Wednesday, October 12, 2011

ለስዕልና ለምስል ስግደትና በእነርሱ ፊት መጸለይ ይገባል?





ጥቅስ፤
   ኦሪት ዘሌዋውያን 26፥1 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። ኦሪት ዘዳግም 4 15 እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ 16 እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥ 17 በምድር ላይ ያለውን የእንስሳን ሁሉ ምሳሌ፥ በሰማይም በታች የሚበርረውን የወፍን ሁሉ ምሳሌ፥ 18 በምድርም ላይ የሚሽከረከረውን ሁሉ ምሳሌ፥ ከምድርም በታች በውኃ ውስጥ የሚኖረውን የዓሣን ሁሉ ምሳሌ እንዳታደርጉ፥ 19 ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባየህ ጊዜ፥ ሰግደህላቸው አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ። 

 ጥቅስ፤
   ኦሪት ዘጸአት 20፥4 በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጽ ካወጣ በኋላ አንዱ የሰጣቸው ትልቁ ትእዛዝ ቢኖር ምንም አይነት ምስል ወይም የተቀረጸ ነገር በፍጹም እንዳያደርጉ ነው። የሰውም ይሁን የእንስሳ ወይም የፀሐይና ጨረቃ ወዘተ ማናቸውንም ምስል ወይም ምሳሌ ማድረግ ክልክል ነው። ስለዚህም አይሁዶች እስከ ዛሬም ድረስ በምኩራባቸው የሰውም ይሁን የሌላ ነገር ስእልና ሃውልት ወዘተ አያደርጉም። ምክንያቱም በቃሉ እጅግ የተከለከለ እና ጣኦትን እንደማምለክ የሚቆጠር ስለሆነ ነው።
በመሰረቱ እስራኤላዊ ያልሆኑ አህዛብ በሙሉ ለጣኦቶቻቸው ምሳሌ የሚሆኑ የተለያዩ ስእሎችና ሃውልቶች ይሰሩ ነበር።

    ለእነዚህም ምስሎች ከፍተኛ ቦታ ይሰጧቸው ነበር። በእጃቸው ለሰሯቸው ለእነዚህ ምስሎች ይሰግዱላቸውና ይሳለሟቸው ነበር። ጣኦትን ማምለክ የሚባለውም ዋናው ነገር ራሱ እንደዚህ በሰው እጅ ለተሰሩ ምስሎችና ቅርጾች ትልቅ ክብር መስጠት፣ እነርሱን ማምለክና ለእነርሱ መስገድ እንዲሁም መሳለም ነው። ይሄ የምስል ነገር ታዲያ ከላይ በዘዳግም 4 ላይ እንደተጻፈው የእግዚአብሔርን መልክም የሚያጠቃልል ነው። ማለትም የሰውና የእንስሳት ወይም የሌሎች ነገሮች መልክና ምሳሌ ብቻ ሳይሆን የተከለከለው፤ የእግዚአብሔርን መልክም ጭምር ምስል ማድረግ የተከለከለ ነው።
    
     ለዚህ ነው በዘዳግም 4፡1 ላይ እግዚአብሔር ሲናገር "እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ" የሚለው። የሰውም ይሁን የእግዚአብሔር ወይም የሌላ መልክና ምሳሌ ምስል ማድረግ ስለተከለከለ በዘመናችን በአንዳንድ የክርስቲያን ሃይማኖቶች ዘንድ እንደምናየው የሞቱ ቅዱሳንን ሰእልና ምስልም ቢሆን አይሁዶች አያደርጉም። የሙሴም ይሁን የኤልያስ ወይም የሌላ ታልቅ ነብይ ምስል አያደርጉም ነበር። የመጀመሪያዎቹም የክርስቶስ ተከታዮች እንደዚሁ ምንም አይነት ምስልና ሃውልት አያደርጉም ነበር። የሰውም ይሁን የእግዚአብሔር ምስል ማድረግ የተከለከለ ስለሆነ፤ የመጀመሪያዎቹ ሃዋርያትና ደቀመዛሙርት አንዳችም ምስል አያደርጉም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠነቅቀውን በመተላለፍ ስእልና ምስል ማድረግ የጀመሩት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ150 ዓመታት በኋላ ነው። ያኔም ቢሆን እነዚህን ስእሎች ፊት ለፊት አድርጎ ለመጸለይ ወይም ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እርዳታ እንዲሆኑ ተብሎ የታሰበ አልነበረም።

     እንደ አሁኑ ዘመን ለጸሎትና ለስግደት ወይም ለመሳለም የሚውሉ ስእሎችን ክርስቲያኖች መጠቀም የጀመሩት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ማለትም ይህ በኢየሱስ ወይም በማርያም ወይም በስላሴ ወይም በሌሎች ቅዱሳን መልክ ምስል ማድረግና ለጸሎትና ለመሳለም ወዘተ ጥቅም ላይ ማዋል ጨርሶ የመጀመሪያዎቹ ደቀመዛሙርትና ክርስቲያኖች የማያውቁት በኋላ በተለይ ክርስትና የሮማ መንግስት ኦፊሲያላዊ ሃይማኖት ከሆነ በኋላና ብዙ ጣኦት አምላኪ አህዛብ በመንግስት ተጽእኖ ብቻ ክርስቲያን መሆን ከጀመሩ በኋላ ነው። እነዚህ ዘመናቸውን ሁሉ ጣኦትን በማምለክ የኖሩና አምልኮ ያለ ምስል የሚከብዳቸው አህዛብ በስፋት ወደ ክርስትና ሲገቡ ነው እንግዲህ የራሳቸውን የጣኦት አምልኮ ባህል ወደ ክርስትና ይዘው የመጡት እንጂ የጥንቶቹ ሃዋርያትና ደቀመዛሙርት እንዲህ ያለውን የአህዛብ ባህል አይለማመዱም ነበር። ለማጠቃለል ያህል እንግዲህ፤ አዎ ማናቸውንም ምስል ማድረግና ያንን ምስል ለጸሎትም ይሁን ለመሳለም መጠቀም በመጽሐፍ ቅዱስ እጅግ የተከለከለና ጣኦትን እንደ ማምለክ የሚታይ ነው። ጣኦትን ማምለክ ማለት ራሱ ቀጥተኛ ትርጉሙ በእጅ ለተሰሩ ነገሮች መስገድ ወይም እነርሱን ማምለክ ማለት ነው።    
ጥቅስ
   ትንቢተ ኢሳይያስ 46 5 በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? 6 ወርቁን ከኮረጆ የሚያፈስሱ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፥ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል። 7 በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፥ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም። 8 ይህን አስቡና አልቅሱ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ።
   ሥላሴ በቁጥር ይቆጠራሉ? በፍጹም አይቆጠሩም!! ታዲያ ሥላሴን የሚወክል ሥዕል ነው እየተባለ የሦሥት ሰዎች ሥዕል በተመሳሳይ ዓይነት መልክ እየተሳለ የሚሸጠው ሥዕል ከየት የተገኘ ነው? ያንን ማድረግ በአሃዝ ማስቀመጥ አይደለም? ደግሞስ ሥላሴ ያንን ይመስላሉ ማለት ነው? የሥላሴ ስፉሕነትና ምሉዕነት በአንድ ሥዕል ይገለጻል? እግዚአብሔር በማን ትመስሉኛላችሁ? ሲል በዚህ ትመሰላለህ! ብለን እንናገራለን ማለት ነው?
  ሥዕል የሰዓሊው ችሎታ የሚገለጽበት ነው።  የሰው ችሎታ ደግሞ ከፍና ዝቅ የሚል ውሱን ነው። በዚህ ከፍና ዝቅ በሚል ችሎታ   ለተሰራ የገበያ ሥዕል ሰው እንዴት ተንበርክኮ ይሰግዳል?  ዓይናችን ያረፈበትን፤ ይኼኛው ጥሩ ተስሏል፤ ብለን የምንገምተውንና የልባችንን ምኞት ተከትለን ከምንገዛው በስተቀር ስለተገቢነቱ ማረጋገጫ የለንም።
       ሥዕልን እየሳሉ ለዚሁ መስገድና በሰማያዊው አምላክ መመሰል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ሳይሆን በኋላ ሰዎች  ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገባ የተደረገ የአምልኮ ሥርዓት ነው።
     
    ቅዱሱ  መጽሐፋችን በዮሐንስ ወንጌል 1፤18 ላይ «መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤  ባባቱ እጅ ያለው አንድ ልጁ እርሱ ተረከው» ይለናል። ታዲያ ያላየነውን የሥላሴ ስዕል መሳላችን ስህተቱ ከእኛ ወይስ ከአንድ ልጁ? (ሎቱ ስብሐት)እንላለን ስህተት ከልጁ መቼም ቢሆን አይታሰብምና ነው።
   የክርስቶስ መልክ ነው እየተባለ በየጎዳናው የሚቸበቸበው ሥዕልም ቢሆን ክርስቶስን አይወክልም።  የክርስቶስ መልክ ይህን ይመስላል ወይም ያንን ብሎ በሰው ኅሊና ከሚታሰበው በላይ ነው። ዮሐንስ እንኳን በራዕዩ ያየውን እንኳን በስዕል ማስቀመጥ አይቻልም። የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፥
   
ጥቅስ 
ራዕይ1፤---
 13 « በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።

14- ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፥ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤

15- እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፥ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበረ።

16- በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ» እያለ የሚመስለውን ከተናገረ ይህ መልክ ከሚታሰበው በላይ እጹብ ድንቅ ከሚባልለት በስተቀር ወረቀት ላይ አስቀምጦ ይህንን ይመስላል ብሎ መስገድ ክህደት ነው።

ጥቅስ
    በሌላ ቦታም ኢሳይያስ ነብይ በ53፤
2፤ በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።

3፤ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። 
 ለእኛ በተቀበለው መከራና ስቃይ መልክና ደም ግባት የሌለው፤ የሕማም ሰው ክርስቶስን በወረቀት ላይ አሳምረንና አቆንጅተን፤ የወርቅ ልብስ አልብሰን፤ የወርቅ አክሊል ደፍተን በመሳል ይህንን ይመስላል ማለት ከተነገረለት ትንቢትና እራሱም «ወፎች እንኳን ጎጆ አላቸው፤የሰው ልጅ ግን አንገቱን የሚያስገባበት የለውም» ካለው ቃል የሚጋጭ አፍቅሮተ ሥዕል እንደያዘን ከሚገልጽብን በስተቀር ክርስቶስን እያመለክን እንዳይደለን ማረጋገጫ ነው።
   አሁን አሁን ደግሞ ከድንጋይም እየተቀረጹ የተለያዩ ምስሎች ገበያ ላይ ይሸጣሉ፤ ሰዎችም እነዚያን የተቀረጹ ምስሎች እየገዙ ይሰግዱላቸዋል፤ያጸልዩባቸዋል።
  በአዲስ ኪዳን አንድም ቦታ ሐዋርያት ለምስል ስለመስገዳቸው ወይም ለምስል እንደሚሰገድ ስለመናገራቸው የተቀመጠ ንባብ የለም። ታዲያ የዛሬው የምስል አምልኮ ከየት መጣ? የሰዎች የልብ ፈጠራ ነው። ፈጠራ ደግሞ እምነት ሊሆን አይችልም።
አንዳንዶች ደግሞ «ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት ይላሉ» እንደተባለው ስዕል  በሙሴ ጊዜ ተፈቅዷል በማለት ስለታቦቱ ላይ ኪሩብ ማስቀመጥ አንስተው የተፈቀደበት ነጥብ ሲሉ ይደመጣል። (ዘጸ25፤20) 
  ይህ አባባል ጥቅሱን ለማጣመም በመፈለግ እግዚአብሔር እስራኤል ዘሥጋን ይገናኝ  ዘንድ በአንድ ወቅት የሰጠውንና  ከታቦቱ ግራና ቀኝ ከወርቅ ተቀርጾ ፊት ለፊት እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ  ይቀመጥ ዘንድ አዝዞት የነበረውን ሥርዓት  እንዴት ሆኖ በየቤቱ ስዕል እንዲስል ተፈቅዶልኛል ይላል?  ምክንያቱም ሙሴ ታቦቱ ላይ አስቀመጠ ማለት ዛሬም በየቤታችሁ ታቦች አኑራችሁ እዚያ ላይ ኪሩብ አኑሩ የሚል ተጨማሪ ትዕዛዝ የለውም።። ደግሞም ኪሩብ ከታቦች ውጪ የትም አይቀመጥ!  የኛን የዛሬውን ስዕል በዚህ ድጋፍ የንግድ ፈቃድ ለመስጠት መመሪያው አይፈቅድልንምና ህገወጥነታችንን እንመን!!
   ከዚያም ባሻገር የተቀረጸው ኪሩብ ከወርቅ እንዲሆን ያስፈለገው የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዚያ እንዲቀረጽ የግድ ስለነበረ   ያንን ፈቃድ ለማሟላት ዛሬም ኪሩቡን የሚተካ ስዕል በየቤቱ ከወርቅ መሳል አለበት ማለት ነው? ወይስ ወርቅ ካላገኛችሁ በምትፈልጉት መልኩ ቅረጹ የሚል ማሻሻያ ከእግዚአብሔር ተሰጥቶ ይሆን?  ኪሩብስ ቅርጽ ነው ወይስ ስእል?
      ከቅድስተ ቅዱሳኑ ውጪ እስራኤላውያን ኪሩብ አስመስለው ሰርተዋል የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ የለም። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ካልፈቀደና ዛሬ  ኦሪታዊ ሥርዓት ከሌለ ኪሩብ የሚባል ቀረጻ በየቤቱ ከየት የተገኘ ነው ታዲያ?

ስዕል ስሎ በእሱ ላይ መለማመን፤ ፊት ለፊት አድርጎ መስገድ፤ እጣን ማጠን፤ አምላክን ወይም ጻድቅን ይወክላል ብሎ ማምለክ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ ሳይሆን ከበዓል አምላኪዎች ወገን የተገኘ ነው።

መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 10፤23
«ልብሱንም አወጣላቸው። ኢዩም የሬካብም ልጅ ኢዮናዳብ ወደ በኣል ቤት ገቡ። የበኣልንም አገልጋዮች። መርምሩ፥ ከበኣል አገልጋዮች ብቻ በቀር እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ወገን በእናንተ ዘንድ አንድ እንኳ እንዳይኖር ተመልከቱ አላቸው።»
ስለሆነም እግዚአብሔርን የሚያመልኩ በእንደዚህ ዓይነት አሰራር ውስጥ አይገኙም። ዛሬም እንደዚህ የበዓል ዓይነት ለስዕልና ለምስል አምልኮ መስጠት በሩቅ ምስራቅና በህንድ በሰፊው ይሰራበታል።  የህንድ በዓል ዛሬም እየታጠነችና እየተሰገደላት ከአምላካቸው ከክሪሽና፤ ከቪሽኑና ሺቫ ያማልደናል ብለው ይታመናሉ።