Monday, November 21, 2011

የሚያድን ዕይታ


የዘመኑ መስታወት.......



by Dagnu Amde on Friday, November 18, 2011 at 7:11pm

አቤቱ÷ እኔን ለማዳን ተመልከት
አቤቱ÷ እኔን ለመርዳት ፍጠን
(መዝ.69÷ 1)::

በሕይወታችን ብዙ ነገሮችን ዐይተናል፡፡ ዐይተናቸው በውስጣችን የቀሩ፣ ዐይተናቸው የረሳናቸው፣ ዐይተናቸው ደግመን ለማየት ያልፈቀድናቸው፣ ዐይተን እንዳላየ ያለፍናቸው፣ ዐይተን የታዘብናቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ጽጌረዳን ዐይተን እሾህን እናያለን፡፡ የተንሰራፉ አበቦች በአሜከላዎች ላይ ተጐዝጉዘው እናያለን፡፡ ዐይናችን ሁለቱንም ታያለች፡፡ ኅሊና ግን አጥርታና መርጣ ታያለች፡፡ በዐይናችን ብዙ መልካምና ክፉ ነገሮችን እናያለን፡፡ ላየነው ሁሉ ምላሽ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ምላሻችንን የሚፈልጉ ዕይታዎች ግን አሉ፡፡ ማየት ከመስማት በላይ ነው፡፡ ሰምቶ ምላሽ ያልሰጠ ሲያይ ግን ምላሽ ይሰጣል፡፡ ማየት የተግባር አዛዥ ናት፡፡

 
ሰዎች በቃል ሊገልጹት የሚያንስባቸው የመሰላቸውን ነገሮች መጥታችሁ ተመልከቱ በማለት ይጋብዙናል፡፡ በዐይናችን የሙት ልጆችን የረሀብ ሰለባዎችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ደጋፊ አጥተው የተጨነቁ አረጋውያንን፣ በግፍ የታሰሩ ምንዱባንን፣ በበሽታ የሚያለቅሱ ድውያንን፣ የመጣልና የመረሳት ፈተና የወደቀባቸውን ኅዙናንን፣ ለቀጣይ አንድ ሰዓት የመኖር ዋስትና የማይሰማቸው ቅቡፃንን አይተናል፡፡ ላየናቸው ነገሮች የሰጠናቸው መልሶች ግን የተለያዩ ናቸው፡፡፡ በአገራችን የመጀመሪያ እርዳታ ብቻ ሳይሆን የመጨረሻም እርዳታ የሆነው ከንፈር መምጠጥ ነው፡፡ ላየነው ነገር ከከንፈር ፉጨት የበለጠ ምላሽ አልሰጠን ይሆናል፡፡ የራሳችንን ችግር ከሌሎች ችግር ጋር አወዳድረን እኔ ያለፍኩትና የማልፍበት ይብሳል ብለን ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ዓመት ለታሰረው እንዳናዝን የሦስት ዓመት እስራታችን መሰናክል ሆኖብን ይሆናል፡፡ ላየነው ችግርም የእርዳታ መንገድ ጀምረን በትንሹ በመርካት ቆመን ሊሆን ይችላል፡፡

ዓይኖቻችን ለማየት የሚናፍቁትን ያህል እጆቻችን  የወደቀውን ለማንሣት አይዘረጉም፡፡ ጆሮዎቻችን ምሥጢርን ለመስማት እህ የሚሉትን ያህል አንደበታችን ለመሸፈን አይጠነቀቅም፡፡ የማየት ጥማታችን ከፍተኛ ነው፡፡ በአገራችን ዝናብ ሲዘንብ ወደ ቤት፣ ጥይት ሲዘንብ ወደ አደባባይ የምንወጣው የማየት ጥማት ስላለን ነው፡፡ ልንፈታ የምንችለውን ነገር ማየት አንፈልግም፡፡ ልንፈታ የማንችለውን ነገር ለማየት ግን እንጨነቃለን፡፡ መሬት ላይ ወድቆ የሚያጣጥረውን ሰው በየደቂቃው ሃምሳ ሃምሳ ሰዎች ይከቡታል፡፡ ሃምሳው ለደቂቃ አይቶ ሲያልፍ ሃምሳው ይተካል፡፡ የወደቀውን የሚረዳው ግን ከመቶ አንድ ሰው ነው፡፡ የሚከብ ሁሉ የሚረዳ አይደለም፡፡ የወደቀውን የከበቡት ሰዎች፡- ‹‹ምን ሆኖ ነው?›› ‹‹አገሩ እዚህ ነው?›› ‹‹ያመመው ስኳር ነው?›› ‹‹ሌቦች ጐድተውት ይሆን?››  ‹‹ወይ ማሳዘኑ! እኔ እጥፍ ልበል፣ እናቱ እንኳን ይህን አላየች›› ‹‹ፖሊስ አይቶታል …›› ይላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዓይኖችና ድምፆች ወደ ሞት እየተጓዘ ያለውን ሰው አይመልሱትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ቀዝቃዛ ውሃ በማንኪያ የሰጠው ሰው የሞትን ከባቢ ይበትንለታል፡፡ ከብዙ ትልልቅ ቃሎች አንድ ማንኪያ ውሃ ትበልጣለች፡፡ ትንሽ ተግባር ትልልቅ ቃሎችን ዝም ታሰኛለች፡፡  እነዚህ ሁሉ ድምፆች ከማየት የበለጠ አይረዱም፡፡ ቀርቦ የሚረዳ፣ በቊስል ላይ ዘይት የሚያፈስ ግን ከመቶ አንድ ሰው ነው፡፡
 
የስልክ እንጨት ሲተከል መንግሥት የቀጠራቸው አምስት ሠራተኞችን እናያለን፡፡ ሾፌሩ አንድ፣ እንጨቱን የሚተክሉ ሁለት፣ ግንዱ ጫፍ ላይ ወጥቶ አምፖል የሚሰቅለው አንድ ሲሆን አንደኛው ግን ከብቦ የቆመውን ሰው የሚበትን ነው፡፡ ቻይናዎቹ ሳይቀር፡- “ኢትዮጵያውያን ሌላ አገር አላቸው ወይ?” እስኪሉ ከሚሠራው የሚመለከተው እንደሚበዛ፣ ለአገራችን የእኔነት መንፈስ፣ ለሥራ ልባዊ ፍቅር እንደሌለን ታውቋል፡፡ አዎ ከሚሠራው የሚያየው ይበዛል፡፡ ማየት ሁሉ መሥራት አይደለም፡፡ ማየት ሁሉ መሥራት ቢሆን ስንት ተቺዎች የተቹትን ነገር በአጭር ታጥቀው ባስተካከሉ ነበር፡፡
 
ነቢዩ ግን፡- ‹‹አቤቱ÷ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ እኔን ለመርዳት ፍጠን አለ (መዝ. 69÷1)፡፡ እግዚአብሔር ካየ ረዳ ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዕይታ ማየት ብቻ አይደለም፡፡ ዓይኖቹ ኃይሉን ያስከትታሉ፡፡ እርሱ ሲያይ መፍትሔ አለ፡፡ እግሮቹም ለረድኤት ይፈጥናሉ፡፡ ግራኝ መሐመድ ኢትዮጵያን በኃይል ወርሮ ሕዝቡን በሰይፍ ስለት ባሰለመ ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሥ ለእርዳታ ወደ ፖርቱጋል መንግሥት አቤት ብሎ ነበር፡፡ በወቅቱ ገናና የነበረው የቱርክ እስላማዊ መንግሥት በሃይማኖት አንድነት ግራኝን ረድቶ ነበር፣ በቱርክ መንግሥት አንጻር ገናና የነበረው የክርስቲያን መንግሥት የፖርቱጋል መንግሥት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥም በክርስቲያንነት መንፈስ እንዲረዳቸው የፖርቱጋልን መንግሥት እርዳታ ጠይቀው ነበር፡፡ እርዳታው ግን የደረሰው ከዐሥራ አምስት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ እርዳታው በጊዜው አልነበረም፡፡ የእግዚአብሔር እርዳታ ግን በጊዜው ነው፡፡ ስለዚህ ነቢዩ፡- “ አቤቱ እኔን ለመርዳት ፍጠን አለ፡፡

ሰው የሚያየው ያየውን በአፉ ለማውራት ወይም በልቡ ለመታዘብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለማዳን ያያል፡፡ ሰው ቢመጣም ካለቀ በኋላ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ነገርን በጊዜው ውብ ያደርጋል፡፡ ነቢዩ፡- “ አቤቱ÷ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ÷ እኔን ለመርዳት ፍጠን(መዝ. 69÷1) ያለው በምን ዓይነት ችግር ውስጥ ሆኖ ነው? ስንል የራሱ ጸሎት ይገልጽልናል፡፡
 
ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቊሉም÷
ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም፡፡
እንኳን  እንኳን  የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ››
                                                   (መዝ. 69÷ 2-3)፡፡

የነፍስ አሳዳጆች
ነቢዩ፡- “ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቊሉም÷ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም›› በማለት ማዳኑን የጠየቀበትን ችግር ገልጧል (መዝ. 69÷2)፡፡
ስለበላን፣ ስለጠጣን፣ ስለለበስን፣ ስለደመቅን የሚበሳጩ እንዳሉ ሁሉ በነፍሳችን ብልጽግናም የሚበሳጩ ብዙ ናቸው፡፡  ነፍሳችንን የአሳባቸው፣ የፍልስፍናቸው ደግሞም የተረታቸው ተገዢ ሊያደርጓት የሚያስቡ፣ እነርሱ የሚያዩትን እኛ ግን የማናየውን ወጥመድ የሚዘረጉ፣ ተከታትለን እንያዛቸው ብለው ከቤታቸው የወጡ፣ እስክንወድቅ እንቅልፍ የማይዛቸው ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን እንጠቀም ብለው ይህን ያደርጋሉ? ብንል፡-
  1. የሰይጣን ወኪል በመሆን ያስታሉ፤
  2. አሳባቸውን በግድ ሊጭኑብን ይነሣሉ፤
  3. ኃጢአት ባልንጀራ ይፈልጋልና ተባባሪ ሊያደርጉት ይሻሉ፤
  4. በነፍሳችን ማረፋችን እያበሳጫቸው ይቃወሙናል፤
  5. መድረሻችን እየታያቸው በአጭር ሊቀጩን በክፉ ይመክራሉ፡፡
በሥጋዊ ስኬታችን የተነሡብንን ሰዎች የምንከላከለውን ያህል በነፍሳችን ብልጽግና ባላጋራዎች እንደሚነሡ  መጠራጠር እንኳ አይሆንልንም፡፡ የነፍስ ባላጋሮች ከሥጋ ባላጋሮች ይከፋሉ፡፡ ነቢዩ የእግዚአብሔርን ፈጣን እርዳታ የለመነው ከእነዚህ ክፉ መካሮች እንዲያድነው ነው፡፡ ነፍስ በዋናነነት ሦስት ጠላቶች አሏት፡፡ እነርሱ፡- ሥጋ ዓለምና ሰይጣን በመባል ይጠራሉ፡፡ ሥጋ በውስጣችን ያለው ክፉ የኃጢአት ዘር፣ ዓለም አካባቢያዊ ክፉ ተጽእኖ ሲሆን ሰይጣን  ለዘመናት የመዳናችን ተቃዋሚ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእነዚህ ጠላቶች እንዲያድነን ዘወትር መጸለይ ያስፈልጋል፡፡
 
በሞታችን የሚሠረጉ
ነቢዩ፡- “ እንኳን  እንኳን  የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ በማለት ይጸልያል (መዝ. 69÷3)፡፡
ክፉዎች ደስታቸውን የመሠረቱት በሚጠሉት ሰው ውድቀት ላይ ነው፡፡ ደስታቸው መንፈሳዊ ሳይሆን ሰይጣናዊ ነው፡፡ ሠርጋቸውን የሚያደርጉት ሞታችን ላይ ነው፡፡ ወድቀን ካላዩ ደስታ የላቸውም፡፡ የእኛን መርዶ ለመስማት ጆሮዎቻቸው የነቁ ናቸው፡፡ ታዲያ ውርደታችንን ለሚናፍቁ ትልቁ መፍትሔ ከሚያዋርድ ግብር ተጠብቆ መኖር ነው፡፡ እንድንታመም ክፉ ለሚናገሩን አለመታመም መፍትሔው ነው፡፡ ካልታመምን መልሰው ይታመማሉ፡፡ በእውነት መረጃ አለኝ የሚሉ ነገር ግን መርጃ አለኝ ብለው መናገር የማይችሉ ስንት አሳዛኞች አሉ፡፡ ነቢዩ ከእነዚህ እንዲጠብቀው ጸለየ፡፡

ነቢዩ በመቀጠል፡- ‹‹የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሤት ያድርጉ ደስም ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወዱ ሁልጊዜ፡- እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይበሉ›› ይላል (መዝ. 69÷4)፡፡ ነቢዩ እውነተኛ ወዳጆቹ የእግዚአብሔር ወዳጆች እንደሆኑ ያምናል፡፡ የእኛ ወዳጆች የእግዚአብሔር ወዳጆች ላይሆኑ ይችላሉ፤ የእግዚአብሔር ወዳጆች ግን የእኛ ወዳጆች ናቸው፡፡ የእኛ ወዳጆች ቀን ዐይተው፣ መሐላቸውን አፍርሰው ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ወዳጆች ግን ፍቅራቸው በዘመናት  ውስጥ ያው ነው፡፡ የፍቅራቸው መሠረቱ እውነት እንጂ ሁኔታ አይደለም፡፡ ነቢዩ ስለ መልካሞች ሲጸልይ፣ በእግዚአብሔር ፊትም መልካሙን ሲመኝላቸው እናያለን፡፡ እኛ ስለ መልካሞች መጸለይ የሚያስፈልግ አይመስለንም፤ ነገር ግን በመልካም ሥራቸው እንዲጸኑ ጸጋን መለመን  ተገቢ ነው፡፡ ከእነርሱ ያነስን ደካሞች መሆናችንን ብናምን እንኳ መጸለይ መልካም ነው፤ ምክንያቱም ጸሎትን የሚመልሰው አንዱና ብርቱው እግዚአብሔር ነውና፡፡ በመልካሞች ፊት ስለ መልካምነታቸው ውዳሴ ከማቅረብ፣ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እነርሱ መጸለይ እውነተኛነት ነው፡፡

እውነተኛ ደስታ ያለው እግዚአብሔርን በመሻት ውስጥ ነው፡፡ የዓለም መሻት እንቅልፍ የሚነሣ እንጂ የሚያሳርፍ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ግን ሲሹት እንኳ ያረካል፡፡ የእግዚአብሔርን ትድግና ብቻ የሚጠባበቁም ታላቅነቱን እንደሚያዩ ነቢዩ ተናግሯል፡፡ እኛስ የምንሻው ምንድነው? መዳንን የምንናፍቀውስ ከርእዮተ ዓለሞች ወይስ ከአዋቂዎች ነው? እግዚአብሔር ታላቅ ነው ብለን በሥራው ለመዘመር ተስፋችን እርሱ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር ለማዳን ያያል!! ሰዎች ለትዝብት፣ እግዚአብሔር ግን ለመሸፈን ያያል፡፡ ሰዎች ያዩትን ለማሳየት፣ እግዚአብሔር ግን በጉድለታችን ላይ ሙላቱን ለመግለጥ ያያል! ለትልልቅ ሰዎች ችግራችንን ለማስረዳት፣ የጠቢባንን እርዳታ ለማግኘት ብዙ ዘመን ተገልጠናል፡፡ በነጩ የጽድቅ ሸማ ለሚሰውረው ጌታ ግን ዛሬ እንገለጥ፡፡ ከነቢዩ ጋር እንዲህ እያልን እንጸልይ፡

 ‹‹እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፤ አቤቱ÷ እርዳኝ፤
ረዳቴ ታዳጊዬም አንተ ነህ፤ አቤቱ÷ አትዘግይ››
(መዝ. 69÷5)፡፡
source- dejeselaam.blogspot.com