Wednesday, November 30, 2011

ጉልበተኛው ረባሽ!!




ቦረና ሀገረ ስብከት በክብረ መንግሥት ከተማ በጽርሐ አርያም ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን እስከ ህዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም ላለው ጊዜ የተዘረጋው የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል ጉባዔ መቋረጡን በዚያው ያሉ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ እንደሚደረገው የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ቡችሎች በለኮሱት ሁከት ጉባዔው መቋረጡ ታውቋል፡፡ በተለይም የግጭቱ አስተባባሪ በመሆን ቀዳሚውን ድርሻ የወሰደው ያሬድ ውብሸት የተባለ የማኅበሩ አባል ሲሆን፣ ይኸው ግለሰብ ለማኅበሩ መረጃ በማቀበልና በመሰለል ወንድሞችን ለአደጋ የሚጥል መሆኑ ጭምር ተገልጿል፡፡ በዚሁ ጉባዔ ላይ፣ ለጊዜው ስሙና ማንነቱ ካልተገለጸ ሌላ ግለሰብ ጋር በመሆን ጠቡን እንዳስነሱት የታወቀ ሲሆን፣ ይኸው ግብረ አበር ሰዎችን ከደበደበ በኋላ ጌታዋን እንደተማመነች በግ ከተማዋ ውስጥ በነፃነት ሲንሸራሸር፣ የወንጌል መምህር የሆኑትን ቀሲስ ተስፋዬ መቆያን ለእሥራት እንዳበቋቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

የክብረ መንግሥት ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ ቀሲስ ተስፋዬ መቆያ ከፊደል ቆጠራ እስከ ዲቁና ከዚያም እስከ ቅስና ያገለገሉባት፣ ጥርስ ነቅለው ያደጉባት እናት ቤተክርስቲያናቸው ስትሆን፣ የከተማዋ ምዕመናን የወንጌሉ የምሥራች ቃል እንዲሰበክላቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጎለብቱ፣ የዘማሪያንንና የሰባክያንን ወጪዎች በመሸፈን ጭምር በተደጋጋሚ የወንጌል ጉባዔ ያዘጋጁ ቅን የቤተክርስቲያን አገልጋይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡


"በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል" እንዲሉ፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" ባለበት የወንጌል ቃል መስማት አልተቻለም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወገሩትና የሰቀሉት የአይሁዳውያን ደቀመዝሙር የሆነው "ማኅበረ ቅዱሳን" ዛሬም የአይሁዳውያንን ፈለግ በመከተል የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል እንዳይሰበክ በማገድ ላይ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያን በአንድ በኩል የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትባት የሀዲስ ኪዳን መልክ ያላት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌል የማይሰበክባት ኦሪታዊውና ትውፊታዊው ሥርዓት ብቻ ይዛ እየተጓዘች የምትሄድ ሃይማኖታዊ ተቋም በማድረግ ልጆቿ ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁ ሠይጣናዊ ሥራውን በመሥራት ላይ ነው፡፡

የወረዳው ቤተክህነት ሥራአስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ልሣነ ወርቅ ሁንዴ የክህነት ሥልጣን የሌላቸው በመሆኑ የወረዳው ምዕመናን እንዲነሱላቸው ባመለከቱት መሠረት እንዲነሱ የተወሰነ ቢሆንም፣ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በሲያምር ተክለ ማርያም ተከላካይነት የምዕመናኑ ጥያቄ መደፍጠጡን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ ሊቀ ስዩማን ልሣነወርቅ ሁንዴ ቀደም ሲልም በከተማዋ ለሚገኙ አራቱ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ገቢ ማስገኛ እንዲሆን ከክርስቲያናዊ የልማት ተራድዖ ድርጅት የተሰጠውን የእህል ወፍጮ፣ የግላቸው በማድረግ ወጪ ገቢው የማይታወቅ እና ለ14 ዓመታት ኦዲት አለመደረጉን ታዛቢዎች ገልጸዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሲያምር ተክለ ማርያም በበኩላቸው ባለባቸው የሥነምግባር ችግር ምክንያት ምዕመናን እንዲነሱላቸው ያመለከቱ ሲሆን ከጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት በተላከወ አጣሪ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ቤት እንዲዛወሩ ተወስኖባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቡ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት እና መመሪያ በመጣስ፣ በአይዞህ ባዮቻቸው በ"ማኅበረ ቅዱሳን" እየተረዱ ከቦታዬ አልነሳም በማለት ከስድስት ወራት በላይ በሕገወጥነት ተቀምጠዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ የተቸገረው ጠቅላይ ቤተክህነት በሥራ አስኪያጁ ላይ ክስ በመመሥረት ጉዳዩን ሲመረምር የዋለው የጉጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈባቸው ሲሆን፣ ይህንኑ መሠረት አድርጎ ጽ/ቤቱንና መኪናውን እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ተፈጻሚ አለመሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሀገረ ስብከቱን ደርበው እንዲመሩ ሥልጣን ተሰጥቷቸው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" በመወገን ውሳኔው ተፈጻሚ እንዳይሆን ተከላክለው የነበረ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጥቅምት 2004ቱ ሲኖዶስ ጉባዔ በኋላ ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት የተዛወሩና የቦረና ሀገረ ስብከትም ሊቀጳጳስ የተመደበለት በመሆኑ የምዕመናኑን ጥያቄና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማስቀልበስ ሳይቻላቸው ቀርቷል ተብሏል፡፡ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በዚህ ብቻ ሳይገቱ ጌታቸው ስዩም የተባለውንና ምንም ዓይነት የክህነት ሥልጣን የሌለውን ግለሰብ በአንድ ወቅት ሀገረ ስብከሩቱን በውክልና እንዲመራ አድርገውት እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል፡፡


መንግሥት ይህ የቤተክርስቲያን ውስብስብ ችግር በሠላም እንዲፈታ ባለው ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት መሠረት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማድረግ ከኦሮሚያ ክልል፣ ከጉጂ ዞን አስተዳደር፣ ፍትሕና ፖሊስ የተወከሉ አባላት በተገኙበት ርክክቡ ህዳር 14 ቀን 2004 እንዲካሄድ የተወሰነ ቢሆንም ወደ 15 የሚሆኑ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" አባላት በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ውስጥ በመሰባሰብ ርክክቡን ለማደናቀፍና ያልተፈቀደ ሠላማዊ ሰልፍ ለማደራጀት፣ ሤራ በማውጠንጠን ላይ የነበሩ መሆኑ ስለተደረሰበት ለዚህ ጉዳይ ዕልባት ለመስጠት ሲባል ርክክቡ መስተጓጎሉን ለመረዳት ተችሏል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የሠላም ጉባዔ በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የተላለፈውን ስምምነት በመጣስ በሌሎች ሀገረ ስብከቶችና ከተሞች እንደሚያደርገው ሁሉ፣ በክብረ መንግሥት ከተማ በሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያናትና ቤተክህነት ጽ/ቤት ውስጥ ልዩ ልዩ የሥራ መደቦችን በመቆጣጠር አላፈናፍን ማለቱንና ከላይ እስከታች ያሉ የቤተክርስቲያንን መዋቅር ሰቅዞ መያዙን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በዚህም መሠረት፣ የክህነት ሥልጣን የሌላቸው የወረዳው ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ልሣነ ወርቅ ሁንዴ የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪነት ቦታ ጭምር ደርበው የሚሠሩ በመሆኑ፣ በአስተዳዳሪነት ለሚፈጽሟቸው ሕገወጥ ተግባራት በወረዳ ደረጃም ራሳቸውን ስለሚመለከት ችግሩን ለመፍታት አያስችልም ተብሏል፡፡ እንዲሁም፣ መልአከ ብሥራት መኮንን ጉተማ የተባሉ ግለሰብ የወረዳው ቤተክህነት ፀሐፊ፣ የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መርጃ ክፍል ኃላፊ እና የወረዳው ቤተክህነት ስብከተ ወንጌል ኃላፊ በመሆን አንድ ሰው ብቻውን አራት፣ አምስት ቦታ ደርቦ እንዲይዝ መደረጉን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ "ማኅበረ ቅዱሳን" በርካታ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎችን ደራርቦ በመያዝ ተከሳሽም፣ ዳኛም በመሆን አንድም ሦስትም እየሆነ የማፊያ ዓይነት አደረጃጀት መከተሉን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" ለዓላማው መሳካት ማንኛውንም ሕገወጥ ተግባር ከመፈጸም አይመለስም ያሉት እነዚህ ታዛቢዎች፣ ንጹሃን አባቶችን ሲከስና ሲያዋርድ የራሱን ንቅዘት ግን እንደ ፅድቅ ሥራ ይቆጥረዋል፤ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ እና በወረዳው ሥራ አስኪያጆች ጥምረት የክብረ መንግሥት ከተማና የአዶላ ወረዳ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ከሕገ ቤተክርስቲያን እና ከሥርዓት ውጪ እየተቸገሩ ባሉበት ሁኔታ፣ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት መቀመጫ በኔጌሌ ከተማም "ማኅበረ ቅዱሳን" የኪዳነ ምሕረት አጥቢያን መዋቅር ተቆጣጥሮ አላስወጣ፣ አላስገባ ያለ ሲሆን በቅዱስ ገብርኤልና በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ያሉ ምዕመናንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መቸገራቸውንና የርስ በርስ መከፋፈል አደጋ እንዳዣንበበባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡dejeselaam.blogspot.com