Friday, November 25, 2011

እሬት የተቀባ ጡት ማን ይጠባል?



 ሁላችንም ህጻን ልጅ ሆነን አድገን አሁን ካለንበት መድረሳችን እርግጥ ነው። ህጻናትን በተመለከተም ህጻናት ወንድሞችና እህቶችም ይኖሩን ይሆናል። ምናልባትም ህጻናት ልጆች ይኖረንም ይሆናል። ባይኖረን እንኳን ስለህጻናት ያለን እውቀት ትንሽ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ስለህጻናት ማንሳት የወደድኩት «ምርጥ ምርጡን ለህጻናት» የሚል አስተምህሮ ለመስጠት አይደለም። አእምሮአችሁን ለአፍታ ስለህጻናት እንዲያስብና ላነሳ ስለፈለኩት ጉዳይ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ ነው።
ጥያቄ ላቅርብላችሁ? ህጻናት ጡት የሚተዉት እንዴት ነው? ጡት የሚጠባ ህጻን ጡት ሲያጣ ወይም ጡት ሲከለክሉት እንዴት ያደርገዋል? መቼም እንደማይስቅና እንደማይፍለቀለቅ አናጣውም። ይነጫነጫል፣ያለቅሳል፤ በአቅሚቲ እናቱን ይቧጥጣል፣ጡት አምጪ ብሎ ይማታል ብንል እውነት ነው። ሲያገኝና ሲጠግብ ደግሞ ጤነኛ እስከሆነ ድረስ ይስቃል፣ይጫወታል። እንዲህ እንዲህ እያለ ሁለትና ሶስት ዓመት ሲሞላው ደግሞ ደግሞ ጡቱን ያስጥሉታል።አራትና አምስት ድረስ የሚጠባ ልጅ እንዳለ ሳይዘነጋ መሆኑን ልብ ይሏል? ጡት የምታስጥል የገጠር እናት ያንን የለመደውን ነገር ለማስጣል ከባድ ይሆንባታል። እንዲጠላው ለማድረግ እሬት ይቀቡታል። ይቆነጥጡታል። ሌላም ነገር እያደረጉ ይከለክሉታል። ይሁን እንጂ የህጻኑ ለቅሶ ሲበረታ ልምድ አደገኛ ነውና እንደገና ያጠቡታል። እንደዚያ እንደዚያ እያደረጉ ምግብ እያቀረቡ፣ጡት እየነፈጉ ከህጻንነት የጡት መጥባት ዓለም ያወጡታል።


ጡትን ጥሎ እህልን የተካ ህጻን መቼም ጡትን ለተረኛው ይለቅ ይሆን እንጂ እርሱ ደግሞ አያገኘውም። ትልቅ ከሆነ በኋላ እንኳን ያንን የጠባሁትና የተውኩት የእናቴ  ጡት ምስክር ይሁንብኝ ሲል መሃላውን «የእናቴን ጡት» ብሎ ይምልበት የለ!!
ይህን ሁሉ ከላይ ያመጣሁት ያለምክንያት አይደለም። ነገሩ እንዲህ ነው።
ትልቅ ሰው ማለትም ጎልማሳ ሰው ጡት ወይም የህጻናት ወተት ያስፈልገኛል! እኔ ህጻን ነኝ ቢል ምን ትሉታላችሁ?
ይህ ማደግ የማይፈልግና ከህጻንነት የማይወጣ፣ ባለበት የሚረግጥ፤ የማይሻሻል ብንለው ይስማማዋል። የእግዚአብሔር ቃልን በለውጥና በእድገት የማያሳይን ሰው ጳውሎስ እንዲህ ይለዋል።
 «ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና» ዕብ5፣12-13
ዛሬ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችን ያለነው በእድሜ ትልልቆች፤ ብዙ ስብከት የሰማን፣ ያነበብን፣ ቆመን ያስቀደስን፣ ሀገር ላገር ደብር ለደብር የዞርን፣ በጻድቃኔ ሱባዔ የያዝን፣ ግማደመስቀሉ ካለበት የዞርን ወዘተ ሃይማኖት እንጂ የጽድቅን ቃል ገና ያላወቅን ህጻናት ነን። ጳውሎስ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ እንደገና ወደኋላ ተመለሳችሁ የህጻናት ወተት ትምህርት መጋት አለባችሁ። እናንተ ገና የጽድቅን ቃል ለማወቅ ብስለት ይቀራችኋል ይለናል።
ለዚህም ማሳያ እንደህጻን ያንን የልምድ ጡት በመተው ወደ ወጣትነት ብስለት ከመሄድ ይልቅ እሬት የተቀባውን ጡት ላለመተው እንደህጻን እናስቸግራለን። አጥንት መጋጥና የአዋቂዎችን ምግብ መመገብ በሚገባን ወቅት የጽድቅን ቃል እንደማያውቅ ህጻን እናለቅሳለን። ጳውሎስ የተናገረው ለዛፍ ወይም ለተራራ ሳይሆን ትልልቆች ሆነው ዛሬም በጥንቱ ልምድና ባህል በመኖር ጽድቅን ለማወቅ ላልቻሉ ሰዎች ሁሉ ነውና ከሰዎቹ አንዱ ነን።
ምሳሌ እናንሳ- ዙሐል ወር በገባ በ12 ቀን ይከበር ስለነበረና ህዝቡ ይህንን አደገኛ የቀን አከባበር ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሚካኤልን ታቦት አስገብቶ ለዙሐል ሲመጡ ሚካኤልን እንዲያከብሩበት ተደረገ ሲባል ለአዋቂና የጽድቅ ቃል የገባው የበሰለ ሰው፣አዎ ይላል እንጂ 12ኛው ቀን የዙሐል ነበር ግን አሁን ይህንን መናገር ልምዳችንን መሸርሸር ነውና ዝም በሉ! ቢል ምን ይባላል? እሬት የተቀባውን ጡት እየጠባ መኖር እንደሚፈልግ ህጻን መሆን ነው።
ከሁሉም የሚያሳዝነው በእድሜ ትልቆች፤ በእውቀት ዛሬም እንደልጅነታችን ያልበሰልን መሆናችን የሚያሳዝነው ለህጻን አእምሮአችን የተነገረውን ሁሉ ይዘን ሌላ እውነት ቢነገረን ጆሮአችንን በእምቢታ መጠቅጠቃችን ነው።
ወላዲተ ቃል ማርያም ታላላቅ ብርሃናትን ብቻዋን ፈጥራለች የሚል ድርሰትን ስህተት ነው ማለት ሲገባ ይህንን ከጽድቅ ቃል ጋር የሚጋጭ ነገር እንዲቆይ በመሟገት እሬት የተቀባውን ጡት እየጠባሁ በእውቀት ሳላድግ ልኑር ማለትን ምን ይሉታል?
መልአኩ ስለስግደት ለዮሐንስ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ያለውን ትሁት ለመሆን ፈልጎ ነው እንጂ ስግደትን ጠልቶ አይደለም በማለትና እንዲያ ማለቱን ለማረም መሻት ምን ይሉታል? ይህ ለዚያ በቃሉ ማደግ ባልቻለ የእድገት እምቢተኛ ህጻን አእምሮ ላይ ጠላት በስጋ ለበስ ሰዎች የዘራው የጥፋት እውቀት ውጤት ነው።
ማርያም የሚባል ጽላተሙሴ አልነበረም ቢባሉ አዎ አልነበረም፤ እግዚአብሔር የጻፈበት ጽላት 10ቱን ትእዛዛት ነው ማለት ሲገባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ከተናገረው ይልቅ ጠላት በውስጣቸው ያስቀመጠውን ውሸት የሚያምኑ እነዚህ ምን ይባላሉ?
እሬት የተቀባውን ጡት እየጠባ ለመኖር እንደሚፈልግ የማያድግ ልጅ መሆን ነው።
አሁን ያለው የጽላት አሰራር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፣ ቢባሉ ሙሴ አስመስለህ ቅረጽ ተብሏል ብለው ጠላት ያቀበላቸውን እሬት የተቀባውን ጡት ሊያጠቡን ይሻሉ። ሙሴ ቅረጽ ሲባል ወርዱ፤ቁመቱ፣ስፋቱ፣ብዛቱ ምን ነበር ሲባሉ የኦሪቱን ህግ ትተው የራሳቸውን ህግ ይነግሩናል። ይህንን ህግ እንዲያሻሽሉ የተነገራቸው ሳይኖርና በአንድ በኩል ህግንና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ብሏል እያሉ እያስተማሩ፣ እሬት የተቀባውን መልስ በማምጣት ስርዓት ሊሻሻል ይችላል ብለው የጠላትን ምክር ያቀርባሉ። እነዚህን የጽድቅ ቃል እውቀት የማያውቁ ሁልጊዜ ብስለት የሌለባቸውን ጳውሎስ ምን ይላቸዋል?«ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና» ዕብ5፣12-13
ብዙው ትምህርታቸው ልምድ፤ ባህልና ትውፊት እንጂ የወንጌል መሰረትነት የለውም ተብሎ ማስረጃ ሲቀርብበት ለመደበቅና ለመሸፋፈን ሲታገሉ ስድብ፤ ጢቅ ማለት፣ መነጫነጭና ማልቀስ ብሎም ተሃድሶ በማለት ስም ማውጣት ይቀናቸዋል።
«መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው»ዮሐ1፣18
«አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም»መዝ 86፣8
ይህንን ቃል ተቃውሞ ሥላሴን ለርስእክሙ፤ለዝክረ፤ስምክሙ፣....ለአፍንጫችሁ፣ለጥርሳችሁ፤ለጆሮአችሁ፤ ለሽንጣችሁ፤ለወገባችሁ፣ለጣታችሁ፣ለክርናችሁ ለምናችሁ፣ ለምናችሁ ወዘተ በማለት ሥላሴን ያዩ ይመስል ወይም ሰው እንደሚያስበው የአካል ክፍልና መጠን አበጅተው ለሥላሴ የአካል ብልት ማውጣት ምን ይሉታል? ከየት የተገኘ ትምህርት ነው? ማን ጻፈው? ማንስ አጸደቀው? በምን ተመዘነ? ምንስ ለማምጣት?
«መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው»ዮሐ1፣18  ይህ እንግዲህ የጽድቅ ቃልን ለሚያውቁ አዋቂዎች የተነገረ ነው። እሬት የተቀባ የጡት ወተትን አንተውም የሚሉ የቃል ህጻናት ዛሬም በእምቢታቸው እንደጸኑ የሥላሴን ጆሮና አፍንጫ ሳያዩ አይተናል በማለት ጽፈው ለአፍንጫችሁ፣ ለጥርሳችሁ እያሉ ይደግማሉ፣ ያስደግማሉ። ስህተቱ ሲነገራቸው አይሰሙም። ለመስማትም በፍጹም አይሹም። ሲነገራቸው ከኖሩበት ውጪ ግራና ቀኝ ማየት አይፈልጉም።
አፍንጫና ጥርስ፣ጆሮና ዳሌ በመጥራት ሳይሆን እግዚአብሔር የሚመለከው በእምነት ነው ሲባሉ አይቀበሉም። ሮሜ 10፣17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። እንደሐዋርያትም እምነት ጨምርልን ከማለት ይልቅ ነጋ ጠባ ለጥርሳችሁ፤ ለጣታችሁ፣ ለሽንጣችሁ ማለት ምንድነው?
«ሐዋርያትም ጌታን። እምነት ጨምርልን አሉት»ሉቃ17፣5 ያኔም ይጨመርላችሁ።
እባካችሁ የትኛውንም ከመጥላትና ከመሸሽ በፊት እንደእግዚአብሔር ቃል መርምሩ! ግራና ቀኝ እዩ!! አዋቂዎች ሆናችሁ አጥንት ለመጋጥ በሚያበቃችሁ እድሜ ላይ እሬት የተቀባውን ጡት በመጥባት አትኑሩ!!!!!