Sunday, November 27, 2011

ታቦት በአዲስ ኪዳን እንዴት?




ታቦት በአዲስ ኪዳን እንዴት?to read in PDF

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በዲያቆን ዓባይነህ ካሴ የተሰጠውና ስለጽላት የአዲስ ኪዳን ዘመን አስፈላጊነት ስብከቱ የተነሳ ነው። አባይነህ ካሴ ያልገለጻቸው፣ ያልመለሳቸውና ያላብራራቸው፣ ነገር ግን በምንም መልኩ ሊታለፉ የማይገባቸው ነጥቦች ስላሉ በዚህ ጽሁፍ ይዳሰሳሉ። ምክንያቱም ለክርስቲያኖች ከየትኛውም መረጃ በላይ የእምነታቸው መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን እሱም ሳይሸፋፍን ለብሉይ ኪዳኑ ሥርዓትም ይሁን ለአዲስ ኪዳኑ ዘመን እምነት መመሪያን፣ትእዛዛቱንና መንገዶቹን በግልጽ አስቀምጦት ስለሚገኝ ነው።
ዓባይነህ ካሴ ስሜቶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያዛመደ በዚህ የጽላት ዓለም እምነት ላሉ፣ በዚያው እንዲጸኑ፣ ይህንን ለማይቀበሉት ደግሞ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ በመስጠት የሁለት ወገን ስራውን ለመስራት ሞክሯል። ይሁን እንጂ መረጃውን በማብራሪያ ለማጠናከር ከመሞከር ባለፈ በተጨበጠ ማስረጃ ማስደገፍ ባለመቻሉ ግልጽ እውነቶችን እያነሳንሥነ አመክንዮ «Give reasons or cite evidence in support of an idea, action, or theory, typically with the aim of persuading others to share one's view» እንሰጥበታለን።
ታቦት ለእስራኤል ዘሥጋ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት
ነብዩ ሙሴ ከእግዚአብሔር ቃል እየተቀበለ ለሕዝቡ መልእክቱን ያደርስ ነበር።
ዘጸ 3፣15 እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ። የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።


18 ፣15-16 ሙሴም አማቱን። ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ
ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው። እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
ይህ ሙሴ ብቻውን ከእግዚአብሔር ቃል እየሰማ የሚያስተላልፈው መልእክት ከሕዝቡ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ስለሌለው፣ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የኔ አምላክ ከማለት ይልቅ የሙሴ አምላክ ወደማለትና የሚሰጠውን ቃል ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ያህል ገምቶ መጠራጠርን በመፍጠሩ የተነሳ እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት መግለጽ ስላለበት የመጣ ሕግ ነው።
ከሕዝቡ እንጉርጎሮዎች መካከልም እነዚህ ይጠቀሳሉ።
ዘጸ 15፣23 «ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ»
ዘጸ 16፣3 «እስራኤልም ልጆች። ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው»
ዘጸ 17፣2 «ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት። የምንጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት። ሙሴም፦ ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ? አላቸው»
ዘጸ 17፣7 «ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር። እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም? ሲሉ እግዚአብሔርን ስለተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም ማሳህ፥ ደግሞም መሪባ ብሎ ጠራው»
ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ባለመቻሉ ማንጎራጎር ፣መጠራጠርና ረጅሙን የእግዚአብሔር ዓላማ ለመረዳት ባለመቻላቸው እየመራቸው ያለው እግዚአብሔር መሆኑን እንዲያውቁ ከፊት ፊት መሪ ምልክት መስጠት አስፈልጓል። ለዚህም ሲባል ለሙሴ የሚመጣውን ድምጽ እነሱም እንዲሰሙ በማስፈለጉና ከማንጎራጎር ይልቅ ቃሉ የእግዚአብሔር እንደሆነ ራሳቸው አምነው እንዲቀበሉ እግዚአብሔር በመካከላቸው እንደሆነ እንዲረዱና እግዚአብሔር ርስት ምድርን የማውረስ ቃሉን ስለመጠበቁ፣ ሕዝቡም የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆኑን ለመቀበል ቃል ኪዳንና የክብሩ መገለጫ ጽላት መስጠት እግዚአብሔር መርጧል።
ይህ ሥርዓት የተሰጣቸው ከግብጽ ምድር ከወጡ ከሦስት ወር በኋላ ነው። ዘጸ 19፣1 «በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ»
ስለጽላቱ አሰራር ወደኋላ ላይ የምንመጣበት ሆኖ በምክንያቱ ላይ አትኩሮታችንን ስናደርግ ሙሴ በእግዚአብሔር ጥሪ ሲና ተራራ ላይ ወጥቶ እስኪመለስ ድረስ ያ ችኩል ሕዝብ ድምጽ ያመጣላቸው የነበረው ሰው ነብዩ ሙሴ ከፊታቸው በመጥፋቱ ምክንያት በቀደመው ዐመጻቸው ማስቸገራቸው አልቀረም።
ዘጸ32፣1 «ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት»
ጣዖት ሰሩ፣አመለኩ። ሙሴም ሲመለስ የዘፈን ድምጽ ሰማ፣ጽላቶቹንም በጣዖቱ ላይ ሰበረ።
የመጀመሪያው ጽላት መሰበር 1/ የሕዝቡን የጣዖት ልብ የሚሰብር
2/ ከህዝቡ ዐመጸኞችን የሚሰብር
3/ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር የራቀበትን ድልድይ የሚሰብር ነበር።
ይህም በእነዚህ ጥቅሶች ታይቷል።
ዘጸ 32፣27 «ርሱም፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእናንተ ሰው ሁሉ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩም ውስጥ በዚህና በዚያ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፥ የእናንተም ሰው ሁሉ ወንድሙን ወዳጁንም ጎረቤቱንም ይግደል አላቸው»
ዘጸ 33፣6 «የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ጌጣቸውን አወጡ»
ዘጸ 33፣8 «ሙሴም ወደ ድንኳኑ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፥ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር»
እግዚአብሔር ለሙሴ ጽላቱን ከሰጠ በኋላ እንደሥርዓቱ መደረግ የሚገባውን ሁሉ እያደረገና እያስደረገ ሕዝቡን ወደርስት ምድር ይመራ ነበር። ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ለመቀበል የትም መሄድ አያስፈልገውም። ሕዝቡም ሙሴ፣ ሄደ-መጣ እያለ በመለያየት ሃሳብ አልኖረም። ይልቁንም ሙሴ ብቻ ይሰማ የነበረውን ድምጽ በቀጥታ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እያየ እንዲቀበልና እንዲፈጽመው ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ክብር ማየት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህንንም ይህ ቃል ይነግረናል።
ዘጸ 33፣8-10 «ሙሴም ወደ ድንኳኑ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፥ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር»
አሁን በሙሴና በእግዚአብሔር፣ በሙሴና በሕዝቡ መካከል ያለው የግንኙነት መስመር በቃልኪዳኑ ታቦት በኩል እየተከናወነ መገኘቱን እናያለን። ሕዝቡ ከዚህ ግንኙነት በኃጢአት ሲከለከል ራሱን የሚያድስበት የመንጻት መንገዱን ይጠቀማል።
የሚጓዙትም በመገኛው ድንኳን ያረፈው ደመና ሲነሳ፤ የሚያነጋግራቸውም በመገኛው ድንኳን የእግዚአብሔር ደመና ሲያርፍ ነበር።
ዘጸ 40፣35 ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም።
ዘጸ40፣36 ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር።
ኦሪት ዘፍጥረት የስነፍጥረትን መነሻና ከስነፍጥረት የሰውልጅ ታሪክ ውስጥ የእስራኤል ዘሥጋ መመረጥ፣ኦሪት ዘጸአት ዐመጻንና የዐመጻን ልብ በመሻርና በመምራት ለእስራኤል ዘሥጋ የቃል ኪዳን ጽላት መስጠት፣ ኦሪት ዘሌዋውያን ቃልኪዳኑ የሚጠበቅበትን ሥርዓት የማሳወቅ ሕግ መሆኑን እንመለከታለን።
እንግዲህ ጽላቱ ለእግዚአብሔር ሕዝብ መስጠት ያስፈለገው እግዚአብሔር ቃሉን ስሰጥ የሚገለጽበት፣ ሙሴም ሕዝቡም ትእዛዙን የሚሰሙበት ሲሆን ሙሴ መካከለኛ ድልድይ ሆኖ ህዝቡን ከእግዚአብሔር፣ እግዚአብሔርን ከህዝቡ የሚያገናኝና ከምድራዊዋ ርስት የሚያደርስ ነብይ ነበር።
የጽላቱና የታቦቱ ሥርዓት ምን ይመስላል?

የጽላቱን ዓላማ ከላይ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ለማየት ሞክረናል። አሰራሩስ የሚለውን ደግሞ ለቀጣይ ሃሳቦቻችን ማጠናከሪያ በአጭር በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን።
የመጀመሪያዎቹን የእግዚአብሔር ጽላት ሙሴ ከሰበራቸው በኋላ ዳግመኛ እርሱ ራሱ ቀርጾ ወደ ሲና ተራራ ይዞ እንዲወጣ ተነግሮታል።
ታቦቱ( ማኅደሩ)ርዝመቱ 2 ክንድ ተኩል፣ ወርዱ 1 ክንድ ተኩል፣ ከፍታው 1 ክንድ ተኩል ከግራር እንጨት የተሰራ ነበር። (ዘጸ 25፣10)
ውስጡና ውጪውም በንጹህ ወርቅ የተለበጠ ነው። 4 የወርቅ ቀለበቶች የተንጠለጠሉበትና 2 መሎጊያዎች ለመሸከሚያ የሚሆኑ በወርቅ የተለበጡት ግራና ቀን ነበሩ።
የታቦቱ መክደኛ 2 ክንድ ተኩል ርዝመት፣ 1 ክንድ ተኩል ወርድ የሆነ ሲሆን፣ ዳርና ዳር ከወርቅ የተሰሩ ኪሩቦች እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ፊት ለፊት አተያይቶ እንዲሰራ ተደርጓል።
የህብስቱን ማስቀመጫ(ዘጸ25፣23) የመብራቱን መቅረዝ (ዘጸ 25፤32) የማደሪያውን ድንኳን (ዘጸ 25፣26)የሚቃጠል መስዋእት ማቅረቢያ (ዘጸ 27፥1) የመቅረዙ ዘይት (ዘጸ 27፣20) ኤፉድ(ዘጸ 28፣15) የዕጣን መሠዊያ (ዘጸ 30፣1) የመታጠቢያ ሰን ወዘተ ለታቦቱ ሥርዓት የግዴታ ሕጎች ሁሉ ተሰርተዋል። እነዚህን ለማሳያ ያህል ጠቀስናቸው እንጂ ከታቦቱ ሥርዓት ጋር የሚደረጉት ሕጎች እነዚህ ብቻ አይደሉም።
እንግዲህ ሙሴ ቀርጾ ወደተራራው ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር በጣቱ በጽላቶች ላይ 10ቱን ትእዛዛት ጽፎ እንደሰጠውና(ዘዳ10፣4) ከዚያም በታዘዘው መሰረት እየፈጸመ ወደርስት ምድር እንደመራቸው እንረዳለን።
በአጭሩ ካስቀመጥናቸው ኦሪታዊው ሕግና ሥርዓት አንጻር በመግቢያችን ላይ እንዳመለከትነው ዲያቆን ዓባይነህ ካሴ ወዳስተማራቸው፤
የአዲስ ኪዳን ታቦትና ጽላት ጉዳዮች የምናነሳቸው ተጨባጭ ነጥቦች ከታች የተቀመጡት ናቸው።

1/ የኦሪቱ ታቦትና ጽላት ወደአዲስ ኪዳን ተሻግሯል የሚለን ከሆነ የአዲስ ኪዳኑ ታቦት ወርድ፣ ቁመት፣ርዝመት የኦሪቱን የጠበቀ ነው ወይ?
2/ቀለበቶቹ፤ መሎጊያዎቹ፣ ኪሩቦቹ፣ የስርየት መክደኛው ወዘተ ሁሉ አሁን አሉ? የካህናቱ ኤፉድ፤መጋረጃ፤የመቅደሱ የወርቅ ሳህኖች ዋንጫዎች ሁሉ እንደዚያው እንደጥንቱ ነው?
3/ጽላቶቹን በተመከተ ሙሴ ከእብነ በረድ ቀርጾ ወደተራራው ወጥቶ እግዚአብሔር እንደጻፈባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገር ውጪ ሙሴ ጻፈባቸው አይልም። ዛሬስ ከእብነበረድ እየጻፋችሁ ሲና ሄዳችሁ ወይም እግዚአብሔር የሚጽፍበት የሰራችሁት ሲና ኖሮ እዚያ እየሄዳችሁ ነው የምታስጽፉት?
4/ የሙሴን ጽላቶች እግዚአብሔር ጽፎባቸው የእግዚአብሔር ቃልኪዳን ጽላቶች ተብለዋል። የዛሬውን ማን ጽፎባቸው ነው የቃልኪዳን ታቦት የሚባሉት? ማን ከማን ጋር የገባበት ኪዳን ነው?
5/ሙሴ እንዲቀርጽ የተነገረው ሁለት ጽላት ብቻ ነበር። እግዚአብሔርም የሰጠው ሁለቱን ብቻ ነው። 12 ቱ ነገደ እስራኤል ርስት ምድራቸው ከገቡ በኋላ ያመልኩ የነበረው በማዕከል ባለው የእግዚአብሔር ኪዳን ላይ ብቻ ነው። ለምን በ12ቱ ነገደ እስራኤል ከድካምና ከጉዞ እንዲያርፉ እግዚአብሔር ብዙ ጽላትን አልፈቀደም? የዛሬውስ ስራ የኦሪቱን ይከተላል ከተባለ ለምን ኦሪቱ ሲሰራባቸው ከነበረውና ሙሴ ከተቀበለው ተላልፎ በሺዎች የሚቆጠር ሆነ?
6/የሙሴን ሥርዓት ተረክበናል ካልክ የሙሴን የመቅደስ ሥርዓት አለመጠበቅህ መሻርህን አያሳይም?
7/ በኦሪቱ የስርየት መክደኛ ላይ የእግዚአብሔር ክብር ከመገለጹ በፊት ደመናው በዓምዱ ላይ ሲወርድ ሕዝቡ ሁሉ ያይ ነበር። ዛሬስ ህዝቡ እንደያኔው ያያል?
7/ ወደቅድስተ ቅዱሳኑ ሊቀካህናቱ በዓመት አንድ ቀን ለራሱም ሆነ ለሕዝቡ መስዋእት አድርጎ ይገባ ነበር። ዛሬስ ይህ ሥርዓት በታቦታችሁ ላይ ይደረጋል?
8/እግዚአብሔር 10ቱን ትዕዛዛት በጽላቶቹ ላይ መጻፉን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የሙሴን የጽላት ስርዓት ተከትለናል ካልክ ሙሴ ያላደረገውን የ10ቱን ትዕዛዛት ሽረህ የራስህን ፈቃድ ስእልና ስም ዛሬ የምትቀርጸው ለምንድነው? ለቅዱሳን መታሰቢያ በጽላት ቀረጻ አድርጉ የሚል ትእዛዝ ከየት መጽሐፍ የተገኘ ነው? ፍጡርና ፈጣሪ በአንድ ሰሌዳ(ጽሌ) ላይ እንዴት ይከብራሉ? ኦሪት ያንን አሳይታለች?
9/ አክሱም አለች የምትባለው ጽላተ ሙሴ የሰሎሞን ቤተመቅደሷ ጽላት ከሆነች እንዴት እርሷ የነበራትን ስርዓት የጣሰ የጽላት ቀረጻ በመላ ኢትዮጵያ ይከናወናል?
10/ በአንድ በኩል ክርስቶስ ሕግና ነብያትን ለመሻር አልመጣሁም ብላችሁ ስታስተምሩ በሌላ በኩል ደግሞ የኦሪቱን የታቦት ሕግ የሻረ ስርዓት ለምን ትሰራላችሁ?
ማጠቃለያ፣
ዲያቆን ዓባይነህም ሆነ ማኅበሩ የእግዚአብሔርን ቃል ወደልባቸው መሻት ለማጣመም የተልዕኰ ሰዎች ይመስሉኛል። ትንሽ የቃል ሽታ ያላቸውን ደጋፊ ጥቅሶችን ፈልጎ በመልቀም መዓዛ ያለው ዘይት ጨምቆ ለማውጣትና እንዲያሸቷቸው የማይቆፍሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ የለም። እውነቱ ግን አፍጥጦ ይታያል፣ የኦሪቱን የታቦት ሥርዓት ሽራችሁት ፣የራሳችሁን ስርዓት ተክላችኋል ፣ያም የሚመዘነው በመጽሐፍ ቅዱሱ የሥርዓት ሕግ ነው።
በሰውና በእግዚአብሔር መካከል አስታራቂና አገናኝ የነበረው የእስራኤል ዘሥጋ ነብይ ሙሴ ነበር። የእስራኤል ዘነፍስ አስታራቂና መካከለኛ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሙሴ ቃሉን ከእግዚአብሔር እየተቀበለ ለሕዝቡ ያደርስ ነበር። ኢየሱስ ግን ለህዝቡ የደረሰ ራሱ እግዚአብሔር ቃል ነው። ሙሴ ከርስት ምድር ውጭ ሞቶ ተቀበረ። ኢየሱስም ከቅድስቲቱ ከተማ ውጭ ሞቶ ተቀበረ። ሙሴ የተቀበረበትን እስራኤል ዘሥጋ አላወቀም። እስራኤል ዘነፍስ ሞቶ ያልቀረውና በአብ ቀኝ የተቀመጠውን ነብይ ያመልካል።
ቃሉን የሚሰሙበትና ክብሩን የሚገልጽበት የታቦት ኪዳን እስራኤል ዘሥጋ ተሰጠው። ቃሉን ራሱ የሚሰጥና ክብሩንም በሞቱ ለሕዝቦቹ የገለጸ ሰማያዊ ጽላት ኢየሱስ ነው።
ዘዳ 18፣18 ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል
2ኛ ቆሮ 3፥3 እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው።
የኦሪቱን የታቦት ሥርዓት ሳይጠብቁ ሙሴን የውሸታቸው ምስክር አድርገው የሚጠሩ ሰዎች ምን ይባላሉ?
እግዚአብሔር ፍርዱን ያሳይ!! ከምንል ውጭ የምንለው የለም።