Saturday, August 11, 2012

አዲሱ የግብጽ ሕገ መንግሥት እስልምና የመንግስት ሃይማኖት መሆኑን ያውጃል!

የሙስሊም ወንድማማቾች መሪና በሙባረክ ዘመን ከርቸሌ ወርደው የነበሩት ሙሐመድ ሙርሲ ስልጣን ላይ ይወጣሉ ተብሎ ከተፈራበት ጊዜ አንስቶና ስልጣኑ ላይ ከተፈናጠጡ ጀምሮ የግብጽ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ። ከግብጽ ክርስቲያኖች ውስጥ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኞች እስከ 15 ሚሊዮን በሀገር ውስጥ ሲኖሩ ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉት ደግሞ በተለያዩ ዓለማት ውስጥ ተሰደው ይገኛሉ። እስከ 640 ዓ/ም ድረስ የግብጽ ሕዝብ 100% የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የነበረ ሲሆን በእስልምና ወረራና መስፋት የወደደ በውድ፤ ያልፈለገ በግድ እስልምናን እንዲቀበል ተደርጎ፤ የተረፈውም የእስልምናን የበላይነትና የሚጣልበንት ቅጣት ለመቀበል የመስማማት ውል ገብቶ እንደክርስቲያን ለመኖር የቻለ ቢሆንም ከመገደል፤ ከመሰደድና ንብረቱን ከመቀማት አላመለጠም ነበር።  ከጋማል አብደል ናስርና፤ በይበልጥም በሁስኒ ሙባረክ አገዛዝ ዘመን የተሻለ ዋስትና የነበራቸው ቢሆንም ከግብጹ የአመጽ እንቅስቃሴ ወዲህ ነገሮች ሁሉ ተለዋወጠው ኮፕቲኮቹና የሶሪያ ኦርቶዶክስ፤ የግሪክ ኦርቶዶክስ፤ የሮማ ካቶሊክ፤ ፕሮቴስታንትና ሌሎች ክፍሎችም ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ክርስቲያኖች አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ። ይህ አደገኛ ሁኔታም በመረቀቅ ላይ ባለው አዲሱ የግብጽ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 2 ላይ እስልምና የመንግሥቱ ሃይማኖት መሆኑን በማስቀመጡ የተነሳ ነው። ይህም ማለት ይላል «ክሪስቲያን ፖስት» ጋዜጣ ህግ አውጪው ህጎችን የሚያወጣው በእስልምና ሃይማኖት መሰረትነት ላይ ስለሆነ በአጭር ቃል የሀገሪቱን ህግ የሸሪአ ህግ ይመራዋል ማለት ነው ይለናል።
በዚህ የእስልምና ህግ ስር ክርስቲያኖች ለመኖር የሚችሉት እስልምናው በሚፈቅድላቸው መንገድና መጠን ስለሚሆን በሀገሪቱ ውስጥ እንደዜጋ ሳይሆን እንደባሪያና አሳዳሪ ስርዓት የመኖር ግዴታን የሚቀበሉ ይሆናሉ ማለት ነው። መሐመድ ሙርሲ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንደሚያቋቁሙ ቃል ቢገቡም እየሆነ ያለው ግን ዲሞክራሲውን የሚለካው የመንግሥቱ ሃይማኖት እንጂ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እንዳይደሉ እየታየ ነው።
በሸሪአ ህግ መሰረት የሰረቀ እጁን እያፈራረቁ መቁረጥ፤ በዝሙት የተገኘ በድንጋይ ተደብድቦ መገደል፤ ከእስልምና ወደክርስትና የገባውን አልመለስም ካለ ማረድ፤ እንዲቀየር ያባበለውን ዛፍ ላይ መስቀል ወዘተ ቅጣቶች ክርስቲያኖችን ይጠብቃቸዋል ወይ? ለሚለው ጥያቄ እስካሁን በይፋ የተነገረ ባይሆንም የእስልምና መንግሥት እስከተቋቋመ ድረስ ይህ መሆኑ ስለማይቀር ብዙዎቹን ክርስቲያኖች ድንጋጤ ላይ ጥሏቸዋል።
ሰላፊዎች የሸሪአ ህግ በሀገሪቱ እንዲተገበር ጫና እየፈጠሩ ሲሆን ክርስቲያን የሆነ ማንም በእስልምናው መንግሥት ውስጥ መስራት የለበትም የሚል አክራሪነት እያወጁ ይገኛሉ። ምንም እንኳን በቀጥታ ክርስቲያኖችን ወደእስልምና ማምጣት እንደማይችሉ ቢያምኑም ሰለፊዎች የሚያደርጉት ግፊት ክርስቲያኖች መጪውን ጊዜ በመፍራት ሀገሩን እየለቀቁ ወደምእራቡ ዓለም እንዲሰደዱ ተጽእኖ  የማድረግና ፍርሃትን የማስፈን ስራ እየሰሩ እንደሆነ ተገምቷል።
ይህ እንቅስቃሴ በገፍ በሚፈሰው የፔትሮ ዶላር ድጋፍ  አፍሪካን በሸሪአ የመንከር ትልቁ ዘመቻ አካል ሲሆን ግብጽን በምታክል ትልቅ የዐረቡ ሀገር ምሳሌ ውስጥ ክርስትና እንዴት ይታሰባል? የሚል ቁጭት አላቸው። አህመድ ዲዳት የሚባል የእስልምና ቀንደኛ ሰባኪ በአንድ ወቅት ግብጽ የዐረብ ሊግ ዋና ተጠሪ ሆና ሳለ በግብጽ ውስጥ ሚሊዮኖች ክርስቲያኖች መኖራቸው የሙስሊሙ ዓለም የስንፍና ውጤት ነው በማለት በቁጭት ሲናገር መደመጡ የቁጭቱ ጣሪያ የት ድረስ እንደሆነ ያሳያል።
 ከሊባኖሱ ሂዝቦላህ፤ ከፓለስቲናው ሃማስ እና የመሐመድ ሙርሲው ብራዘር ሁድ የተሳሰረ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ቁርኝት እንዳላቸው ስለሚታወቅ መካከለኛው ምሥራቅን በዚህ የሰለፊ ባህር ውስጥ የመንከር ስውር ዘመቻ አንዱ ክፍል በግብጽ ላይ መቀመጡ የክርስቲያኖቹን መጪ ዘመን ከባድ ያደርገዋል። እስልምናዊ መንግሥት ማለት የዚያ ትግል ውጤታቸው ነው።
የዚሁ ዘመቻ ዋና አካል የሆነው የሰለፊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመቻውን  እያጧጧፈ ይገኛል። የሰለፊ እስልምናን ምንነትና የመስፋፋት ዓላማ በውል ያልተገነዘቡ፤ ከዚያም አለፍ ሲል በጭፍን የጥላቻ ፖለቲካ የታወሩና ስልጣን በቦሌ ወይም በባሌ እጃችን ይግባ እንጂ የሚሉ የጥፋት ተባባሪዎች የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መብት ይከበር ከሚሉ ሰይፍ አምላኪ ሰለፊዎች ጋር  ቀንና ሌሊት ሲጮሁ መስማት አሳዛኝ ነው።  የኢትዮጵያ መንግሥት አንባ ገነን ስለሆነ እንታገለዋለን ማለት አንድ ነገር ነው። እስልምናው ውስጥ ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን እየተቃወሙት ሳለ የእስልምና መብት ተከራካሪ ለመሆን የሚፈልጉ ሃይማኖት የለሾች ለእስልምና እንታገላለን ሲሉ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል። ሰለፊዎች እስልምናን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማራመድ በህግ ወይም ያለህግ  ታገድን ሳይሆን እያሉ ያሉት አሁን ያሉትን መጅሊሶች እናውርድ  ነው። ጥያቄውን ከሃይማኖት መብት ጋር በማስተሳሰር የመብቴ ተነካ ጩኸት በማሰማት ከሚመኙት ግብ ለመድረስ የሚደረግ ሩጫ እንጂ እስልምናን  እንደሃይማኖቴ እንዳላመልክ ተከልክያለሁ አይደለም የሚለው።  የመጅሊሱ ችግርና የአዲስ መጅሊስ ምርጫ ፈላጊዎች ማንነት በተነጻጻሪ የሚታይ ነገር እንጂ በዘመቻና በሆ በለው የሚተገበር አድርጎ ማቅረብ ጉዳዩን አጡዞ ሀገር ዐቀፍ ለማድረግ በመሞከር እቅዱ እስኪሳካ መሄድ የተፈለገበትን መንገድ የሚጠቁም እንደሆነ ያሳያል። መጅሊሱን በዓላማው አስፈጻሚ ሰዎች ከቀማ በኋላ በሚጫንለት የፔትሮ ዶላር አክራሪነት መኪና እንደፈለገ ለመሽከርከር ተፈልጎ መሆኑ ለመረዳት ከማንነት ባህሪው መረዳት አይከብድም።

መሐመድ ሙርሲ ስልጣን ላይ ባይመጣ ኖሮ ሰለፊዎች የእስልምና መንግሥት ማግኘት አይችሉም ነበር። እንደዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰለፊዎች መጅሊስ የተባለውን ስልጣን በምርጫ ቀምተው የእስልምና አመራር በራሳቸው አክራሪዎች መተካት ካልቻሉ በስተቀር የሀገሪቱን እስላም መቆጣጠር አይችሉም፤ ስለዚህ «ዓባይም ይገደባል፤ መጅሊስም ይወርዳል» በሚል መርህ ሁለት ስለት ያለውን ሰይፍ ይዘው ቢጮሁ ለእስልምና መብት ጥሰት መከበር ሳይሆን የሰሃባዎች መሸሸጊያ ሀገር ዳሩ ቢላል ኢትዮጵያ እንዴት ከዐረብ ሊግ ውጪ ትሆናለች የሚል እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ለአፍታ የዘነጋ ቢኖር የችግሩን ጥልቀት ለማወቅ  የግብጽ ክርስቲያኖችን ሄዶ እንዲጠይቅ እንመክረዋለን።
ግብጽ ዛሬ እስልምና የመንግሥቱ ሃይማኖት መሆኑን የሚያውጅ ህገ መንግሥት እያረቀቀች ትገኛለች።
 እንደዚሁ ሁሉ ነገ፤ ተነገ ወዲያ  ቢያንስ በአንድ ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ እስልምና የመንግሥት ሃይማኖት መሆኑ ይታወጅ ባይሉ 99%  እስልምና ባለባቸው አፋር፤ ሀረሪና ሱማሌ ክልሎች እስላማዊ ሸሪአ ይቋቋም የማይሉበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እስላሞች የሚጠቀሙበት አንዱ ስልት እስልምና በበዛበት ቦታ ህዝቡ  ይወስን የሚል መከራከሪያን ከዲሞክራሲያዊ መብት ጋር የሚያያይዙበት ጥበብ ለአብነት ይጠቀሳል። ዛሬም የመጅሊሱ ይውረድ ዜማ የዚህ ዘዴ ማሳያ ነው። መንግሥት መሰሪዎች የሚፈነጩበት የተነቃነቀ ቤት እንዳይኖር ማገሩን እንዲያጠብቅ እንመክራለን፤ እንጠይቃለንም። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተበደሉ እያሉ «ከአልጀዚራ ሙባሸር፤ እስከ አል- አረቢያ ጣቢያዎች የሚጮሁት የተወጠነው እቅድ ከግብ ሳይደርስ ስለተጨናገፈ እንጂ ለሰብአዊ መብት ተጨንቀው አይደለም። በሳዑዲ ዐረቢያ ስለታሰሩ ክርስቲያኖች ነጻነት ምነው አልተነፈሱ?
ዓላማቸው ግብን ጠቅልለው ወዳስገቡበት የራሳቸው እስላማዊ ኪንግደም  ኢትዮጵያንም የመጠቅለል ራእይ ስላላቸው ብቻ  እንደሆነ ልናውቀው ይገባል። ግብጽ አሁን እየተገፋች ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት ወደፊት የጥፋት አውድማም ልትሆን ትችላለች ብሎ መገመት ይቻላል።  ወደ ሃያ ሚሊዮን የሚጠጋ ክርስቲያን በምን ስሌት ነው መንግሥታዊ እስላም ውስጥ በእምነት ነጻነት መኖር  የሚችለው የሚል ዋና ጥያቄ ይሆናል። ግብጽና መካከለኛውን ምሥራቅ፤ ግብጽና ዓለም ዐቀፉ የጂኦ ፖለቲካ ትኩሳት እንዲሁም የክርስቲያኖቹንና  የእስላማዊ መንግሥቱን መጪ ሂደት አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይገመታል።
ግብጽ በታሪኳ አንድም ጊዜ ጠፍታ የምታውቅ ሀገር አይደለችም። ዓባይም ደም ከመሆኑ በስተቀር ደርቆ፤ ምድረ በዳ ሆኖ የሚያውቅበትን ዘመን ታሪክ ጽፎልን አልተወም።  የግብጽ ወደአክራሪ እስልምና የመሄድ ጉዞ ለእርስ በእርስ እልቂት ይዳርጋት ይሆን?  ሰዓቱ ደርሶ የዓባይ ወንዝ መገደብም  ምናልባት በኢሳይያስ 19 ላይ የተጠቀሰው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ዘመን ቀርቦ ይሆን? ብለን ብንጠይቅ ከሊቃውንቱ ብዙ ትርጉም ጋር ግምቶቻችንን ብናስቀምጥ የትንቢቶች ፍጻሜ ደረሰ እንዴ? እንላለን ።   የዚህን ትንቢት መቼት ማን ይንገረን?
«ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል። ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ። በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም። ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ።«ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል»
 እስከዚያው ግን ግብጽ የአክራሪ እስልምና ሀገር የመሆኗ ነገር ተጀምሯል፤ መጨረሻውስ?