ሰልሞንና ካሌብ ሊሰልሉ ወጥተው
ከዔናቆች መንደር አጥር ከከበው፤
ኢያሪኰ ገቡ ዮርዳኖስን አልፈው።
ግዙፋን አህዛብ ጥብቅ ሆኖ በራቸው ፤
ጥንካራ የነበር መግቢያና መውጪያቸው።
መሹለኪያ በሌለው መዝጊያ ገረገራ፤
ሰርጎ ይገባ ዘንድ ፤እስራኤል አመራ፤
ጸጉረ ልውጥ ሰው ቢታይ በመንደሯ
ከበባ ታወጀ ከዔናቆች ጭፍራ።
ሰልሞንና ካሌብ በነፍስ አድን ሩጫ
መሸሸጊያ ሲሹ ከገዳይ ማመለጫ
ፈጣሪ አዘጋጀ፤ የከተማ ዋሻ
ከዔናቅ ሰራዊት መዳኛ መሸሻ
አንድ ሴት ነበረች ዘማነቷን ፈታ
ባል አልቦ የሆነች፤ በሕይወት ከርታታ
ብለው የሚጠሯት ረዓብ ጋለሞታ።
ሰዎቹን ሸሸገች ከቤቷ ውስጥ ጓዳ፤
በተልባ እግር ሽፋን፤ አድርጋ መከዳ።
ገዳይ ወገኖቿ አልፈው እንደሄዱ
ካሌብ፤ ሰልሞንም ውለታ እንዳይክዱ
ቃል ታስገባ ጀመር፤ ሀገሯን ሲንዱ።
ሰባ ነገሥታትን ከፊት ያደቀቀ
ዮርዳኖስን ከፍሎ በየብስ ያደረቀ
ሕዝቡን እየመራ ለድል የጠበቀ
ነውና አምላካችሁ ክንዱ የታወቀ
ኢያሪኰን መጣል እንደሚችል አየሁ፤
ኃጢአት የከበዳት፤ ረዓብ እባላለሁ፤
እባካችሁ ያኔ፤ ታደጉኝ እኔን፤
አብሬ አልጥፋ፤ ምሕረት አርጉልኝ
ብላ ብታነባ፤ ሰባብራ ልቧን
ገረመው ካሌብን፤ ደነቀው ሰልሞንን
ከሴት አመንዝራ፤ ድንገት ማግኘቱን
የእስራኤልን አምላክ፤ የሚያውቅ አምላኩን
ካሌብም ነገራት፤ አንቺና ቤትሽ፤
በዚያን ቀን ስንመጣ ሲፈርስ ሀገርሽ፤
በኛና ባንቺ ይሁን ይሄ መለያሽ፤
ጉበን ላይ ይንጠልጠል፤ መግቢያ ከበርሽ፤
እርቃችን ቀዩ ነው፤ ከሞት ማምለጫሽ፤
ከርስታችን ርስት፤ የሚሆን ቁጥርሽ፤
አደራ ሴቲቱ፤ አደራ ብለናል፤
የደም ምስል ጨርቁ፤ አጥብቆ ይንጠልጠል ፤
አሉና ነገሯት፤
ሲደርስ የቀኑ ቀን ፤ ኢያሪኰን ጥለን፤
አትጠራጠሪ እናድንሻለን።
እንዳሉ ሆነላት፤ ባዳኝ ምልክቱ፤
በቀዩ ጥለት ላይ ተሻረላት ሞቱ።
አዲሱ ሰው ዛሬ፤ ረዓብን የመሰልህ፤
ከሞት የሚያድንህ ሕያው ምልክትህ፤
መስቀል ላይ ተሰቅሎ፤ የተንጠለጠለው፤
በልብ ጉበን ላይ ሰቅለህ ስትይዝ ነው።