Wednesday, October 5, 2011

መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበት የሰማይ መሰላል
















"አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:-


ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ::" ሐጌ 1፣5


የእግዚአብሔር ቃል ልባችንን በመንገዳችን ላይ እንድናደርግ ይመክረናል:: በምን አይነት መንገድ ላይ እየተጓዝን እንዳለን ልንመረምር ይገባናል:: ከሁሉም በላይ መንገዱ ወዴት እንደሚወስድና እንደሚያመራ በትክክል ማወቅ አለብን:: በምድር ላይ ብዙ መንገዶች አሉ፣ ሁሉም ግን ያሰብነው ስፍራ አያደርሱንም:: ስለዚህ ትክክለኛውን መንገድ መምረጥና መጓዝ ከዚያም ልባችንን በመንገዳችን ላይ አድርገን መመርመር ይገባናል::

ዛሬ ብዙ ሰዎች በመኪናቸው ወዴት እንደሚሄዱ ያውቃሉ፣ የተሳፈሩትም አውቶቡስ የት እንደሚያደርሳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፣ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች እጅግ የሚያስገርም የመንገድ እውቀት አላቸው:: ነገር ግን ብዙዎቹ የሕይወታቸው ጉዞ ወዴት እንደሚያደርሳቸው አያውቁም:: የመረጡት ሕይወት መጨረሻው ምን እንደሆነ እርግጠኞች አይደሉም:: የተሳሳተ መንገድ ላይ ይሁኑ አይሁኑ የሕይወታቸውን መንገድ የማይመረምሩ ጥቂቶች አይደሉም::

ወገኔ ሆይ፣ ወዴት እየሄድክ ነው? ይህ አኗኗርህ ወዴት ያደርስሃል? ትክክል ነው ብለህ የምትከተለው ሕይወትህና ሃይማኖትህ መጨረሻው ምንድነው? የተሳፈርክበት የሕይወትህ አውቶቡስ ወዴት እንደሚወስድህ በእርግጥ ታውቅ ይሆን? ወይስ ወዴት እየሄድክ እንደሆነ ቆም ብለህ አትመረምር ይሆን? ምናልባትም የትኛውንም መንገድ ብመርጥ ግድ የለም ትል ይሆናል:: የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ሲል ይመክረናል:-
"ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ"!



ወገኔ ሆይ፣ ልብህን በመንገድህ ላይ አድርግ ! ወይስ ወዴትና በምን መንገድ ላይ እንደምትሄድ የማታውቅ ግራ የተጋባህ ሰው ነህ? እንደዚህ አይነት ሰው ከሆንክ አንድ ነገር ከእግዚአብሔር ቃል አብረን እንድንመለከት እጋብዝሃለሁ::

ያዕቆብ የሚባል አንድ ሰው ከቤተሰቦቹ ተሰድዶ በማያውቀው መንገድ ወደማያውቀው አገር በጉዞ ላይ እያለ እግዚአብሔር በሌሊት ተገልጦ አንድ አስገራሚ ሕልም ያሳየዋል:: በመሬት ተተክሎ ራሱም ሰማይ የሚደርስ በላዩ ላይም መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበትን ታላቅ መሰላል ይመለከታል:: በመሰላሉም ራስ ላይ ሆኖ እግዚአብሔር ያዕቆብን ይናገረዋል:: ያዕቆብም ይህን አስገራሚ መሰላል ካየ በኋላ ከእንቅልፉ ሲነቃ ምን እንዳለ ታውቃለህ? "...ይህም የሰማይ ደጅ ነው::" አለ:: ዘፍ 28፣10-19 ስለዚህ የዚያን ሕልም ያየበትን ስፍራ ስም ቤቴል ብሎ ጠራው ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው::

ያዕቆብ ወደማያውቀው አገር በጉዞ ላይ እያለ እግዚአብሔር ያሳየው አንድን ታላቅ መሰላል ነበረ:: ለመሆኑ በመሬት ላይ ተተክሎ ራሱ ሰማይ የሚደርስ መሰላል ምንድነው? እንደዚህ አይነትስ መሰላል አለ ወይ? ወገኔ ሆይ፣ በምድር ላይ የተተከሉ ብዙ መሰላሎች ቢኖሩም ራሱ እግዚአብሔር ዘንድ የሚደርስ መሰላል በዚች ምድር የለም:: ይህ ሰው ሰራሽ ምድራዊ መሰላል ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሆነ ሰማያዊ መሰላል ነው::
ያዕቆብ ከወንድሙ ተሰድዶ ወደማያውቀው አገር በማያውቀው መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ እያለ ነበረ እግዚአብሔር ይህንን የሚያስገርም መሰላል ያሳየው:: ወገኔ ሆይ፣ በማታውቀው የሕይወት መንገድ ላይ እየተጓዝክ ነው? ወዴት እንደምትሄድ እርግጠኛ አይደለህም? ወደማታውቀው ስፍራ እየሄድክ ነው? ዛሬም እግዚአብሔር የሚያሳይህ ይህን ታላቅ መሰላል ነው:: ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ ብቸኛ መሰላል!


ነገር ግን ይህ መሰላል ምንድነው? ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ መሰላል የት ነው የሚገኘው? መሬትና ሰማይ የሚገናኙበትስ የሰማይ ደጅ ማነው? መላእክትስ የሚወጡበትና የሚወርዱበት ምን ዓይነት መሰላል ነው? መልሱን በዮሐንስ ወንጌል ላይ እናገኛለን::


"ኢየሱስ መልሶ:- ...እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው::" ዮሐ 1፣51-52

ወገኔ ሆይ፣ መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበት ታላቁ መሰላል ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ሰማይንና ምድርን፣ ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ ብቸኛ መንገድ ጌታ ኢየሱስ ነው:: ማንም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ቢፈልግ ትክክለኛውን መንገድ መያዝ አለበት:: ራሱ ሰማይ የሚነካውንም መሰላል ማግኘት አለበት:: እርሱም ክርስቶስ ነው:: ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ ብቸኛ መንገድ ነውና::

"ኢየሱስም:- እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም::" ዮሐ 14፣6
ይህ ሊለወጥ የማይችል የጸና የእግዚአብሔር ቃል ነው:: በኢየሱስ በሰተቀር ወደ እግዚአብሔር ሊመጣ የሚችል ማንም የለም::
ወገኔ ሆይ፣ በምድር ላይ የተዘረጋ መሰላል ሁሉ ወደ እግዚአብሔር አያደርስም:: መሰላል ሁሉ ራሱ ሰማይ አይነካም:: ስለዚህ ልብህን በመንገድህ ላይ አድርግ ! በየትኛው መሰላል ላይ እየወጣህ ነው? የትኛውን መንገድ ነው የያዝከው? የደኅንነት መንገድ የሆነውን ኢየሱስን ይሆን?
ሰው ሰራሽ የሆኑ በምድር ላይ የተተከሉ ራሳቸው ግን ሰማይ የማይደርስ ብዙ ሃይማኖቶችና የኑሮ መሰላሎች አሉ:: ያንተስ መሰላል ራሱ የት ነው? በእርግጥ ወደ እግዚአብሔር ያደርስህ ይሆን? ወገኔ ሆይ፣ ልብህን በመንገድህ ላይ አድርግ ! ራሱ ሰማይ የሚነካ መሰላል ኢየሱስ ብቻ ነው:: የሕይወትህ መንገድ ኢየሱስ ነው ወይ? ካልሆነ ከወጣህበት መሰላል ላይ ውረድ ! ወደ እግዚአብሔር ሊያደርስህ በሚችለው ሰማያዊ መሰላል ላይ ውጣ ! ያዕቆብ በማያውቀው መንገድ በጉዞ ላይ እያለ እግዚአብሔር ያመለከተው ወደዚህ ልዩ መሰላል ነው:: እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::

ወገኔ ሆይ፣ በምድር ላይ የተዘረጋ መንገድ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር አያደርስም:: ሁሉም መንገድ የሕይወት መንገድ አይደለምና:: ሁሉም ደጅ የሰማይ ደጅ አይደለም::
"በጠበበው ደጅ ግቡ፣ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፣ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው::" ማቴ 7፣13-14
በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት ሁለት ደጆችና ሁለት መንገዶች ብቻ ናቸው:: ወይ ወደ ጥፋት የሚወስድ ደጅ ወይም ወደ ሕይወት:: ወይ ወደ ጥፋት የሚወስድ መንገድ ወይም ወደ ሕይወት:: ወገኔ ሆይ፣ ወዴት እየሄድክ ነው? የጥፋት መንገድ ላይ ወይስ የሕይወት መንገድ ላይ ነህ? ልብህን በመንገድህ ላይ አድርግ ! መንገድህ ኢየሱስ ካይደለ የጥፋት መንገድ ላይ እንደሆንክ እወቅ:: በየትኛው ደጅ ይሆን የገባኸው? በሕይወት ወይስ በጥፋት ደጅ? የገባህበት ደጅ ክርስቶስ ካይደል የጥፋት ደጅ መሆኑን እወቅ:: እውነተኛ ሰማይንና ምድርን፣ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያገናኝ መሰላል ኢየሱስ ብቻ ነውና:: ክርስቶስ እውነተኛ የሰማይ ደጅ ብቸኛም የመዳን በር ነው::

"በሩ እኔ ነኝ፣ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል..." ዮሐ 10፣9

በያዕቆብና በእግዚአብሔር፣ በሰማይና በምድር፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተዘረጋ ሌላ መሰላል የለም:: ወገኔ ሆይ፣ ሌላው መሰላል ሁሉ ሰው ሰራሽ ነው:: በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ብቸኛ መንገድ፣ ወደ ሕይወት የሚወስድ ብቸኛ በር የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነውና::
"አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፣" 1ጢሞ 2፣5

የጀመርከው መንገድ የማያድንህ ከሆነ ተመለስ ! የምትወጣበት መሰላል ወደ እግዚአብሔር የማያደርስህ ከሆነ ውረድ ! የሕይወትህ ጉዞ መጨረሻው ምን እንደሆነ እርግጠኛ ካልሆንክ ቆም ብለህ አስተውል ! ወገኔ ሆይ፣ በዚች ምድር የምትኖረው አንድ ጊዜ ብቻ ነውና በተሳሳተ መንገድ ተጉዘህ ወደ ጥፋት ከደረስህ በኋላ ተመልሰህ እንደገና ማስተካከል አትችልም:: "የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ..." መክ 12፣1 ስለዚህ ትንፋሽህ በአንተ ዘንድ እያለች ዛሬ ልብህን በመንገድህ ላይ አድርግ:: ብቸኛ የእግዚአብሔር መንገድ የሆነውን ኢየሱስን ተከተል ! እርሱ በእርግጥ ወደ እግዚአብሔር ያደርስሃል፣ ወደ ሕይወትም ይመራሃል::