Thursday, November 3, 2011

እርግማንና ረጋሚዎች!



ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በኦሪቱ በኋላም በወንጌል የበራላትንና ከእግዚአብሔርም የተሰጣት ከአፍሪካ እስከ በመካከለኛው ምስራቅ ገናና ታሪክ እስከ የመንም ድረስ የነበራትን የግዛት እንዲሁም የጸጋ፤የበረከት፤ መሬቷ ወርቅ፤ ወንዞቿ ወይን፤ ደኖቿ ኤደን፤ ሕዝቦቿ ታታሪ ሆነው የኖሩበትን ዘመን የቀየረውና የገለበጠው ምንኩስና የሚባለው የሰነፎችና «የአጸድቃለሁ፤ እኔም በስራዬ እጸድቃለሁ» የሚለው ማኅበር ከተንሰራፋ በኋላና ወንጌልን አሽቀንጥሮ ቤተመቅደሱን የሞላው ገድል የሚሉት የእግዚአብሔርን ክብር በመጋረድ ቅዱሳን ለተባሉት ክብርና መንቀጥቀጥን እንዲሰጥ የሚያስገድደው መጽሐፍ ቦታውን ከያዘና ተአምር የሚባል የዘርዓ ያዕቆብ የግዝት መጽሐፍ ብዙ ደም አፋስሶ፤ አፍንጫና ጆሮ አስቆርጦ፤ በሕይወት ሳሉ ከጉድጓድ አስቀብሮ የደም መሬት ኢትዮጵያ ላይ ከነገሰ በኋላ ነው። በኦርቶዶክስ ቤ/ክ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ማንበብ የተጀመረው የፕሮቴስታንት እምነት መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ ስለሚሰብክ እሱን ለመቋቋም ተብሎ እንጂ ከእቃ ግምጃ ቤት ወጥቶ አያውቅም። በትግራይ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ይዞ የታየ ጴንጤ ወይም ካቶሊክ ያሰኝ እንደነበር አይዘነጋም። ድርሳነ ሚካኤልን ወይም የሆነ ተአምርን ከተሸከመ እሱ የወንጌል ሰው ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ እንደሆነ ይቆጠራል።
ሌላው ቀርቶ« ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ «ኢየሱስ ጌታ ነው»ብሎ መናገር እንደጴንጤ ያስቆጥራል። ማር 12፤29...ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው» የሚለውን መመስከር ወንጀል ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለው 78 ሰው ቅርጥፍ አድርጎ በላ የሚባለውን የተረት ታሪክ መናገር እንደክርስቲያን የሚያስቆጥረው በምን ስሌት ነው?


እኔ ኦርቶዶክሳዊ እምነት ተከታይ ነኝ። እግዚአብሔር የሰጠኝን ክርስትና ሲኖዶስ አይወስድብኝ፤ ማቅ አይከለክለኝ። ይህንን ተአምር የሚባለውን የዘርዓ ያዕቆብ የተረት መጽሐፍ ገመና በማጋለጥና ከተቀመጠበት የወንጌል ስፍራ በማውረድ ወደመጣበት ለዚያውም ወደማያውቁት ግብጾች እመልሰዋለሁ፤ ከወንድሞች ጋር እንመልሰዋለን። እስኪ ይህንን ልብ በሉት!«ላቲ ይደሉ ክብር ወስብሐት ዘምስለ ወልዳ አምልኰ ወስግደት» መስተብቍዕ ዘማርያም። ትርጉሙ- ለእርሷ ክብርና ምስጋና ከልጇም ጋር አምልኰና ስግደት ይገባታል፤ ማለት ነው። ማርያም በድንግልና በንጽሕና ጌታን ወልዳለች፤ ቅድስትና ብጽዕት እያለ ትውልድ ሁሉ ይጠራላታል፤ ይህ የተጻፈ እውነት ነው። ያ ማለት ግን ማርያም እግዚአብሔር ሆና አምልኰና ስግደት ይደረግላታል ማለት አይደለም። እርሷም የእግዚአብሔር አምልኰና ስግደት ይገባኛል አትልም። የነገረችን እውነት ተጽፎ ተቀምጧል፤ « ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች»ሉቃ 1፤47 ነው ያለችው እንጂ እኔ ጌታና አምላክ ስለሆንኩ አምልኰና ስግደት እፈልጋለሁ አላለችም። ይህንን መቃወም ተሃድሶ ወይም ጴንጤ መሆን አይደለም። የተቀበረውን እውነት መግለጥ እንጂ!! ይህ ተአምር ከእስላሞች ጋር ሊያጋጨን የመሐመድ ሚስት ግመል ናት ይለናል። ብልቱም በወገቡ ላይ እንደገመድ የታሰረ ነው ሲል ሲዋሽ ይገኛል። (ተአምር 19) መሐመድ የታወቁ 9 ሚስቶችና ብዙ እቁባቶች እንዳሉት «ሳሂህ አልቡካሪ ቡክ5፤ ምእራፍ45 ቁጥር 282 በግልጽ ይናገራል። የሚስት ችግር እንኳን መሀመድ ተከታዮቹም ችግር የለባቸውም። ደግሞም ብልቱ በወገቡ ላይ ይጠመጠማል የሚለው «የጭራቅ መጣልህ» ተረት ያለዘርዓ ያእቆብ ተአምር በስተቀር የትም አይገኝም። ለመሀመድ ያለውን ጥላቻ ከማንጸባረቅ ባሻገር የመሀመድ የወንድ ብልት እንደማንኛውም ሰው የሆነና ሚስቶችም አግብቶ ልጆች የወለደ ሰው መሆኑ ይታወቃል። ይህንን የተረት ተአምር እሁድ አሁድ ለመስማት ያልመጣ በማይፈታ ጽኑ እስራት ፈጽመን አወገዝን ይባልለታል። ብልቱ ወገቡ ላይ የተጠመጠመውን የመሀመድ ተረት ያዳመጠ ስጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይቆጠርለታል ተብሎ ሰው ከቁርባን እንዲዘናጋ ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ሲታወጅ ይገኛል። ወገቡ ላይ እንደገመድ ብልቱ መጠምጠሙም አውቃለሁ ተብሎ የሀሰት ምስክርነት በመስጠት ሰዎች ይሳለሙታል። ምንኛ አሳዛኝ ነው?

ድንግልና ንጽሕት፤ ቅድስትና ብጽእት እሙ ለእግዚእነ የሆነችው ማርያም ፍቅር ትናገራለች እንጂ አትራገምም!!
የ(እስመ ክብርት አርኬ) ግን የዚህን ተቃራኒ ይናገራል።

ቅድስት ማርያም በፍጹም የሰውን ልጅ አትራገምም፤ አንገትም አትቆርጥም። እኛ ሥጋውያን ነን የምንጠላቸውን አንገታቸውን ለመቁረጥ፤ ዘራቸውን ለማጥፋት ስንጣጣር የምንውለው። ፍላጎታችንን በጸሎት አስመስለን ወደማርያም የወሰድነው የኛ የአመጽ ተባባሪ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ማርያም እንደወንጌሉ ቃል «ጠላትህን ውደድ» ያለውን የልጇን ቃል የምትጠብቅ እናት ናት እንጂ የረጋሚዎች ወዳጅ አይደለችም።
ለሰይጣን እንኳን የስድብ ቃል ተናገሩ አልተባለም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ይገስጽህ እንጂ!!

የይሁዳ መልእክት
1፥9
«የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር። ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም» ታዲያ እነዚህ ረጋሚዎች ለምን ማርያምን ለመወንጀል ይፈልጋሉ?
ሌላው ደግሞ በዓላቶቼን አክብሩ፤ ስራም አትስሩ ብላለች የሚሉት ፈጠራ አላቸው። ማርያም ግን እንደዚህ አትልም፤ ይልቁንም 6ቱን ቀን ስሩ በ7ኛው እረፉ ያለውን የእግዚአብሔር ትእዛዝ ከልጅነቷ ጀምሮ የተማረች ስለሆነ የሰዎችን የፈጠራ ሃሳብ አትቀበልም።
እንደዘርዓ ያዕቆብ ፍልስፍና በ1 ልደቷ፤ በ3 በዓቷ፤ በ7 ጽንሰቷ፤ በ8 ቁስቋሟ፤ በ10 ፤በ12(ያልተገለጸ)በ16 ኪዳኗ፤ በ21 ቅዳሴ ቤቷና ጎልጎቷ፤ በ22 ደቅስዮስን ያናገረችበት፤በ26 ስደቷ፤ በ29 መውለዷ እያለ ይቀጥላል።እንግዲህ 33ቱን ዝርዝር ትተን ይህን ብንቆጥር በወር ውስጥ 12 እንደእሁድ ሰንበት ሊከበሩ የሚገባቸው ግዝቶች አሉ ማለት ነው። አራት እሁድ ሲጨመርበት በድምሩ 16 ቀናትን በወር ውስጥ ምንም ምን ስራ አትስሩባቸው ተብሏል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ህዝቡን በግዝትና በማስፈራሪያ አስረውት የፈረንጅ እጅ ጠባቂ አድርገውታል። የሚገርመው ደግሞ ፈረንጅ ከእሁድ በስተቀር አንድም የግዝት በዓልን ሳይጠብቅና በመሻር ያፈራውን የእርዳታ እህል ይሄ በዓል ተሽሮ የተመረተ ነውና አንቀበልም ብሎ የሚያውቅ አለመኖሩ ነው። ለምን የማርያምን በዓል የሻሩ የኃጢአተኞችን እህል እንቀበላለን? በፈረንጅ ሀገር ያለው ኢትዮጵያዊስ ይህንን የግዝት በዓል አከብራለሁ ቢል ማን አንድ ቀን ያኖረዋል? ስራ መስራቱስ ግዝቱን እንደጣሰ ያስቆጥረዋል ማለት ነው? መቼም ግዝቱ በፈረንጅ ሀገር ኗሪ አበሻ ላይ አይሰራም የሚል ነገረ የለውምና «ዘኢያከብር በዓላ ከመእሁድ ሰንበት አሰርነ ወአውገዝነ በማዕሰር ዘኢይትፈታህ» እየተባለ ሲረገም ይኖራል እንጂ!! ደግነቱ ማርያም እንደዚህ ዓይነቱ ግዝት ስለማይወጣት ሰርተው መኖራቸው ምንም ኃጢአት የለውም። ማርያምም ስራ ሳትሰሩ በዓሌን እያከበራችሁ ቁጭ በሉ አላለችም፤ አትልምም። ይልቁንም «ጥረህ ፤ግረህ በላብህ ወዝ ብላ» ያለውን የምታስተምር ወላዲተቃል መሆኗን አንጠራጠርም።
እነግዝት ዘበከንቱ ግን ይኼው ከ15ኛው ክ/ዘመን አንስቶ ሲራገሙ ይገኛሉ።
እርግማንና ረጋሚዎች እስካልጠፉ በሀገራችን ሰላምና በረከት አይወርድም።