ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ እነሆ አንድ ሳምንት ሊሆናቸው ነው። የሚወዷቸው አዝነዋል፤ የሚጠሏቸውም ደስ ተሰኝተዋል። አንዳንዶች ቢጠሏቸውም እንኳን ሞት የጋራ ርስት መሆኑን በማመን እግዚአብሔር እረፍቱን ይሰጣቸው ዘንድ ከልባቸው ተመኝተዋል።
አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ መጪው ዘመን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገሪቱ ምን ይመጣ ይሆን? በሚል ሃሳብ ረጅሙን ጊዜ በማስላት ይጨነቃል። በእርግጥም ሟቾች ጥፋትም ይስሩ ልማት ላይመለሱ ሄደዋል። የነበሩበት ቦታ ትልቅ የመንፈሳዊና የሥጋዊ ሥልጣን ደረጃ በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱን በመንፈሳዊ አባትነት ሊመራ የሚችልን ሰው በማግኘት አንጻር ቢያሳስበን አይገርምም። በስጋዊ ሥልጣን ደረጃም እንደዚሁ በሀገር መሪነት ደረጃ የሚመጣው ሰው የነበሩ ድክመቶችን በማስተካከል፤ የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ስለመቻሉ ቢያሳስበን እንደዜጋ ከተገቢነቱ የወጣ አስተሳሰብ አይደለም።
ቀና ቀናውን አስበን፤ መጪውን ጊዜ ብንፈራ ሰው ነንና ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ ክፉም ሆነ ጨካኝ ገዢ የሚመጣብንና የመጣብን መሪዎች ክፉ ወይም ደግ ለመሆን ስለፈለጉ ሳይሆን ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተላልፎ የተሰጠ አምልኰ ስላለን መሆኑን አምነን ልንቀበል ይገባል።
እግዚአብሔር ለዳዊት በተናገረው ቃል ላይ ከወገቡ የሚወጣው ልጅ እንደሕጉ ከሄደ መልካም የሆነው ነገር ሁሉ ከፈጣሪው እንደሚሆንለት፤ ክፋትን በፈጸመ ጊዜ ደግሞ የሰው መቅጫ በትር እንደሚላክበት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጾ ይገኛል።
2ኛ ሳሙ 7፤14
እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ ።
እኛ ደጎችና የእግዚአብሔር ፈቃድ ፈጻሚዎች ሆነን ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በቅጣት ወይም በመከራ ውስጥ አይተወንም ነበር። ስለዚህ ለሆነውና ለሚሆነው ሁሉ ጥፋተኞች እኛ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም።
ኢዮብ 34፤12
በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።
የሚያሳዝነው ነገር ኢትዮጵያውያን በማንነታችን ስንመዘን ፊታችንን ወደእግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኞች ያልሆንን እልከኛ ህዝቦች መሆናችን ሲታይ መከራ የምንለው ነገር ማብቂያው ገና ረጅም ነው። ከጣዖት አምልኰ ገና አልተላቀቅንም። አምልኮቶቻችን ብዙዎች ናቸው። እግዚአብሔርን በከንፈሩ የሚያከብር በልብ ግን ከፊቱ የራቅን ሕዝቦች ነን። ከመበላላት ገና አልወጣንም። ሥልጣንን ጠልፎ ለመውሰድ ከሚደረግ የሽንገላና የተንኮል ተግባር ገና አልተላቀቅንም። ቤተክህነቱም ሆነ ቤተመንግሥቱ ለእግዚአብሔር ይገዛ ዘንድ ለፈቀደ ሕዝብ ገና ዝግጁ አይደለም።
ሁሉም ያሰፈሰፈው ለወንበሯ ነው። ሀገሪቱ በሃሳብ ነውጥ ተወጥራለች። ሰላም ነን እያልን ራሳችንን ካልሸነገልን በስተቀር አየሩ በሁከትና በሃሳብ ተበክሏል። ይህ ካልጸዳ የሀገሪቱ ችግር አላባራም ማለት ነው። አዎ መጪው ዘመን ያስፈራል። አመላችንና አኗኗራችን ገና አልተስማማም።
ስለኢትዮጵያውያን ጠባይና የእምነት ጠንካራነት አንዳንዶች የጥሩ ማንነታችን መገለጫ አድርገው የሚጠቅሱት የኤርምያስ ትንቢት የሚታየው በበጎ ጎኑ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም። ይልቁንም ስለኢየሩሳሌም መከራና መበተን በተነገረበት በዚህ ትንቢት ውስጥ የኢትዮጵያውያን ማንነት መነሳቱ የሚያሳየው መከራችን እንደኢየሩሳሌም መከራ ብዙ መሆኑንና (ኤር 13፤22 በልብሽም፤ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ? ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል) በማለት የተነገረው የኢየሩሳሌም የመከራው ጽናት የሚያመለክተን ለመመለስ ዝግጁ የሆነና ለእግዚአብሔር እንገዛ ዘንድ ፈቃዱ የሌለን ግትር ህዝቦች መሆናችን ለማመልከት እንደቀረበ አለመረዳቱ አስቸጋሪ ነው።
ኤር 13፤ 23 በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ።
የነብር መልክና ሁሌም እንደማይለወጠው የኢትዮጵያውን ጠባይ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ ከኃጢአትሽ ካልተመለስሽ መከራሽ ይበዛል ማለቱ እንደሆነ የምንገነዘብ ከሆንን አመላችንና ያለብንም መከራ ማስተዋል እንችላለን።
ስለሆነም መጪውን ጊዜ የሚወስነው የእኛ ማንነት እንጂ የአባ ጳውሎስና የአቶ መለስ ሞት አይደለም። ከዚህ የተነሳ የሀገራችን መጪ ዘመን ከምንም በላይ ያሰጋናል። ያስፈራናል።
እግዚአብሔር መልካሙን ጊዜ ያምጣልን፤ለቃሉ የሚታዘዝ ሕዝቦችም እንድንሆን ያደርገን ዘንድ እንጸልይ!