Wednesday, August 1, 2012

ይድረስ ለፖሊስ !! "ማኅበረ ቅዱሳን"ም ያደረገው ይህንኑ ነው!


                         ምንጭ፤ http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
የእሁድ ሐምሌ 22 ቀን 2004 የፖሊስና ኅብረተሰብ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም በሀገራችን ስለተከሰተው የአክራሪ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ አብራርቶታል፡፡ በዘገባው ክቡር ወርቅነህ ገበየሁ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት እንዲሁም ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በተሰጠው ማብራሪያ አክራሪዎቹ በሥራ ላይ የነበሩትን ዑለማዎች ከየመስጊዱ በመደብደብና በማባረር፣ ጥበቃዎችን ከየሥራ ክፍሎች በማሰወገድ፣ የድምፅ ማጉያዎችን ከተቆለፈባቸው ቦታ ነቃቅሎ በመውሰድ የመብራት ሲስተሙን በማጥፋት፣ ለሶላት የሄዱትን ወገኖች በማገት፣ እኛ ያልፈቀድንለት ሰው አያስተምርም፣ በማለት እጅግ አሳፋሪ እና የአሸባሪነት ድርጊት መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው የጽንፈኝነት አካሄድ መሆኑ ጭምር ተብራርቷል፡፡
በእርግጥ አንድ ሕጋዊ ተቋም ባወጣው ድንጋጌ መሠረት ሊተዳደር የግድ ነው፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የሚወከሉ ባለሥልጣናቱ ሥራቸውን በአግባቡ መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በኃይል የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ፀረ ሠላም መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል።
የፖሊስ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ክፍል ከወደ ሙስሊሞቹ በኩል ያጣራው ሐቅ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩልም የጽንፈኝነት አካሄድ ያለው ቡድን መኖሩ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይኸው ቡድን ማለትም "ማኅበረ ቅዱሳን" አባላቶቹ በቤተክርስቲያን የተወከሉ አባቶችን ሥልጣን በመጋፋት፣ የማይተባበሯቸው ካህናቶችን በመስደብ፣ በመደብደብና በማሳደድ፣ ተመሳሳይ ጥፋት ፈጽመዋል፤ እየፈጸሙም ነው፡፡
በተለይም ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ላይ የተፈጸመው እንደማሳያ ቢሆን በቅዳሴ ሰዓት የድምፅና የመብራት ሲስተሙን ቆርጠዋል፤ የጄኔሬተር ክፍሉን ቁልፍ በመስበር በራሳቸው ቁልፍ ከርችመዋል፡፡ በጥቅምት 2004 የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ዋዜማ ላይ የአባቶችን ሥርዓተ ፀሎት ደወል በመደወልና ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት አውከዋል፡፡ በክብረ መንግሥት ከተማ የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓለ ንግሥ እንዳይካሄድና ታቦት ከመንበሩ ወጥቶ ዑደት እንዳይደረግ የሁከት እንቅስቃሴ ፈጽመዋል፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን" ከመስከረም 12 ቀን 2002 . ከተካሄደው ሀገር አቀፍ የሠላም ጉባዔ ወዲህ እንኳን የፈጸማቸው ድርጊቶች ለቁጥር ይታክታሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተክርስቲያን ላወጣችው ሕግና መመሪያ እንደማይገዛ በይፋ አሳይቷል፡፡ ፖሊስ በያዘ እጁ ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ቤተረክርስቲያናት እንዲሁም ሁከት በተካሄደባቸው ከውጭ ሀገር እስከ ሀገር ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በአርባ ምንጭ፣ በክብረ መንግሥት፣ በሞያሌ፣ በዲላ፣ በሐረር፣ በሀዋሳ፣ በአዲግራት፣ በሎስ አንጀለስ፣ በዳላስና በሌሎችም ሀገረ ስብከቶችና ከተሞች የፈጸማቸው የሁከትና የሽብር ድርጊቶች ኅብረተሰቡን ጭምር በማነጋገር ሰፊ ጥናት ቢያካሂድ ሕዝብና ሀገርን፣ መንግሥትንና ቤተክርስቲያንን ይታደጋል የሚል እምነት አለን፡፡ "ማኅበረ ቅዱሳን" አደረጃጀቱና አባላቱ ህቡዕ የሆኑ፣ የገንዘብ ዝውውሩ ሚስጥራዊ የሆነ፣ የንብረትና የገንዘብ አስተዳደሩን ኦዲት ለማስደረግ ፈቃደኛ ያልሆነ፣ በተፈጥሮው ምንም ዓይነት መንፈሳዊነት የሌለው እና ፖለቲካዊ ቅኝት የተቃኘ ሃይማኖት ለበስ ማፊያ ቡድን ነው፡፡
ለዚህም ነው "ማኅበረ ቅዱሳን" የሰለፊያ ግልባጭ ነው የሚባለው፡፡