Sunday, February 23, 2014

ጾም


(ነብዩ ዮናስ በነነዌህ የሥዕል ምንጭ ባይብል ጌት ዌይ)
(የጽሁፍ ምንጭ፦ የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ)

ጾም ለመንፈሳዊው ዓለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ቁርጥ ልመናን ለማቅረብ፣ እውነተኛ ንሰሐን ለመፈጸም፣ የዕንባ መሥዋዕትን ለማቅረብ፣ በትሕትና ጸጋን ለመቀበል ጾም አስፈላጊና ግዴታ ነው፡፡
ጾም አዋጅና በአዋጅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡  በስውር የሚደረግ ጾም አለ፡፡  ግለሰቡ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብበት፣ መጾሙንም የማያሳውቅበት ነው፡፡  የማኅበር ጾም ግን በአዋጅ የሚደረግ፣ ስለ አገርና ስለ ወገን የእግዚአብሔር ማዳን የምንጠባበቅበት ነው፡፡  ጾምን ሰው ለራሱ ያውጃል፣ ቤተ ክርስቲያንም ታውጃለች፡፡
ጾም ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናዋርድበት ነው፡፡  በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ልመና ግዳጅን ይፈጽማል፡፡  ፈጽሞም መልስ ያገኛል፡፡  ጾም ለትሑት ጸሎት እጅግ ይረዳል፡፡  ሥጋን በማድከም ወደ ነፍስ ልዕልና የምንቀርብበት ምሥጢር ነው፡፡  ጾም የርኅራኄ መገኛ፣ የዕንባ ምንጭ፣ የትሕትና መፍለቂያ ናት፡፡  ራሳችንን በጾም ስናዋርድ እግዚአብሔር ከፍ ያደርገናል፣ ምሪትን ይሰጠናል (ዕዝ. 8÷21)::
ጾም አዋጅን የሚሽር አዋጅ ነው፡፡ በመጽሐፈ አስቴር ላይ እንደምናነበው በአይሁድ ላይ የታወጀው የሞት አዋጅ ወደ ሹመትና ክብር የተለወጠው በጾምና በጸሎት ነው (አስቴ. 4÷3)፡፡  የተዘጉ ደጆች እንዲከፈቱ፣ በአገር በወገን ላይ የመጣ የክፉ አዋጅ ማለት ሞት፣ መከራ፣ በሽታ እንዲወገድ ጾም ጸሎት ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡  የጾምና የጸሎት ትጥቅ አይታይም፣ የሚታየውን ጠላት ግን ያሸንፋል፡፡  
ጾም ይቅር ብለን ይቅርታ የምንለምንበት ነው፡፡  እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን (ይቅርታን) ይወዳል (ማቴ. 9÷13)፡፡  በጾም በጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ስንለምን ይቅር እያልን፣ በረከቱን ስንለምን ለተራቡት እያበላን ሊሆን ይገባዋል፡፡ አማኝ ከጫጫታ ስፍራ ገለል ብሎ፣ ከዘፈን ይልቅ ዝማሬን መርጦ፣ ከወሬ ይልቅ በጸሎት ተጠምዶ እንዲባረክ ጾም ቀስቃሽ ደወል ነው፡፡
ዘፈንና ዝሙት እንዲሁም ስካር በአገር ሲበዛ ቀጥሎ ትልቅ ጥፋትና ልቅሶ ይኖራል፡፡  "የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም" እንዲሉ ዘፈን ሲበዛ መጾምና ማልቀስ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም የበሬ ሥጋን ከመብላት መከልከልን ብቻ ሳይሆን ከሰው ሥጋም እንድንርቅ ነው፡፡  ያለ ቢላዋ በሐሜት የሰውን ሥጋ መብላት ጾምን እንደ መግደፍ ነው፡፡  እኛ ግን የበሬ ሥጋ እንጂ የሰው ሥጋ አንተውም፡፡ ሠራተኞቻችንን እያስለቀስን፣ ደመወዛቸውን እየበላን፣ ቂምን በልባችን ሞልተን የምንጾመው ጾም የረሃብ አድማ እንጂ ጾም አይባልም (ኢሳ. 58÷5-6)፡፡ የጾም መሰናዶው ነጠላን ማጽዳት ሳይሆን ልብን ማጽዳት፣ በየልኳንዳ ቤት ደጆች መሰለፍ ሳይሆን ንስሐ መግባት፣ ዕቃን ማጣጠብ ሳይሆን ከቂም መጽዳት ነው፡፡  የጾምን መረቁን እንጂ ሥጋውን አልበላንምና ከንቱ ልፋተኞች ሆነናል፡፡ ምክንያቱም ለጾማችን የምናደርገው ዝግጅት ሜዳዊ እንጂ ውስጣዊ አይደለምና፡፡ ትልቁ ጾም ከኃጢአት መከልከል ነው፡፡  ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ኃጢአት ነው፡፡  በአገራችን በጾም መግቢያና መውጫ ስካርና ዝሙት ይደራል፡፡  ቅበላውና ፋሲካው በኃጢአት በመሆኑ ከጾም የሚገኘውን በረከት ማግኘት አልቻልንም፡፡
ጾም ለእግዚአብሔር እንጂ ለታይታ አይደለም (ዘካ. 7÷5)፡፡  ከማኅበረሰቡ ላለመለየት፣ ሆዳም ላለመባል፣ ዶሮ ለመባረክ መጾም ከንቱ ጾም ነው፡፡ የምንጾመው ከእግዚአብሔር ዋጋ ለማግኘት እንጂ ጾመኛ ለመባል መሆን የለበትም፡፡ የጾምና የጸሎት ዋጋ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ “በጾም አፌ ክፉ አታናግሩኝ” ለማለት መጾም አይገባንም፡፡  ባንጾምም ክፉ መናገር አይገባንም፡፡  በጾማችን የሚታየን እግዚአብሔር ነው?  ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡
ጾም እውነትና ሰላም ያለበት ነው፡፡  በጾማችን ወራት ከድሆች ጋር ማሳለፍ፣ ብድር መመለስ ለማይችሉ ቸርነት ማድረግ ይገባል፡፡ እኩያን ሲጠሩ መኖር እውነተኛነት አይደለም፡፡ ከእኛ ባነሰ ኑሮ ለሚኖሩት እጅን መዘርጋት ግን የጾም መገለጫው ነው፡፡  ጾም ሁለት እጆች አሏት፡፡  አንደኛው የጾም እጅ ጸሎት፣ ሁለተኛው የጾም እጅ ምጽዋት ነው፡፡  ጾም ሁለት አንደበት አሏት፡፡  አንደኛው ቃላችን ሲሆን ሁለተኛው ዕንባችን ነው፡፡ ጾም እውነትን ትፈልጋለችና ለተጨቆኑ ምስኪኖች፣ ፍርድ ለተጓደለባቸው እስረኞች፣ በግፍ ከገዛ አገራቸው ለሚሰደዱ አቤት የምንልበት፣ ግፍ አድራጊዎችን በቃችሁ ብለን የምንገስጽበት የእውነት ሰይፍ ነው፡፡ ጾም ሰላም ስለሆነ ግለሰብ ከግለሰብ፣ ማኅበራት ከማኅበራት፣ አገር ከአገር ጋር የሚታረቁበት፣ እንዲታረቁም ጥረት የምናደርግበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ እርቅን የጠሉና የገፉ የሃይማኖት አባቶች ጾምን የማወጅ አቅም የላቸውም፡፡ ስለዚህ ታርቀው የሚያስታርቁበት እንዲሆን ሊያስቡ ይገባቸዋል፡፡ የጾም የመጨረሻው ውጤት ወይም በዓሉ እግዚአብሔር በሚሰጠን መልስ ሆታና ደስታ ነው፡፡  መልስ እንዲመጣ ግን እውነትና ሰላም መርጋት አለባቸው፡፡ ግፈኞች፣ የሌላውን ድርሻ እየነጠቁ የሚበሉ፣ ለሀብታም እያደሉ በድሃ የሚፈርዱ ሊገሰጹ፣ ንስሐ ሊገቡ ይገባል፡፡  ያ ሲሆን የጾም ዳርቻው ተድላና ደስታ ይሆናል (ዘካ. 8÷19)፡፡
 የነነዌ ሰዎች ምሕረትን የተቀበሉት በሦስት ቀን ጾምና ጸሎት ነው፡፡  የመጣው መዓት የተመለሰው፣ የራቀው ምሕረት የቀረበው በአንድ ልብ ሆነው አቤት በማለታቸው ነው፡፡  እኛ ግን ዓመት ሙሉ እየጾምን ለምን በረከት ራቀን? ብለን ጠይቀን አናውቅም፡፡ 

እንደጸሎታችን መብዛቱ ረሃብና ቸነፈር፤ ስደትና እንግልት፤ የሰላምና ፍቅር እጦት፤ አንድነትና ኅብረት አለመኖር የሚያጠቃን ለምንድነው? የጾም ጸሎት ምላሹ ይህንን ለማስቀረት ካልሆነ የጾምና የጸሎታችን ጉዞ የተተከለ ደንብ ከመፈጸም ውጪ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር አልተገናኘም ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾም፡-
    1.     ርዕስ ልንይዝ
    2.    ይቅር ልንባባል
    3.    ንስሐ ልንገባ ይገባናል፡፡
ብዙ አንገብጋቢ ርዕሶች አሉን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል፣ በመንፈሳዊ ቦታ መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎች መቀመጣቸው፣ እርቅን የማይወዱ ሰዎች መሙላታቸው፣ በአገር ያለው የኑሮ ውድነት፣ ድሆች በደንብ እየደኸዩ መሆናቸው፣ ፍትሕና ፍቅር መጥፋቱ፣ የገንዘብ ጣኦት በምድራችን መቆሙ፣ የዝናብ መታጣት፣ የበሽታ መበርከት፣ የአንድነት መጥፋት፣ የትዳር መናጋት፣ የልጆች ዋልጌነት፣ የሐሰት መምህራን መብዛት፣ እግዚአብሔርን መርሳት…….  ይህ ሁሉ የጾምና የጸሎት ርዕሳችን ነው፡፡  ክርስቲያን መንፈሳዊ ኃይልን አጥተóል፡፡  በየደረሰበት ውጊያ አሸናፊ ሳይሆን ተሸናፊ ሆኗል፡፡
ይኸውም፡-
    -      ቃሉን ስለማያጠና
    -      የጸሎት ሰዓቱ ስላልተከበረ
    -      ጾምና ጸሎትን ስለተወ
    -      ምጽዋትን ስላስቀረ
    -      የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስላልቻለ …. ነው፡፡
በእውነት ጾመን በዓሉ ተድላ እንዲሆን፣ በጾም ዘርተን በፈውስ እንድናጭድ እግዚአብሔር ይርዳን!

Sunday, February 16, 2014

ዕርቅና ሰላም፤ የሕይወት ቅመም


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደውለታ ቢስ ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ መልስ የሚሆን ጽሁፍ እነሆ!
በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ 
 
   አንድ ጥናት ሳነብ፥ ምናልባት እናንተም አንብባችሁት ይሆናል፥ የተፈጥሮ ሀብት ባላት ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ከተራቡ፥  የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ቢሆን ነው ሲል አገኘሁት። "ጥልቀት የሌለው ረጋ-ሠራሽ ጥናት ነው" ብዬ ጣልኩት። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋ መሆኗን እርግጥ ባለሞያዎች የመሰከሩት ነው። ማዳበሪያ የማያስፈልገው መሬት ታርሶ አያልቅም። የወንዞቿ ውሀ ለጎረቤት አገሮች ሳይቀር ይተርፋል። ይኸንን እውነታ በቀጥታ ከተመራማሪዎቹ  አፍ ለመስማት የፈለገ ፕሮፌሰር ስዩም ገላየን ማዳመጥ ይችላል።  
   እንዲህ ከሆነ፥ ትኩረቱ በኢትዮጵያውያን የማሰብ ችሎታ ላይ ሊሆን ነው። እውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመጽዋች ሆኖ የቀረው የማሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ሆኖ ነው? አይመስለኝም።  ሰውየው ጥናቱን ማስተካከል አለበት። አለዚያ፥ ከዚያ ቀጥሎ፥ "አንድ ሰው እሱቁ ውስጥ ከመስተዋቱ በስተኋላ ድፎ ዳቦ እያየ ከተራበ የአስተሳሰብ ችሎታው ዝቅተኛ ቢሆን ነው" ሊለን ነው። ምንም ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ቢኖረው፥ ዳቦውን እንደማያገኘው ለማንም ግልጽ ነው። 
  እርግጥ ነው፥ በአስተሳሰብ ደከም የሚል ሰው ሊጎዳ ይችላል። ሌላው ቢቀር፥ የብልሁ ጓደኛውን ያህል አይደላውም።  ግን በከፍተኛ ደረጃ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰውም ሊቸገር ይችላል።  ስንቶች ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በችግር የሚኖሩ፥ መውጫ ቢያገኙ ግን ለሌላው ሳይቀር የሚተርፉ? በአፍሪካ፥ በአውሮፓ፥ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በማስተማርና በምርምር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቊጥር ቀላል አይደለም። በንግዱ ዓለምም ቢሆን፥ "የሺ ብር ጌቶችን" ጓዳ ይቊጠራቸው። 
የለም፥ የተፈጥሮ ሀብት ባለጠጋ የሆነች ኢትዮጵያ ብልሁ ሕዝቧ ለምን እንደሚራብ የተከበረ ጥናት መደረግ አለበት። ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች ፕሮፌሰር ስዩም ገላየ ደርድሯቸዋል። አንዱ፥ የመሬት ይዞታ መበላሸት ነው ይለናል። "የመሬት ላራሹ" ጩኸት ውጤቱ "መሬት ለነጋሹ" ሆኗል፤ ለገበሬው የታሰበውን መሬት ወያኔ ወሰደው። የዱሮ ንጉሣዊ ገዢዎቿ ቤተ ሰቦች ስለነበሩ በቊጥራቸው ማነስ ምክንያት እነሱን በማር ግብር ለማጥገብና በሰላም ለመኖር ቀላል ነበረ። የዛሬዎቹ ገዢዎች ብሔረ ሰቦች ስለሆኑ እነሱን ሁሉ በሚሊዮን ዶላር ማጥገብ መራቆትን አስከትሏል። ሌላው፥ አገሪቱ በክልል መከፋፈል ነው። ማንም ሰው በገዛ ሀገሩ ከመሰለው ክፍለ ሀገር ሄዶ በሰፊው ማረስ አይችልም። ዛሬ ኢትዮጵያ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ሙሉ በሙሉ አገሩ አይደለችም። ኢትዮጵያ ለልጆቿ እናትነቷ በሙሉ ሰውነቷ እንዳይሆን ተከልክላለች። 
 የታሪክ ተመራማሮዎችም ያዩት ምክንያት ይኖራቸዋል። ክርስቲያኖችና እስላሞች፥ ኦሮሞዎችና ሌሎች መሆናችንን ዐውቀን በብልህነት አለማስተናገዳችን ጒዳት እንዳመጣብን ይናገራሉ። ሁላችንም የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች፥ አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብንሆን ኖሮ ከምሰሶ ጋር በእግር ብረት እንደተቈራኘ ሰው እጃችንን ብቻ ወደ እግዚአብሔር እያደረስን አንድ ዘመን ላይ ቆመን አንቀርም ነበር ይላሉ።  
  በሃይማኖት አንድ ባለመሆናችን ያስከተለውን ጕዳት ለማሳየት የአክሱምን ሥልጣኔ ያከሰመውን የጉዲትን አመፅና የአምሐራን ("የአማራን" ማለቴ አይደለም)ሥልጣኔ እሳት የለቀቀበትን የግራኝን ወረራ ይተርካሉ።

እነዚህ ሁለት ሥልጣኔዎች ኢትዮጵያን በዚያ ዘመን ከገነኑ አገሮች እኩል አስሰልፈዋት ነበረ፤ ጠፉ፤ ባለንበት ቆመን ቀረን። 
ዛሬ ስለሁለቱ ሥልጣኔዎች የምናውቀው ከመጥፋታቸው በፊት ከተጻፈው ታሪካቸውና ከጥፋት ካመለጠው  ርዝራዣቸው ነው። ሀገሪቱ ከግራኝ ምች ልታንሰራራ አልቻለችም። የግራኝ ምች የምለው እስላሞች በዓሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጒዳት ነው;ታሪኩን ክርስቲያኖቹ በሐዘን፥እስላሞቹ በደስታ መዝግበውታል፤ ዛሬም በዚያው ስሜት ያስታውሱታል። የደረሰው የሰውና የንብረት ጥፋት ሁሉ የሚያሳዝን ቢሆንም፥ሁልጊዜ የሚታወሱኝ ቅጂ ያልተገኘላቸው ስማቸው ብቻ የቀረልን ብርቅ ድርሰቶች ናቸው።
እስላሞቹ ክርስቲያኖቹን ለማጥፋት ከጂሃድ በቀር ሌላ ምንም ምክንያትአልነበራቸውም። መንግሥቱን ተወደደም ተጠላ ያቋቋሙት ክርስቲያኖቹ  ነበሩ። ከሀገሪቱ ክፍል ሱማሌዎችና ይፋቴዎች እንደሚኖሩባቸው አንዳንድ ክፍሎች ሲሰልሙ፥ በኢትዮጵያ ስር ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበረ። በዛሬው ዓይናችን እንኳ ስናየው፥ የንጉሣዊው መንግሥት ከዚህ የተሻለ ሌላ ምን አማራጭ አገዛዝ ነበረው? የጂሃዱ መንሥኤ ኦርቶዶክሱን ሕዝብ በሞላ አስልሞ በሸሪዓ ሕግ መግዛት  ነበር። 
እስላሞቹ፥ "መንግሥቱን ወስደን፥ ክርስቲያኖቹ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ እናደርጋለን" ቢሉ እንኳን ያባት ነበር። ኦሮምኛ ተናጋሪዎችና ሌሎች መሆናችን ያስከተለውን ጕዳት ለማሳየት ደግሞ የኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎችን ወደማህል ኢትዮጵያ የመፍለስ ታሪክ ይተርካሉ። ለአባ ባሕርይና የዘመኑን ነገሥታት ታሪክ ለጻፉ፥ በተለይም ለተክለ ሥላሴ ጢኖና ለተክለ ኢየሱስ ዋቅጂራ ምስጋና ይድረሳቸውና የኦሮሞ ጎሳዎች ወደማህል ኢትዮጵያ ፍልሰት ያስከተለው የሥልጣኔ ውድመት ከብዙው በጥቂቱ ተመዝግቧል። ኦሮምኛ የሚናገሩ ጎሳዎች የእስላሞቹ አመፅ በተገታ ማግስት ፈልሰው፥ ከእስላሞቹ የተረፈውን የሥልጣኔ ምልክት ጠራረጉት። ጋዳ በሚሉት ሁሉን ለጦርነት በሚያሰልፍ የማፊያ ሥርዓት በውትድርና ተደራጅተው፥ በግብርና፥ በንግድ፥ በድብትርና ("በዕውቀትና በምርምር"ማለቴ ነው) የሚተዳደረውን ሰላማዊ ሕዝብ አረዱት፤ ንብረቱን አወደሙት። በእርሻው፥ በሰብሉ ላይ ከብታቸውን አስሠማሩበት። በባህላቸው መሠረት፥ ክርስቲያን ያልገደለ በቅማል ይሰቃያል እንጂ ራሱን አይላጭም ነበር። ሸዋን፥ ጎንደርን፥ ጎጃምን፥ አምሐራን (የዛሬውን ወሎ) ደመሰሷቸው።  
እስላሞቹ የክርስቲያኖቹን ሥልጣኔ አጥፍተው በራሳቸው ሥነ ጽሑፋዊ ሥልጣኔ ሊተኩት አስበው ነበረ። ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ግን እረኞች ስለነበሩ ሥልጣኔን በሥነ ጽሑፋዊ ሥልጣኔ የመተካት ግዴታ አልነበረባቸውም። ግን በባህል ረገድ ከወረሩት ሕዝብ አብዛኛውን እንደነሱ ኦሮምኛ ተናጋሪ፥ የቀረውን ገበር (አሽከር) አደረጉት። እስላሞቹና ኦሮምኛ ተናጋሪዎቹ ሰውና ቅርስ ባወደሙበት ቦታ ሁሉ ሐውልት ቢቆም ሀገሪቱ "ሀገረ ሐውልት" ትሆን ነበረ።  
  ከግድያቸው ሰለባቸው ይብስ ነበረ። ባለቅኔው፥ "ጃዊ ቀደደ ሆድ ሆድሆዶሙ ወሰለቦሙ እስከ ሕምብርት" (ጃዊ ሆድ ሆዳቸውን ቀደደው፤ እምብርታቸው ድረስ ሰለባቸው) ያለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት የደረሰውን መቅሠፍት አይቶ ነው። የሆነውን በታሪክ ዓይን አይቶ በማለፍ ፈንታ፥ ዛሬ አቻው እንዲሆን ታስቦ ያልሆነ፥ ያልተደረገ የአረመኔነት ታሪክ ለራስ ጎበና ዳጨ ወታደር መፍጠር፥ ግፋ ቢል ሞኞችን በሞኝነታቸው እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ አገልግሎት አይኖረውም። ውሸት ታሪክ አይሆንም።  
  ማንም መጥቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሰፍር የኢትዮጵያ ነገሥታት አይከለክሉም ነበር። ሰው የሌለበት ሰፊ ቦታ ስለሞላ ማንም ከዚያ ቢሰፍር ማን ነህ የሚለው አልነበረም። ችግሩ፥ ኦሮምኛ  ተናጋሪ ጎሳዎች ከአንድ ቦታ ፈልሰው ከባዶ ቦታ በመስፈር ፈንታ፥ ሌሎች ያቀኑትን ቦታና ያተረፉትን ቅርስና ውርስ እንንጠቅ ማለታቸው ነበር። በዚያ ላይ፥ ማህል ኢትዮጵያን ከያዙ በኋላ፥ ለኢትዮጵያ መንግሥት አንገብርም ማለትን አመጡ። በዚህ ጊዜ የንጉሣዊው መንግሥት ምርጫ ምን መሆን ነበረበት?  

  
ያምናው በሽታ፤ 

  በዚህ እኛ ባለንበት ዘመን፥ እስላሞች ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉ፥ አንዳንድ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ሰላማዊውን ሰው በሕይወት ገደል ሲሰዱ፥ በ ዩቲዩብ  (youtube) ሳይ፥ ሰውየው፥ "ኧረ እናንተ ሰዎች ሰው አይድንም ታሞ፤ ያምናው በሽታየ አገረሸ ደግሞ፡" ያለው ትዝ አለኝ። በሽታውን ማስገርሸት አንዱን ጠቅሞ ሌላውን አይጐዳም። ሁሉም ተጐጂ ነው የሚሆነው። ሁል ጊዜ ሳይሞቱ መግደል አይቻልም። 
ሌላውን የሚገድሉት እየሞቱ ነው። በዚያ ላይ በማህል ቤት የሚሆነውን ማንም አያውቀውም። ለምሳሌ፥ የኦሮሞን አመፅ ይመሩ የነበሩ የወለጋ ፕሮቴስታንቶች እንደነበሩ ይታወሳል። አሁን አመፁን ከነሱ ተቀብለው በኦሮሞ ስም የሚያካሂዱት፥ "ከኦሮሞው ሕዝብ አርባ በመቶው እስላም ነው" የሚሉ የኦሮሞ እስላሞች ናቸው። ቊጥራቸውን ቢያጋንኑትም፥ እስላሞቹ ከፕሮቴስታንቶቹ መብለጣቸው አያጠራጥርም።  እንግዲህ፥ የፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች መንግሥት  ላይ  ያካሄዱት ትግል በፍትሐ ነገሥት ቀርቶ በሸሪዓ ሕግ በሚያምኑ ወገኖች ለመተዳደር ሊሆን ነው።  የግብጽ ክርስቲያኖች የመለካውያን ክርስቲያኖችን የበላይነት በመጥላት አገሪቷን ዐረቦች እንዲወስዷት ረድተው፥ ዋጋ ከሌለው ጸጸት ላይ እንደወደቁ የምናየው ነው። 


 የመጀመሪያው እርምጃ፤ 

ከላይ እንደገለጥኩት፥ እስላሞችና ኦሮምኛ ተናጋሪ ጎሳዎች ኢትዮጵያን እንዴት እንዳቈረቈዟት ታሪኩ እንዳይፋቅ ሆኖ ተጽፏል፤ የሚፈለገው ግን ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ ነው።ዕርቅና ሰላም የሚወርድ ከሆነ፥ታሪኩ ባይፋቅም ተከቶ ከድንቊርናና ከረኀብ የምንላቀቅበትንና ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለን የምናስመሰክርበትን ብልሀት ልንፈልግ እንችላለን።ለዚህም መሆን ያለበት የመጀመሪያው እርምጃ አባቶቻችንን እንወክላለን የሚሉ እስላሞችና ኦሮሞዎች የአባቶቻቸውን ጥፋት ከመቀጠል አባቶቻችው በኢትዮጵያ ላይ ላደረሱት መጠን አልባ ጥፋት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይሆናል። 
የጥፋቱን ታሪክ ጸሐፊዎቹ ለወገኖቻቸው እያዳሉ ጽፈውታል እንዳይሉ፥የጻፉት ራሳቸው እስላሞቹ እነሽሀብ እዲን ዐረብ ፈቂህ፥ የአማራውና የኦሮሞ ተወላጆች እነ አባ ባሕርይ፥ እነ ተክለ ሥላሴ ጢኖ፥ እነ ተክለ ማርያም ዋቅጂራ ናቸው። ታሪካችንን ደብተራዎች አይጽፉትም የሚሉ ካሉ፥ የጸሐፊዎቹን ማንነት ባለማወቅ ሊሆን ይችላል። የሌሎችም ታሪክ ጸሐፊዎች ስማቸውና ሥራቸው "የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ"  በተባለው መጽሐፌ ውስጥ ተዘርዝሯል።  ይህን መጽሐፍ ብዙ ሰው ስለሚፈልገው፥ ማንም ሰው  እያወረደና እያተመ  እንዲያነበው በማሰብ፥ www.ethiopiawin.net or www.ethiopiawin.org  ብለን ካቋቋምነው ድረ ገጽ ላይ ተለጥፏል። ኢትዮጵያን ለማገልገል ላቋቋምነው ድርጅት እርዳታ የሚሆን በፈቃድ ከሚሰጥ ገንዘብ በቀር የመጽሐፉን ዋጋ አንጠይቅም።  

ሁለተኛው እርምጃ፤ 

ሁለተኛው እርምጃ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን የሚመለከት ነው፤ አፄ ምኒልክና ራስ ጎበና ዳጨ ስፍር ቊጥር በሌለው ጎሳ የተበታተኑትንና እርስ በርሳቸው የሚባሉትን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አንድ ያደረጉበትን ቀን በየዓመቱ ማክበር አለባቸው። ግን ሁሉንም አንድ ያደረጉት በአንድ ቀን ድል ስላይደለ፥  የትኛውን ቀን እንደሚያከብሩ በጨፌያቸው ሊወስኑት ይችላሉ። ሆኖም በአፄ ምኒልክ ሐውልት ስር አበባ ማስቀመጥ የበዓሉ ክፍል መሆን አለበት። ራስ ጎበና ሐውልት ስለሌላቸው፥ ሳይውል ሳያድር ከተከበረ አደባባይ ላይ የጎላ ሐውልት እንዲተከልላቸው ባለውለታዎቹ መገፋፋት ይኖርባቸዋል።        

ሶስተኛው እርምጃ 

ሶስተኛው እርምጃ አስተሳሰብን ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወደ ሰብአ ዘመን አስተሳስብ ማራመድ ነው። '"ሰብአ ትካት" በእንግሊዝኛ  primitive people የሚባሉት ናቸው። አስተሳሰባቸው ከመንደራቸው ርቆ አይሄድም፤ የዚያኛው መንደር ሰው ጠላታቸው ነው፤ የዚያኛው ብሔረ ሰብ አባል ባለጋራቸው ነው። "ሰብአ ዘመን" modern man ነው። መንደሩ ጠቅላላዋ ሀገር ነች። በሰብአ ዘመን አስተሳሰብ የዚያ መንደር ወይም የዚህ መንደር ነባር መሆንና የዚያ ቋንቋ ወይም የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን ዋጋ ሊሰጠው የማይገባ አጋጣሚ ነው። የሰብአ ዘመን አስተሳሰብ ከዚያም መጥቆ ሄዶ ዓለም አቀፍ ላይ ይድርሳል። በሰብአ ትካት አስተሳሰብ ያሉ ብሔርተኞችን በአንድ ጊዜ ወደዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ይሸጋገራሉ ብለን አንገምትም፤ ለጊዜው ፍላጎታችንም አይደለም። ግን በሰላምና በብልጽግና ለመኖር ከብሔርተኛነትና ከሰብአ ትካት አስተሳሰብ ወጥቶ ዲሞክራት መሆን አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው። በአካል የሰብአ ዘመን አባል ሆኖ በአስተሳሰብ ሰብአ ትካት መሆን፥ "የሚራቡት የማሰብ ችሎታቸው ዝቅተኛ ቢሆን ነው"  ለሚለው ጥናት ማስረጃ መሆን ነው። እንደማየው፥ ብሔርተኞች ከዲሞክራሲ ጋር ያላቸው ግንኙነት በፍቅርና በጥላቻ የተሳሰረ ነው። የዲሞክራሲ ዋና መለዮ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር ነው። በአሁኑ ሰዓት ከገዢዎቹና ከደጋፊዎቻቸው በቀር ይኸንን የማይቀበል ያለ አይመስለኝም። እዚህ ላይ ብሔርተኞችና ዲሞክራሲ ፍቅረኞች ናቸው። ግን  ሰብአዊ መብቶች የሚባሉት የግለሰብ ብቻ ናቸው ወይስ ማኅበሮችና ብሔረ ሰቦችም ሰብአዊ መብቶች አሏቸው? የላቸውም ከተባለ፥ ብሔርተኞች ዲሞክራሲን አይቀበሉም።  

መብት በመሠረቱ የግለሰብ ነው። ሆኖም ብሔረሰቦች በደፈናው መብት የላቸውም አይባልም። አቅም ካላቸው ቋንቋቸውንና ሌላ ሌላ ባህላቸውን ማዳበር መብታቸው ነው። ይኸንን በሥራ ላይ ለማዋል ሲሰበሰቡ ጸጥታቸውን መንግሥት ያስከብርላቸዋል። የአንድ ሀገር ሕዝብ ሆኖ ብሔረሰባዊ  ፓርቲ መመሥረት ግን ከሌላው ብሔረ ሰብ ጋር የጋራ ጥቅም የለንም ማለት ይሆናል። የፓርቲ መሠረቱ የግለሰብን ሕይወት በኢኮኖሚ እድገት ማሻሻል ነው። ለዚህ ዓላማ ፓርቲው ጉራጌ፥ አደሬ፥ ጉጂ፥ ወዘተ መሆን የለበትም።  ሆኖም፥ የብሔረሰብ አባላት በይፋ አድመው ድምጻቸውን ይጠቅመናል ለሚሉት ፓርቲ ሊሰጡ ይችላሉ። በዲሞክራሲ አስተዳደር ብሔርተኞች ብሔራቸውን የሚጠቅሙት በዚህ መንገድ ብቻ ነው።            
 
 

Saturday, February 15, 2014

ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ሀገራዊ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ማገዳቸው ትክክል ነው!!


«መታገድ» የሚለውን ቃል በአሉታዊ ምልከታ ለማራገብ ካልተሞከረ በስተቀር ባለእባብ ዓርማው ማኅበረ ቅዱሳን የጠራውን ስብሰባ መታገድ በተመለከተ የሚያሳየው  የትርጓሜ እውነታ ግን በትክክለኛነቱ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው። ለዚህም ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሉን።
1/ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለውን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኗ ያላቋቋመችውና ከብላቴ ጦር ምላሽ በጎ ፈቃደኞች የመሠረቱት ሲሆን የቤተ ክርስቲያኗ የውክልና ድርሻ ስለሌለው የትኛውንም የቤተ ክርስቲያን አባል በመጥራት መሰብሰብ አይችልም።
2/ ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂት ደጋፊዎቹ ተነስቶ የሲኖዶስ አባል የሆኑትን ጳጳሳት በመጠምዘዝ፤ በማስፈራራትና በጥቅማ ጥቅም በማታለል ለራሱ ብቻ የሚጠቅመውን መተዳደሪያ ደንብ በማስጸደቅ ቤተ ክርስቲያንን ተለጥፎ በሕይወት ለመቆየት ከመቻሉ በስተቀር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደልማት ማኅበር ወይም እንደ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም እንደመንፈሳዊ ተቋም የመሠረተችው አይደለም። ስለዚህ አሀዳዊትና ሐዋርያዊት በሆነችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሌላ ማኅበር ሊኖር ስለማይገባው ማኅበረ ቅዱሳን ማንንም የቤተ ክርስቲያን አባል በማደራጀት መንቀሳቀስ አይችልም።
3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤቶች በተዋረድ ያላት ተቋም ሆና ሳለ በሽብልቅ የገባው ማኅበር ይህንን የመዋቅር ሰንሰለት በጥሶ ለራሱ ዓላማና ግብ በመንፈሳዊ ካባ ተጠልሎ ስብሰባ የማካሄድ፤ የመጥራት፤ የማደራጀት፤ የመምራት ስልጣን የለውም።

4/ ማኅበረ ቅዱሳን በልማት ማኅበር ወይም በእርዳታ ድርጅት ወይም ራሱን በቻለ መንፈሳዊ ተቋምነት ወይም በሌላ መሰል ስያሜ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው አግባብ እውቅና አግኝቶ የተፈቀደለትንና የሚችለውን ሀገራዊና መንፈሳዊ ዓላማ ከማከናወን በስተቀር በሲኖዶስና በማኅበር የሚመራ ሁለት አስተዳደር ቤተ ክርስቲያኒቱ መሸከም የለባትም። ስለሆነም የፓትርያርኩ እግድ የስልጣን ተዋረድንና ኃላፊነትን ያገናዘበ በመሆኑ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
5/ ለወደፊትም ቢሆን ቁርጡ በታወቀ ቁመና የማኅበረ ቅዱሳን ማንነት መታወቅ አለበት። ስለሆነም እጅ እየጠመዘዘ ያስጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ቀሪ ሆኖ በራሱ ግዘፈ አካል፤

   ሀ/ በሰንበት ትምህርት ቤቶች አወቃቀር የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበር ለመሆን ከፈለገ ያለውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማስረከብ ለሰንበት ተማሪዎች በተሰጠው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ መመሪያ መሰረት መተዳደር አለበት።
  ለ/ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማደራጀት በወጣው ህገ ደንብ የመተዳደር ፈቃደኝነቱ ከሌለው የአባልነት ምልመላ፤ የገንዘብ አቅምን የማጎልበት፤ አስተዳደራዊ መዋቅሩን የመዘርጋትና የማንነት አቅም ማጎለበቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውጪ የመሆን አዝማሚያ እንዳለው እያየን ነውና ሀገሪቱ በምትሰጠው መብት በፍትህ ሚኒስትር ተመዝግቦ ሊንቀሳቀስ ይገባዋልና ቅዱስ ፓትርያርኩ የጀመሩትን መልክ የማስያዝ ጅማሮ ከፍጻሜ እንዲያደርሱ እንጠይቃለን።