Tuesday, August 27, 2013

የማይቀረው ለውጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘቱ አይቀርም!




ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው!
ክፍል ሁለት / ነሐሴ 21/ 2005/

በክፍል አንድ ጽሁፋችን ስለለውጥና የለውጥ አስተሳሰብ ጥቂት ለማለት ሞክረን ነበር። ጊዜውን ጠብቆ በመጣው ለውጥ ሳቢያ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስላቋቋመችው የለውጥ ማስታገሻ መንገድና ስለኢየሱሳውያን/ JESUIT/ አመሰራረት መንስዔም በመጠኑ አስቃኝተናል። ስለጀስዊትስ ዓላማና ግብ በዝርዝር እዚህ ላይ እንዳንሄድ የተነሳንበት ርእስ መሠረተ ሃሳብ ይገድበናልና ትተነዋል። አንባቢዎቻችን ተጨማሪ መረጃ ያገኙ ዘንድ በዚህ ሊንክ እንዲገቡ እንጠቁማለን።/http://www.biblebelievers.org.au/jesuits.htm የጀስዊትስ መመሥረት የአዲስ አስተሳሰብና የለውጥ እንቅስቃሴን ባያቆምም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ከመፈራረስ በተወሰነ መልኩ አግዟታል። ወደማትፈልገውና ወዳላሳበችው የለውጥ መንገድ እንድትንሸራተት ያስገደዳት ሲሆን የነበራትን የሮማን ህግና ደንብ በየሀገራቱ ውስጥ ከመትከል ይልቅ የየሀገራቱን ባህልና ወግ ከካቶሊክ አመለካከት ጋር እያስማማች ለመጓዝ ረድቷታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ካቶሊክም ኢትዮጵያዊ ካቶሊክ እንዲመስል እንጂ ቫቲካናዊ ካቶሊክ እንዲመስል ስለማይጠበቅበት ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግልባጭ ነው። ታንዛንያ ስንሄድ ደግሞ ታንዛንያዊ ቋንቋ፤ ባህልና ወግን ይከተላል። ሌላ ቋንቋ፤ ባህልና ሥርዓት አምጥቶ ከመጫን ይልቅ ሕዝቡ በሚኖርበት ቋንቋ፤ ባህልና ሥርዓት ሲያስተምሩት ውጤታማ መሆኑ አይጠረጠርም። ሐዋርያው ጳውሎስም ያደረገው እንዲሁ ነበር። ያልተገረዘ ወደ መገረዝ አይሂድ ማለቱ ወንጌል ማለት አይሁዳዊውን ሥርዓት በሌላ ሕዝብ ላይ በመጫን የሚፈጸም እንዳልሆነ መግለጡ ነበር። እንኳን ግእዝን አማርኛን በውል ለማይሰማ ለሸኮ መዠንገር ሕዝብ ሄደህ የያሬድ የቅዳሴ ዜማ ነው ብለህ ብትጮህለት ለምሥጋናህ እንዴት አሜን ሊል ይችላል? ክርስትና የሰዎችን ቁጥር የማብዛት ጉዳይ ባይሆንም ወንጌል ያልደረሳቸውን ለማዳረስ ትክክለኛው መንገድ እኛ የምንኖርበትን ሥርዓትና ሕግ በማያውቀው ሌላ ሕዝብ ላይ የመጫን ጉዳይ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን መድኃኒት መሆኑን ከማስተማር ባለፈ አሳማ በመብላትና ባለመብላት የማትገኘውን የጽድቅ መንገድ በላተኛውን በመከልከል ሊሆን አይችልም።
በዚህ አንጻር የካቶሊክ ተገዳዳሪ ሆኖ ለመጣው አዲስ የፕሮቴስታንት ዓለም ያልተፈለገውን የለውጥ መንገድ ለመጀመር ምክንያት ሆኗል። በ 12ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ ላይ ካቶሊክ የፈጠረችውን የመካነ ንሥሐ/ purgatory/ ጽንሰ ሃሳብ የግድ ህግ እንደሆነ ማስተማርን ለመተው ተገዳለች። ኃጥእ ሰው ንስሐ ሳይገባ ከሞተ፤ የንስሐ ቦታ በሰማይ አለው የሚለው ጸረ ወንጌል አስተሳሰብ በአዲስ ለውጥ እንቅስቃሴ ተቀባይነቱን አጥቷል። በእርግጥ ይህ አስተምህሮ ዛሬም ሳይጠፋ ተጠብቆ በሀገራችን ይገኛል።  መጽሐፈ ግንዘት «እምድኅረ ሞቱ ለሰብእ አልቦቱ ንስሐ» ሰው ከሞተ በኋላ የንስሐ ጊዜ የለውም» ቢልም ፍታትና ተስካር ንስሐ ሳይገባ የሞተውን ሰው ሥርየት ለማሰጠት የሚደረገው ሥርዓት አሁን ድረስ አለ። በካቶሊክ አስተምህሮ ላይ ከተነሳው የለውጥ ጥያቄ አንዱ ይህ ነበር።

ማርቲን ሉተር ባነሳው ባለ 95 አንቀጽ የለውጥ ጥያቄ ምክንያት ካቶሊክ ውጥረት ውስጥ የገባች ሲሆን ይህ አዲስ የለውጥ አስተሳሰብና የአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት አዲስ የእምነት መንገድ ይዞ በመምጣቱ እንደአሸን የፈሉ ሃይማኖታዊ ስሞችና አስተምህሮዎች ብቅ ብቅ ለማለት ችለዋል። ምንም እንኳን የወንጌል  መሠረት በሌለው አስተምህሮ ምክንያት አዲስ ለውጥ የተነሳ ቢሆንም አዲሱ የለውጥ አስተሳሰብም ራሱ ሌሎች ችግሮችን ማስከተሉ አልቀረም። ከላይ ስንገልጽ እንደቆየነው ለውጥና የለውጥ አስተሳሰብ በሂደት እየተገመገመ እርምጃ መወሰድ ሲቻል ችግሩ አናሳ የመሆኑን ያህል ያለምንም ዝግጅት በአዲስ የለውጥ አስተሳሰብ መመታት በራሱ ችግሮችን መውለዱ አይቀሬ በመሆኑ በወቅቱም አውሮፓ በአዳዲስ መጤ ባህልና አስተምህሮ፤ አልፎ ተርፎም በስመ ክርስትና ደም የሚያፋስስ ውጤትን አስከትሎ ነበር። ከ1618- 1648 በፕሮቴስታንትና በካቶሊክ መካከል የተደረገው የ30 ዓመት ጦርነት ተጠቃሽ ነው። የካቶሊክ ጫናና ኃያል የሥልጣን መንሰራፋት የሰለቻቸው ገዢዎች የፕሮቴስታንትን ነጻ አስተሳሰብና ሸክም የሚቀንስ አስተምህሮ በሚደግፉ ክፍሎች መካከል ብዙ ፍጅት አስከትሎ የ8 ሚሊዮን ህዝቦችን ሕይወት የቀጠፈ ነበር። አዲሱን ለውጥ በይበልጥ የደገፉት የሉተር መነሻ የሆነችው ጀርመንና አስተሳሰቡን በፍጥነት የተቀበሉት ስካንዲናቪያን ሀገሮች ማለትም አይስላንድ፤ ኖርዌይ፤ ስዊድን፤ ዴንማርክና ፊላንድ ከፕሮቴስታንቱ የለውጥ አመለካከት ጋር ቆመው ታይተዋል። ጦርነቱ ከበረደና ካቶሊክ በነዚህ ሀገሮች የነበራት ኃይል ከወደቀ በኋላ ሀገራቱ ከኢንዱስትሪው አብዮት ጋር በአዲስ አስተሳሰብ የተቀላቀሉ ሲሆን በአንጻራዊነት የተረጋጋ ኢኮኖሚና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ሀገራት ለመሆን የቻሉበትን እመርታ ሲያዝመግቡ ለካቶሊክ ጥብቅና ቆመው የነበሩት ስፔን፤ ጣሊያን ፓርቱጋል፤ ቀደም ሲል የነበራቸውን ኃያልነት እያጡ ሲመጡ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ በስመ ሃይማኖት የተደረገው ጦርነት ዋነኛ መነሻው አዲስ ለውጥንና አስተሳሰብን ለመቀበል በመፈልግና ባለመፈለግ መካከል የተከሰተ የሁለት ጽንፍ የተቃርኖ ውጤት በመሆኑ ለውጡን ለመፍታት የተኬደበት መንገድ በአስከፊነቱ ተመዝግቧል።
ሁኔታዎች እየተረጋጉና እየጠሩ ሲሄዱ የካቶሊክ ኃያልነት የግድ ሊሰክን ችሏል። የአዲስ ለውጥ አስተሳሰቦችን እያደኑ ለማጥፋት መሞከር ይልቅ በተመሳሳይ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማርና ለለውጡ መነሻ የሆኑ ጉድለቶችን ማረም እንደሚገባ እንደታመነበት ከዚያ በኋላ የተወሰዱ ማስተካከያዎች የለውጥ ፍንጭ ሆነው ታይተዋል።
እንደተቃዋሚ የተመዘገበው የፕሮቴስታንቱ አዲስ የእምነት መንገድ ቶሎ በመስፋፋት የሀገራት ወይም የሕዝቦች የእምነት መገለጫ ለመሆን ጊዜ አልወሰደበትም። እምነቱ ለሃይማኖት በሚደረገው የሥርዓት ሕግ ላይ ብዙም ትኩረት ስለማይሰጥ በተንዛዛ ሥርዓትና ሕግ ለተሰላቸ ሕዝብ እረፍት ያስገኘ ያህል በመቆጠሩ ተቀባይነቱ ትልቅ ነበር።
 ይሁን እንጂ የፕሮቴስታንቱ አዲስ የእምነት አስተሳሰብና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መሠረት ያደረገ አስተምህሮ አለኝ የሚልበት ተመካሂ አስተሳሰብ በራሱ ወጥ ስላልነበረ ወደ መፈረካከስና መበጣጠስ መሄዱ አልቀረም። በዚህ የተነሳ ልዩ ልዩ ስሞችንና የአስተምህሮ መንገዶችን የያዙ ክፍልፍሎች ከዚህም ከዚያም ብቅ ብለዋል። በመካከላቸው የእምነትና የሥርዓት ሽኩቻ አልፎ አልፎ ቢከሰትም አዲስ የለውጥ አስተሳሰብና የእምነት አስተምህሮ አውሮፓን ማጥለቅለቁን አላቋረጠም።
 አውሮፓ እየተረጋጋችና ወደኢንዱስትሪው አብዮት በመግባት ኢኮኖሚዋ እያደገ የመጣበት ሁኔታ ስለነበር ከአዲስ የለውጥ አስተሳሰብ ጋር ከመስማማት በስተቀር ለግጭት ጊዜ እንደሌላት በማሳየት ለእድገትና ለለውጥ ዝግጁ ሆናለች። ከ 1760 እስከ 1860 ድረስ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ነበር። የውሃ ፤ የእንፋሎትና የንፋስ ኃይልን የመጠቀም ፈጠራ ትልቅ እመርታ ላይ በመድረሱ በአዲስ የለውጥ አስተሳሰብ ውስጥ መግባቷን ያመላከተ ነበር። ይህም የጨርቃ ጨርቅ፤ የወረቀት፤ የመስታወት፤ የብረታ ብረት፤ የእርሻ፤ የኬሚካል፤ የማእድን ወዘተ ውጤቶች መገኘት እንዲሁም የባቡር፤ የመንገድ፤ የቤት ግንባታ እንዲስፋፋ ማስቻሉ ከተመዘገቡት መልካም የእድገት ምልክቶች ውስጥ የተከታቱ ነበሩ።
ያለማንም ከልካይ መጽሐፍ ቅዱስን በአደባባይ መስበክ፤ ማስተማር፤  አማኙ በሥነ ምግባርና በግብረ ገብነት የታነጸ እንዲሆን ለማስቻል አዲሱ የእምነት አስተሳሰብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚህም የተነሳ ከአውሮፓ ሀገራት 96% ክርስቲያኖች መሆን የቻሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛው በየቤተ እምነቱ እየተገኘ በእለተ እሁድ የሚጸልይ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ ለውጥ ሂደት እንደመሆኑ መጠን አውሮፓ በአዲስ የእምነት ለውጥ ስትጠመቅና በአዲስ የእድገት ጎዳና ላይ ስትገሰግስ ነገሮች ባሉበት ጸንተው የሚሄዱ ባለመሆናቸው ሌላ የለውጥ አስተሳሰብና ተግዳሮት ከፊት ለፊቷ መደቀኑ አልቀረም። የኢንዱስትሪው እድገት የሚያመጣው ጫናና የየእምነት አስተምህሮው ወጥ ያለመሆን ጉድለት ሌላ ለውጥ እንዲመጣ ያስገደዱ ሁኔታዎች ሲሆኑ አውሮፓ ለዚህ ተግዳሮት የሚሆን ዝግጅት ባለማድረጓ ትልቅ ኪሳራ ውስጥ ትገባ ዘንድ እንደገፋት ማወቅ ይቻላል። የኢንዱስትሪው እመርታ ሰዎች ለእምነት የነበራቸውን ግንዛቤ ሸርሽሮታል። የእምነት ዓይነቱ መበራከትና የሥነ ምግባር ጉድለቱ ተጠራቅሞ አማኙን ከእምነት ተቋማት እንዲርቅ ያደረገበትን ሁኔታ ሂደቱ ፈጥሯል። አውሮፓውያን መሪዎች ርካሽ ሀብትና ጉልበት ለኢንዱስትሪዎቻቸው ለማግኘት አፍሪካን ወደመቀራመት እንዲሁም በ1ኛውና በ2ኛው ዓለም ጦርነት የደረሰው ውድመት እያንሰራራ የነበረውን የእምነት ትጋት አደብዝዞታል። በዚህም የተነሳ ሰዎች ለእምነት ያላቸው ጥንካሬ ተሸርሽሮ ወደእምነት የለሽነት ወይም የግል እምነት ተከታይነት አለያም ስለምንም ሳያስቡ ዝም ብሎ እየበሉ መኖር ወደሚል ባህል ሊለወጥ ግድ ሆኗል። ካቶሊክን የሚቃወምና አዲስ የእምነት ፈለግን የፈጠረው የለውጥ እንቅስቃሴ በተራው በሌላ የለውጥ ምች መመታቱ አልቀረም። 96% (ከመቶ)የነበረው የአውሮፓ ክርስቲያን ቁጥር እስከ 1980ዎቹ ድረስ ወደ 74% አሽቆልቁሎ ነበር። ዛሬ በፈረንሳይ ብቻ 40 ከመቶው እምነት የለሽ ወይም ስለእምነት ጉዳይ ደንታ የለሽ ለመሆን በቅቷል። አዲሱን የለውጥ አስተሳሰብ ገቢራዊ በማድረግ ረገድ አስቀድሞ በተሰራና በተጠና መልኩ ቀናውን ተቀብሎ አሉታዊውን መጣል የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ ካቶሊክን የአንጃ መፍለቂያ ባላደረጋትም ነበር። አንጃዎችም የተቀበላቸውን የአዲስ ትውልድ አስተሳሰብ እየሸረሸሩ ወደሞት ለሚነዳ የእምነት ጠላትነት አሳልፈው ባልሰጡትም ነበር። አንድ የእንግሊዝ ሃይማኖታዊ ተቋም ስለአውሮፓ የእምነት መዳከም ገፊ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ጥናት አድርጎ የደረሰበት መደምደሚያ  በአምስት ዋናና በሌሎች ንዑሳን ርዕሶች አጠቃሎታል።
 ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ሃሳብ ገላጭ የሆነውን እንዲሁም ለሃይማኖትና አማኞች መዳከም መንስዔ ተደርገው ከተመዘገቡት ውስጥ ስድስት ነጥቦች  እዚህ ላይ እንጠቅሳቸዋለን።
ለአውሮፓ የእምነት ማሽቆልቆል ዋና ዋና ገፊ ምክንያቶች፤
1/ የኢንዱስትሪው አብዮት በሚፈልገው የሰው አቅምና በሚወስደው ረጅም የሥራ ጊዜ ሳቢያ የክርስቲያኖች አእምሮ ያለእረፍት መባከኑ፤
2/ ኢንዱስትሪው በየጊዜው በሚፈጥረው ትንግርታዊ እድገትና ጥበብ የሰው ልብ መማረኩ፤ ያልነበሩና የማይታወቁ ልምዶችን፤ ባህሎችንና ሥነ ምግባርን የሚያላሽቁ ክስተቶች መምጣታቸው፤
3/ የኑሮ ምቾትና ድሎት መጠን የለሽ በመሆኑና የአእምሮ ድንዛዜን በማስከተሉ፤
4/ የቤተክርስቲያን መሪዎች የምግባር ጉድለትና የስህተት አስተምህሮዎች መበራከት፤
5/ ተረካቢው ትውልድ ለሳይንስና ለትምህርት እውቀት ራሱን አሳልፎ በመስጠት፤ ሃይማኖት የትርፍ ጊዜ ሥራ ወይም የተስፈኞች ዓለም ጉዳይ አድርጎ መመልከቱ፤
6/ እግዚአብሔር የለሾች የፖለቲካ ሥልጣኑን ቦታ መረከባቸው ፤ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በነዚህና በተጓዳኝ ምክንያቶች ሳቢያ ዛሬ ከአውሮፓ አባል ሀገራት ውስጥ 51% ብቻ በእግዚአብሔር መኖር የሚያምኑ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
የጽሁፋችን ዓላማ ስለአውሮፓ የለውጥ፤ የእድገትና  የአሉታዊ ክስተቶች ትንተና መስጠት ሳይሆን እነዚህን ገፊ ምክንያቶች መጥቀስ ያስፈለገው ወደኢትዮጵያችን በመመንዘር የአፄያዊው በደርግ፤ የደርጉ ደግሞ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የአዳዲስ ለውጥ አስተሳሰቦች ኩነት መለወጥ፤  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የት እንዳደረሳት የምንመለከትበት መስታወት እንዲሆነን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተከታዮቿ ቁጥር ከየት ተነስተው የት ደረሱ? የአውሮፓውን የፕሮቴስታንት ጎራ በርቀት ታየው የነበረችው ቤተ ክርስቲያን  በማኅበር አባልነት አብሮአት መቀመጥ የመቻሉ ምክንያት ምንድነው? ስለወንጌልና ስለሥርዓት፤ ስለስብከትና ስለድኅነት ያለው አስተምህሮ፤ ስለመሪዎች የምግባር ዝቅጠትና የአስተዳደር ጉድለት የት ደርሷል? የሚለውን እንድንመለከት ያግዘናል። ነጃሺ የሚባል ኢትዮጵያዊ ንጉሥ እንደሌለ ስትከራከር ነጃሺ የተባለው ሰው የተቀበላቸው 75 ሰዎች ቁጥር ዛሬ ካለበት የኢስላም ቁጥር ደረጃ የደረሰበትን አመክንዮ ማወቅ አለመፈለጓን ለመመልከት አጋዥ የሚሆኑን ነጥቦች ስለሆኑ እዚህ ላይ ጠቅሰናቸዋል። ስለሆነም ከላይ በተዘረዘሩት 6 ርዕሶች መነሻ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እንደትልቅነትዋ እና የፕሮቴስታንቱ ጎራ እንደአዲስ የእምነት ባህል ያለበትን ደረጃ በቀጣይ ጽሁፍ ለመመልከት እንሞክራለን። ለውጥ የሂደት ውጤት በመሆኑ ለውጥ ስለሚያስከትለው ውጤት አስቀድሞ ራስን ከእውነታው ጋር ማገናኘት ጉዳቱን ይቀንሳል ነው። ( If you can change before you have to change, there will be less pain) የተባለውም ለዚህ ነው።