Monday, August 20, 2012

ሰበርዜና፡-በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘወረ ያለውና መሪውን ያጣው ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ከአመራር ሰጪነት ለማውረድና ዐቃቤ መንበር በአፋጣኝ ለመሰየም ለነገ ቀጠሮ ይዟል

 የደርግ  ርዝራዥ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን፤ ደርግ ሲያስተጋባ እንደነበረውና « ተፈጥሮን ሁሉ በቁጥጥራችን ስር እናደርጋለን» ሲል እንደነበረው ሁሉ ብላቴ ጦር ካምፕ ላይ ከውትድርና ወደ ስመ ቅድስና ሺፍት በማድረግ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ስሩን የዘረጋው ማኅበር፤ የቅዱስ የፓትርያርኩ ሞት ሳይታሰብ እንደተገኘ ሎተሪ በመቁጠር የራሱን ንጉሥ ቀኑ ሳይመሽ ለማሾም የሞት ሽረት ትግሉን እያደረገ «ቤተክርስቲያንን በቁጥጥራችን ስር እናደርጋለን» በሚል መንፈስ እንደአባቱ ደርግ እየሰራ ይገኛል። ቁጭ ብለው የሰቀሉት፤ ቆሞ ማውረድ እስኪቸግር ድረስ ይህ ማኅበር ጳጳሳቱን እያስፈራራና በገመናቸው ሳቢያ እያሸማቀቀ ተሰብሰቡ ሲላቸው፤ የሚሰበሰቡ፤ ተበተኑ ሲላቸው የሚበተኑ የምስኪናን ጉባዔ ሆነዋል። የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ ዐቃቤ መንበር እንዲሾም፤ እስከዚያው ድረስ በዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስና ቋሚ ሲኖዶስ እንዲመራ የተወሰነ መሆኑ ቢታወቅም የዚህንን ቆይታ ጊዜ በማስላት ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል ያረጋገጠው ክፉው ማኅበር፤ ሲኖዶሱ በአስቸኳይ ተሰብስቦ አስተላልፎ የነበረውን ውሳኔ እንዲሽርና አቡነ ናትናኤልን ዐቃቤ መንበር አድርጎ እንዲያስቀምጥለት ባስተላለፈው ትእዛዝ መሠረት አቤት፤ ወዴት እያሉ ለመሰብሰብ ፈቃደኛ ሆነውለታል።  እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ የሚባለው ዛሬ ነው። አስተዳዳሪዎች፤ ካህናትና፤ዲያቆናት፤ አበው መነኮሳት ዛሬ ያልተናገራችሁ ነገ መራራ ዘመናችሁ ከደጃችሁ ቆሟል።
የዓውደ ምሕረትን ዘገባ ከታች አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ!

ማኅበረ ቅዱሳን አቡነ ናትናኤል ይሁኑልኝ ብሏል።

(ዐውደ ምሕረት፤ ነሐሴ 13 2004 ዓ.ም. / www.awdemihret.blogspot.com //www.awdemihret.wordpress.com) የአቃቤ መንበሩን ምርጫ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር በኋላ ይፈጸማል ብሎ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ የአቡነ ፊሊጶስ የሰሞኑ አካሄድ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ስላልተወደደ የአቃቤ መንበሩን ምርጫ በነገው ዕለት ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን ወስኗል ተባለ።
     ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ መልካም ሥራዎቻቸውን እያኮሰሱና እንከን እየፈለጉባቸው ክፉኛ ሲያብጠለጥሏቸውና ሲያሳዝኗቸው የነበሩ ብዙዎች፣ ቅዱስነታቸው ካንቀላፉ በኋላ የእርሳቸው መልካም ስራዎችና ተሸክመው የነበሩት ትልቅ ሀላፊነት ከባድ መሆኑንና ብዙ ኅልፈታቸው እንዳጎደለ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ በመሆኑም ያለማንም አስገዳጅነት የቅዱስነታቸውን መልካምነት በመመስከር ሥራ ተጠምደዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ይጠቀሳሉ፡፡
   በማኅበረ ቅዱሳን ወዳጅነታቸው የሚታወቁትና ማህበሩ አውጆት በየአዳራሹ ሲያካሂድ ለነበረው የተሀድሶ ግንዛቤ ማስጨበጫና ገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ባራኪ የነበሩት ብፁዕነታቸው አሁን የቅዱስነታቸውን በአይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ መልካም ገጽታቸውን መገንባታቸው በማኅበረ ቅዱሳን ዘንድ አልተወደደም፡፡ ስለዚህ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ከዚህ ወሳኝ ጨዋታ ውጪ ለማድረግ ሲባል፣ ከቅዱስነታቸው ስርአተ ቀብር በኋላ ሊከናወን ቀጠሮ የተያዘለት የዐቃቤ መንበር ምርጫ በነገው ዕለት እንዲካሄድ በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘወረ የሚገኘውና ሁነኛ መሪውን ያጣው ሲኖዶስ መወሰኑን ውስጥ አዋቂዎች ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
     ቅዱስ ሲኖዶሱ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ ባደረገው የመጀመሪያ ስብሰባው ብጹዕ አቡነ ፊልጶስ እስከ ሥርዓተ ቀብር ድረስ በሲኖዶስ ሰብሳቢነት እንዲቆዩ ወስኖ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ግን በፓትርያርኩ ድንገተኛ ሞት የተነሳ ቤተክርስቲያኒቱ ወደ አለመረጋጋት እንዳትሔድ ብጹዕ አቡነ ፊልጶስና መሰሎቻቸው በሚያደርጉት አዎንታዊ እንቅስቃሴ ለማህበረ ቅዱሳን ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ ተገዢ ባለመሆናቸው እና ማኅበርዋ ባቀደችው መሰረት ነገሮች ሊሄዱላት ስላልቻሉ፣ በሰብሳቢነት እንዲቆዩ ከተወሰነ ከሁለት ቀን በኋላ የዐቃቤ መንበሩ ምርጫ በነገው ዕለት እንዲደረግ ተወስኗል።
     ቅዳሜ ዕለት የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴው የቅዱስነታቸው ቀብር በስራ ቀን ስለተደረገ ወደቅዳሜ ይዘዋወርልን የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ “አንዴ ለሚዲያ የተናገርነውን ነገር አንሽርም ህጻናት አይደለንም።” በማለት ውድቅ ያደረጉት ጳጳሳት አሁን ግን የማኅበረ ቅዱሳንን ፍላጎት ለመፈጸም ሲሉ የአቃቤ መንበሩን ሹመት ከቅዱስነታቸው ቀብር በኋላ ይፈጸማል በማለት ለሚዲያ የተናገሩትን ቃላቸውን ሽረው በእነሱው አነጋገር “የሕጻን ስራ” ሰርተዋል።
     ማኅበሩ መንግስትን በጣልቃ ገብነት እየከሰሰና ስሙን እያጠፋ ራሱ ግን ይህን ዕድል ተጠቅሞ የራሱን ሰው ለማስመረጥ መንገድ ጠራጊ የሚሆኑለትን በዐቃቤ መንበርነት ለማስመረጥ ተግቶ እየሰራ ሲሆን፣ ስውሩም ግልጹም አመራር በከፍተኛ ስብሰባ ተጠምደዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሥራቸውን ሁሉ ትተው በጉዳዩ ላይ ተግተው እየሰሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡
   ከቀድሞ ጀምሮ በጳጳሳቱ በኩል ያለውን ስራ በማከናወን የሚታወቀውና አቡነ ጳውሎስን አምርሮ የሚጠላው ማንያዘዋልም ጳጳሳቱን የማግባባት ስራውን እየተወጣ ሲሆን፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ያመነበትን ሰው ለማስቀመጥ ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደሌለው አውቆ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በነገው ዕለት ሊደረግ ለተወሰነው የአቃቤ መንበር ምርጫ ሊመረጡ የሚገባቸው አቡነ ናትናኤል መሆናቸውን ዛሬ ማምሻውን እየዞሩ ጳጳሳቱን በማግባባት ስራ ተጠምደው ያሉት አቡነ ህዝቅኤል እና በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ለፓትርያርክነት ተስፈኛ የተደረጉት አቡነ ሉቃስ መሆናቸው ታውቋል።
   አቡነ ናትናኤል ከእርጅና ብዛት ሽንታቸውን እንኳ መቆጣጠር የማይችሉ አባት ሲሆኑ ስብሰባ የመምራትም ሆነ ተናግሮ የማሳመን ብቃት የሌላቸው ሰው መሆናቸው ይታወቃል። በእሳቸው በኩል ያሉት ጉድለቶች እና የጤና እክላቸው የታወቀ ቢሆንም የማኅበረ ቅዱሳንን አላማ በማስፈጸም ረገድ የተሻሉ ሰው በመሆናቸው እንዲመረጡ የማግባባት ስራው ተጀምሯል። የማኅበሩ አላማ እሳቸውን ዝም ብሎ አስቀምጦ በ2001 ዓ.ም. ቅዱስ ፓትርያርኩን ከስልጣን ለማውረድ ተቋቁሞ የነበረው አቡነ ጢሞቴዎስ፣ አቡነ ሳሙኤል አቡነ እስጢፋኖስ እና አቡነ ሉቃስ የሚገኙበት የማኅበረ ቅዱሳን ታማኝ የሆኑ ጳጳሳት ኮሚቴ እንዲመራው ለማድረግ ነው።


     የማኅበሩ ጉዳይ አስፈጻሚ ከሆኑት ጳጳሳት ጋር በመመካከርም ማኅበሩ አሁን በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ የስልት ለውጥ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ወጣቶቹና ብዙ ጉድ ያለባቸውን፣ እንኳን ለጵጵስና ለሌላም የማይታጩትን እነአባ ሳሙኤልንና የጉድ ሙዳዩን አባ አብርሃምን ተናጋሪ በማድረግ ቅዱስነታቸውን ሲያሳዝኑ የነበረ መሆኑ ሲታወስ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እነዚህን ወጣቶቹን ጳጰሳት ዝም እንዲሉና ከሽማግሌዎቹ ወገን የሆኑት እንዲናገሩ ትእዛዝ ያስተላለፈላቸው ሲሆን በዚሁ መሰረት አቡነ ቄርሎስ፣ አቡነ ጢሞቴዎስ እና አቡነ ናትናኤል ተናጋሪዎች ሆነዋል፡፡
     አለብቃታቸው ፕትርክናውን በእጄ አስገባለሁ ብለው ሲደክሙና ቅዱስነታቸው አርጅተዋል፤ እንደራሴ ያስፈልጋቸዋል የሚል ቅስቀሳ በማድረግ የመንግስትንም ሰዎች ይዣለሁ ሲሉ የበሩትና በችኮላቸው ከቅዱስነታቸው ጋር እስከ መጋጨት ደርሰው የነበሩት አባ ሳሙኤል፣ ማኅበሩ ለክፉ ቀን ሲጠቀምባቸው እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፣ የማኅበረ ቅዱሳን ተከፋይ መጽሔት እንደሆነ የሚታወቀው ዕንቁ መጽሔት እንኳ፣ የሲኖዶስ ስብሰባ በቀረበ ቁጥር የቅዱስነታቸውንና የአቅሙን አያውቅ አባ ሳሙኤልን ፎቶ ግራፍ በፊት ለፊት ገጹ ላይ በጉልህ በማውጣት ቀጣይ ፓትርያርክ እርሳቸው ሊሆኑ ይገባል በሚል አይነት የገጽታ ግንባታ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ አባ ሳሙኤልም የተለያዩ ሰዎች የጻፉትንና በስማቸው ያሳተሟቸውን ጥቂት መጻሕፍት በመደርደር ብዙ መጽሐፍ የጻፈ ጳጳስ እኔ ነኝና ፕትርክናው ለእኔ ይገባል የሚል አይነት የገጽታ ግንባታ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን የእነሚጡ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ከፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰትና ቅጥ ያጣ ሙስና አንጻር እንኳን ለፕትርክና ለጵጵስናም የማይመጥኑ መሆናቸውታውቋል፡፡
     ማኅበረ ቅዱሳን ለፓትርያርኩ ምርጫ መንግስት እጁን ሊያስገባ ይችላል ስለዚህም ጥንቃቄ ይደረግ እያለ መንግስት ምንም አይነት የሚታይ ፍላጎት ባላሳየበት ሁኔታ በርና መስኮቱን ዘግቶ የራሱን ፍላጎት ለማስፈጸም ያለእረፍት እየተሯሯጠ ይገኛል። ጣልቃ ገብነት በማንም ይምጣ በማን ሊገታ የሚገባው ተግባር ነው። መንግስትን ኮንኖ የኔን ተቀበሉ ማለት ግን የበሽተኛነት ምልክት ነው። ስለዚህም አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆምና ለመከታተል ህጋዊ ስልጣን ያለው መንግስት ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር እያደረገ ያለውን ህገወጥ እንቅስቃሴ እንዲያስቆም እና ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተተኪውን አባት የምትመርጥበት ሁኔታ እንዲኖርና አባቶችም ከማኅበረ ቅዱሳን ወከባ ተላቀው ያመኑበትን እንዲወስኑ ተገቢውን የህግ ከለላ በመስጠት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ ቢያደርግ ይበጃል እንላለን።