Tuesday, August 14, 2012

ሃሌ ሉያ

የሕይወታችን ባለቤት፤ የመዳናችን ዋስትና፤ የዘላለማዊነት ርስት ለሆነው ለእግዚአብሔር ብቻ የተገባ ይህንን የግጥም ምስጋና ስለወደድነው ከቤተ ጳውሎስ ብሎግ ላይ ወስደን አካፍለናችኋል። ለመዳናችን ሌላ ምስጋና ለማን? ዳዊትም ያለው ይህንን ነው።

መዝ 44፤20-21
የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥
እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና።

ቤተ ጳውሎስ ማክሰኞ ሐምሌ 8/2004 ዓ.ም.

ሃሌ ሉያ ለአብ
ሃሌ ሉያ ለወልድ
ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ
ሃሌ ሉያ በአርያም ላለኸው
ሃሌ ሉያ በልቤ ለነገሥከው
ሃሌ ሉያ ለጥልቁ መሠረት
ሃሌ ሉያ ለምጥቀቱ ጉልላት
ሃሌ ሉያ ለዳርቻዎች ወሰን
ሃሌ ሉያ ከአድማስ ወዲያም ላለኸው
ሃሌ ሉያ ዓመታትን ላስረጀው
ሃሌ ሉያ ሕዝቡን ለታደግኸው
ሃሌ ሉያ ብርሃናትን ለፈጠርከው
ሃሌ ሉያ ስሜን ለለወጥከው
ሃሌ ሉያ ለድካሜ ምርኩዝ
ሃሌ ሉያ ለምስኪንነቴ ሞገስ
ሃሌ ሉያ ለተጨነቁት ዕረፍት
ሃሌ ሉያ ለታወኩት ፀጥታ
ሃሌ ሉያ ሸክም ለተጫናቸው ወደብ
ሃሌ ሉያ ስንጥቁን ልቤን ገጥመህ ለያዝከው
ሃሌ ሉያ በመጽናናትህ ለጎበኘኸኝ
ሃሌ ሉያ ከጥልቁ ስጮህ ለሰማኸኝ
ሃሌ ሉያ ከደጅ ስፈልግህ በውስጤ ላገኘሁህ
ሃሌ ሉያ በማይቻለው ቀን ለቻልኩብህ
ሃሌ ሉያ ለባልቴቲቱ ዳኛ
ሃሌ ሉያ ለሙት ልጅ ሰብሳቢ
ሃሌ ሉያ ለበረሃ ጥላዬ
ሃሌ ሉያ ለምድረ በዳው ጓደኛዬ


ሃሌ ሉያ አፍረህ ለማትገባው
ሃሌ ሉያ ለሰልፉ ጌታ
ሃሌ ሉያ ክንድህ ለማይታጠፈው
ሃሌ ሉያ እጅህ ለማይነጥፈው
ሃሌ ሉያ ፊትህ ለማይጠቁረው
ሃሌ ሉያ ልብህ ለማይጨክነው
ሃሌ ሉያ ብቸኛውን ለምትፈልገው
ሃሌ ሉያ የተበተኑትን ለምትሰበስበው
ሃሌ ሉያ የተገፉትን ለምታስጠጋው
ሃሌ ሉያ ለድምፅ አልባዎች ለምትሟገተው
ሃሌ ሉያ በሚፈርዱት ላይ ለምትፈርደው
ሃሌ ሉያ የሚያስፈሩት ለሚፈሩህ
ሃሌ ሉያ ጨካኞች ለሚገዙልህ
ሃሌ ሉያ አጋንንት ለሚንቀጠቀጡልህ
ሃሌ ሉያ ብርቱዎች ለማይችሉህ
ሃሌ ሉያ ጀግኖች ለሚማረኩልህ
ሃሌ ሉያ ነገሥታት ዘውድ አውልቀው ለሚሰግዱልህ
ሃሌ ሉያ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ለሆንከው
ሃሌ ሉያ ለጥንቱ አልፋ
ሃሌ ሉያ ለዛሬው ሕያው
ሃሌ ሉያ ለመጨረሻው ዖሜጋ
ሃሌ ሉያ ለማትቀረው ተስፋ
ሃሌ ሉያ ወዳጅነትህ ለማይለወጠው
ሃሌ ሉያ ዳርቻችንን ላሰፋኸው
ሃሌ ሉያ ስለ ታማኝነትህ ላሰብከን
ሃሌ ሉያ ከጥሩ ውኃ ላጠጣኸን
ሃሌ ሉያ በሞገስ ለከለልከን
ሃሌ ሉያ በግርማ ላጠርከን
ሃሌ ሉያ በስምህ ለሰበሰብከን
ሃሌ ሉያ በክብርህ ላከበርከን
ሃሌ ሉያ በሥራህ ላስደነቅኸን
ሃሌ ሉያ ዘንበል ብለህ ለሰማኸን
ሃሌ ሉያ ታናሽነታችንን ላልናቅኸው
ሃሌ ሉያ ብዙ ዘመን ለታገሥከን
ሃሌ ሉያ በምሕረት ለከለልከን
ሃሌ ሉያ በመልካም ላሰብከን