Thursday, August 9, 2012

ማኅበረ ቅዱሳንን ሲኖዶስ አላዋቀረውም፤ ማኅበሩን በአክራሪነት መፈረጅም ቤተክርስቲያንን መፈረጅ አይደለም!


የዚህ አክራሪ ማኅበር ድረ ገጽ ብጹእ አቡነ እስጢፋኖስ የተናገሩት ነው በማለት እራሱን የሲኖዶስ ተጠሪና የቤተክርስቲያኒቱ ራስ የሆነ ያህል ክብር እንደተሰጠው በመቁጠር «ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበር በአክራሪነት መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን መፈረጅ ነው» ብለዋል ሲል የእወቁልኝ ዜና ለመስራት ሞክሯል።
የተወሰደው ቃል:
«በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት በአንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ስም መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን መጥቀስ በመሆኑ ይህን የሚያደርጉ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸው መታረም እንዳለባቸው አሳስበዋል»
በመሠረቱ ማኅበሩ ራሱ ለደርግ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ብላቴ የጦር ካምፕ ውስጥ ተመሰረትኩ፤ የዳቦ ስሜንም አቡነ ገብርኤል «ማኅበረ ቅዱሳን» ብለው ሰጥተውኛል እያለ በአዋጅ ሲናገር አቡነ እስጢፋኖስ የለም፤ እኛ ሲኖዶሶች ነን የቆረቆርንህ ሊሉ አይችሉም።   የሕይወት ታሪኩ ስለሚታወቀው ማኅበር አፋቸውን ሞልተው ሲኖዶስ ነው የመሰረተው ይላሉ ብለን አንገምትም። ብለው ከሆነም ስህተት ስለሆነ ተቀባይነት የለውም። እውነቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን በድሮው አቶ፣ በኋለኛው ቄስ እንትና የሴቶች ድንግልና የተመሰረተ መሆኑን ጋዜጠኛ ግዛው ዳኜ በፖሊስ ፕሮግራም ላይ ዜና እንደሰራበት የሚዘነጋ አይደለም።
አቡነ እስጢፋኖስ ማኅበረ ቅዱሳንን የመሰረተው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው ብለው ከሆነ መቼ፤ የት፤ እንዴትና ለምን? ተብለው ቢጠየቁ መልሳቸው ምን ይሆናል? ቅዱስ ሲኖዶስ እንደማኅበር ይንቀሳቀስ ዘንድ መተዳደሪያ ደንቡን ስላጸደቀለት እኛ ነን ያደራጀነው ሊሉ አይችሉም። ራሱ ተደራጅቶ በመምጣት እውቅና ስጡኝ ብሎ በጠየቀ ማኅበርና ሲኖዶስ ራሱ ወጣቶችን  በመጥራትና በማቋቋም፤ እንደማኅበር በማዋቀር ይሰራ ዘንድ በማሰማራት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ።  ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን በንጹሃን ሴቶች ደም ጭዳ፤ በእነቄሱ በኩል የተመሰረተና ጥቂት የዋሃንን በማሰባሰብ የተቋቋመ፤ በኋላም ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ሰተት ብሎ በመግባት ያለከልካይ መተኛት እንዲችል፤ የመተዳደሪያውን ቁርበት አንጥፉልኝ ያለ  የጅብ እንግዳ ማኅበር ነው። ከዚህ የወጣ የምስረታ ታሪክ የለውም።
ሌላው አስገራሚውና  ምስክርነት ተሰጠኝ በማለት ጅቡ ያቀረበው የውሸት ቃል፤  «ማኅበሩን በአክራሪነት መፈረጅ፤ ቤተክርስቲያንን መፈረጅ ነው» የሚለው የጅቡ የጩኸት ድምጽ በቤተክርስቲያኒቱ ከለላ ለመብላት ያዘጋጃቸው ጠቦቶች እንዳሉ ያመላከተ ፍንጭ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እኔን መንካት ቤተክርስቲያንን መንካት በመሆኑ በእኔ ላይ ክፉ ነገር የምትጎነጉኑ ሁሉ በየትኛውም ዓለም የቤተክርስቲያኒቱ ክፍል ውስጥ የምትገኙ ሁሉ  ወዮላችሁ! ከመበላት አትድኑም በማለት ራሱን በማግዘፍ ለጥፋት የመዘጋጀቱ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከዚያ ባሻገር ብላቴ ላይ የተቋቋመ የጎረምሶች ቡድን ቢነካ ቤተክርስቲያኒቱ እንደተነካች የሚቆጠርበት አንዳች ምክንያት ሊኖር አይችልም። ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም የዛሬ 2000 ዓመት ገደማ የተመሠረተች ሆና ሳለ የ20 ዓመቱ ጅብ ቁርበቱን አንጥፎ ውስጧ ስለተኛ ብቻ ራሱን የ2000 ዘመን ነባር እንግዳ አድርጎ ሊቆጥር የሚችልበት ምክንያት አይታየንም።

አዎ! ማኅበሩ ይህንን ቢል አያስገርምም።  በአበው የተረት ታሪክ ውስጥ እንደሚነገረው «ፈሪው ልጅ እግሩን እየተበላ፤ ዝም በሉ ጅቡ እየበላኝ ነው» እንዳለው ሁሉ የቤተክርስቲያን መሪዎች  ጅቡ ቤተኞቹን እየቀረጠፈና ለመብላት እያሳደደ ፤ እኔ ነኝ የ2000 ዓመቷ የቤተክርስቲያን ተጠሪ ብሎ ቢናገር አይፈረድበትም። አባቶች መሪዎችን መስክሩልኝ እያለና ያንን የመሪዎች ምስክር ይዞ የቤተክርስቲያኒቱን ጠቦቶች ለመምረጥ ሁኔታዎችን የማመቻቸት መፈክር ካልሆነ በስተቀር ማኅበሩን መንካት ፤ ካዝናውን አላሳይሽም ያላትን ቤተክርስቲያን እንደመንካት ሊቆጠር አይችልም። ይህች « ማኅበሩን መንካት፤ ቤተክርስቲያንን መንካት ነው» የምትለው ምልክት አልባው የጅቡ ዜማ ሊበሉ የተዘጋጁ ጠቦቶች መኖራቸውን አመላካች ነው። ምናልባትም ክስና ውንጀላ የሚቀርብባቸው ጠቦቶች ይኖሩ ይሆናል። አያ ጅቦ አለምክንያት፤ የእሱ መንካት ከቤተክርስቲያን መነካት ጋር ለማያያዝ ባልፈለገም ነበር።
በአፄ ቴዎድሮስ ኃይለኝነት ቤተሰቦቿ ሰለባ የሆኑባት ምንትዋብ የተባለች ጎንደሬ ሴት በአንድ ወቅት በአስለቃሽነት የተጠቀመችውን ቅኔ እዚህ ላይ ብንጠቀም አባባላችንን ያጠናክረዋል።
«አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ
አንድዶ ለብልቦ፤ አቃጥሎ ይፍጃችሁ……»
አለች ይባላል።
ዛሬም ይህ በእንግድነት መጥቶ ቁርበቱን ካስነጠፈ በኋላ እኔን መንካት የ2000 ዓመቷን ቤተክርስቲያን መንካት ነው፤ እኔ የተቋቋምኩት በሲኖዶስ እያለ የጅብ ዜማውን ሲያስተጋባ ዝም ማለት እናንተም ጅቡን ካልሆናችሁ በስተቀር በቤተክርስቲያን ጠቦትነት አንድ በአንድ ተቀርጥፋችሁ መበላታችሁ ሳይታለም የተፈታ ነው።   አንድዶ ለብልቦ እስኪበላችሁ ድረስ ትጠብቃላችሁ?
እኛም ባለን አቅም «ማኅበረ ቅዱሳንን ሲኖዶስ አላዋቀረውም፤ ማኅበሩን በአክራሪነት መፈረጅም  ቤተክርስቲያንን  መፈረጅ አይደለም!» እንላለን።