Monday, October 31, 2011

እውነቱን ብንናገር ምን ይለናል?


በዚህች ምድር ላይ ከተስፋፋውና በሰዎች ልቡና ላይ ከተማውን ከመሠረተው አስፈሪ ኃጢአት መካከል እውነትን ለመናገር የሚችል ሰው እየጠፋ መምጣቱ ቀዳሚውን ይዟል። ዓይኑ ያየውን፤ ጆሮው የሰማውን ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ልቡ ያመነጨውን እውነት አድርጎ ማውራትና ማስወራት፤ ይህንንም እንደእውነተኛ ምስክርነት መቁጠር ባህል እየሆነ መጥቷል። ሰዎች ከሥልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥም ሆነ ከሥልጣን ኮርቻ አስፈንጥሮ ለመጣል እውነቱን በሃሰት ቀይሮ እንደዘመናዊ የውጊያ ስልት መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበትም መታየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። የሀሰት ምስክር ቀርቦበት ሞት የተፈረደበትን፤ ከርቸሌ የወረደውን፤ የተደበደበውን፤ የተንገላታውን፤ መልካም ስሙ የጎደፈውን፤ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለለውን፤ ከማእረግ፤ ከሽልማት የታገደውን፤ ረዳት አጥቶ አልቅሶ የቀረውን ሰው ቤቱ ይቁጠረው! በማለት ብቻ ምንም እንዳልተፈጠረ የራሳችንም ሆነ የአካባቢያችንን ሁኔታ ላለመልከት የኅሊናችንን በር መዝጋት እንዴት ይቻለናል? ይልቅስ ለመናገር እንድፈር።
በዚህች ምድር ላይ የሀሰት መንገስ ጉዳይ በሥጋውያን ሰዎች ዘንድ አሳዛኝ መሆኑ ባይካድም አስተሳሰባቸው በሥጋዊ ደማዊ ኅሊና ላይ የሚመሠረት በመሆኑ ሀሰትን እንደመሳሪያ መጠቀማቸው ላይደንቅ ይችላል። አሳፋሪውና አሸማቃቂው ነገር እግዚአብሔርን እናውቃለን፤ የጽድቅ ልጆች ነን በማለት ዘወትር ስለቃሉ በመናገር ላይ ያለነው የእምነት ሰዎች ዘንድ እውነትን በሀሰት ተክተን እንደዘወትር ጸሎት በልባችን ላይ ጽፈን መያዛችንና ጠቃሚ መስሎ በታየን ጊዜና ቦታ ለዓላማችን ማስፈጸሚያ አገልግሎት ላይ ማዋላችን ነው። የሚዋሹ የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ጊዜ እውነትን እውነት በምትመስልና ወደእውነት በተጠጋጋች ውበት የሚፈጽሟት ስለሆነ የዋሹ መስሎ አይሰማቸውም ወይም ውሸት መስሎ በተሰማቸው ጊዜ የኅሊናቸውን ቆሻሻ ለማጠብ ትንሽ ናት በምትል ምላሽ ውስጣቸውን አረጋግተው ከመንፈሳዊ ሰውነታቸው ምንም እንዳልጎደለ ራሳቸውን በራሳቸው አሳምነው ያንኑ መደበኛ ውሸታቸውን በተለመደው ጥበብ ይቀጥላሉ።
አንዳንዶቹም መዋሸታቸውን ቢያውቁም ምንም አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረና ነባራዊ ክስተት አድርገው በመቁጠር ባገኙት ቦታ ሁሉ የአዞ እንባ እያነቡ፤ ለሃይማኖታቸው የሚውል እስከሆነ ድረስ ይህንኑ በዘመናዊ ውሸት አንዳንዴም ባስ ሲል ዘመነኞቹ «ቀደዳ »የሚሉትን ዓይነት ውሸት የዕለት ሕይወታቸው አድርገው ይዘውት ይታያሉ። ለምሳሌ«ኬንያ ውስጥ አንድ ግለሰብ ባንድ ጊዜ አንድ በርሜል ውሃ ጭልጥ አደረገ የሚልና ጃፓን ከምድር እስከሰማይ የሚደርስ እስክሪብቶ ገበያ ላይ አዋለች» የሚል የውሸትና የቀደዳ ንጽጽሮች ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ የሃይማኖት ሰዎች የሚባሉት ይህንኑ የንጽጽር ተግባር ዘወትር ሲፈጽሙት ይታያሉ። ግን ሰዎች እውነትን እንዳይናገሩና ውሸትን ሥራቸው እንዲያደርጉ ያስገደደ ማነው?
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ