Thursday, August 22, 2013

የማይቀረው ለውጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መጎብኘቱ አይቀርም!

ባልተዘጋጀችበትና በማትፈልገው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው!

ክፍል አንድ፤

ለውጥና የለውጥ አስተሳሰብ
ለውጥ የሂደት ውጤት ነው። ስለወደድነው አይመጣም፤ ስለጠላነው አይቀርም። አንዳንዶች ለውጥን ለማስቀረት ይታገላሉ፤ ወይም በእነሱ ትግል የሚቀር ይመስላቸዋል። የለውጥ ህግጋት ግን አይቀሬ መሆኑን ስለሚያሳይ ይዘገይ እንደሆን እንጂ ያ የተፈራው ለውጥ እንደሚሆን አድርገው ለመቀበል ካልፈለጉት እንደማይሆን ሆኖ ይመጣል። በዚህ ምድር ላይ ባለበት ችክ ብሎ የኖረ ነገር የለም። ድንጋይ እንኳን ተፈረካክሶ አፈር ይሆናል። ፀሐይም በጭለማ ትጋረዳለች። በጋም በክረምት ይቀየራል። ብሉይም በሐዲስ ተሽሯል። ከእስራኤል ዘሥጋ ይልቅ እስራኤል ዘነፍስ የጸጋ ፍሰት ደርሶታል።በመወለድና በመሞት፤በመምጣትና በመሄድ፤ በመፈጠርና በማለፍ መካከልም የለውጥ ሕግጋት አለ። እግዚአብሔር ነገሮችን በጊዜ ዑደት ውስጥ እንዲያልፉ አድርጎ ፈጠረ እንጂ ባለበት ቆሞ እንዲቀር ያደረገው አንዳች ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ ያለንባት ሰማይና ምድር እንኳን በአዲስ ሰማይና ምድር ትለወጣለች። መቼም የማይለወጠው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ዘመን የማይቆጠርለትና የማይለወጥ እሱ ብቻ ስለሆነ ነብዩ ዳዊት እንዲህ አለ።
«አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም» መዝ 102፤27      
  የሀገራችን ገበሬ ክረምት ከመድረሱ አስቀድሞ የወራቶችን ለውጥ አስልቶ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ መጻዒውን ጊዜ ይጠባበቃል። ዘመኑን ጠብቆ በሚመላለሰው ለውጥ ውስጥ ራሱን አስማምቶና ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን በየተራ ካልፈጸመ በስተቀር የበጋው በክረምት መለወጥ በራሱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖውን አሳርፎ ያልፋል።    በሰለጠነው  ዓለም ያሉ ምሁራን በማይቀረው የለውጥ ሂደት የተነሳ ስለለውጥ ያላቸው ግንዛቤ ትልቅ ስለሆነ ሥራቸውን ከለውጥ ጠቀሜታና ተግዳሮት አንጻር ቅድመ ምልከታ በማድረግ ለምላሹ አስቀድመው ይዘጋጃሉ።                                                                                                                                    
 
                             
የአሜሪካ ኢንጂነሮች ተቋም ስለለውጥ አይቀሬነት በሰጠው ትንታኔ እንዲህ ይገልጸዋል።
Change is something that presses us out of our comfort zone.  Change is inequitable; not a respecter of persons. Change is for the better or for the worst, depending on where you view it. Change has an adjustment period which varies on the individual. It is uncomfortable, for changing from one state to the next upsets our control over outcomes. Change is measured by its impact on all who are connected to it.  Change is only a waste to those who don’t learn from it. Change happens in the heart before it is proclaimed by our works. Change chaps those moving slower than the change itself.  If you can change before you have to change, there will be less pain. Change can flow or jerk, depending on our resistance to it. Change uses the power invested in the unseen to reinvent what is seen. Change is like driving in a fog – you can’t see very far, but you can make the whole trip that way.

(ተዛማጅ ትርጉም፤) ለውጥ ካለንበት መደላድል የሚያወጣን ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ለውጥ በራሱ ሚዛናዊ አይደለም። ለባለጉዳዩም አክብሮትን አይሰጥም። ስለለውጥ ባለህ እይታ ላይ ተመስርቶ ለውጥ ወደተሻለ እመርታ ወይም ወደከፋ ሁኔታ ሊያደርስህ ይችላል። ለውጥ እያንዳንዱ ስለለውጥ ባለው  የጊዜ ስፍር የተነሳ ይለያያል። ለውጥ በሚያስከትለውና ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሂደቱ ምቾትን አይሰጥም። ለውጥ ባለው የጊዜ ልኬታ ለእያንዳንዱ የተለያየ ነው። ከነበርክበት ሁኔታ ወጥተህ ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ውስጥ አዲስ ለውጥ ምቾትን ላይሰጥህ ይችላል። ለውጥ የሚለካው ከለውጡ ጋር ግንኙነት ያላቸው ክፍሎች ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው። ከለውጥ መማር ለማይፈልጉ ክፍሎች ለውጥ ጊዜ ማባከን ነው። ለውጥ የሚከወነው ገቢራዊ ከማድረግ በፊት በልቡና ውስጥ ነው። ከለውጥ ውጤት ይልቅ ለውጥን ለመቀበል በሚዘገዩት ላይ ችግሩ ይብሳል። ለውጡ ግድ ከማለቱ በፊት ቀደም ብለህ ከለወጥከው ጉዳቱ አናሳ ነው። ስለለውጥ ባለን ጥንካሬ የተነሳ ለውጡ ቀጥተኛ ወይም አባጣ ጎርባጣ ሊሆን ይችላል። ለውጥ በጭጋግ ውስጥ የሚነዳ ሰውን ይመስላል። ርቀት ማየት አይችልም። ነገር ግን ቅርቡን ተከትሎ ረጅሙን ጉዞ ይፈጽማል።(የትርጉሙ መጨረሻ)

    ቀስቃሽና አስተዋሽ የማያስፈልገው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ፍጡር ግን በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የሚሰራውን ለይቶ መፈጸም ይጠበቅበታል። የትኛው ሥራ፤ በየትኛው ጊዜ መሠራት እንዳለበት የማወቅና የመፈጸም ድርሻ የሰው ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን ይህንን በመዘንጋት በሚመጣበት ጉዳት ለውድቀቱ ከራሱ ወዲያ ማንንም ተጠያቂ ማድረግ አይችልም። እግዚአብሔር «አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አወርዳለሁ» አለ።  በአዲሲቱ ሰማይና ምድር ላይ ለመኖር የሚያበቃ ተገቢ ሥራ የመፈጸም ኃላፊነት የሰው ድርሻ ነው። እግዚአብሔር ለፍሬ የሚያበቁ ሁኔታዎችን ያመቻቻል እንጂ እህል ሰፍሮ ጎተራ አይጨርም። በተሰጠው የጊዜ ሂደት ውስጥ ሰው ድርሻውን መወጣት ይገባዋል። እግዚአብሔር ፈጣሪ እንጂ የሰዎች ጉዳይ ፈጻሚ አይደለም። ስለዚህም በዘመን ለውጥ ውስጥ ሰው ዘመኑን እየዋጀ የሚጠበቅበትን ይሰራ ዘንድ ለውጥ ግድ ይለዋል። በጊዜ ለውጥ ውስጥ ገበሬ ራሱን እየለወጠ ያዘምራል። ለማዝመር ካልፈለገ ደግሞ ለውጡ ሕይወቱን ባልሆነ መልኩ ለውጦት ያልፋል። ኃጥእ ራሱን ከበደል እድፍ አውጥቶ በአዲስ ማንነት ካልለወጠ የሞት ለውጥ በማይፈልገው ማንነት ውስጥ ይለውጠው ዘንድ የግድ ነው። የለውጥ ሃሳብ አስቀድሞ የሚሰራው ከልቡና ውስጥ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።

አንዳንዶች ለውጥን ይቃወማሉ። አለያም ስለለውጥ መዘመር የጊዜ አመጣሽ ሰዎች ጉዳይ አድርገው ያዩታል። አንዳንዴ ደግሞ የስም ዘርፍ አብጅተውለት ለውጥንና መታደስን ሲያጥላሉ ይታያሉ። የሚገርመው ነገር ስለለውጥ የሚዘምሩትንም ሆነ ለውጥን የሚቃወሙትን ያመጣቸው ራሱ ለውጥ መሆኑን አለማወቃቸው ነው።  ራሳቸውን ማየት ባልቻሉበት መጠን የጊዜ ለውጥ በተራው እንዳመጣቸው ይሸኛቸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነገሥታትን ትሾም፤ ትሽር ነበር። ዛሬ በጊዜ ለውጥ የተነሳ ያ ነገር የለም። ይህ ለውጥ ይመጣ ዘንድ አስቀድሞ የለውጥ ሕግጋትን ባለማወቅ የተነሳ ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ መከራን ልታሳልፍ ተገዳለች። የጥንት ተሰሚ ድምጿ ዛሬ የለም። ኃይሏ ቀንሷል። ያልጠፋችውም ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ ነው። ዛሬም ከታሪክ ወይም ከመከራ የተማረች አይመስልም። ስለለውጥ የሚዘምሩትን አትቀበልም። ትቦተልካች ወይም ይቦተልኩባታል። የሩቁን ትተን የቅርቡን ብናነሳ አቡነ ቴዎፍሎስን ለሞት ያበቃው ይህ የለውጥ አስተሳሰብ ነው። አንዱን ስታስገባ አንዱንም ስታስወጣ ከመጓዝ አዙሪት አልወጣችም። ስለለውጥ ባላት ዘገምተኛጉዞ የተነሳ የደረሰባት የታሪክ ጠባሳ ከባድ ነው። የአሜሪካው ኢንስቲቲዩትም ያለው ተመሳሳዩን ቃል ነው። ( If you can change before you have to change, there will be less pain)  ለውጡ ግድ ከማለቱ በፊት መለወጥ ከቻልክ ጉዳቱ አናሳ ነው።

በአንድ ወቅት የአውሮፓ ነገሥታት ሻሚና ሻሪ ወይም አንዱን ደጋፊ አንጃ አስነስታ የበላይነቷን ባልተቀበላት ላይ ታዘምት የነበረችው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማርቲን ሉተርን በመሳሰሉ የአዲስ ለውጥ ባለቤቶች ጥያቄ የተነሳ ካልጠበቀችው አዲስ ነገር ጋር ተላትማለች። የተቃዋሚ ጎራ/ protestant/እንዲፈጠርባት ሆኗል። የአውሮፓ የኢንዱስትሪ አብዮት መነቃቃት፤ አዲስ የተሐድሶና የማሻሻል አስተሳሰቦች መወለድ ካቶሊክን ወደማያበራ ጦርነት እንደከተታት ታሪክ ይናገራል።
ለውጥ የሂደት ክስተት እንጂ ድንገት ብልጭ የሚል የዝናብ መብረቅ ባለመሆኑ ስለለውጥ የሚኖረን ጊዜ ሰፊ ነው። ችግሩ ግን የሚነሳው በዚያ ጊዜ ውስጥ ያለን እይታ ተጋርዶ መቆየቱ ነው። ለውጡ ሰዓቱን ጠብቆ ሲመጣ ማስተናገድ የምንችልበት እውቀት ስለሌለን ለውጡን ለማስቀረት እንታገላለን። ማስቀረት ባልቻልነው መጠን የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ ነው። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን አስተምህሮና ሃይማኖታዊ ባህል በወቅቱ ከተሰከተው የአውሮፓ የተሐድሶ አስተሳሰብና የኢንዱስትሪ አብዮት አዲስ የለውጥ እውቀት ጋር አስማምታ መሄድ ሳትችል በመቅረቷ እንግዳ ከሆነባት ነገር ጋር ለመጋጨት በቅታለች።  ይህንን አዲስ አስተሳሰብና አዲስ የለውጥ ጥያቄ ለመግታት ካቶሊክ በፖፕ ሎዮላ አማካኝነት /regimini militantis ecclesiae/  ወይም የቤተ ክርስቲያን መንግሥት ሠራዊት የተባለውን የጀስዊት ማኅበርን አቋቋመች። ይህም ማኅበር አንድም ተቃዋሚዎችንና /protestants/ ለውጥ ፈላጊዎችን /reformist/ የተባሉትን የሚገዳደር ሠራዊት ሲሆን በማይቀረው ለውጥ ውስጥ ጥገናዊ እርምጃም ለመውሰድ ታስቦ ነበር።
ይቀጥላል//