Wednesday, September 19, 2012

‹‹ባለራእዮች ይሞታሉ ራእያቸው ግን አይሞትም›

ዲያቆን ፈታሂ በጽድቅ ከተባለ የብሎጋችን ተከታታይ የተላከ ጽሁፍ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የመለስ ዜናዊን ዜና ዕረፍት ከሰማን በኋላ ብዙዎቻችን አዝነናል፡፡ በሰውኛ አቅሙ ሁሉም ምንም ማድረግ ስላልቻለ ነው እንጂ አንዳንዶች እሳቸው ከሞት ተርፈው እኔ በተተካሁ ሲሉ ሌሎች ደግሞ ምንም እንኳ ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ባያስቡም በሆነ መንገድ ከሞት አስነስተው የማቱሳላን እድሜ ቢቸሯቸው ደስተኛ እንደሚሆኑ በየመጓጓዣው፣ በየስራ ስፍራውና በየመዝናኛ አካባቢዎች የነበሩት ጭውውቶች ይናገሩ ነበር፡፡

ከሞት ማስነሳት ባንችልም ግን ሁላችንም ሐዘናችንን በተለያየ መንገድ ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ምንም እንኳ ሐዘኑ አሁን እየቀነሰ ያለ ቢሆንም የሐዘኑ ስሜትና የሐዘን መግለጫ መልእክቱ አሁንም በቴያ መልኩ እንዳለ ነው፡፡ ከብዙዎቹ የሐዘን መግለጫዎቻችን መካከል ከላይ በርዕስነት ያነሳነው አንዱ ነው፡፡ ይህን መልእክት ጎላ ጎላ ባለ ፊደል ከአቶ መለስ ፎቶግራፍ ጋር በተደጋጋሚ በተለያየ ይዘትና ስፍራ ላይ ተስቅሎ አይተነዋል፡፡

ይህን መልእክት የሰቀሉ ሰዎች ሊሉ የፈለጉት ምንም እንኳን አቶ መለስ ዜናዊ የዚህ ዓለም ቆይታቸውን ጨርሰው በሞት ቢለዩንም ራእያቸውን ግን ቀደም ሲል ጀምረውት ወይም አካፍለውን ስለሆነ የሄዱት ራእያቸው አይሞትም፡፡ ይልቁንስ እኛ እንጨርሰዋለን የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ቃል እየገቡ እንዳሉት ለማድረግ ከቻሉ የአቶ መለስ ራእይ አይሞትም ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ግን. . .

በዚህ መልእክቴ ለማሳየት የፈለኩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር የአቶ መለስ ዜናዊን ራእይ እንዴት እንፈጽም? እንዴትስ እንዳይሞት ለማድረግ እንችላለን? የሚለውን ማሳየት አይደለም፡፡ እርሱን ለማድረግ ያለሁበት ስፈራ፣ ዕውቀትና ሁኔታ አይፈቅድልኝምና ወደዚያ አልገባም፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ሊገድሉት ተማምለው ስለወጡበት አንድ ራእይ ነው ለማሳየት የምፈለገው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ወደቀደመ ትምህርቷና ወደሐዋርያት እምነት እንድትመለስ እስጢፋኖሳውያን ሕይወታቸውን ሰውተዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው ጨካኝና ከሃዲ መሪ ሰዎቹ እንዲደበደቡ፣ እንዲታሰሩ፣ እንዲሰደዱ እንዲሁም እንዲሞቱ ሲያደርግና ሲያስደርግ በእሱ እምነት ራእያቸውም አብሮ ይሞታል ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ታሪካቸው እንደሚለው መሰደዱም፣ መገደሉም፣ መታሰሩም ሰዎቹ እንዲጠፉ ከማደረግ ይልቅ ‹‹እግዚአብሔር የተጋዙበትን ሀገር እየከፈተላቸው ብዙዎችን በስብከታቸው እያሳመኑ ክርስቲያኖች እንዲያውም መነኮሳት አድርገዋቸዋል›› (ደቂቀ እስጢፋኖስ በህግ አምላክ ገጽ 35)፡፡ ጨካኙ መሪ እንደጠበቀው ሳይሆን ካሰበው ውጪ ሲሆንበት ጭካኝና ፀረ ወንጌል በመሆኑ የሚከተሉትን የማሳቀያና የመግደያ መንገዶች ወደመጠቀም ዞረ፡-

1.         በድንጋይ ደበደቧቸው፡፡
2.         ቆመውም ሆነ ተንበርክከው መጓዝ እንዳይችሉ የእግሮቻቸውን ጅማቶች አወጡባቸው በዚህ ምክንያት ደብረ ብርሃን ከተማ ወድቀው ቀሩ፡፡
3.         በጅራፍ ገረፏቸው፡፡
4.         በመሬት ላይ አስተኝተው እንደሚለፋ ቆዳ በመርገጥ ጤማይ የተባለ የንጉሡ ወንጀለኞች መግረፊያ ሁሉም የሠራዊቱ አባል እጃቸው እስኪደክማቸው ገረፏቸው፡፡
5.         አንዲትን ሴት ሁለት እግሮችዋን ግራና ቀኝ ወጥረው በማሰር ራቁትዋን አስተኝተው እሳት ካነደዱ በኋላ በፍሙ ቀኑን ሙሉ ጭኗን እና ብልቷን በእሳቱ እየጠበሷት ሲያቃጥሏት በስቃይ ሞተች፡፡
6.         እጃቸውንና እግራቸውን በመቁረጥ በድንጋይ በመደብደብ የተገደሉም ነበሩ፡፡
7.         አንገታቸውን የተቆረጡም ነበሩ፡፡
8.         በጣም በሚያሰቅቅ ብርድና ቅዝቃዜ ውስጥ ራቁታቸውን እንዲሆኑ በማድረግ በቅዝቃዜውና በእርጥበቱ ምክንያት ከመጣው ተላላፊ በሽታ የተነሳ 98 ሰዎች ሞቱ፡፡
9.         ጆሮአቸው ውስጥ ጉንዳን የተጨመረባቸው ነበሩ፡፡


10.     አስከሬኖቻቸው ከተቀበረበት እየወጣ እንዲቃጠል ተደርጓል
11.     አንደኛው ቅዱስ ጨካኙ መሪ ሳያሰቃየው በመንገድ ላይ ሌሎች ገርፈውት ቢሞትባቸው ሬሳውን እጁና እግሩ ተቆርጦ በእሳት እንዲቃጠል አስደረገ፡፡
12.     ሴት መነኮሳት ጡታቸውን ተቆረጡ፡፡
13.     በገመድ አስረው መሬት ለመሬት እንደ ግንድ የተጎተቱም ነበሩ፡፡
14.     ኮሶ በማጠጣት ማሰቃየት፡፡
15.     በጦር ወግቶ በቀዳዳው ውስጥ ድንጋይ በመወተፍ ማሰቃየት፡፡
16.     18 ቅዱሳን እህልና ውኃ በመከልከላቸው በረሃብ ሞቱ፡፡
ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን ባለራእዮቹ ሞቱ እንጂ ራእያቸው አልሞተምና ይሄው ዘመናትን ተሻግሮ እኛ ተቀበልነው ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ኃላፊነቱን ተቀብለናል፡፡ የሚሞት ሳይሆን የሚሞትለት ቅዱስ ራእይ ያለው ሕዝብ የተባረከ ነው፡፡

የጨካኙ መሪ ልጆች የሆኑትና የሞተ ራእይ ያላቸው አሁንም ፀረ ወንጌልነታቸውን ምንም እንኳን እነሱ ስመ ክርስትናን ብቻ የተሸከሙ ቢሆንም ቆመንለታል የሚሉትን ክርስትናን የሚከተሉ ወንድሞቻቸው ላይ የዘመኑ የውጊያ ስልት የሆነውን ስም የማጥፋት፣ የማግለልና ከአገልግሎታቸው እንዲታገዱ የማድረግ እንዲሁም የአባታቸው ግብር የሆነውን የመደብደብ እና የአካል ጉዳት የማድረስ ከተቻለም ለመግደል የመሞከር ተግባር ውስጥ የመግባት (ለዚህም በመሪጌታ ጽጌ ተድርጎ የነበረውን ሙከራ ማንሳት ይቻላል) አሳይተዋል፡፡ ይህን ሁሉ ለማደረግ የተነሳሱት ባለራእዮቹን ሲገድሉ ራእዮም አብሮ የሚሞት መስሏቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ‹‹ባለራእይ ቢሞትም ራእይ አይሞትም›› ሆኖባቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ ግራ ገብቷቸዋል፡፡ መፍትሄው ግን መግደል ማቁሰልና ማባረር ሳይሆን የራእዩን ምንጭ ከየት እንደሆነ አጥርቶ በማየት ከራእዩ ጋር መተባበር ነበር፡፡ ምክንያቱም ሳያውቁት ሊያቆሙት እየተንደፋደፉ ያሉት የእግዚአብሔርን ራእይ ነውና፡፡