Thursday, October 13, 2011

ምን እናድርግ?








የብዙዎቻችን ምርጫ አንድ ዓይነት አይደለም። እንደየመልካችን ይለያያል። በሥጋዊ አስተሳሰብ ልዩነት ውበት ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ሥጋ ያለነፍስ ምውት እንደሆነ ሁሉ ለነፍሳችን የምንሰጠው የልዩነት ውበት ነው አባባል ዋጋ የለሽ ይሆናል። በነፍስ ዘላለማዊነት ውስጥ ልዩነት ውበት ነው የሚባል ታሪክ የለም። በዚህ ምርጫ ላይ ዘላለማዊ ውበትን ለማግኘት የግድ ምርጫችን አንድ ዓይነት ብቻ መሆን አለበት። የምንጊዜም ምርጫችን በሥጋ ዓለም እስካለን በክርስቶስ ላይ ካልተመሠረተ በነፍስ ዘላለማዊነት ላይ ልዩነት ውበት ነው የሚባል ሥጋዊ አባባል ዋጋ የለውም። ፍላጎታችንን የሚከተል ምርጫ የህይወታችን መሠረት ላይሆን ይችላል። እምነታችንን የሚከተለው ምርጫ ግን ለዘላለማዊ ኑሮ ወሳኝ ነው። ስለሆነም ምን እናድርግ?
ማንም ሰው የእግዚአብሔርን የፍቅርና የምህረት እንዲሁም የደህንነትን ጥሪ ከተቀበለ፣ ለመዳንና ኃጢአቱ እንዲሰረይለት የሚከተሉትን እንዲያደርግ መጽሕፍ ቅዱስ ያስተምረናል::

1ኛ ንስሐ መግባት:- "ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፣ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት:- ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ? አሉአቸው:: ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ...አላቸው::" ሐዋ 2፣37-38

"እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ፣ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል..." ሐዋ 17፣30

"ኃጢአታቸሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም::" ሐዋ 3፣20


ንስሐ መግባት ማለት በመጀመሪያ ኃጢአተኝነታችንና ፍርድ እንደሚጠብቀን አውቀን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአታችን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲታጠብ መለመንና ከአሁን ጀምሮም በአዲስ ሕይወት እንጂ በድሮ በአጸያፊና ከእግዚአብሔር በተለየ ኑሮ ላለመኖር መቁረጥ ወይም መወሰን ነው:: ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን አዲስ ሕይወትን ለመጀመር የእኛ ውሳኔ አስፈላጊ ነው::

2ኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን:- ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ለሰው ልጆችም ብቸኛ የመዳን መንገድ እንደሆነ፣ ለኃጢአታችንም ሲል በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰና እንደ ሞተ እንዲሁም በሶስተኛው ቀን እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣውና በቀኙ እንዳስቀመጠው ከልብ ማመን:: በዚህ ምድር ላይ ቢሆን ወይም ከሞት በኋላ የነፍሳችን ጌታና ጠባቂ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ፣ እርሱም ከዘላለም ፍርድ ነፍሳችንን ሊያድን የሚችል ብቸኛ አዳኝ እንደሆነ ማመን::





"...ልዩነት የለምና፣ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፣ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በፀጋው ይጸድቃሉ::" ሮሜ 3፣22-24


"በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፣ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም::" ዮሐ 3፣36


"ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፣ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል::" ገላ 2፣16


"...መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፣ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላል ፊት ተደፋ ወደ ውጭም አውጥቶ፣ ጌቶች ሆይ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? አላቸው:: እነርሱም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ አሉት::" ሐዋ 16፣29-31

ከቀድሞ ሕይወትህ ንስሐ ለመግባት ከወሰንህ፣ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በሙሉ ልብህ ካመንህ፣ የኃጢአትህን ስርየት ታገኝ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በፀሎት ቅረብ:: እግዚአብሔር ይቅር እንዲልህ ከልብህ ለምነው፣ እንዲህም በለው:- እግዚአብሔር ሆይ፣ በደለኛና ኃጢአተኛ እንደሆንኩ አውቃለሁ፣ ኃጢአቴን ሁሉ በልጅህ ደም እጠብልኝ:: ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝ እንደሆነ አምናለሁ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የሕይወቴ ጌታና የነፍሴ ጠባቂ እንዲሆን እፈልጋለሁ:: እርሱንም ለመከተል ወስኛለሁ፣ በነገር ሁሉ እርዳኝ:: አሜን

እንደዚህ አይነት የንስሐ ፀሎት ብቻህን ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆነህ መጸለይ ትችላለህ:: የጸለይከውና የለመንከው እውነት ከልብህ ከሆነ እግዚአብሔር ኃጢአትህን ይቅር ብሎ ይታረቅሃል፣ ልጁም ያደርግሃል:: "ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙም ለሚያምኑት ለእነርሱ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው::" ዮሐ 1፣12

ለእግዚአብሔር እንደተናገርከው ሁሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል መወሰንህን ለሌሎች ሰዎች በአፍህ ለመመስከር (ለመናገር) አትፍራ::


"በአፍህ፣ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፣ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው:: ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህ፣ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና መጽሐፍ:- በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና::" ሮሜ 10፣8-11

ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ከወሰንክ:-

1. ስለ ኢየሱስ የበለጠ እንድታውቅ መጽሐፍ ቅዱስን፣ በተለይ ከዮሐንስ ወንጌል ጀምረህ አንብብ:: 1ጴጥ 2፣2-3

2. ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ተነጋገር:: ምናልባት እኔ መጸለይ አልችልም ትል ይሆናል:: ግድ የለም ብዙ አትጨነቅ ብቻ የሚሰማህን ችግርህንም ደስታህንም በራስህ ቋንቋ ንገረው:: እርሱ አባትህ ነውና ሊረዳህና ሊያግዝህ ሊመክርህም ይፈልጋል:: ማቴ 7፣7-11

3. የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ ወደምትሰብክ እንዲሁም በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አምላክነትና በኢየሱስ ክርስቶስም ብቸኛ አዳኝነት ወደምታምን ቤተ ክርስቲያን እየሄድክ በእግዚአብሔር ቃል እደግ:: 2ጴጥ 3፣1
ምንጭ፤(iyesus.com)