Sunday, August 4, 2013

የማኅበረ ቅዱሳን የተሸፈነ ማንነት በአሜሪካ ተገለጠ!



One of his loyal bishop
እንደስንዝሮ ታሪክ ሰኞ ቀን ዩኒቨርስቲ ተረከዝኩ፤ ማክሰኞ ብላቴ ላይ ተወለድኩ፤ ረቡዕ ዕለት በአቡነ ገብርኤል ማኅበረ ቅዱሳን በሚል የክርስትና ስም ተጠመኩ፤ ሐሙስ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ልሰብር የነገር እንጨት ለቀማ ሄድኩ የሚለው ይህ ማኅበር ብዙዎቹን ለማሰለፍ ቢችልም የስንዝሮ ታሪኩ እየተገለጠና እየተገፈፈ በመታወቅ ላይ ይገኛል። በተለይም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ይህንን ማኅበር በጭለማ መንፈስ የሚነዳ፤ የክፋት ኃይል አድርጎ በመመልከቱ ደረጃ ትልቅ ግንዛቤ እንዳለ ይታወቃል። ወጣቱ ትውልድም ቢሆን እየዋለ እያደረ የማኅበሩን እንቅስቃሴና እርምጃ ፤ የገንዘብ አቅሙን ማደርጀትና ወደንግዱ ዓለም ጎራ ማለቱን በማየት ከየት ተነስቶ ወደየት? ለመሄድ እንደፈለገ በተፈጠረበት ግርታ የተነሳ ባለበት ቆም ብሎ ለማስተዋል መገደዱን የምናገኛቸው ትዝብቶች ያስረዱናል። አንዳንዶቹም ርቀው ሲያዩት ወርቅ የመሰላቸው ይህ ማኅበር ቢቀርቡት የመዳሪያና የገንዘብ መሸቀጫ ስብስብ መሆኑን ተመልክተው አፍረውበት እርባና እንደሌለው ሲናገሩም ይደመጣል።  ይህ ማኅበር ከራሱ ከንግድ ተቋሙ ኃላፊዎችና የእንደጋሪ ፈረስ ከሚነዱለት ጥቂት ተከታዮቹ በስተቀር እንደመንፈሳዊና ጠቃሚ ማኅበር የመቆጠሩ ነገር እንደገለባ በመቅለል ላይ ይገኛል
በ1950 ዓ/ም የተቋቋመውና  ከሃይማኖት የለሹ የደርግ መንግሥት ጋር በመተባበር የጠቅላይ ቤተክህነት ሹማምንት በ1975 ዓ/ም እንዲፈርስ የኢሠፓአኮ ሠይፍ የመዘዙበት «ሃይማኖተ አበው» የተሰኘውን አንጋፋ ማኅበር ከደርግ ውድቀት በኋላ እንደገና ነፍስ ዘርቶ ሊቋቋም ሲንቀሳቀስ ከእኔ ሌላ ማንንም አልይ የሚለው የብላቴው የወታደሮች ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳንና ደጋፊዎቹ ሁለተኛ ጊዜ ሠይፍ አሳርፈውበት ከነአካቴው እንዳይኖር አድርገው አከርካሪውን እንደመቱት የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከክፋቶቹ ሁሉ የላቀው ክፋት ከእርሱ በስተቀር አንድም ማኅበር ኅልውና አግኝቶ እንዳያንሰራራ በተለጣፊ ጳጳሳቶቹና በአገልጋዮቹ በኩል ማስመታት መቻሉ ነው። እንኳን ማኅበራት ጳጳሳሶቹ እንኳን ከፓትርያርኩና ከፌዴራል ፖሊስ በላይ የሚፈሩት ይህንን ማኅበር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በሹክሹክታ የሚያወሩትን የሚሰማቸው እስኪመስላቸው ድረስ ይህንን ማኅበር እንደሚከተላቸው ጥላ ይከታተለናል ብለው ይንቀጠቀጡለታል። ገሚሶቹም ነውራሞች ሳይወዱ እየሳቁ በታማኝ ሎሌነት ያገለግሉታል።

ደጋግመን እንዳልነው ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማውና ግቡ ቤተ ክርስቲያንን በራሱ ሰዎች መረከብ ነው እንጂ ወንጌልን የማስፋፋት ብቃት፤ ችሎታና ማንነት ቅንጣት ታህል እንደሌለው እሙን ነው። ማኅበሩ በምንም ዓይነት መልኩ የወንጌልን እውነት የማይቀበል የጨለማ መንፈስ አገልጋይ ነው። ይባስ ብሎ የወንጌሉን እውነት አለመቀበል ብቻ ሳይሆን ወንጌሉን ደፍጥጦ ለተረት፤ ለእንቆቅልሽ፤ ለቅዠትና ለህልም ታሪኮች ከፍተኛውን ቦታ በመስጠት ሰው ሁሉ በዚያ መንገድ እንዲነጉድ የሚያመቻች የጥፋት ኃይል ነው። የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ያሳድዳል፤ ያስወግዛል፤ ያሳድማል። ማኅበሩ ባለበት ቦታ ሁሉ ሁከት አለ። በደቡብ ኢትዮጵያ ከሀዋሳ እስከቦረና ረጅም እጁ እስካሁን አልተሰበሰበም። በሐረርና በድሬዳዋ፤ በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅና በየአድባራቱ የሁከት መንፈሱን ጊዜ እየጠበቀ ይረጫል። ጎጋ አባላቱ ነፍሳቸውን እንኳን ለመገበር እንደማይመለሱ ብናውቅም ብዙዎቹ የማኅበሩ አባላት እውነቱን እያወቀ  ከእውነቱ ጋር ለመታረቅ ያሰገራቸው መንፈስ እድል ስለማይሰጣቸው ምንም የሌላቸው ባዶዎች፤ ከሚታየው ከፍታ መውረድ የማይፈልጉና ከሚበላው ሠርከ ኅብስት ጋር ሆዳቸውን አስታርቀው የሚኖሩ የአእምሮ ደሃዎች ሆነው ቀርተዋል።
ይህ ማኅበር እውነት ምን እንደምትመስል ቢያውቅ እንኳን ከእውነት ጋር ለመስማማት ተፈጥሮው አይፈቅድለትም። ራሱን እያገዘፈና ተጠሪ የሆነ ያህል ሰይሞ በየቦታው ራሱን የሚያስገባው ይህ ማኅበር በሰሜን አሜሪካ ብዙ ብጥብጥ አስነስቶ ቆይቷል። ለምሳሌም በላስቬጋስ ሐመረ ኖኅ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪውን ቄስ አባሮ በራሱ ምልምል ጢም አልባ መነኩሴ ቤተ ክርስቲያኑን መረከቡ አይዘነጋም። በሲያትል፤ በኒውዮርክ፤በዳላስና በካሊፎርንያ ለማስነሳት የሞከረው ብጥብጥና በአንዳንዶች ቦታም  ምዕመናን ከፍሎ በመገንጠልና በሥነ ምግባር ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ በሚፈለገው ጳጳስ በኩል እያስባረከ የራሱን ንግድ እያጧጧፈ ይገኛል። ይህንን ተግባሩን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል። ይህንን መሠሪ አድራጎቱን የተመለከቱ የሰሜን አሜሪካ አድባራት ሰሞኑን በዚህ ማኅበር ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ውይይት አድርገዋል። በማኅበሩ ማንነትና አቋም ዙሪያ አንድ ውሳኔ በማሳለፍ ማኅበሩ ከተሸሸገበት ከቤተ ክርስቲያን ጉያ እንዲወጣ ለመምከር በተሰበሰበው ጉባዔ ላይ የተገኙ የማኅበሩ አባላት ጨርቃቸውን ጥለው እስኪሄዱ ድረስ እብደት ቃጥቷቸው እንደነበር ተሳታፊ የማኅበሩ አባላት በምሬት ሲናገሩ ተደምጧል። ስለማኅበሩ ቅዱስ መሆን ለማስረዳት እድል የጠየቁትና ማንንም ሰሚ ሳያገኙ ከንፈራቸው ደርቆ የቀሩት እነዚህ ሰዎች ማኅበሩ እርቃኑን እየቀረ መሄዱንና እዚህ ድረስ ያደረሳቸው የአክራሪ ተሐድሶዎች ሴራ እንደሆነ ሲለፈልፉም ተሰምቷል። ይሁን እንጂ የማኅበሩን ማንነት እያጋለጠ ያለው ሌላ ማንም ሳይሆን የማኅበሩ ግብር ራሱ ነው። በሰሜን አሜሪካ የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ አድባራቱ ይታወካሉ፤ ይታመሳሉ ወይም የተገነጠለ አዳራሽ ያቋቁሙባቸዋል። ይህንን የማኅበሩን ሴራ ለመቋቋም የመከሩት የሰሜን አሜሪካ አድባራት ሊመሰገኑ ይገባል። ከእንግዲህ በሰሜን አሜሪካ የራሱን ሦስተኛ ሲኖዶስ ከሚያቋቁም በስተቀር በየአድባራቱ ውስጥ ስፍራ እንደሌለውና ማንነቱ በደንብ በመገለጹ የክስረት ጎዳናውን የመጀመሩ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።
በኢትዮጵያ ውስጥም በዚህ ማኅበር ዙሪያ ትልቅ ግንዛቤ ተይዟል። ይሁን እንጂ ከማኅበሩ ጋር እንዳይጋጩ በነውሬን ሸፍንልኝ ቃለ መሃላ የተያዙ ጳጳሳት አንዳንዶቹ በፍርሃት፤ ገሚሶቹም በጥቅም ተደልለው እስትንፋሱ እንዲቆይ እየረዱት ይገኛሉ። ይህም ቢሆን ለጊዜው ነው። ይዘገይ እንደሆን እንጂ እውነት በአናቷ ቢቀብሯት እግሯ ትወጣለች። አሁንም እያየነው ያለው ያንን ነው። በሰሜን አሜሪካ ያሉ አድባራት በዚህ ማኅበር ዙሪያ ያደረጉት ምክክር የሚያሳየው በማኅበረ ቅዱሳን ማንነት ዙሪያ እየተሠራ የቆየው ሥራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ነው።