Saturday, September 22, 2012

መንፈሳዊ ሃሳብ ላለው ሰው ሁሉ ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቅ ይቀድማል!

ስለእርቅ ብዙ ብዙ ተብሏል።  ሰዎች እርቅን ከሁኔታዎችና ከአዋጭነቱ አንጻር መዝነው ይፈጽማሉ። በእርቁ የሚያገኙትን ሂሳብ ቅድሚያ ያሰላሉ። አንድ የተጨበጠ ነገር ካላገኙ እርቅን ሰማያዊ ዋጋ ከማግኘት ጋር አያይዘው  ለመወሰን ይቸገራሉ። ብዙ እርቆች በዚህ መንገድ የሚከናወኑ ናቸው። ፖለቲከኞቹ እንኳን /Give & Take/ ሰጥቶ መቀበል ይሉታል። ይህ የሥጋዊ እሳቤ ውጤት በመሆኑ በዚህ እርቅ ምድራዊ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ከላይ ከአምላክ ዋጋ ያስገኛል በሚል ስላልሆነ ውጤቱ ጊዜያዊና ምድራዊ ነው። ሰማያዊ አስተሳሰብ ምን ጊዜም የእርቁን ጥቅም ከአዋጭነቱ ወይም ከሚያስገኘው የሚታይ ዋጋ በላይ በመሆኑ ለዚህ እርቅ ራስን የመስጠት ዋጋ እስኪከፈልበት ድረስ ግዴታን ያስከትላልና ከባድ ነው። እንኳን የበደሉትን፤ የበደለንን ይቅር እስከማለት የሚያደርስ ህግጋት ስለሆነ ሚዛናዊነቱ በመንፈስ ዓይን ብቻ የሚታይ ነው። በዘወትር ጸሎት «ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ» እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል…» እያልን በደላችንን ሁሉ በደሙ እንዳጠበው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛም የበደሉንን ይቅር እንላለን እያልን የምናውጀው የጸሎት አዋጅ ዋጋ የሚኖረው በእውነትም ለእርቅ የተዘጋጀ ልቡና ሲኖረን ነው። ያለበለዚያ እየዋሸንና ጌታችንንም ለዚህ ዋሾ አንደበታችን ተባባሪ እንዲሆነን እየጠራነው ካልሆነ በስተቀር  በተግባር ይቅርታ በሌለበት ልባችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በምንም መልኩ ሊያድር አይችልም። ይቅርታ የሌለው ልቦና መንፈሳዊ አይደለም።


«እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም» ማር 11፤26

ይቅርታን የማያውቅ ሲኖዶስ ወይም ማኅበር እንዴት ለሀገርና ለህዝብ ይጸልይ ዘንድ ይችላል? ከማን ዘንድ ይቅርታን ለማግኘት? አንዳንዶች በስም ብጹእና ቅዱስ ተብለው በተግባር ግን ከቅድስና ማንነት የሚመነጨው መንፈሳዊ ብቃት ሲታይ፤ ፍሬ አልባዎች ናቸው። የክብርና ዝና፤ የገንዘብና ሥልጣን ምኞቶች ይቅር ማለት በሚገባው ልባቸው ላይ ተቀምጠው ይገኛሉ። ከዚህም የተነሳ ለሌሎች ይቅርታን ለማድረግ ጊዜን ይፈጃሉ፤ እነርሱ ግን ለኃጢአታቸው ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ እንዲወርድላቸው ሲጸልዩ ይታያሉ።  በእርግጥም ለጸሎታቸው ምላሽ ያልመጣላቸው ከዚህ እልከኛ ልባቸው የተነሳ ይሆናል። «አድን ሕዝበከ ወባርክ ርስተከ» ብለው ይጸልያሉ። ህዝቡም አልዳነም፤ በበረከትም ተሞልቶ በስደት ከመሞት አልዳነም። በእልከኝነት መንፈስና ይቅር ባለማለት  የእግዚአብሔርን የይቅርታ ፈቃድ በእጃቸው ያሰሩ ሰዎች እንዴት፤ የይቅርታ እጅ ለእነሱ ከሰማይ እንዲወርድ ይለምናሉ? እግዚአብሔር ልብና ኩላሊት ያመላለሰውን እልከኛ ልብ አይመረምርም ማለት ነው? ለይቅርታ ባልተዘጋጀ ማንነት ያሉ ጨካኞችና ክፉዎች ይቅርታን አያውቁም፤ ልበ ርኅሩኆችና ቸሮች እንጂ!!

«እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ» ኤፌ 4፤32

እንግዲህ እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባባልን ይቅርታን ገንዘብ ማድረግ የማይችሉት ክፉዎችና ጨካኝ መሪዎች ሁሉ ናቸው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተባራሪና አባራሪ፤ የውስጥና የውጪ፤ የሕገ ወጥና ሕጋዊ፤ ሲኖዶስ ስያሜ ሕልውና ኖሮት በየራሱ ክፍል ተለያይቶ መኖር ከጀመረ እነሆ ሃያ አንድ ዓመት አስቆጠረ። እንዴትና ምክንያቱን ለመዘርዘር የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ባለመሆኑ ወደዚያ የቆሸሸ ታሪክ መግባት አያስፈልግም።   በተወጋገዘ የጳጳሳት ቡድንና ደጋፊ የቤተክርስቲያኒቱ አንድ ማኅበር ልዩነቱ ዛሬም መኖሩን በማመን መፍትሄ በመፈለግ ላይ ለማተኮር ይሻል። 21 ዓመት በልዩነትና በክፍፍል የቆየነው ለምንድነው? አሁን ያህ ክፍፍል እንዳይቀጥል ምን የሚታይ ነገር አለ? ወደፊትስ ምን ማድረጉ ይበጃል? በሚሉት ላይ ጥቂት ለማለት እንወዳለን።

1/ ለይቅርታ የተዘጋጀ ወገን የለም!

በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል በክርስቲያን ይቅርባይ የእምነት ማንነት ላይ ሆኖ ይቅር ለመባባል የፈለገ ማንም  ወገን የለም። የክርስቶስ አማኝ ይቅርታን በሁኔታ፤ በአዋጭነቱና በሚያስገኘው የሚታይ ዋጋ ላይ ተመስርቶ ለይቅርታ ድርድር አይቀመጥም። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሲኖዶሶች ለይቅርታ የሚነጋገሩት የሚያዋጣቸውን ስልት ነድፈው ጥቅሞቻቸውን በማስጠበቅ ውጤታማ ለመሆን የሚታገሉለት ምድራዊ አስተሳሰብ የነገሰበት ሆኖ በመቆየቱ አንዳችም ውጤት ማምጣት አልተቻለውም። የቤተክርስቲያን አንድነት ሰዎች ስለፈለጉት  ወይም ስላልፈለጉት ሳይሆን የተመሰረተው በክርስቶስ ደም ስለሆነ አንዳችም ቅድመ ሁኔታ የሌለበት ነገር ነው።
«ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም » ማር 3፤25
«በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» የሐዋ 20፤28
የክርስቶስን መንጋ ለሁለቱ የከፈሉ ሲኖዶሶች የክርስቶስን ቤት በአንድነት ለማቆም ያለመቻላቸው ዋናው ምክንያት ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸውን ሹመት ወደ ሥጋዊ አስተሳሰብና የድርድር ሂሳብ ስላወረዱት ብቻ ነው። እንዲያ ካልሆነማ 21 ዓመት ለእርቅ ያንሳል? ከእንግዲህስ ስንት 21 ዓመት ያስፈልጋል? በሁለቱም ወገን ለቤተክርስቲያን አንድነት የተዘጋጀ ማንነት ባለመኖሩ ውጤቱ ከህልም ዓለም አልፎ እውን መሆን አልቻለም። አሁንም ይህን አስተሳሰብ አስቀምጠው የክርስቶስን ማኅበር መሰብሰብና የቤተክርስቲያንን አንድነት ማስቀደም እስካልቻሉ ድረስ ከመንፈሳዊ ውጤት ላይ መድረስ አይቻላቸውም።

2/ የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ የበለጠ ችግር አለበት።

አንዳንዶች ማለትም ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ የፓትርያርክ መርቆሬዎስን ሀገር ለቆ መሄድ ሲኮንኑ ይታያሉ።  የመንፈሳዊ አባቶችን የጥንት የስደት ሁኔታ ከታሪክ አምጥተን እዚህ ላይ ብዙ መከራከሪያ ጭብጥ በማቅረብ መሞገት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጉልጭ አልፋ እንዳይሆን እንለፈውና የፓትርያርክ መርቆሬዎስን ስደት ተገቢ እንዳልነበረ ብንቆጥረው እንኳን ስህተታቸውን አጉልቶ የማያሳይ ነገር አለ። ይኼውም  ፓትርያርክ መርቆሬዎስ መንፈሳዊ ሥልጣናቸውን የሚጠሉት ኢህአዴግ ሲገባ ሊሆን አይችልም። ታመዋልም ቢባልም እንኳን  በሞት ከዚህ ዓለም ተለይተዋል ማለት አይደለም። በሞት እስካልተለዩ ድረስ በህመም ይሁን በሌላ ምክንያት ከመንበሩ ላይ ካልተገኙ በምትካቸው ሌላ ፓትርያርክ ይመረጣል የሚል ሕግ አለ ወይ?    ምንም እንኳን ፓትርያርክ መርቆሬዎስ እስከመጨረሻው ድረስ ባሉበት መቆየት እንደነበረባቸው ባያጠያይቅም እውነታው ግን የፓትርያርክ መርቆሬዎስን መባረርና ከስልጣን በህመም ይሁን በሞት መሰናበት የሚፈልጉ የሲኖዶስ አባላት መኖራቸውን ልንክድ አይገባም። ምክንያቱም ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ አንሾምም ያለ አንድም የሲኖዶስ አባል አልነበረም። ይልቁንም ከባለጊዜው ንፋስ ጋር ሲነፍሱ ታይተዋል። አንዳንዶቹም ለመሾም ሲሯሯጡ ነበር።  በህመም ወይም በሌላ ምክንያት መሥራት ባይችሉ እንደራሴ የማይመራበት ምክንያቱ ምን ይሆን? ሕጉን በሕግ ባለማሻሻል ለመጣስ ያደረሰው ምን ይሆን?  ተወደደም ተጠላ፤ ፓትርያርኩን በመጥላትና በማስወገድ ሥልጣኑን ለመጨበጥ የፈለጉ ቡድኖች ለቤተክርስቲያን መከፋፈል ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። ብዙዎቹን ባለድርሻዎች እናውቃቸዋለን። ገሚሶቹም ሞተዋል፤ በህይወት ያሉትም አሉ። ይህ ከሆነ እነሆ 20 ዓመታት አለፉ።  ስህተቶችን በማመን ለማስተካከል መሞከር ግን አሁንም ቁርጠኝነቱ ካለ አልረፈደም። በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ለመተራረም ያለውን ነገር ብዙም አያሳይም።
 የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ከውጪው ሲኖዶስ ጋር ለሚደረገው እርቅ እንቅፋት ናቸው ብሎ የክስ መዝገቡን በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲለጥፍ የነበረ ቢሆንም  ከሞታቸውም በኋላ ይህ እርቅ በየምክንያቱ እንዲጨናገፍ የሚፈልግ አካል እንጂ ከአቡነ ጳውሎስ በተሻለ መልኩ ለእርቁ ቀናዒ  ስለመሆኑ የምንሰማውና የምናየው ነገር የለም። ይልቁንም ከወዲያ ወዲህ የሚናፈሰው ስለ 6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ነው። ምናልባትም አቡነ ጳውሎስን ከመጥላት የተነሳ  ውንጀላን የሚቆልሉባቸው ከሳሾቻቸው እሳቸው በሞት ዘወር ሲሉ  የከሳሾች የሀሰት ክስ ጊዜውን ጠብቆ እየተገለጸ እያየን ነው። ስለ6ኛው ፓትርያርክ በተዘዋዋሪና በቀጥታ መነገሩ እርቁ አልተፈለገም ማለት ነው። ድሮውንም ፓትርያርክ ጳውሎስን የሚወነጅሉት ለስም ማጥፋት እንጂ እርቁን ፈልገውት አልነበረም። ምክንያቱም እርቁ እውን ሆኖ የውጪዎቹ ጳጳሳት ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ቢችሉ፤ አሁን ባለው የሀገር ውስጡ ሲኖዶስን ጉባዔ በሚፈልጉት መንገድ የሚጠመዝዙ ቡድኖች ከልዩ ልዩ አስተሳሰብና ከእውቀት ብልጫ አሰላለፍ አንጻር የመዋጥና የያዙትን የወሳኝነት  ወንበር በመልቀቅ ወደጥጉ እንገፋለን የሚል የስነ ልቦና ፍርሃት አላቸው። ያን ጊዜ የማኅበረ ቅዱሳን ነደ እሳት የሚባል ጳጳስ አይኖርም፤ እገሌ ጧፍ ነው፤ እገሌ ደግሞ ሻማ እያሰኘ የሚያሞካሸውን ጀግና ደጋፊ አያገኝም።  ስለዚህ ሁሉም ቡድኖች እርቁ በፍጥነትና በሁኔታዎች አጋጣሚ እንዲፈጸም አይፈልጉም። ከእነዚህም አንዱ የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ አጫፋሪ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ከነተባባሪ አባቶቹ እርቁን አይፈልጉትም።

3/ የውጪውም ሲኖዶስ ችግር አለበት።

 ፓትርያርክ መርቆሬዎስ እድሜአቸው መግፋቱ እውነት ነው። በዚህ እድሜያቸው አሁን ያለውን የቤተክርስቲያን ተግዳሮቶች ፈጥነው በመረዳትና በመንቀሳቀስ ተፈላጊውን መፍትሄ በመስጠት ላይ ተገቢውን አመራር መጠበቅ እንደሚቸግር መረዳት አይከብድም። በዚህ ላይም ሕመም እንዳለባቸውም እንሰማለን።  ብዙ ጊዜም የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ድምጽ በውክልና ከሚሰማ በቀር የፓትርያርኩ ድምጽ ርቋል። ይህም እንደ አንድ ችግር ቢነሳ አግባብነት ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪም እርቅን የሚያክል ትልቅ ኃላፊነትና ተልእኮ የሚጠብቀው የውጪው ሲኖዶስ አባላት ለእርቅ እንቅፋት የሚሆኑ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መሰል መግለጫዎችና አሰላለፎችን ሲያሳዩ ይታያሉ። ከሀገር ውስጥ ሲኖዶስ ጋር በመስማማት ብቻ ያለ ኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እርቁ ከግብ ሊደርስ እንደማይችል ይታወቃል።  የውጪው ሲኖዶስ አባላት የፖለቲካ ሰልፎችን በማስተባበር የኢትዮጵያን መንግሥት ማስኮረፍ በራሱ ችግር አለው። መቃወም መብት ቢሆንም የፖለቲካ «ሀሁ» ብዙም በሀገሩ ውስጥ ባላስፋፋ መንግሥት ጉዳይ እየገቡ ወደእርቅ እንደርሳለን ለማለት እንዴት ይቻላል? እርቁ ቢቀርም፤ ይቅር ካልተባለ በስተቀር  እስከ ኤርትራ የደረሰ የሲኖዶስ አባል ያለው የውጪው ሲኖዶስ አቋሙ ጥርት ያለና ለእርቅ ዝግጁነት ያለው ነው ለማለት ይቸግራል።  እስካሁንም እነዚህ ጉዳዮች ለእርቅ ያላቸውን ጉዳት ገምግሞ ዝግጁነቱ እስከየት ድረስ እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅለት ነገር የለም። ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንም እንደሚያነሳ ይሰማል። ቤተክርስቲያንን አንድ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ሲኖዶስ ለፖለቲካዊ ጥያቄ መፍትሄ የቅድሚያ ስራው እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚቀድመውን ማስቀደምና በሂደት ደግሞ የሚከተለውን ከመስራት ይልቅ አቀላቅሎ ሁሉንም ፍላጎቶች በአንዴ ለማሳካት መፈለግ ሁሉም እንዳይሆን ለማድረግ ከመጣር የተለየ አይደለምና ሊታሰብበት ይገባል።


4/ ምን ይደረግ?

ሀ/ የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ እርቁ እስኪፈጸም 6ኛ ፓትርያርክ የሚለውን ዜና ማቆም አለበት።

ኃላፊነት እንደሚሰማውና የቤተክርስቲያን መከፈል እንደሚቆጨው አካል  ከእርቅ በፊት የፓትርያርክ ምርጫ ስለማድረግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚሰጠውን ዜና ማቆም አለበት እንላለን። ይህ የሹመት ዜና እርቁን አንድ ጫፍ ሳያደርስ እውን ካደረገ በእርግጥም የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ እርቅን የማይፈልግ መሆኑን አረጋግጧል ማለት ነው። በዚህ የተነሳ ፓትርያርክ መርቆሬዎስ በሕይወት ካሉ ተጨማሪ ጳጳሳትን እንዲሾሙ ይገፏቸዋል። ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ እንኳን  ሌላ ፓትርያርክ መሾሙ አይቀርም። ልዩነቱ እንደሰፋ ቀረ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሁለት ባላንጣ ሲኖዶስ ስትመራ ትኖራለች ማለት ነው። ይህ አሳዛኝና የመንፈሳዊ ውድቀት የመጨረሻው ደረጃ ነው። ፓትርያርክ በመምረጥ ብቻ ቤተክርስቲያን ተጠቃሚ ብትሆን ኖሮ በ5 ፓትርያርኮች ያገኘነውን ጉድለትና ውጤት አስልተን ብዙ መናገር በቻልን ነበር። ይሁን እንጂ ለ1600 ዓመት ፓትርያርክን በወርቅ ስናስመጣ ከኖርንበት ዘመን ይልቅ ራሳችንን ችለናል ያልንበት የ50 ዓመት የፓትርያርክነት ዘመናችን ታሪክ እጅግ ውስብስብ ነው። ፓትርያርክን እንደመምረጥ ቤተክርስቲያንን አንድ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለምና ለአንድነቱ አጥብቆ መትጋቱ ሊቀድም ይገባል። ፓትርያርክን እንዴትና ለምን እንደምንመርጥ ሳናውቅ በይድረሰኝ፤ ይድረሰው ፓትርያርክ በመምረጣችን ብቻ ተጠቃሚ አንሆንም። ዝግ ብሎና ግራና ቀኝ አይቶ የሚደረግ ምርጫው ሂደት የሚፈታው መሆን አለበት።

ለ/ ፓትርያርክ መርቆሬዎስ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በፓትርያርክነት እየተጠሩ፤ ቤተክርስቲያኒቱ ግን በእንደራሴ ልትመራ ይገባል።

 እውነቱን በግልጽ ብንናገር ፓትርያርክ መርቆሬዎስ ቤተክርስቲያንን በዚህ እድሜና ጤና መምራት ይከብዳቸዋለች። ያ ማለት ግን በሕይወት እስካሉ ፓትርያርክ አይደሉም ማለት አይደለም። እሳቸው የቀራቸውን ዘመን በእረፍት ሆነው መንፈሳዊ ተግባራትን ግን እንደራሴ መርጦ እንዲያከናውን ቢደረግ የተሻለ ይሆናል።  ዋናው ነገር የቤተክርስቲያን አንድነት ነው። መንፈሳዊ ቅንነቱ እስካለ መሪው ክርስቶስ ስለሆነ ስለቤተክርስቲያን የሚያሳስብ አይኖርም። ስለዚህ ፓትርያርኩ ይመለሱ፤ እንደራሴ ተመርጦ ሲኖዶሱ ይመራ የሚል ሃሳብ አለን። ይህንን የምንለው እርቁ እውን እንዲሆንና ሰላማችን በስልጣን ሽኩቻ እንደተከፋፈለ እንዳይቀር ከማሰብ የተነሳ ነው።

ሐ/ መንግሥት ለእርቁ ስኬት ተገቢውን ሚና መጫወት አለበት።

የደርግ መንግሥት የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ መሪ ገደለ፤ ሀብቷን ወረሰ፤ አባሎቿን ፈጀ፤ አሳደደ። በኢህአዴግ መንግሥት ደግሞ ቤተክርስቲያን ለሁለት ተከፈለች። ይህ አስቀያሚ የታሪክ አጋጣሚ ነው። የመንግሥት ሚና እንደዚህ ነበረ፤ እንደዚያም ሆኗል እያልን ጊዜ አናጠፋም። ይልቅስ ለሁለት የተከፈለችውን ቤተክርስቲያን አንድ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት አለበት። ይኼውም የውጪው ሲኖዶስ አባላትና ደጋፊዎች ወደ ሀገር ቤት በእርቁ ለመመለስ የመንግሥትን  ዋስትና ሊያገኙ የሚችሉት የመንግሥት ፈቃደኝነቱ ሲኖር ብቻ ነው። በተዘዋዋሪ መንግሥትም ከእርቁ ተጠቃሚ ነው። ምክንያቱም የውጪውን ሲኖዶስ በመንግሥት የተገፋ አካል አድርገው የፖለቲካ ጫወታቸውን የሚሸፍኑ ወገኖች ከእርቁ በኋላ በቤተክርስቲያን መከፋፈል የሚያነሱትን ምክንያትና የሚሸሸጉበትን ካባ እንደሚገፍ እርግጥ ነው። በሌላ መልኩም በቤተክርስቲያን መከፋፈል ያዘኑ ሚሊዮኖች ምእመናን በሀገር ቤት ውስጥ በመኖራቸው እርቁ እንዲሳካ ለሚጫወተው የመንግሥት ሚና ትልቅ አክብሮት ይኖራቸዋልና ነው። ስለዚህ መንግሥት እርቁን በሚጠበቅበት መንግሥታዊ ድርሻው ቢደግፍ ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አይሆንም።

መ/ እርቁን ወደ አልሆነ አቅጣጫ የሚገፉ ቡድኖች መታቀብ አለባቸው።

ከሀገር ውስጡ ሲኖዶስ አባላት ውስጥ እርቁ እውን እንዲሆን የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ እርቁ እንዲደናቀፍ የሚፈልጉም ይኖራሉ። መግለጫና ዲስኩር፤ ጥያቄና ማብራሪያ፤ እንደዚህና እንደዚያ የሚሉ ድምጾች ከጀርባቸው ያላቸውን ተልእኮ በመሸፈን የሚቀርቡ እንቅፋቶች እያሳዩን ነው። ከእነዚህም አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን የተሰኘው ነጋዴ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከእርቁ ቤተክርስቲያን እንጂ እርሱ ተጠቃሚ እንደማይሆን አሳምሮ ያውቃል። እርቁ እውን ከሆነ እንደፈለገ የሚያሾረው የጳጳስ ሾፌር ላይኖር ይችላል። ቢኖር እንኳን ውጤቱን ባሰበው መንገድ ማስቀጠል አይችልም። ስለዚህም እርቁን እንደሚፈልግ ሆኖ እየታየ፤ ነገር ግን የሚፈለገው ነገር እንዳይሆን ይሰራል።  በድረ ገጹ ፓትርያርክ መርቆሬዎስን በመሸሽ ሲወቅስ አንብበናል። በፓትርያርኩ መሸሽና ጸንቶ አለመቆም ጣቱን ሲቀስር በተቃራኒው ያልተሰደደው ሲኖዶስ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ  ስለመሾምና  ስለሕገ ሲኖዶስ መከበር ያደረጉት ትግል ካለ አልነገረንም። በሕመም ይሁን በጡረታ የተለየ ፓትርያርክ መንበር የሚያዘው እንዴት ነው? ለሚለውም ጥያቄ ምንም ያለው ነገር የለም።  ፓትርያርክ መርቆሬዎስ የሸሹ ስለሆነና አሁን ስላረጁ አያስፈልጉንም የሚል ድምጸትን ሊነግረን ይፈልጋል። በተዘዋዋሪ ስለፓትርያርክ መርቆሬዎስ አሁን መነጋገር ጊዜ መፍጀት ነው ማለቱ ነው። ማኅበሩ ፓትርያርክ መርቆሬዎስንም፤ ፓትርያርክ ጳውሎስንም አይወድም። አሁን ግን ባገኘው አጋጣሚ የሚወደውን ሰው ለመሾም እንደወርቃማ እድል የቆጠረ ይመስል ስለ 6ኛ ፓትርያርክ ሱባዔ መያዙንና መግለጫ መሰጠቱን በገደምዳሜ ሊነግረን ይፈልጋል።
በዚህና በዚያ እያሉ ጥቂት በጥቂቱ ውስጣዊ እቅዶቻቸውን ዜና እየሰሩ በድረገጾች ካወጡ በኋላ የሲኖዶስ ጽ/ቤት የፈረሰ ይመስል አንድ ባለትዳር  ስለ 6ተኛው ፓትርያርክ ምርጫ እርግጠኝነት መግለጫ አውጥቷል። ምናልባት የሚመረጠው ቀጣይ ፓትርያርክ ባለትዳር ይሆን ይሆናል።   ምርጫው በታቀደው ጊዜ የሚደረግ ሆኖ ከታሰበም የሚሰጠው መግለጫ ደረጃውን ጠብቆ  ስለፓትርያርክ መመረጥ የመናገር ሥልጣን የማን መሆን ይገባው ነበር?   በአንድ ቢሮ የሚሰራ ባለ ትዳር ስለፓትርያርክ ምርጫ እርግጠኝነት በግል ፊርማው መግለጫ ማውጣቱን ስንመለከት ነገሩ እንዴት ነው? እንድል ያደርገናል።
 በመግለጫ ሰጪው በአቶ እስክንድር ገ/ክርስቶስ እጅ ድብቁን አጀንዳ  ዜና አድርገው ለመስራት የፈለጉ ድብቅ ሰዎች ይኖራሉ ብለን እንገምታለን። 
የፓትርያርክ ምርጫ በበጠቅላይ ቤተክህነቱ ህዝብ ግንኙነት መምሪያ የሚነገር ዜና መሆኑ አሳፋሪም፤ አሳዛኝም ነው። ሥጋውያን ሰዎች እንኳን ሊቀመንበራቸውን የመረጡት በገዢ ፓርቲያቸው በኩል ነው። ሊቀ መንበራቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት በሕግ አውጪው ውሳኔ ነው። የኛዎቹ ግን ከዚህ ያነሰ አቅም ኖራቸዋል ብለን ለመናገር ባንደፍርም ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ለመስራት ያልፈለጉበት ስውር ምክንያት እንዳለ ግን ብንጠረጥር ተገቢ ነው።

 ሲኖዶሱም  ስለ6ኛው ፓትርያርክ መግለጫ በኦፊሴል ለመስጠት ያልደፈረው የእርቁን ነገር መተዉን ስለሚያሳብቅበት  አቶውን ሰውዬ መጠቀም ፈልጓል ማለት ይቻላል።  ያለበለዚያማ  ስለ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ደረጃውን ጠብቆ በሲኖዶስ ጽ/ቤት መሰጠት የሚገባው መግለጫ የባለትዳሮች ምርጫ ይመስል ባለትዳር ስለፓትርያርክ ምርጫ መግለጫ ሊሰጥ ተገቢ ደረጃው አልነበረም። በሌላ ሰው እጅ የእባብን ጉድጓድ ለመድፈን የፈለጉ  ይመስላል።
እንደምንታዘበው እርቁ በጠማማዎች ቡድን ወደአልሆነ አቅጣጫ እየተገፋ እንደሆነ ይሰማናል። ውጤቱ ደግሞ ከቀድሞው የባሰ ይሆናል እንጂ የተሻለ አይመጣም። በመከፋፈልና በመጠላላት ያሉ ሰዎች የእርቅና የሰላም አምላክ እንዴት አብሮአቸው ሊቆም ይችላል? ባይሆን የጥል ወዳጅና የእርቅ ጠላት የሆነው ሰይጣን እድሉ የሰፋ ይሆናል እንጂ! 
ዙፋኑንም በዚያ ይተክልና ብጥብጡን ያስፋፋል  ማለት ነው። ትንቢት አይደለም የምንናገረው፤ በእርግጠኝነት እርቅና ሰላም በሌለበት ቦታ ከክርስቶስ የሆነ ፍቅር ስለማይኖር የቤተክርስቲያን የመዳከም ቀጣይነት እርግጥ ነው። ፈትፋቾችና አቡኪዎች ሲያምሷት ይታየናል። ከቀደመውም ጥፋት የኋለኛው የባሰ ይሆናል። 
በዚህ የጠማማዎች የስውር እጅ መግለጫ ላይ የእነማን ስውር ስምምነት ይኖር ይሆን? የምንገምታቸው አካላት በቁጥር እንዳሉ ብናስብም ሂደት ስለሚያወጣቸው እስኪ ጥቂት እንጠብቅ።
እስከዚያው እንደእኛ ሃሳብ ከፓትርያርክ ምርጫ በፊት እርቁ ይቀድማል! ከእርቅ በፊት 6ኛ ፓትርያርክ ስለመምረጥ ቁርጠኛ እቅድ የአቶ እስክንድርን መግለጫ ሲኖዶሱ ያውቀዋል? አቶ እስክንድር ገ/ክርስቶስ ስለፓትርያርክ ምርጫ መግለጫ መስጠት የሚችለው በምን ስሌት ነው? ስውር እጆቻችሁን ወደ ብርሃኑ አምጡና እስኪ እንየው!!