Saturday, September 1, 2012

የደጀ ብርሃንን ኢሜል በመሰርሰር ከሰርቨር ለማውረድና ብሎክ ለማድረግ የተሞከረው ከየት ነው?

ከዚህ ቀደም ከብሎገር ጀማሪዎች ተርታ የምትመደብ ነገር ግን ብዙ መረጃዎችን ፈልፍላ በማውጣት የመልካም ነገር ሁሉ ጠላት በሆነ ቡድን ባለመወደዷ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሎክ የተደረገችው «ዓውደ ምሕረት» ብሎግ አንድ ሰሞን ከኢትዮጵያ አድማስ ላይ ተሰውራ እንደነበር ይታወሳል። ከድርጊቶቹ ጀርባ ማን እንዳለ ለጊዜው የተገለጸ ነገር ባይኖርም ተመልሳ ለመንፈሳዊ አገልግሎቷ መብቃት ከመቻሏም በላይ የወርድ ፕሬስ አካውንትም እስከመክፈት መድረሷ ይታወቃል።
ምንም እንኳን እንደ ዓውደ ምሕረት ብሎግ ከጉግል ሰርቨር ማውረድ ባይችሉና ብሎክ አድርገው ከአገልግሎት ማስወጣት ቢያቅታቸውም ደጀ ብርሃን ብሎግንም ለማጥቃት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጋቸው አልቀረም። ኢሜላችንን በመሰርሰር ብሎጋችንን ለመዝጋት፤ የሀሰት መልእክቶችን በመላክ ለማሰናከል ተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል።
ይህንን ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገብንን  የኢንተርኔት ፕሮቶኰል አድራሻ በመመዝገብ ማን? ከየት? መቼ? እንዴት? ሙከራውን እንደሚያደርግና የዚህ ፕሮቶኰል ቁጥር በዓለም ዓቀፉ የስፓም መልእክት ማጣሪያ ኔት ወርክ ውስጥ ያለው ሊስት፤ በዓለም አቀፍ የፕሮቶኰል ቁጥሮች ዝርዝር ውስጥ ያስተላለፋቸው መልእክቶች ዓይነትና ምንነት፤ አድራሻውን፤ የሚጠቀምበትን የሽፋን ሰርቨር የተመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ አደገኛነቱን ለማረጋገጥ ችለናል። ይህ ፕሮቶኰል ቁጥር  በአደገኛ ጥቁር መዝገብ /BLACK LIST/ የሰፈረ ሲሆን ይህንን በተመለከተ ኢትዮ ቴሌኮም ምን እንደሚል አናውቅም። ይሁን እንጂ የመንግሥትን ፖለቲካዊ ማንነት በመንቀፍ ይሁን በመደገፍ ያይደለ፤ በመንፈሳዊ ልኬታ ማለት የሚገባንን ብቻ የምንጽፍ ሆነን ሳለ ብሎጋችን በመንግሥት በኩል ጥቃት ይፈጸምበታል ብለን ቅንጣት አንጠራጠርም። ይልቁንም ጽሁፋችን ደስ የማያሰኛቸው የሁከት አባት፤ አባላት ያልገቡበት የመንግሥት ቢሮ ባለመኖሩ ይህንኑ ፍቅራቸውን ለማሳየት ይህንን አስጸያፊ ተግባራቸውን በመንግሥት አገልግሎት ሽፋን ሊጠቀሙ ይችላሉ ብለን እንጠረጥራለን።
የፕሮቶኰል ቁጥሩ ባለቤት ነኝ የሚል አካል ካለ ለምን በተለያዩ ዓለም የመረጃ መረብ ኔት ወርክ ውስጥ በአደገኛ ቁጥር ውስጥ ሊመዘገብ እንደቻለ፤ የሀሰት ኢሜሎችን በመላክና ኢሜል ለመሰርሰር/EXTRACT/ በማድረግ  ለምን እንደተጠመደ መልስ ይኖረው ይሆን?
በተለይም ኢትዮ ቴሌኰም ውስጥ በዚህ ፕሮቶኰል መስመር ላይ በኃላፊነት የተቀመጡ ግለሰብ ምን ዓይነት ምላሽ አላቸው? አድራሻቸውን ያገኘነውን ከዓለም አቀፉ የሲስኮ ካምፓኒ ኔትወርክ ነው።



ለማንኛውም ያገኘነውን ሙሉ መረጃ ከታች ያለውን ሊንክ ተጭነው በዝርዝር እንዲመለከቱ ጋብዘናል። ምናልባትም እርስዎም ከጥቃቱ ሰለባ አንዱ ሆነው ይችላልና። መልካም እይታ!!!

( ሙሉውን መረጃ ለመመልከት .click here )