Tuesday, October 15, 2013

«እስኪ በቁጣ ሳይኾን በጥሞና ነገሩን አስተውሉት!»

(ይህ ጽሁፍ በአባ ሰላማ መካነ ድር ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ ያቀረበው ሲሆን ስለማኅበረ ቅዱሳን ወቅታዊ ሁኔታ በአጭሩ ስለገለጸ ማቅረቡን ወደነዋል።)

የማኅበረ ቅዱሳንና ደጋፊዎቹ ትልቁ ችግር ይኽ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ፣ የነገረ መለኮት ዕውቀት የላቸውም፡፡ ኹለተኛ፣ ራሳቸውን የቤተክርስቲያን ወታደሮች አድርገው ይስላሉ፡፡ እነርሱ የቤተ ክርስቲያቱ ወታደሮች ናቸው የሚለውን ሐሳብ የተቀበለ ኹሉ ከእነርሱ ጋር የማይተባበር ኹሉ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው የሚለውን አቀንቅኖት መቀበሉ አይቀርለትም፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ነው! የቤተ ክርስቲያኒቱ የመከላከያ ሠራዊት ነው!” የሚለው ዐረፍተ ነገር በራሱ የጽንፈኝነት ወጥመድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ጠበቃ የምንፈልገው የተጠቂነት ፍርኀት ሲኖርብን ነውና፡፡ ምናልባት ይኽ ነገሮችን ጥቁር ወይም ነጭ ብቻ ናቸው ከሚለው ጽንፈኝነት ከሰፈነበት ባህላችን የተወለደ ይመስለኛል፡፡ አለማወቅ ላይ ፍርኀት ሲጨመርበት ጽንፈኝነት መወለዱ አይቀርም፡፡ (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን “ምስክሮቼ ናችኹ፡፡” እንጂ “ጠበቆቼ ናችኹ፡፡” አላለም፡፡)
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አላስተዋለው እንደኾነ እንጃ እንጂ የተናገረው ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን ጽንፈኝነት በደንብ ያሳያል፡፡ ማኅበሩንም በመንግሥት በደንብ ሊያስመታው ይችላል፡፡ እኛ የምንለውን የማይሉ፣ በእኛ ቅኝት ያላቀነቀኑ ኹሉ የቤተ ክርስቲያኒቷን ህልውና ለማጥፋት የሚታገሉ ናቸው ከማለት በላይ ጽንፈኝነት አለን? ዳንኤል ይኽን በማለቱ የማኅበሩን እውነተኛ ማንነት ዐደባባይ አውጥቶታል፡፡ ጽንፈኛ ደግሞ ከራሱ ውጪ ማንንም ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም፡፡


የሰለፊዎችና የማኅበረ ቅዱሳን አንዱ የጋራ ነጥብ ይኽ ነው- ከእነርሱ ውጪ ማንም ትክክል አይመስላቸውም፡፡ ከራሳቸውና ከደጋፊዎቻቸው ድምፅ ውጪ ማንንም ማድመጥ አይፈልጉም፡፡ እነርሱም ኾነ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ (ብዙዎቹን እንዳየኹት) ከፍተኛ የኾነ የነገረ መለኮት ዕውቀት እጥረት ያለባቸው ናቸው፡፡ እነርሱ ከሚያውቁት የተለየ ሐሳብ የሚያነሣ ሰው ሞቱ በደጁ ነው፡፡ በጥይት ባይገድሉት እንኳ ስሙን በማጥፋት ማኅበራዊ ሕይወቱን ይገድሉበታል፡፡ ከሀገር ያሰድዱታል፡፡ ተሰድዶም ግን ዕረፍት አይሰጡትም፡፡ ለምሳሌ፣ እነ አባ ወልደ ትንሣኤን፣ እነ ቀሲስ መላኩን፣ ወዘተ. ማየት በቂ ይመስለኛል፡፡ እነ አቡነ መርሐ ክርስቶስን፣ ዓለማየኹ ሞገስን፣ ዐፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና አቡነ ጳውሎስን፣ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴን ጭምር መናፍቅ ብሎ ስም ለመለጠፍ የደፈረ ማኅበር ነው- ማኅበረ ቅዱሳን፡፡ ሲኖዶሱን ሳይቀር እጁን እየጠመዘዘ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ያስወገዘ ማኅበር ነው፡፡ ይኽንን ማየት ከፈለግን፣ በ2002 ዓ.ም. ሲኖዶሱ አወገዛቸው የተባሉት ሰዎች ስም ዝርዝር ያለበትን ዶሴ፣ የሊቃውንት ጉባኤ የሚባለው የፈረመበትን ዶሴና ማኅበሩ ሰዎቹን የከሰሰበትን ዶሴ ማነጻጸር ይበቃል፡፡ የሚሌኒየሙ መጽሐፍ ቅዱስ በሚባለው ውስጥ ከአበው ትምህርት ውጪ በኾነ መልኩ ያልተጻፈው ነገር ተተርጉሞ እንዲቀርብ የተደረገውም የማኅበረ ቅዱሳን አለማወቅ ቤተክርስቲያኒቱ ላይ ባሳረፈባት ተጽዕኖ ይመስለኛል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከየይሖዋ ምስክሮች ቀጥሎ እንዲኽ የተበረዘ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያዘጋጀች የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የኢኦተቤ ሳትኾን አትቀርም፡፡ የሚያሳዝነው፣ ዕውቀት የሌለውን ሰው ዕውቀት የሌለው ሰው ሲመራው መጨረሻው አለማማሩ ነው፡፡
እስልምና ዐለም ኹሉ ሊገዛበት ይገባል ብሎ የሚያምንበት የሸሪዐ ሕግ ሰዎችን በእኩልነት አያይም፡፡ በሸሪዐ ሕግ ፊት ሰዎች ኹሉ እኩል አይደሉም፡፡ ሙስሊሞች (በተለይ ደግሞ ሙስሊም ወንዶች) ከኹሉ በላይ ናቸው፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ያልተጻፈ ሕግ (de facto) ፊትም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ኹሉ እኩል አይደሉም፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ደጋፊዎች ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ኹሉ የበላይ ናቸው፤ በኼዱበት ቦታ ኹሉም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ ሊያገኙና ቤተ ክርስቲያኒቱን በቅኝታቸው ሊያስዘፍኗት ይገባል የሚል አመለካከት ያለው ይመስላል፡፡
ኹለተኛ፣ ሰለፊዎች በሚያቀነቅኑት የሸሪዐ ሕግ መሠረት በዐለም ላይ ሊኖሩ የሚገባቸው ሰዎች እነርሱ፣ እነርሱን የሚደግፉና እነርሱን ባይደግፉም አንገታቸውን ደፍተው ለእነርሱ የሚገብሩ ናቸው፡፡ የዳንኤል ክብረት አባባል እንደሚጠቁመውም ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው የማኅበሩ አባላት፣ ደጋፊዎችና ባይደግፉም አንገታቸውን አቀርቅረው የሚኖሩ በገዛ አባታቸው ቤት ኹለተኛ ዜጎች ኾነው የሚኖሩ ሰዎችን ነው ብል የምሳሳት አይመስለኝም፡፡ ከማኅበሩ ቁጥጥርና ዕውቀት ውጪ የኾነ አንዳችም እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ሲኖር ማኅበሩ በጣም ይፈራል፡፡ ይኽንን ዲ.ን ዳንኤል ክብረት ራሱ ለደጀ ሰላም በጻፋት ታሪካዊ ደብዳቤ በአንድ ወቅት ጠቆም አድርጎን ነበር፡፡ ጥቂት እናስታውስ እሰኪ፡-
ይህ የፍርሃት ድባብ ደግሞ «ቤተ ክርስቲያናችን አንዳች ትሆናለች» ከሚል የመጣ ሳይሆን «ማኅበራችን ይፈርሳል» ከሚል የሚመነጭ ነው፡፡ አመራሩ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን የተመሠረተ መሆኑን ዘንግቶታል፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያን ለማኅበሩ ወደሚል አመለካከትም ዞሯል፡፡ ይህ ፍርሃት ማኅበሩ የሚጠበቅበትን ከመሥ ራት ይልቅ ራሱን ለመከላከል ከፍተኛ ወጭ እንዲያወጣ አድርጎታል፡፡ ቤተ ክህነቱ ቢበላሽ፣ ቤተ ክርስቲያን ብትጠፋ፣ ችግሮች እየተባባሱ ቢመጡ እርሱን እስካልነካው ድረስ ዝምታን ይመርጣል፡፡ ዲያቆን በጋሻው ማስተማር የጀመረው መቼ ነው) ማኅበሩ በነዲያቆን በጋሻው ላይ ሃሳብ ዛሬ መሠንዘር ለምን ጀመረ) በጋሻው ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው ብሎ ስላሰበ አይደለም፡፡ በጋሻው ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ስለ ተናገረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም ያልተናገረው ማኅበር ስሙ ሲነሣ ቤተ ክርስቲያን ተነካች ብሎ ተነሣ፡፡ ማኅበሩ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝ የጀመረው መቼ ነው) «እር ሳቸው ማኅበሩን ሊያፈርሱ ነው» ብሎ መሥጋት ከጀመረ በኋላ፡፡ አባ ሠረቀንም ቢሆ ንኮ ዛሬ ዛሬ በእምነት ችግር ይከሳቸዋል እንጂ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው ዋናው ችግሩ ማኅበሩ መነካቱ ነው፡፡ አባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳንን ሳይነኩ የፈለጉትን ቢሆኑ ኖሮ አይናገራቸውም ነበር፡፡ ባለፈው ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ችግር ሲፈጠር፣ ዝምታን መርጦ የነበረው አመራር የመንግሥት አካላት ከቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ስለ ማኅበሩ ሲያወያዩት ግን አገር ይያዝልኝ አለ፡፡ የአዋሳ ምእመናንን ችግር በዝምታ ያለፈው አመራር አባ ሠረቀ አንዳች ነገር ተናገሩ ብሎ ድምፁን አሰምቶ ተናገረ፡፡ እነዚህ እና መሰል ሁኔታ ዎች አመራሩ የሚቆረቁረው ማኅበሩ ሲነካ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትነካ አለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ካረን አርምስተሮንግ (Karen Armstrong) የምትባል ጸሐፊት “Battle for God” በተሰኘ መጽሐፏ የአክራሪነት ምንጩ ፍርኀት ነው ትላለች፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም በኼደበት ኹሉ የሚያቀነቅነው ይኽንኑ “እነ እገሌ ሊያጠፉን ነው!”፣ “አውሮጳውያን ቅዱሱን ባህላችንን ሊበርዙብን ነው፡፡”፣ “የምዕራባውያን ተላላኪዎች የኾኑት መናፍቃን ኢትዮጵያን ለቅኝ ግዛት አሳልፈው ሊሰጡን ነው፡፡”፣ ወዘተ. ነው፡፡ እስኪ በቁጣ ሳይኾን በጥሞና ነገሩን አስተውሉትና ማኅበረ ቅዱሳን እውነት ጽንፈኛ ማኅበር አለመኾኑን አስረዱኝ፡፡ ከተሳሳትኹ እታረማለኹ፡፡