Thursday, August 2, 2012

በአሜሪካ ምዕራብ ስቴቶች እየተደረገ ያለው የካህናት ውይይት ተጠናክሮ ይቀጥል!


«ሕመሙን የሸሸገ መድኃኒት የለውም» እንዲሉ አበው በአሜሪካ ምዕራብ ስቴቶች የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ልዩ ልዩ ክፍል ሠራተኞች በመካከላቸው ያለውን ፈውስ ያጣ በሽታ ምንነትና መንስኤ በማጥናት ውሳኔ ላይ ለመድረስ መወያየት ከጀመሩ ሰንብተዋል።
አንዳንድ ተሰብሳቢዎች ግን ስብሰባውንና የውይይቱን መንፈስ የሚደግፉ እየመሰሉ ውጤት ላይ ከመድረሱ በፊት መረጃ በማሹለክና የስብሰባውን የውይይት መንፈስ በማጦዝ ጊዜ ሲገድሉ ታይተዋል። በቅዱስ ፓትርያርኩ በኩል ያላቸውን ተደማጭነት ለማስጠበቅ ጠቃሚ ሃሳብ ለጉባዔው የሚያቀርቡ በመምሰልና በሌላ በኩልም በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ያላቸውን ስውር ታማኝነት ላለማጣት  በውይይት ወቅት ጊዜ በመፍጀትና አንድ ሃሳብ ላይ ችክ በማለት የሴራ ጥበባቸውን ለማሳየት ሞክረዋል።
ስለሆነም ለካህናቱ የውይይት መንፈስ የምናቀርበው ሃሳብ በሰዎች ብዛትና ባላቸው ታዋቂነት ላይ እምነት ከመጣል ይልቅ ውጤታማ ሃሳብ በሚያቀርቡና ሥራውን ተፈጻሚ ለማድረግ በሚተጉ ጥቂት በሳል ሰዎች ላይ በመመስረት ለመስራት መሞከሩ የተሻለ ነው። ምክንያቱም ይህንን ቀና ሃሳብ የሚደግፉ ብዙ ካህናት ቢኖሩም እንኳን ሸምቆ ወጊው ማኅበር የስም ማጥፋት ዘመቻውን ይከፍትብናል ብለው ይፈራሉ። አንዳንዶችም ከዚያ መሰሪ ማኅበር ጋር ሳይለያዩ እና በቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ሳይላተሙ አስመስለው መኖር የሚፈልጉ ስለሆኑ እንደዚህ ዓይነት ጠቃሚና አስፈላጊ ስብሰባ ላይ ብዙ ሰው ለማሳተፍ መሞከር ትርፉ መረጃ እያሾለኩ እንጀራቸውን የሚጋግሩ ሆድ አደሮችን ማፍራት ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
እንደሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ ባሉት አድባራት ውስጥ በፈለፈላቸው ተባይ ደጋፊዎቹ አማካይነት በየአድባራቱ ጉባዔ ውስጥ ሃሳብ በመጠምዘዝ፤ ካህናቱን በማከፋፈል፤ ሽኩቻ የሚፈጥር አጀንዳ በማስነሳት እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱ ያታወቃል። የትም ቦታ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች እስካሉ ድረስ ሁከትና ብጥብጥ አለ። ሀገሩ የሕግ ሀገር መሆኑ በጀ እንጂ እንደማኅበሩ መሰሪ አባላቱ አካሄድ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ማኅበሩን ነቅፈውና ተቃውመው አንድም ቀን ስራቸው ላይ መቆየት አይችሉም ነበር። አስተዳዳሪዎች አሜን ብለው እጃቸውን በመስጠት ኪሳቸውን ማስቦጥቦጥ ይጠበቅባቸዋል። እምቢ ካሉ ደግሞ የስድብና የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፈትባቸዋል። አሁንም እየታየ ያለው እውነታ ይህንን ያመላክታል።
ከዚህ በፊት ባቀረብነው ጽሁፋችን እንዳነሳነው የላስቬጋስ  ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ጢም አልባው መነኩሴ የማኅበሩን ጭነት ተሸክሞ እየተንገዳገደ ሲበጠብጥ፤ የደብሩን አስተዳዳሪ አስፈንጥሮ ለመጣልና በአቡነ ፋኑኤል ላይ የተልእኰ ዘመቻውን በመክፈት ደብዳቤ ሲጽፍ ከመቆየቱ ባሻገር አሁንም ደግሞ አጠናክሮ መቀጠሉ ይሰማል።


በዳላስ ደ/ፀሐይ  አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያንም ገበሬ አስደንግጥ ሰባኪዎቹ ከተባረሩ በኋላ ቂም ቋጥረው የቆዩትና ጭነት የማይከብዳቸው ተላላኪዎች አባ ፋኑኤልን በመቃወም መገንጠላቸው ይታወሳል። በየአድባራቱ የሊቀ ጳጳሱ ስም እንዳይጠራ ትልቅ ዘመቻ ተደርጓል። የተቃውሞ ደብዳቤ እየተጻፈባቸው በደጀ ሰላም ላይ እንዲወጣ ለማድረግ ተሞክሯል። አንዳንዶቹ የተቃውሞ ደብዳቤ በመጻፍ ስማቸውን ለኢንተርኔት መስጠቱን ባይፈልጉም በግብር ግን ተቃውሞ ውስጥ ውስጡን ማቅረባቸው አልቀረም።
አቡነ ፋኑኤል ሊቀ ጳጳስ ከመሆናቸው በፊት  በአስተዳዳሪነት ዘመናቸው ማኅበረ ቅዱሳን ስማቸውን አንስቶ አይጠግብም ነበር። እሳቸውም ማኅበሩ ለሚያደርገው ስራ ያግዛል በማለት ገንዘብ በማሰባሰብ ይደግፉ እንደነበር ይታወቃል። ታዲያ ዛሬ እንዲህ የጠላቸው ለምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ዋናው ምክንያት ገንዘባቸውንና ክብራቸውን ቆንጥረው በመስጠት፤ ተናገር በከንፈሬ፤ ተቀመጥ በወንበሬ ባለማለታቸው ብቻ ነው። አቡነ ፋኑኤል እንደ እነ እንትና…… ሁለ መናቸውን ያውልህ ብለው ቢያስረክቡት ኖሮ  ዘወትር በሐመር መጽሔትና ጽሙአ ጽድቅ ጋዜጣቸው ላይ የልማት አባት፤ ፋና ወጊ አባት፤ የቤተክርስቲያን አባት እየተባሉ ይሞካሹ እንደነበር አይጠረጠርም። ማኅበረ ቅዱሳን የፈለገውን ዓላማ ስለከለሉት ተበሳጭቶ  የምሬት ተግባሩን እየፈጸመ ሲገኝ የአንዳንድ አድባራት ካህናትና አስተዳዳዳሪዎችስ ምን ተነክተው ነው ስማቸውን የማይጠሩት? ተቃውሞ የሚያሰሙት?
ችግር ካለ ደግሞ በቅንነት፤ በእውነትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ወደ መፍትሄ ያልተመጣበትና የማይመጣበት ምክንያት ምድነው? እንደ እውነቱ  ከሆነ ለመደማመጥ የማያደርስና ለዐመጽ የሚጋብዝ አንዳች ነገር የለም።
ነገር ግን  ኢምንት ስህተቶችንና እንከኖችን በማራገብ፤ በማባዛትና ከዳር ዳር በማዳረስ የብጥብጥ ስራውን በመሰሪ አባላቶቹና ድረ ገጾቹ የሚያራግበው ማኅበረ ቅዱሳን በሚያደርሰው የማከፋፈል ዘመቻ ነው። አድባራት አቡነ ፋኑኤልን በመቃወም የሚያተርፉት ንግድ ምንድነው? ከጥላቻና ከቂም ኢ- መንፈሳዊ ተግባር በስተቀር  አንድም የጽድቅና የቅንነት ምሳሌነት የለውም። በእርግጥ ማኅበሩን ደስ ያሰኙ ይሆናል፤ እራሳቸው ተቃዋሚዎቹም በፈጸሙት በቀል ይረኩ ይሆናል። ከዚህ ባሻገር አንዳችም መንፈሳዊነት የለውም። የማኅበሩ ጭነት እስካልከበዳቸው ድረስ መሸከሙ ቢያሳዝንም  የዚህ ማኅበርን መሰሪ ዓላማ የተረዱ ሌሎች ይህንን ለማስቆም መሞከራቸው የሚመሰገን ሆኖ አግኝተዋል። ስለሆነም በምድረ አሜሪካ ባሉ አድባራት ውስጥ የዚህን ማኅበር ሁከት መግታት ካልቻሉ አድባራት ተገዢነታቸውን በደብዳቤ ለማሳወቅ እስከመገደድ ይደርሳሉ፤ ጳጳሳት ደግሞ ማኅበሩን አዛዥና ናዛዥ አድርገው ቢሮ ሲሰጡት፤  ቤተክርስቲያን ሲከፍቱለትና አውደልዳዩን ሁሉ ቄስና ዲያቆን እያሉ ሲሾሙለት መኖር ይጠበቅባቸዋል።
 ስለዚህ እነ ቀሲስ ሳሙኤል ደጀኔ፤ ቀሲስ ታደሰ አርአያ እና ሌሎች ካህናት ሁሉ የጀመራችሁትን ውይይት አጠናክራችሁ ቀጥሉበት እንላለን።  የእናንተ ትግል ለሁሉም ነጻነት ይጠቅማል።  ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጉባኤያችሁ ላይ ጆሮ ጠቢዎችን፤ ቦርባሪዎችን፤ አድርባዮችን፤  ነገር ጠምዛዦችንና ቃላት ሰንጣቂ አዋቂ መሳዮችን  ከውስጣችሁ አጽዱ።
ውጤታማ ፍጻሜአችሁን እንጠብቃለን።