Sunday, September 16, 2012

«ሰምና ወርቅ»


 ከካሳሁን ዓለሙ ድረ ገጽ ተመርጦ የተወሰደ ቅኔ፤
*********************
እንኳን ደኅና ገባህ ከሄድክበት አገር፣

ጠላቶችህ ሁሉ ይቅር ብለው ነበር፡፡

***************

‹ትግራይ› አይደለም ወይ መለስ ትውልድህ፣

የጁ ነው በማለት የደበደቡህ፡፡
*****************

‹መለስ ዜናዊ› ታላቅ መስፍን፣

ነበሩ ሲሉ ባገራችን፣

እንዲያ ሳያጡ ሰገነት፣

ምነው አደሩ ፈረስ ቤት፣

ሞከሩት እንጂ አልኖሩም፣

ከዳሞት አልቀሩም፡፡

***************
በዓለ ድባብ ንጉሥ ባለ ጥና አቡን፣

እየዞሩ ፈቷት አገራችንን፡፡
****************

አሁን ምን ያደርጋል ሱሰኛ መሆን፣

ብዙ ቤት ፈረሰ ትላንት በዚያ ቡን፡፡
***************

ይድናል እያልን ዓይን ዓይኑን ስናይ፣

እንዲያ እንደፈራነው እውነት ሞተ ወይ?
************

የዛሬ ዘመን ወዳጅም፣

ከሽሕ አንድ አይገኝም፣

አንቱ ብትለው ይኮራል፡

አንተ ያልከው ግን ይኖራል፡፡
*********

አሻግሬ ባይ መንገዱን፣

ኧረ ሰው ምናምን፡፡
************
ተስቦ ገብቶ ከቤቴ፣

አልወጣ ካለኝ ዓመቴ፡፡
**************

ወደ አደባባይ ወጥተህ፣

ከባላጋራህ ተሟግተህ፣

ክርክር ገጥመህ ወደ ማታ፣

ዓለም አፈር ነው ስትረታ፡፡
***************
‹ዋልድባ› ወርጄ ቀስሼ፣

ልብሰ ተክህኖ ለብሼ፣

ታዩኛላችሁ እኔን

ነገ ገብቼ ሣጥን፡፡
**************

ክፉ ቢናገር ተቆጥቶ፣

ጠላትህ ደሙ ፈልቶ፤

እሱም እንዳንተ ሰው ነው

ኧረ ተው ሰብቀህ አትውጋው፡፡
*************

ዛሬ ጠጅ ማን ጠጥቶ፣

ሁሉ ጠላ ቤት ገብቶ፡፡
************

ሠሪው ፍጥረቱን አታለለ፣

በኖራ ሠራሁ እያለ፤

መች ይፈርስ ነበር ቤታችን

እውነት ኖራ ቢሆን፡፡
********

መልካም ፈረስ ጭነህ፣

ስትወጣ ስትወርድ አየንህ፤

ከሜዳ ስትደርስ ዝግ አድርገው

መቼም ጊዜው ጣይ ነው፡፡
***********

ስማኝ ልንገርህ አትስነፍ፣

ተው እየሠራህ እለፍ፡፡
****************
ምንጭ፤www.kassahunalemu.wordpress.com