Saturday, November 26, 2011

ይድረስ ለቀሲስ ደጀኔ!!


«እስራኤል ዘሥጋን በመንገዳቸው ሁሉ የጠበቃቸው፥ መና ከሰማይ ያወረደላቸው፥ ተአምራትን ያደረገላቸው፥ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ርስታቸው የመራቸው፥ በደመና መጋረጃ የጋረዳቸው፥ በክንፎቹም የሸፈናቸው መጋቤ ብሉይ የተባለ ቅዱስ ሚካኤል ነው»በማለት በብሎግዎ ላይ ጽፈዋል። ገረመኝና አንዳንድ ጥያቄዎችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን አቀረብኩልዎ!!
ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው- ይህንን ከየትኛው መጽሐፍ ላይ አገኙት? ሚካኤል ነው የሚል ተጽፏል? ወይስ ነገረ ሥራው ሚካኤልን ይመስላል ብለው ያልተገለጸውን አቅኚ ሆነው ነው? እግዚአብሔር ሚካኤል ስለመሆኑ ያልገለጸው ረስቶ ወይም ተሳስቶ እርስዎ ግን በትርጉም ፈትተውት ያገኙት እውቀት ነው?
መቼም እንደማይቀበሉኝ አውቃለሁ፣ እኔን ሳይሆን ለዚያውም መጽሐፍ ቅዱስን።
ዘፍ  21፥17
    31፥11
     48፥16
ዘጸ  3፥2
    14፥19
    33፥1-3
ዘኁ  22፥22 - 22፥23 - 22፥24 - 22፥25 - 22፥26 - 22፥27 - 22፥31   -  22፥32    22፥34   22፥35  
አንድም ቦታ ሚካኤል የሚል ስም ተጠቅሶ አይገኝም። እግዚአብሔር ስሙን ያልጠቀሰው ለምን ይመስልዎታል? እኛስ ስሙን መጥቀስ ለምን ይገባናል? የኛ መጥቀስ እግዚአብሔር ያልጠቀሰውን ጉድለት ለመሙላት ነው ወይስ ስውር  የሆነውን ሚካኤል በትርጉማችን ገልጸን በማውጣት መልአኩን ለማክበር?
ለዚያውም ስሙ ባልተገለጸ መልአክ እጅ እግዚአብሔር ያደረገውን ድንቅና ተአምራት ለሚካኤል ለመስጠት «እስራኤል ዘሥጋን በመንገዳቸው ሁሉ የጠበቃቸው፥ መና ከሰማይ ያወረደላቸው፥ ተአምራትን ያደረገላቸው፥ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ርስታቸው የመራቸው፥ በደመና መጋረጃ የጋረዳቸው፥ በክንፎቹም የሸፈናቸው መጋቤ ብሉይ የተባለ ቅዱስ ሚካኤል ነው» ማለት በፍጹም ትልቅ ስህተትና ክህደት ነው።
 እርስዎ እግዚአብሔር ያለውን ለምን መተው ይወዳሉ?
 ዘፍ 28፣15 «እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና»
 ዘጸ 6፣6 «ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ»

ዘጸ 6፣7ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

ዘጸ 6፣8 «ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ»
ዘጸ 10፣3 «ሙሴም አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ አሉትም። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በፊቴ ለመዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ»
ዘጸ 13፣21 «በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ»
ዘጸ 14፥24
ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። 25 የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አገባቸው ግብፃውያንም። እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ አሉ»
ዘጸ 15፥3 «እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው»
ዘጸ 16፥15
የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው። ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም፦ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው»
ከብዙ በጥቂቱ እስራኤል ዘሥጋን የመገባቸው፣የጠበቃቸው፣ያሻገራቸው፣ የጋረዳቸው እግዚአብሔር እንጂ እርስዎ እንዳሉት ሚካኤል የሚባል መልአክ አይደለም።  
ዘሌ20፥24 ነገር ግን እናንተን፦ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ»
ዘዳ 26፣8 እግዚአብሔርም በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ድንጋጤ፥ በተአምራትም፥ በድንቅም ከግብፅ አወጣን
ዘዳ 26፣9 ወደዚህም ስፍራ አገባን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን።
ቀሲስ- እርስዎ ግን በድፍረት በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀው ላልተገለጠና ላልተጻፈ የመልአክ ስም ሰጥተው፣ ያሻገራቸው፤ መናን የመገባቸው፣ ወተትና ማር የምታፈሰውን ሀገር ያወረሳቸው ሚካኤል ነው ይላሉ። እግዚአብሔር እኔ ነኝ እያለ እርስዎ ግን የለም ሚካኤል ነው ማለትዎ ለምን ይሆን? ላልተገለጠ መልአክ ክብሩን ከእግዚአብሔር ላይ ወስደው ሲሰጡ ለእኔ እንደተደረገ ይቆጠራል የሚል ይመስልዎት ይሆን? ላልተገለጠና ላልተጻፈ የመልአክ ስም ክብሩን ሁሉ መስጠትዎ ሳያንስ ሌሎችም ይህንኑ ስህተትዎን እንዲቀበሉና ፊታቸውን ወዳልተነገረውና እግዚአብሔር ወዳልገለጸው መልአክ እንዲመልሱ ማስተማርዎ ያሳዝናል !! በዘለበ ምላስ የሚናገሩትና የሚጽፉትን ለራስዎ እንዲመች ተርጉመው የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ማጣመምዎ ለምንድነው?
ምናልባት እግዚአብሔር ይቅር ቢልዎ ንስሐ ይግቡበት!! ምክንያቱም እኔ ሰራሁ ያለውን ላልተጻፈ መልአክ ሰጥተው፣ አስቀንተውታልና!!
እርስዎ እግዚአብሔር ያደረገውን ተአምራት ሁሉ ለሌላ አውለው እንዳስቀኑት ሰዎች ሆነዋል።
ዘኁ 14፣22-23 በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥
 ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም» ይላልና ያስቡበት!!!!!!