Monday, October 31, 2011

እውነቱን ብንናገር ምን ይለናል?


በዚህች ምድር ላይ ከተስፋፋውና በሰዎች ልቡና ላይ ከተማውን ከመሠረተው አስፈሪ ኃጢአት መካከል እውነትን ለመናገር የሚችል ሰው እየጠፋ መምጣቱ ቀዳሚውን ይዟል። ዓይኑ ያየውን፤ ጆሮው የሰማውን ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ልቡ ያመነጨውን እውነት አድርጎ ማውራትና ማስወራት፤ ይህንንም እንደእውነተኛ ምስክርነት መቁጠር ባህል እየሆነ መጥቷል። ሰዎች ከሥልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥም ሆነ ከሥልጣን ኮርቻ አስፈንጥሮ ለመጣል እውነቱን በሃሰት ቀይሮ እንደዘመናዊ የውጊያ ስልት መሳሪያ አድርጎ ሲጠቀምበትም መታየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው። የሀሰት ምስክር ቀርቦበት ሞት የተፈረደበትን፤ ከርቸሌ የወረደውን፤ የተደበደበውን፤ የተንገላታውን፤ መልካም ስሙ የጎደፈውን፤ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለለውን፤ ከማእረግ፤ ከሽልማት የታገደውን፤ ረዳት አጥቶ አልቅሶ የቀረውን ሰው ቤቱ ይቁጠረው! በማለት ብቻ ምንም እንዳልተፈጠረ የራሳችንም ሆነ የአካባቢያችንን ሁኔታ ላለመልከት የኅሊናችንን በር መዝጋት እንዴት ይቻለናል? ይልቅስ ለመናገር እንድፈር።
በዚህች ምድር ላይ የሀሰት መንገስ ጉዳይ በሥጋውያን ሰዎች ዘንድ አሳዛኝ መሆኑ ባይካድም አስተሳሰባቸው በሥጋዊ ደማዊ ኅሊና ላይ የሚመሠረት በመሆኑ ሀሰትን እንደመሳሪያ መጠቀማቸው ላይደንቅ ይችላል። አሳፋሪውና አሸማቃቂው ነገር እግዚአብሔርን እናውቃለን፤ የጽድቅ ልጆች ነን በማለት ዘወትር ስለቃሉ በመናገር ላይ ያለነው የእምነት ሰዎች ዘንድ እውነትን በሀሰት ተክተን እንደዘወትር ጸሎት በልባችን ላይ ጽፈን መያዛችንና ጠቃሚ መስሎ በታየን ጊዜና ቦታ ለዓላማችን ማስፈጸሚያ አገልግሎት ላይ ማዋላችን ነው። የሚዋሹ የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ጊዜ እውነትን እውነት በምትመስልና ወደእውነት በተጠጋጋች ውበት የሚፈጽሟት ስለሆነ የዋሹ መስሎ አይሰማቸውም ወይም ውሸት መስሎ በተሰማቸው ጊዜ የኅሊናቸውን ቆሻሻ ለማጠብ ትንሽ ናት በምትል ምላሽ ውስጣቸውን አረጋግተው ከመንፈሳዊ ሰውነታቸው ምንም እንዳልጎደለ ራሳቸውን በራሳቸው አሳምነው ያንኑ መደበኛ ውሸታቸውን በተለመደው ጥበብ ይቀጥላሉ።
አንዳንዶቹም መዋሸታቸውን ቢያውቁም ምንም አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረና ነባራዊ ክስተት አድርገው በመቁጠር ባገኙት ቦታ ሁሉ የአዞ እንባ እያነቡ፤ ለሃይማኖታቸው የሚውል እስከሆነ ድረስ ይህንኑ በዘመናዊ ውሸት አንዳንዴም ባስ ሲል ዘመነኞቹ «ቀደዳ »የሚሉትን ዓይነት ውሸት የዕለት ሕይወታቸው አድርገው ይዘውት ይታያሉ። ለምሳሌ«ኬንያ ውስጥ አንድ ግለሰብ ባንድ ጊዜ አንድ በርሜል ውሃ ጭልጥ አደረገ የሚልና ጃፓን ከምድር እስከሰማይ የሚደርስ እስክሪብቶ ገበያ ላይ አዋለች» የሚል የውሸትና የቀደዳ ንጽጽሮች ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ የሃይማኖት ሰዎች የሚባሉት ይህንኑ የንጽጽር ተግባር ዘወትር ሲፈጽሙት ይታያሉ። ግን ሰዎች እውነትን እንዳይናገሩና ውሸትን ሥራቸው እንዲያደርጉ ያስገደደ ማነው?
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

Saturday, October 29, 2011

«ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ እንዲሁ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም»ኢዮ7፤9



የትኛውም ሃይማኖት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ (theoretically) ከሚያመልከው አምላክ ሕግና ትእዛዝ ከወጣ ቁጣና ቅጣት እንደሚጠብቀው የወል የእምነት ስምምነት አለ። ይህንኑ ቅጣት አስቀድሞ ለመከላከል በሕይወታቸው ሳሉ ያደርጉ ዘንድ የሰጣቸውን መመሪያ በሚችሉት አቅም ሁሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለታቸውም አይቀሬ ይሆናል። እንደዚያም ሆኖ ከሞተ በኋላ መልካሙ ሥራው መልካም ዋጋው ሆኖ ስለመከፈሉ ወይም ቁጣን ስለመቀበሉ ማረጋገጥ አይችሉምና ከአጠገባቸው ለተለየው ሟች በመሪር ልቅሶና በልዩ ልዩ ዓይነት የሥርዓት አቀባበር ሰውዬውን በመንከባከብ እንዲሁም በማሰማመር የልባቸውን ስሜት በጥሩ መንፈስ ለመሙላት ይጥራሉ። ምግብና መጠጥ፤ ማብሰያ ቁሳቁስና አልባሳትን ጭምር እዚያ በጉድጓዱ ከተማ እንዳይቸገር አብረው በመቅበር የችግሩ ልባዊ ተካፋዮች ለመሆን ሁሉን ያደርጉለታል። ጉድጓዱን ጥልቅ በማድረግ፤ ወደ ጎን ልዩ የኪስ ጉድጓድ በማዘጋጀት፤ የሬሳውን የማረፊያ አቅጣጫ ወደምሥራቅ፣ ወደምዕራብ ወይም በቁመት በመቅበርም ዘላለማዊ እረፍት ያገኝ ዘንድም ይደክሙለታል። አንዳንዶችም ሬሳውን ዛፍ ላይ በመስቀል ወይም በእሳት በማቃጠል ከአምላኩ እንዲታረቅ ይጥሩለታል። ይህንና ይህንን የመሳሰለውን ሁሉ ማድረጋቸው ሰውየው ዘላለማዊ እረፍትን እንዲያገኝ ከሚያመለከው አምላክ እንዲታረቅና ማድረግ ያለባቸውን ባለማድረጋቸው የሟች ነፍስ እንዳትከሳቸው ከመፍራት የተነሳ ነውጽሁፉን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

Thursday, October 27, 2011

ማኅበረ ቅዱሳን ....




ይህ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው ድርጅት ከብዙዎች ጋር እየተላተመ ነው። ይህንን መላተም ሚዲያዎች ሁሉ እያራገቡት ይገኛሉ። ነገሩ ምን ይሆን? እንዲያው ባጋጣሚ እየሆነ ያለ አይመስልም። «ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ» እንዲሉ የማይገባበትና ቤተክርስቲያኗን ከጥቃት ለመከላከል በዚህ ዘመን ከሰማይ የወረድኩ እኔ ነኝ እያለ ነው ብለው ያሙታል። ጳጳሳቱ ተኝተዋል፤ ሰባክያኑም ጰንጥጠዋል፤ ተሃዳስያኑም በርክተዋል እያለም ይናገራል ሲሉ ብዙዎቹ ያወሩበታል። ጳጳሳቱ ከተኙ መንፈስ ቅዱስ እየመራቸው አይደለም ማለት ይሆን? ሰባክያኑ ከጰንጤቆስጤ ጎራ ከተቀላቀሉ እሱ ከየትኛው መንፈስ ጋር መሆኑ ነው? መታደስን የሕይወታቸው መመሪያ የሚደርጉ ከበዙ ታዲያ እሱ(ማኅበረ ቅዱሳን) ከምኑ ላይ ነው የቆመው? ለማንኛውም እንዲወገዙና እንዲረገሙ የጠየቀበትን አቤቱታ ለማወቅ እስኪ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡለት።
(ጽሁፉን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)