Thursday, September 20, 2012

የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ደስተኛ አለመሆናቸውን ቤተክህነት አካባቢ በሚያናፍሱት ወሬ እየገለጹ ነው

ዐቃቤ መንበሩ «መናፍቃኑ ኃይለ ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጉት እየጸለዩ ነው አሉ፤ እርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ማለት ለእኛ እጅግ ክፉ ነገር ነውና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን» ብለዋል

ምንጭ፦ አባ ሰላማ ድረ ገጽ


 ዐቃቤ መንበሩ «መናፍቃኑ ኃይለ ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጉት እየጸለዩ ነው አሉ፤ እርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ማለት ለእኛ እጅግ ክፉ ነገር ነውና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን» ብለዋል.
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ሊቀመንብር ሆነው መመረጣቸውንና በቀጣይም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ መሆናቸው ከተገለጸ ጊዜ ጀምሮ፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆናቸው ምክንያት በማኅበረ ቅዱሳን መንደርና በቤተክህነቱ አካባቢ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ግንኙነት ባላቸው አካላት ዘንድ «ጴንጤ አይገዛንም» የሚል ቅስቀሳ ውስጥ ውስጡን እየተደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
በዘመን መለወጫ በዓል ላይ በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ በተዘጋጀው መርሀግብር ላይ የተገኙትና ንግግር ያደረጉት አቃቤ መንበር አባ ናትናኤል ትዝብት ላይ የጣላቸውን ንግግር ማድረጋቸውን በስፍራው የነበሩ ምስክሮች እየገለጹ ነው። አቡነ ናትናኤል በአቃቤ መንበርነት ከተሾሙ ጀምሮ ጊዜውን እየተሻሙና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ለመምሰል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን እያደረጉ ካለው እንቅስቃሴ መታዘብ ተችሏል፡፡ «እርሳቸው ወንበር ላይ አስቀምጡኝ» ከማለት «እርሳቸው የሚበሉትን ስጡኝ» እስከማለት መድረሳቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ በዘመን መለወጫ በዓል ለሚደረገውና ቅዱስ ፓትርያርኩን እንኳን አደረስዎ ለሚባልበት መርሐግብር ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ለተገኙ የደብር አለቆች፣ ካህናትና ዲያቆናት ባደረጉት ንግግር ውስጥ «መናፍቃኑ ኃይለ ማርያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያደርጉት እየጸለዩ ነው አሉ፤ እርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ማለት ለእኛ እጅግ ክፉ ነገር ነውና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን» ያሉ ሲሆን፣ ከበዓሉ ጋር የተገናኙ ሐሳቦችን ካቀረቡ በኋላም መጨረሻ ላይ «ቅድም ያነሣሁላችሁ የመናፍቃኑ ጉዳይ ምሥጢር ነውና በምሥጢር ያዙት» ብለዋል፡፡ ይህም የተናገሩት ተገቢ ያልሆነ ቃል እንደወቀሳቸውና ሀሳቡ መጀመሪያም ቢሆን ከራሳቸው ያመነጩት እንዳልሆነ ግምት እንዲወሰድ አድርጓል፡፡ አባ ናትናኤል ከእርጅናም ዲፕሎማሲያዊ አቀራረቡንም በሚገባ ባለማወቃቸው የተነሳ በብዙዎች ፊት የሰነዘሩትን ይህን ሀሳብ እነማንያዘዋል ሹክ እንዳሏቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ገልጸዋል፡፡
አቶ ማንያዘዋል የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀብር እለት ወደቤተመንግስት እገባለሁ አትገባም በሚል ቤተመንግስት በር ላይ ከአስተናጋጆች ጋር ሲወዛገብ በቴሌቪዥን መስኮት ያዩትና የሚያውቁት ሁሉ መነጋገሪያ አድርገውት የሰነበቱ ሲሆን፣ «አባ ናትናኤልን ደግፌ የምይዝ ነኝ» በሚል በትግል መግባቱ ታውቋል፡፡ ይህም ማኅበሩ ቀድሞም ያደርግ እንደነበረ የሚፈልገውን በእርሱ በኩል ወደአባ ናትናኤል እያቀረበ ለመሆኑ በቂ ምስክር ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ሹመት በመቃወም በዋናነት እያቀነቀነ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን ምንጮቻችን እየተናገሩ ነው፡፡ ቤተክህነት አካባቢ «ጴንጤ ሊገዛን አይገባም» የሚል ወሬ እያናፈሰ ሲሆን፣ አንዳንድ ወዳጆቹ ጳጳሳት ግን «ከዚህ በኋላ አንዳች ስሕተት ከተገኘባችሁ የምትከፍሉት ዋጋ ቀላል አይሆንምና ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ነው ማድረግ ያለባችሁ» የሚል ምክር እንደለገሷቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡



እንደሚታወቀው በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ በመሆናቸው መንግሥት በሃይማኖት ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም፡፡ በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያ ያለው ሃይማኖታዊ መንግስት ሳይሆን ሁሉንም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚያይና የሁሉንም በነጻነት የማምለክ ሕገ መንግስታዊ መብት ለማስከበር የቆመ መንግስት ነው፡፡ ስለሆነም የትኛውም የመንግስት ባለሥልጣን ሃይማኖት ሊኖረው ቢችልም፣ ሃይማኖቱን በግሉ ማራመድ ይችላል እንጂ የሃይማኖቱ ሰባኪ ወይም ደጋፊ ሆኖ ስልጣኑን ሊጠቀምበት አይችልም። እንደመንግስት ባለሥልጣን ሁሉንም ሃይማኖቶች በእኩል መመልከትና መብታቸውን ማስከበርና ሕጋዊ ጥበቃ ማድረግ እንጂ ከዚህ ያለፈ ተግባር ሊኖረው አይችልም። ይሁን እንጂ ይህን እውነት መቀበል የማይፈልጉና የሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት በታወጀባት ኢትዮጵያ የሌላውን ሃይማኖት አሳንሰውና አንኳሰው የራሳቸውን ሃይማኖት የበላይነት ማስከበር የሚፈልጉ አንዳንዶች፣ በዱሮ በሬ ለማረስ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ሳይሆን የእርሱ ኮፒ የሆኑት ሰለፊያዎችም ኢትዮጵያ ላይ እስላማዊ መንግስትን ለማቋቋም መከጀላቸው ከላይ የተገለጸውን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታና ሕገመንግስቱንም የሚጻረር ተግባር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ወገን ማኅበሩ አላማው ሃይማኖት ሳይሆን ፖለቲካ ጭምር መሆኑን በግልጽ የሚያንጸባርቅ ነው። በመሆኑም ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ ለውስጥ እያሰማ ያለው የተቃውሞ ድምፅ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድም ሆነ በሌሎች እምነት ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው እየተነገረ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ሃይማኖት ቢኖራቸውም በስልጣን ላይ ሲወጡ የመንግስትን ፖሊሲ ለማስፈጸም እንጂ ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት እንዳልሆነ መተማመን ላይ ካልተደረሰ ፖለቲካና ሃይማኖት እንደተምታቱ ይቀጥላሉ፡፡
«ከእኔ በቀር ማንም አይኑር» የሚል መርህ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን በተደጋጋሚ እንደሚከሰው በኢህአዴግ ዘመን የአምልኮ ነጻነት በመታወጁ ሌሎች ሃይማኖቶች በመስፋፋታቸው ደስተኛ አይደለም፡፡ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንደኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የአንድን ሃይማኖት የበላይነት የሚያስተናግድ ህገመንግስት የላትም፡፡ እርሱ ከንጉሱ ጋር አብሮ ተቀብሯል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማንም ተሾመ ማን ነገሩ የሚቀጥለው በዚሁ መንገድ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የተሾመው ባለስልጣን ከዚህ መንገድ አፈንግጦ ቢገኝና የመንግስት ባለሥልጣን መሆኑ ቀርቶ ሃይማኖቱን አስፋፊ ከሆነ ግን ያን ጊዜ ጥያቄው ቢነሳ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ የእኛ እምነት ተከታይ አይደሉም በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን መቃወም ምንም መሠረት የለውም። እርሳቸው በችሎታቸው፣ በፖለቲካ አቋማቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው እንጂ በሃይማኖታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልሆኑም መታወቅ አለበት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቡነ ጳውሎስና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ትልቅ አጋጣሚ የፈጠረላቸው የመሰላቸው የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ቤተክህነቱን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት ያህል እየተሰማቸው ሲሆን፣ በቤተክህነት አካባቢ የተለያዩ ወሬዎችን በማናፈስ የፕትርክናውን ሥልጣን በእነርሱ ሰው ለማስያዝ ጥረታቸውን አጠናክረዋል እየተባለ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በማንያዘዋል የሚመራ አንድ የስለላ ቡድን አስርገው በማስገባት «መንግሥት ነው የላከን እገሌን ምረጡ ተብሏል» የሚል ወሬ በጳጳሳቱ መካከል በማናፈስ በመንግስት ስም የራሳቸውን ሥራ እየሠሩ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የዚህ ወሬ አላማም መንግስትን በጣልቃ ገብነት ለመወንጀልና በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲያደርጉ እንደነበረው ፓትርያርኩን ያስቀመጠው መንግሥት ነው ለማስባል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በወሬው የሚፈቱ አባቶችን በመያዝ የራሳቸውን ሰው ለማስቀመጥ የዘየዱት መላ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች እየተናገሩ ነው፡፡