታይተዋልና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውም ተመሳሳይ ክስተት መሆኑን ነው። ለውጥ ሂደት ነውና
ሁሉም በጊዜው ሳንፈልገው ይሆናል። የምንፈልገው እንዲሆን የማይሆነንን ማየት ያለብን ዛሬ ነው።