Showing posts with label ስብከት. Show all posts
Showing posts with label ስብከት. Show all posts

Friday, November 18, 2011

ቅዱሳን መላእክት ትእዛዝ ይጠብቃሉ!


መልአክ የሚለውን ለማየት የግስ ዘሮቹን መመልከት ይጠቅማል። ይህንን በተመለከተ ዓይናማው የቤተክርስቲያን ሊቅ የነበሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(በማቅ ተሃድሶ ተብለዋል) «መጽሐፈ፡ሰዋስው፡ወግስ፡ወመዝገበ፡ቃላት፡ሐዲስ» በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 549 ላይ እንዲህ ሲሉ አትተዋል። ልኢክ፤ ልኢኮት(ለአከ፤ይልእክ) መላክ፤መስደድ ማለት ሲሆን ባለቤቱን ሲያመልክት ለአኪ ማለት ላኪ፤ ሰዳጅ ማለት ነው። መልአክ ማለት በቁሙ ሹመኛ፣ አለቃ ሲሆን በረቂቃን ፍጥረታት አጠራር ደግሞ በእለተ እሁድ ተፈጥረዋል የሚባሉትን የእግዚአብሔር መላእክቶችን ስም ይወክላል። ከዚህ የትርጉም ጽንሰ ሃሳብ የምንረዳው መላእክት ማለት የሚላኩ፣ የሚታዘዙ ፍጥረታት ሲሆኑ ላኪያቸው ወይም ሰዳጃቸው የፈጠራቸው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። በእለተ እሁድ ተፈጥረዋል የተባሉት መላእክት ማለት እንግዲህ የወደቁትንም መላእክት ጨምሮ ነው። የወደቁት መላእክት ላኪያቸውንና ሰዳጃቸውን ለመታዘዝ ባለመፈለጋቸው ከእግዚአብሔር ቅዱሳን የመባል ሀገር ወጥተው በጭለማ ሀገርና አሰራር ወዲያና ወዲህ እያሉ የሚኖሩ መላእክት ሆነዋል። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ትእዛዝ ሲደርሳቸው በጌታ ሲላኩ እናያለን። «ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ» የሐዋ 12፣11 ጴጥሮስን ሄዶ እንዲያድን የላከው ጌታ ነው። መልአኩ የተላከውም ጴጥሮስን እንዲያድን ነው። ቅዱሳን መላእክት እንደስማቸው ለሚገዙለት ጌታ ይላካሉ። አድኑ የተባሉትን ያድናሉ። እንዲሁም በመጨረሻው ዘመንም ቅዱሳኑ መላእክት ይላካሉ። «በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል» ማር13፣27 በሌላ ስፍራም እንዲህ የሚል አለ፤ «በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ»ዘጸ23፣20
እንግዲህ ቅዱሳኑ መላእክት ከምስጋና ከተማቸው፤ ሊታዘዙና ሊገዙለት ከወደዱበት የአምላካቸው ቃል (ልኢክ፣ልኢኮት) ሲደርሳቸው ብቻ ይወጣሉ እንጂ እንደወደቁት መላእክት በገዛ ፈቃዳቸው ወዲያና ወዲህ አይዞሩም፤አይሄዱም።
የወደቁት መላእክት ግን የሚከሱትንና የሚወነጅሉትን ሲፈልጉ፣ ሲያሳስቱ በገዛ ፈቃዳቸው ሲዞሩ ይኖራሉ። ሲዞሩ ነበር፣ ማሸነፍ ያልቻሉትን የእግዚአብሔር ሰው ኢዮብን መልካም ስራ አይተው የቀኑበትና ክስ ያቀረቡበት። «እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ»ኢዮብ 1፣7 እንግዲህ ራሱ ሰይጣን እንደተናገረው ዟሪና ምድርን ለክፋት ስራው የሚያስሳት፣ በራሱ ፈቃድ የሚመላለስ ሲሆን ቅዱሳኑ መላእክት ግን ስራቸው ፈጣሪያቸውን ማመስገን«...ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም» ራእይ4፣8 እንዳለው ምስጋና መስጠት ነው። መልእክት ሲደርሳቸው ደግሞ በመላእክት አለቃ ሚካኤል በኩል (1ኛ ተሰ4፣16 እና በይሁዳ መልእክት 1፣9) እንደተመለከተው ትእዛዙ ተፈጻሚ ይሆናል።
እንግዲህ ይህ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ነው። ቅዱሳኑ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ሲኖር ሰዎችን ያድናሉ፤ይረዳሉ፤ይታደጋሉ፤ይነግራሉ፤ ያስተምራሉ፣ በቅዱሳንና ንስሃ በሚገቡ ሰዎችም ይደሰታሉ። ያለእግዚአብሔር ትእዛዝ ግን የትም አይሄዱም፤ አይዞሩም። ይህንን የሚያደርግ ሰይጣን ብቻ ነው። ራሱ ምድርን አሰስኳት፣ዞርኩባት እንዳለው በኢዮብ 1፣7 ላይ። ምክንያቱም ከአገዛዙ ውጭ ለመሆን ባይችልም ከአገልግሎቱ ቁጥጥር ውጭ ያለው እሱ ስለሆነ ነው። በዚህ ዓለም እንኳን ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጭ በመጥፎ ስነምግባሩ የተባረረ ልጅ ውሎና አደሩ እንደልቡ ሲሆን በስርዓት ያደገው ግን ቤተሰቡ ከሚያሰማራውና ከፈቀደለት ወይም ከሚገባው ቦታ ውጭ አይዞርም።
በመጨረሻም ሊሰመርበት የሚገባው ነገር እኛ የሰው ልጆች የትኛውንም መልዓክ ስለጠራነው ወይም ስለጨቀጨቅነው በምንፈልግበት ቦታ ሁሉ ስሙ ስለተጠራ አይመጣም። ለተልእኮ የተፋጠኑ ተላኪዎች እንጂ ከቁጥጥር ውጭ የወጡ ዟሪዎች አይደሉምና ነው። ምናልባት ዟሪውና ምድርን የሚያስሰው የክፉ መልአክ «የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና»2ኛ ቆሮ 11፣14 እንዳለው እኔ ሚካኤል ነኝ፤ እኔ ገብርኤል ነኝ ብሎ ሊመጣ ይችላል። ቅዱሳኑ መላእክት ግን ለሰዎች የሚደርሱት ጸሎታችን ወይም ጥያቄያችን ወይም ለቅሶአችንና ሀዘናችን በእግዚአብሔር ዘንድ ሲሰማና ምላሽ የሚሰጠን ሲሆንና ሲላኩ ይመጣሉ። ጸሎታችንና መልካም ስራችን በእግዚአብሔር ዘንድ ሲወደድ እንኳን ቅዱሳን መላእክት ቅዱሳን ሰዎችም ሊላኩልን ይችላሉ። ልክ ለቆርኔሌዎስ ጴጥሮስ እንደተላከለት ማለት ነው። «ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ»የሐዋ10፣31 እንዳለውና ጴጥሮስ እንደተላከለት ማለት ነው።
ከዚህ ውጭ ቅዱሳን መላእክትን ስንጠራ ከተፍ ይላሉ ማለት ስለቅዱሳን መላእክት ተፈጥሮና ተግባር ያለማወቅ ብቻ ሳይሆን ከተፍ የሚለው ብርሃንን የሚመስለውን ከተፎ ዟሪ ማንነት ያለመረዳትም ጭምር መሆኑ ያሳዝናል። ቅዱሳን መላእክት እኛ ለእግዚአብሔር በምናቀርበው ጸሎትና ልመና ከእግዚአብሔር ቃል በሚወጣ ትእዛዝ ብቻ ለዚያውም እኛ ይህኛው ጠንካራ ነው፤ ያኛው ሰይፍ አለው፤ያኛው ደግሞ ቁጡ ነው፣ይህኛው ርኅሩኅ ነው ብለን ስለመረጥን ሳይሆን እኛ የማናውቃቸው ከእልፍ አእላፍ መላእክቱ መካከል ለተልእኰ የተዘጋጁትን እሱ የፈቀደውን ይልካል። ያኔም ይራዱናል፤ያግዙናል፤ የታዘዙትን ሁሉ ለእኛ በደስታ ይፈጽሙልናል። ከዚህ ውጭ ግን ቁጡ ወይም ርኅሩኅ ወይም ዓለምን በእጁ ሊገለብጣት ነበር፤ የወረወረው ጦር እስከምጽዓት ይወርዳል ወዘተ የሚሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ድምጾች ቅዱሳን መላእክትን ከሚያውቁ ሰዎች የሚወጡ ድምጾች አይደሉም። ይልቁኑም ከዚያ ከተፍ ከሚልና የብርሃንን መልአክ ሊመስል ራሱን ከሚለውጠው ዟሪ የሚወጣ መሆን አለበት። ምክንያቱም ስማቸው ስለተጠራ የሚመጡ ወይም ስላልተጠራ የሚቀሩ ቅዱሳን መላእክት የሉምና ነው። እነሱ እንደሰይጣን ያለትእዛዝ ወዲያና ወዲህ አይዞሩም። የቅዱሳን መላእክትን ተልእኰና ተግባር የሚያውቅ ልቡናን ከላይ ይስጠን።አሜን።(በዚህ ርእስ ላይ በሰፊው እንመለስበታለን)

Wednesday, November 16, 2011

በትዳር መካከል ያለውን ችግር መፍታት



ባልና ሚስት ፍጹማን ባለመሆናቸው በዚህ ምድር ባሉበት ጊዜ በግልም ይሁን በጋራ ስህተት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ማሰብ አያዳግትም።ባለትዳሮች ሁሉ በሆነ ወቅትና ሁኔታ ውስጥ ይሳሳታሉ። መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ስህተት የማይሰሩ ባልና ሚስት የሉም። የአንዳንዶች በሰዎች ዘንድ ሲታወቅ የአንዳንዶች ደግሞ ሳይገለጥ ሊቀር ይጥላል።የአንዳንዶች ብዙ ኪሳራ የማያስከትል ሲሆን የአንዳንዶች ደግሞ ከእነርሱም አልፎ ትውልድን የሚጎዳ አሉታዊ ውጤት ያለው ይሆናል። ይህ ጽሑፍም መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርጎ ይመለከታልና መልካም ንባብ ለባለትዳሮችና ትዳር ለመያዝ ላሰቡ ሁሉ!!

ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Wednesday, November 9, 2011

ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ!



ሮሜ 13፣7 «ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ»

ክብር ለአንድ ነገር ዋጋ መስጠትን ይመለክታል። ዋጋው ደግሞ በዓይነት፣በገንዘብ፣በጉልበትና
በሃሳብ ወይም በመንፈስ ሊገለጥ ይችላል። የሰው ልጅ በሕይወቱ ዘመን ይህንን ዋጋ ሲከፍል ኖሯል፤ ይኖራልም። ሰው ለፈጣሪውና ለሚያመልከው፤ ለሚበልጠው፤ ለሚወደው፤ ለሚፈራው፤ ለሚመራው ክብርን ይሰጣል። ምናልባት የሚሰጥበት መንገድና የሚሰጥበት ምክንያት ይለያይ እንደሆነ እንጂ ክብርን ስለመስጠት ሃሳብ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ እንዳልሆነ እንስማማለን።

ሰው ፈጣሪው ስላደረገለትና ስለሚያደርግለት ነገር ሁሉ ክብርንና ምሥጋናን ይሰጣል። ክብርን የሚሰጠው ስለተደረገለት ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆኑ ክብር ስለሚገባውም ጭምር ነው።

ነቢዩ ሙሴና ሕዝቡ እግዚአብሔር ከጠላት እንዳዳናቸው ደስታቸውን በዝማሬ ገልጠው ክብር ሰጥተውታል።

«በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ» ዘጸ ፲፭፣፩

ክብሩ ከፍ ከፍ ያለ፣ ኃይልና ሥልጣን በእጁ የሚገኝ፣ ማድረግ የሚፈልገውን ከማድረግ የሚከለክለው ለሌለ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተገቢውን ክብር ሲሰጡ እናያለን። ስለተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን ክብሩ ፍጹማዊ በመሆኑ ለመለኰታዊነቱ ተገቢ ክብር እንደሆነም ሌላ ሥፍራም እንደዚሁ ምሥጋና ሲሰጡ እናገኛቸዋለን።

«በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ» ዘጸ ፳፬፣፲፯

ክብሩ ታላቅና ሰው ሊቀርበው የማይችል መለኮታዊ እሳት ስለሆነ ክብርና ምስጋና የተገባው ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር በቦታና በሥፍራ አይወሰንም፣ መለኮታዊ አገዛዙ ሁሉን የመላ ስለሆነም ጭምር ክብር ይገባዋል። ሁሉን በሙላት መሸፈን የሚችል ያለእሱ ማንም የለምና።

Saturday, October 29, 2011

«ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ እንዲሁ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም»ኢዮ7፤9



የትኛውም ሃይማኖት በንድፈ ሃሳብ ደረጃ (theoretically) ከሚያመልከው አምላክ ሕግና ትእዛዝ ከወጣ ቁጣና ቅጣት እንደሚጠብቀው የወል የእምነት ስምምነት አለ። ይህንኑ ቅጣት አስቀድሞ ለመከላከል በሕይወታቸው ሳሉ ያደርጉ ዘንድ የሰጣቸውን መመሪያ በሚችሉት አቅም ሁሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ማለታቸውም አይቀሬ ይሆናል። እንደዚያም ሆኖ ከሞተ በኋላ መልካሙ ሥራው መልካም ዋጋው ሆኖ ስለመከፈሉ ወይም ቁጣን ስለመቀበሉ ማረጋገጥ አይችሉምና ከአጠገባቸው ለተለየው ሟች በመሪር ልቅሶና በልዩ ልዩ ዓይነት የሥርዓት አቀባበር ሰውዬውን በመንከባከብ እንዲሁም በማሰማመር የልባቸውን ስሜት በጥሩ መንፈስ ለመሙላት ይጥራሉ። ምግብና መጠጥ፤ ማብሰያ ቁሳቁስና አልባሳትን ጭምር እዚያ በጉድጓዱ ከተማ እንዳይቸገር አብረው በመቅበር የችግሩ ልባዊ ተካፋዮች ለመሆን ሁሉን ያደርጉለታል። ጉድጓዱን ጥልቅ በማድረግ፤ ወደ ጎን ልዩ የኪስ ጉድጓድ በማዘጋጀት፤ የሬሳውን የማረፊያ አቅጣጫ ወደምሥራቅ፣ ወደምዕራብ ወይም በቁመት በመቅበርም ዘላለማዊ እረፍት ያገኝ ዘንድም ይደክሙለታል። አንዳንዶችም ሬሳውን ዛፍ ላይ በመስቀል ወይም በእሳት በማቃጠል ከአምላኩ እንዲታረቅ ይጥሩለታል። ይህንና ይህንን የመሳሰለውን ሁሉ ማድረጋቸው ሰውየው ዘላለማዊ እረፍትን እንዲያገኝ ከሚያመለከው አምላክ እንዲታረቅና ማድረግ ያለባቸውን ባለማድረጋቸው የሟች ነፍስ እንዳትከሳቸው ከመፍራት የተነሳ ነውጽሁፉን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

Tuesday, October 18, 2011

የሕይወት ውሃ የት ይገኛል?



በዚህች ሰማርያ በሚባል ከተማ የምትኖር አንዲት ሴት ነበረች። በጥቂቱ በተገለጠው ታሪኳ ፭ ባሎች ነበሯት፤ ስድስተኛውም አብሯት ይኖራል። የምትኖረው በሲካር ከተማ ነው። ሲካርና ሴኬም ጎረቤታሞች ናቸውና የአምልኰ ስግደት የሚፈጽሙበት ገሪዛን የሚባል ተራራ በቅርቧ ይገኛል። ይህ ተራራ የበረከት ተራራ እንደሆነ ተነግሮ ስለነበረ ይኸው በረከት ከእርሱ እንደሚወርድ ከማሰብ ሰማርያውኑ ይሰግዱበታል። በዘዳግም ፲፩፤ ፳፱ ላይ እንዲህ የሚል ተጽፎ ይገኛልና። «....በረከቱን በገሪዛን ተራራ፤ መርገሙንም በጌባል ተራራ ታኖራለህ የሚል ቃል ስላለ በረከት ሲሹ ገሪዛን፤ መርገም ለማውረድ ጌባል ላይ ሲጸልዩ ኖረዋል። ኢዮአታምም በገሪዛን ተራራ ላይ ወጥቶ «የሴኬም ሰዎች ሆይ እግዚአብሔር እንዲሰማችሁ ስሙኝ» ሲል የተናገረውንም ይዘው እግዚአብሔር እንዲሰማቸው እነርሱም እዚሁ ተራራ ላይ ወደእግዚአብሔር ሲጮሁ ዘመናትን አልፈዋል።።( መሳ ፱፤፯) ይህች ውሃ ልትቀዳ ወደያዕቆብ የጉድጓድ ውሃ የወረደችው ሰማርያዊት ሴትም «አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ» ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች። አሁን እዚያ ለስግደት አልወረደችም፤ ይልቁንም ከአባቶቻቸው የውሃ ጉድጓድ አንዱ በሆነው ከያዕቆብ ጉድጓድ ውሃ ልትቀዳ ባዶ እንስራዋን ይዛ ነው የተጓዘችው። እዚያ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ደግሞ ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ አንድ የደከመው ሰው ለእረፍት ተቀምጧል።(ዮሐ፬፤፮) ውሃ ሊቀዳ አይደለም። ስራውንም ጨርሶ እረፍት ይሻ ዘንድ የተቀመጠ እንዳልነበር እረፍት የሌለው ሥራው ማረጋገጫችን ነው። ይልቁንም ለተጠሙ የሕይወት ውሃ ቃሉን እያጠጣ እርካታንና እረፍትን ማግኘት ላይችሉ በገሪዛን ተራራና በጌባል ላይ ሲንከራተቱ ለኖሩት እርካታን ሊሰጣቸው እንጂ! ዛሬም ውሃ እየተጠሙ የሚፈልጉ፤ ጠጥተው ያልረኩ፤ በየጓሮአቸው የሚቆፍሩ፤ ኩሬውን ለማጣራት የሚባክኑ፤ ብዙ ደረቅ ወንዝ የተሻገሩ ሰዎች አሉ። የሕይወት ውሃ የት እንዳለ ቢሰሙም እንዴት እንደሚገኝ፤ አግኝተውትም እንዴት እንደሚጠጡት የማያውቁም ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። አስፈሪው ነገር መፈለጋቸው ሳይሆን በብዙ ፍለጋ ሲባክኑ፤ በአይናቸው ሥር ያለውን የሕይወት ውሃ ተሰውሮባቸው ሳያገኙትና ጠጥተው ሳይረኩበት ሞት ባህረ ኤርትራ እንዳያሰጥማቸው ነው። የእርካታው ውኃ ከሰማይ መጥቶ ሳይጠጡትና ሳይረኩበት ሞት ማዕበል የኑሮ መርከባቸውን ሰባብሮ እስወዲያኛው ይዟቸው እንዳይሄድ ነው የሚያስጨንቀው። እስኪ ከዚህ ዓይነቱ አስፈሪ ጥማትና የሕይወት ውሃን ከማጣት ችግር የተላቀቀችውን የአንዲት ሰማርያዊት ሴት ታሪክ እንመልከትና እንደእሷው የሕይወት ወሃ ፍለጋ አቅጣጫችንን እናስተካክል።
(ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

Thursday, October 13, 2011

ምን እናድርግ?








የብዙዎቻችን ምርጫ አንድ ዓይነት አይደለም። እንደየመልካችን ይለያያል። በሥጋዊ አስተሳሰብ ልዩነት ውበት ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ሥጋ ያለነፍስ ምውት እንደሆነ ሁሉ ለነፍሳችን የምንሰጠው የልዩነት ውበት ነው አባባል ዋጋ የለሽ ይሆናል። በነፍስ ዘላለማዊነት ውስጥ ልዩነት ውበት ነው የሚባል ታሪክ የለም። በዚህ ምርጫ ላይ ዘላለማዊ ውበትን ለማግኘት የግድ ምርጫችን አንድ ዓይነት ብቻ መሆን አለበት። የምንጊዜም ምርጫችን በሥጋ ዓለም እስካለን በክርስቶስ ላይ ካልተመሠረተ በነፍስ ዘላለማዊነት ላይ ልዩነት ውበት ነው የሚባል ሥጋዊ አባባል ዋጋ የለውም። ፍላጎታችንን የሚከተል ምርጫ የህይወታችን መሠረት ላይሆን ይችላል። እምነታችንን የሚከተለው ምርጫ ግን ለዘላለማዊ ኑሮ ወሳኝ ነው። ስለሆነም ምን እናድርግ?
ማንም ሰው የእግዚአብሔርን የፍቅርና የምህረት እንዲሁም የደህንነትን ጥሪ ከተቀበለ፣ ለመዳንና ኃጢአቱ እንዲሰረይለት የሚከተሉትን እንዲያደርግ መጽሕፍ ቅዱስ ያስተምረናል::

1ኛ ንስሐ መግባት:- "ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፣ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት:- ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ? አሉአቸው:: ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ...አላቸው::" ሐዋ 2፣37-38

"እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ፣ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል..." ሐዋ 17፣30

"ኃጢአታቸሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም::" ሐዋ 3፣20


ንስሐ መግባት ማለት በመጀመሪያ ኃጢአተኝነታችንና ፍርድ እንደሚጠብቀን አውቀን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአታችን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንዲታጠብ መለመንና ከአሁን ጀምሮም በአዲስ ሕይወት እንጂ በድሮ በአጸያፊና ከእግዚአብሔር በተለየ ኑሮ ላለመኖር መቁረጥ ወይም መወሰን ነው:: ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን አዲስ ሕይወትን ለመጀመር የእኛ ውሳኔ አስፈላጊ ነው::

2ኛ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን:- ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ለሰው ልጆችም ብቸኛ የመዳን መንገድ እንደሆነ፣ ለኃጢአታችንም ሲል በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰና እንደ ሞተ እንዲሁም በሶስተኛው ቀን እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣውና በቀኙ እንዳስቀመጠው ከልብ ማመን:: በዚህ ምድር ላይ ቢሆን ወይም ከሞት በኋላ የነፍሳችን ጌታና ጠባቂ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ፣ እርሱም ከዘላለም ፍርድ ነፍሳችንን ሊያድን የሚችል ብቸኛ አዳኝ እንደሆነ ማመን::


Sunday, October 9, 2011

የደም መስዋእት






እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሊያደርግላቸው ከሚፈልገው ነገሮች ሁሉ ዋናውና ትልቁ ነገር ኃጢአትን ማስወገድ ነው:: ኃጢአት የሰዎች የችግራቸውና የመከራቸው ዋነኛ ሥርና ምክንያት ነውና:: የሕይወትና የበረከት ምንጭ ከሆነው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ያለያያቸውና ያጣላቸው ዋናው ነገር ኃጢአት ነው:: ኃጢአት በሰዎች ታሪክ ሁሉ የሰው ልጆች የሞትና የመከራ፣ የሃዘንና የለቅሶ ምንጭ ነው:: የሰዎችን ከእግዚአብሔር መራቅ ስለዚህም ደግሞ የሕይወት እርካታ አለማግኘታቸውና የመቅበዝበዛቸው፣ እርስ በርስ ፍቅር የማጣታቸው፣ በመጨረሻም ለዘላለም ፍርድና ስቃይ ለሲኦልም የሚያበቃቸው ዋነኛ ክፉ የሰዎች ጠላት ኃጢአት ነው::            ( የቀረውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)