Friday, October 20, 2017

"ማኅበረ ቅዱሳን ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ብራዘርሁድ"



ማኅበረ ቅዱሳንን ከግብፁ ሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር የሚያመሳስለው ተግባራትና ሂደቶች!

ሙስሊም ብራዘር ሁድ ወይም የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር የተባለው ድርጅት በ1928 ዓ/ም በግብጽ ተመሠረተ። ከሰማንያ ዐመታት በኋላ በጄኔራል አልሲሲ መንግሥት በአሸባሪነት ተፈርጆ ድምጥማጡ እስኪጠፋ ድረስ በ70 ሀገሮች ውስጥ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በዘመናዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች፤ በገበያ ማዕከላት፤ በንግድ ሱቆች፤ በማከፋፈያ ድርጅቶች፤ በሚዲያ ተቋማት ወዘተ የሀብት ማግበስበሻ መንገዶች እየተሳተፈ ክንዱን በማፈርጠም ለእንቅስቃሴው የሚጠቅመውን የገንዘብ ምንጭ ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ የግብጹ ሙስሊም ብራዘር ሁድ በዐረብ ሀገራት ውስጥ ተመሳሳይ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበራትን በማደራጀትና በማሰልጠን መንግሥታቱን ሲያስጨንቅ የቆየ ሲሆን አሁንም እያስጨነቀ ይገኛል።

የሙስሊም ብራዘር ሁድ ለተባለው ሃይማኖታዊ-ፖለቲካዊ ድርጅት ዋነኛ ተቀባይነት ማግኘት ዋናው ምክንያት የሆነው በእስላሙ ሕብረተሰብ ውስጥ ቶሎ ሰርጾ እንዲገባ የሚያካሂደው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱና  ለዚህ እምነት መክፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ከአላህ ዘንድ የሚከፈለውን ምንዳ ለመቀበል ቶሎ መሽቀዳደም ተገቢ መሆኑን አበክሮ በመስበኩ የተነሳ ነው።

1/ የሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅራዊ እንቅስቃሴ

 ሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅሩ በሀገሪቱ የመንግሥት ሲቪላዊ መዋቅር ደረጃ የተዘረጋ ነው። ይህም ከማዕከላዊ ቢሮው ተነስቶ አባል በሆኑ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ በሰንሰለት የተያያዘ ነው። ቤተሰባዊውን የአባልነት ማኅበር «ኡስራ» ይሉታል። አንድ «ኡስራ» አምስት አባላት ሲኖሩት ከአምስት በላይ ከሆነ በሁለተኛ የኡስራ ስያሜ ደረጃ ይዋቀራል። በቤተሰቡ ያሉትን ኡስራዎች የሚመራ ደግሞ የቤተሰቡ አባል የሆነ በእስልምና ሃይማኖቱ የበሰለና የብራዘር ሁድ አስተምህሮት በደንብ የገባውን ሰው የቤተሰቡ ጉባዔ ይመርጠውና «ናቂብ» ተብሎ ይሰየማል። ይህ «ናቂብ» የተባለው ሰው የቤተሰቡ አባላት በእስልምናው ደንብ ዘወትር ስለመንቀሳቀሱ ይቆጣጠረዋል፤ ያስተምረዋል፤ ይነግረዋል። ያልተመለሰውን በማኅበረሰቡ ደረጃ ለተቀመጠውና ከፍ ላለው ሃይማኖታዊ መሪ ያቀርበዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ስለእስልምናው የሚደረግ እርምጃ በመሆኑ በደስታ ከሚቀበል በስተቀር ማንም በተቃውሞ አያንገራግርም፤ ሊያንገራግርም አይችልም። ምክንያቱም ጸረ እስልምና እንደሆኑ ራሳቸውን አስገዝተዋልና። በዚህ ዓይነት አደረጃጀት የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ከላይ ወደታችና ከታች ወደላይ የተሳሰረ መዋቅር አለው።

2/   የገንዘብ ምንጮቹን ማሳደግ

ገንዘብ የዚህ ዓለም እንቅስቃሴ የደም ሥር ነው። አባላት ለመመልመል፤ እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት፤ የሽብር ተግባሩን ለመፈጸም፤ ለመደለል፤ ለመሰለል፤ ሃይማኖታዊ ዶክትሪኑን ለማስተማር  እጅግ ጠቃሚ ነገር መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳው ብራዘር ሁድ የገንዘብ አቅሙን ለሀገር ውስጥና ድንበር ዘለል ተግባሩ ያውለው ዘንድ ተግቶ ይሰራል።

የእስላም ወንድማማቾች ማኅበር ሁለት ዓይነት የገንዘብ ምንጮች አሉት። አንዱ በውጪ ሀገራት ካሉ አባላቱ በመዋጮ የሚሰበሰብ እንዲሁም ብዙ ሃብት ካላቸው የድርጅቱ ደጋፊ ሚሊየነሮች  የሚደረግለት የገንዘብ ፈሰስና በእስላማዊ መንግሥታት ስር ከተሸሸጉ ባለስልጣናት የሚዋጣለት ገንዘብ ነው።  ሁለተኛው ደግሞ በተራድዖ ስም ከውጭ የሚያሰባስበውን ገንዘብ ወደልማት ካዝና በመቀየር በአካባቢ ልማት፤ በትምህርት ቤቶችና መድራሳ ማቋቋም፤ ሥራ አጥ ህብረተሰብን በማደራጀት፤ የራስ አገዝ እንቅስቃሴን በመመሥረት የሚሳተፍ ሲሆን ለዚህም ሀገር በቀል የእርዳታ ስልት በመቀየስ መዋጮውን ቅርጹን ለውጦ ያግበሰብሳል። ይህም፤

ሀ/ ከአባልነት መዋጮና
ለ/ ከንግድ ድርጅቶቹና ከሚዲያ ተቋማቱ የሚገኝ ገቢ ነው። በዚህ አካሄዱ ማኅበረ ቅዱሳን ትክክለኛ ገፅታው የሙስሊም ብራዘርሁድ ግልባጭ ነው። በሚሊየን ብሮችን ይሰበስባል፣ ያንቀሳቅሳል።

ይህንን ገንዘብ በተለያየ የገንዘብ ማስቀመጫ ስልቶችና በብዙ የሂሳብ አካውንቶች ቋት ውስጥ በተለያየ ስም በማስቀመጥ ለሚፈልገው ዓላማ በፈለገበት ሰዓት ማንም ሳያውቅበት ያውለው ነበር።

3/ በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ሰርጎ መግባት

ብራዘር ሁድ አባላቱን ሲመለምል ነጻና ገለልተኛ የሆኑትን ብቻ አይደለም። ከሚኒስትሮች እስከፍርድ ቤቶች፤ ከመከላከያ እስከ ፖሊስ መምሪያዎች፤ ከድርጅት ሥራ አስኪያጆች እስከ አስተዳደር ኃላፊዎች ድረስ በአባልነት መልምሎ፤ አሰልጥኖና ሃይማኖታዊ ትጥቅ አስታጥቆ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር። እነዚህ የመንግሥታዊ አካላት ክፍሎች ድርጅታቸው ለሚነሳበት ተቃውሞና ኅልውናውን ፈታኝ ለሆኑ ችግሮች የግብዓት ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ። አስፈላጊ በሆነ የመረጃ፤ የፋይናንስና የአፈና ሥራው በትጋት ይሰራሉ።
ይህ ድርጅት እንደሃይማኖታዊ ተቋም አራማጅነት ተነስቶ ወደፖለቲካዊ ሥልጣን መቆናጠጥ እርምጃው ለማደግ መሠረት አድርጎ የሚነሳው የእስልምና ሃይማኖትን ነው። ይህም ብራዘር ሁድን መቃወም እስልምናን እንደመቃወም እንዲቆጠር በሕብረተሰቡ ዘንድ የኅልውናውን ስዕል በማስቀመጥ እንዳይነካ ወይም እንዳይጠፋ ረድቶታል። የእስልምናውን አስተምህሮ መነሻ በማድረጉ የማይነቃነቅ ፖለቲካዊ ግብ ለማስረጽ ያገዘው ሲሆን የዚህም መገለጫው በአልሲሲ መንግሥት ላይ በአንድ ጊዜ እስከ 33 ሚሊዮን ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በመላ ሀገሪቱ ማንቀሳቀስ የሚችል ድርጅት አድርጎታል።
 ይሁን እንጂ የጀነራል አልሲሲ መንግሥት እርምጃ ስልታዊ በመሆኑ በአንድ ቀን ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ከፍተኛና ዝቅተኛ አመራሩንና የሃይማኖታዊ ተፍሲር መምህራኖቹን ለቃቅሞ ወደማጎሪያ ካምፕ በመክተቱ ድርጅቱ በ85 ዓመት እድሜው አይቶት የማያውቀውን ውድቀት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያስተናግድ አድርጎታል። በአልሲሲ መንግሥት የተተገበረው «ወፎቹ እንዲበተኑ ቅርንጫፉን መቁረጥ» የሚለው አባባል ብቻ ሳይሆን ግንዱን መንቀል በመሆኑ የብራዘር ሁድ ዋና መሪ መሐመድ ሙርሲን ጨምሮ ከፍተኛውን የሹራ ካውንስል ሳይቀር ከስር ገርስሶታል። በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱም የሞትና የእስራት ፍርድ ተከናንበዋል። አልሲሲ በቲቪ ቀርበው "ብራዘር ሁድን ከስረ መሠረቱ ነቅለን ካላጠፋን ሰላም የለንም" በማለት ድራሹን አጥተውታል። ዛሬም ድረስ የተቃውሞ ሰልፎች ያሉ ቢሆንም በሃይማኖት ካባ ስር በተሸፈነው ድርጅት በኩል የአእምሮ አጠባ ተደርጎ የተታለለው ሕብረተሰብ እንጂ ብራዘር ሁድ እንደተቋም በግብጽ ታሪክ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል። ያ ማለት ግን ብራዘር ሁድን የሚደግፍ፤ የሚጠባበቅና እንዲያንሰራራ የሚፈልግ የለም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያዊው ሙስሉም ብራዘርሁድ ማምጣት የሚፈልገው ለውጥ በራሱ ቅኝት የሚዘወር ቤተ ክህነትና በአባላቱ ተሳትፎና ስውር እጆቹ የሚቆም አዲስ ስርአተ መንግስት ነው። ያ ካልሆነ በኦርቶዶክስ መንፈሳዊ መዋቅር ውስጥ ሳይዋጥ የራሱን ልእልና እያስጠበቀ ተከልሎ ለመቆም ባልፈለገም ነበር።

4/ማኅበረ ቅዱሳን እንደክርስቲያን ብራዘር ሁድ ስንል ምን ማለታችን ነው?

1/ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ከመንግሥትም፤ ከቤተ ክህነትም ቁጥጥር ነጻ መሆኑ
2/ የራሱን አባላት የሚመለምልና የሚያደራጅ መሆኑ
3/ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ ያለውና የንግድ ተቋማትን የሚያንቀሳቅስ መሆኑ
4/ ከአባላቱ ልዩ ልዩ መዋጮዎችና የስጦታ ገቢዎችን በመሰብሰብ በልማት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንዳለ የማሳየት ብልሃት ያለው መሆኑ
5/ በመንግሥት ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች፤ ፍርድ ቤቶች፤ ፖሊስ መምሪያዎች፤ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ስውር መዋቅር ያለው መሆኑ
6/ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላዕላይ መዋቅርና እስከ አጥቢያ ድረስ በተዘረጋው አስተዳደር የራሱ አደረጃጀት የዘረጋ መሆኑ
7/ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ውስጥ የራሱን ጳጳሳት በመመልመል ማስሾም የቻለ መሆኑ፣




በመመልመል ማስሾም የቻለ መሆኑ
9/ ከሀገር ውጭ ዓለም አቀፍ ቢሮዎችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስና አባላት ያሉት መሆኑ
10/ ከዓለም አቀፍ የገቢ ፈጠራው ውስጥ በልማት ሰበብ የሚያጋብስ መሆኑ
11/ የመረጃ፡ የስለላና የትንተና መዋቅር ያለው መሆኑ
12/ የቤተ ክርስቲያኒቱን አደረጃጀቶች ለራሱ ዓላማ የመጠቀም አቅም ያለው መሆኑ
( ሰንበት ት/ቤቶችን፤ የጥምቀት ተመላሽና የጽዋ ማኅበራትን)
14/ የግለሰቦችን ስም በማጥፋት ወይም ራሳቸውን በማጥፋት፡በማባረር፡በመደብደብ ወይም ግለታሪካቸውን ለራሱ ዓላማ ጠምዝዞ በማዋል እርምጃ መውሰድና ማስወሰድ የቻለ መሆኑ
15/ ስሙን ለማግነን፤ ክብሩን ለማስጠበቅ የሚያስችል በራሱ የሚመራ እንዲሁም በፖለቲካ የተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ደጋፊዎችና በስውር መረብ የሚንቀሳቀስ የሚዲያ ተቋም ያለው መሆኑ፤
ማኅበረ ቅዱሳንን ክርስቲያናዊ ብራዘር ሁድ እንድንለው ያስችለናል።

እስካሁንም ማንም ምላሽ ሊሰጥበት ያልቻለው ዋናው ነጥብ ማኅበረ ቅዱሳን ከመንግሥት እይታ ውጪ መሆን ባይችልም ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ክርስቲያናዊ ማኅበር መሆኑ ሲሆን እንደክርስቲያናዊ ተቋምነቱ  ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ ላይ ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ችሎታ አንዳችም አቅም የሌላት በመሆኑ ያሳዝናል:: በመንግሥትም፤ በቤተ ክህነቱም ማንም ጠያቂ የሌለው ሆኖ መቆየቱን ለማመን ያለመፈልግ ዝንባሌ መኖሩም ያስገርማል::  ማኅበሩ እንደምክንያት ሁልጊዜ የሚያቀርበው ሲኖዶስ በሰጠኝ ደንብ እመራለሁ ቢልም እውነታው ግን ብራዘር ሁድ በሆኑ ጳጳሳት አባላቱ በኩል የሚመቸውን ደንብ አስጸድቆ ያለጠያቂ በነጻነት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የገቢ አቅሙን እያሳደገ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባላት እየመለመለ፤በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁመናና መልክ የራሱን አደረጃጀት፤ መዋቅርና እንቅስቃሴ እያከናወነ ያለ ማኅበር መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው። ለምሳሌ የማኅበሩ ብራዘር ሁድ አባላት ጳጳሳቱ አባ ማቴዎስ፡አባ ቀውስጦስ፡ አባ ቄርሎስ፡ አባ ያሬድ፡አባ አብርሃም፡አባ ሳሙኤል፡ በአባ ማቴዎስ አደራዳሪነት የትግሬን መንግስት በጋራ መዋጋት በሚል ፈሊጥ ከማኅበሩ እግር ላይ ወድቀው የታረቁት አባ ፋኑኤል ተጠቃሾች ናቸው:: አባ ገብርኤል ግን ከአቶ ኢያሱነታቸው ጀምሮ የተጠጋቸው የውግዘት በሽታ  መቼም አይለቃቸውም::

5/ ለመሆኑ አሁን ያለው ማኅበረ ቅዱሳን አደረጃጀት፤  

የሰንበት ት/ቤት ስብስብ ነው? እርዳታ ድርጅት ነው? የልማት ተቋም ነው? የበጎ አድራጎት ማኅበር ነው? ራሱን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ውጪ አስደርጓል። በዋና ሥራ አስኪያጅ ሥር የሚተዳደር ነገር ግን የቤተ ክህነቱ መምሪያ ያልሆነ መምሪያ ነው?
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሥፍራው ከየት ነው? በምንስ እንመድበው? ማኅበሩ በምን ሂሳብ እንደተቋቋመና በምን አደረጃጀት ኅልውና እንዳገኘ አይታወቅም::

እስከሚገባን ድረስ እንቅስቃሴውንና ያለውን አደረጃጀት ተመልክተን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳናዊ ብራዘር ሁድ ብንለው ተግባሩ ያረጋግጣል።
በሌላ መልኩ መንግሥት በኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እንዲህ ዓይነት ማኅበር ከእስልምና ምክር ቤቱ ውጪ እንዲቋቋም ይፈቅዳል ወይ ብለን እንጠይቃለን? መልስ የሚያሻው ጥያቄ ነው።

Saturday, September 30, 2017

ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ምንድነው?



ከማኅበረ ቅዱሳን መሥራቾች አንዱ እንደሆነ የሚናገረው የሜሪላንዱ ኤፍሬም እሸቴ  ስለማቅ ጥንስስ እንደተረከው ብላቴ ጦር ካምፕ ውስጥ ተቀፍቅፈን፤ ዝዋይ ላይ በመፈልፈልና አዲስ አበባ ላይ ኅልውና አግኝተን ሕይወት ዘራን ሲል ይተርክልናል። የኅልውናቸውን መስራቾችና ፈልፋዮች ማንነት ኤፍሬም ዘለግ አድርጎ ሲገልፅ በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ በመንደር ምሥረታ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሰዎች ሲሆኑ እነሱ ባሉበት የዳቦ ስም ወጥቶላቸው «ማኅበረ ቅዱሳን» እንደተባሉ «አደባባይ» በተሰኘው መካነ ጦማሩ በአንድ ፅሁፉ አውግቶናል። ለጠቅ አድርጎ: «ተማሪው በጋምቤላ፣ በመተከል፣ በወለጋ … ጎጆ ቤት ሲሠራ፣ ተፈናቃዩን ሲያቋቁም ቆይቶ ተመለሰ። በደህና ወጥቶ ለመመለስ ያልቀናውም ነበር። እነዚያ መንደር ሊመሠርቱ የወጡት ታላላቅ ወንድሞቻችን በየዛፉ ሥር፣ በየመንገዳቸው ጸሎተ ማርያም ማድረሳቸውን፣ ሲችሉም ተገናኝተው ቃለ እግዚአብሔር መስማታቸውን እንዳላስታጎሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እኛን ቃለ እግዚአብሔር ያስተማሩን የዚያ “መንደር መሥራች ትውልድ” አካላት የሆኑ ወንድሞች ናቸው። ወደ ዝዋይም የላኩን እነርሱ ናቸው። እኛ እና እነርሱ በአንድ ላይ ስንሆን ጊዜ በጋራ “ማቅ” ተባልን» ይለናል።
  በእርግጥ የዚያን ዘመን መንደር መሥራችና ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት እነማን መሆናቸውን ባናውቅም ረጅም ህልም የነበራቸው: በእውቀትና በሥልጣን ትላልቅ ሰዎች እንደነበሩ መገመት ይቻላል። ለኤፍሬም ሆነ ለማቅ አባላት ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት የማኅበሩ ፈጣሪዎችን ረጅም ዓላማ በግልጽ ያውቁት እንዳልነበር እርግጥ ቢሆንም አብዛኛው የማኅበሩን አባላት ያሰባሰባቸው ግን እምነታቸው ስለመሆኑ ከጥርጣሬ ላይ የሚወድቅ አይደለም። ብዙዎቹን የማኅበሩ ተከታይ ያደረጋቸው የቤተ ክርስቲያናቸው ቅናት ብቻ ነበር። ሲመሰረትም የወንድሞች ማኅበር «ማኅበረ ቅዱሳን» ከዚያ ከትንሹ ጅምር ተነስቶ ይህንን ያህል በመግዘፍ ሀገራዊ ማኅበርና የሲኖዶስ ጉባዔ የየዓመቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል ብሎ የገመተ አይኖርም። ምናልባት ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት እግር በእግር እየተከታተሉና እየኮተኮቱ ያሳደጉበትን  ኅቡእ አጀንዳ ራሳቸው ያውቁ እንደሆን እንጂ ዛሬም ድረስ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው የማኅበሩ አባላት እያገለገሉ ያሉት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንደሆነ ያስባሉ።
 ነገር ግን ከአባላቱ መካከል በተለየ ተልእኮ ተመልምለው ረጅም አላማና ግቡን እንዲጨብጡ የተደረጉ አመራሮች በሂደት አልተፈጠሩም ማለት የማይቻልበት ምክንያት አንድ ተራ የፅዋ ማኅበር ከብላቴና ከዝዋይ ተነስቶና ግዝፈቱ እውን እየሆነ ሄዶ የጳጳሳቱን ጉባዔ ሲኖዶሱን ማነቃነቅና ለህልውናው ዘላቂነት እንዲቆሙ የማድረግ አቅም መጨበጥ መቻሉ ከበቂ በላይ አስረጂ ነው። ከዚህ ደረጃ ላይ  መድረሱ  እንዲደርስ የተፈለገበት ረጅም ህልምና ራእይ የለውም ማለት ጅልነት ነው። ኅልውናውን የሚያስጠብቅበትን የሕግ ማዕቀፍ በመጎናጸፍ፤ ማኅበሩን ለማሳደግ የሰው ኃይል በማደራጀት፤ የገንዘብ አቅሙን በማጎልበት፤ በአሰራር ውስጥ ጠልቆ በመግባት ራሱን የሚያስጠብቅበት ቅርጽና መዋቅር ቤተክርስቲያኒቱን መስሎና አኅሎ እየያዘ እንደመጣ እርምጃዎቹ ዋቢዎቻችን ናቸው። ዓላማና ግብ ሳይኖረው ኅልውናውን ማስጠበቅ እንደማያስፈልገው ይታወቃል።  እዚህ ይደርሳል ብለው ያልገመቱ ቢገኙም ሂደት ራሱ በሚፈጥረው ስኬት ከተነሳበት ሃሳብ ወጣ ባለ መልኩ ወደሚፈልግበት አዲስ ግብ ለመድረስ  ስትራቴጂ የለውም ማለት ሞኝነት ነው።  ታዲያ የት ሊደርስ ነው? ማኅበረ ቅዱሳን ተሰኝቶ እየደረጀ የሚሄደው?

የታላላቅ ወንድሞች ህልም ማኅበሩን ቅርፅና መልክ እየሰጡ ከትንሹ ትንሳዔው አንስቶ ያሳደጉት ስኬትን እያጎናፀፉ መድረስ ከሚፈልጉት ስውር ግብ ለማድረስ እንጂ በጽዋ ማኅበር ስር ታጥሮ እንዲቀር እንዳልነበር አሁን የደረሰበት ስኬት ያረጋግጥልናል። ዛሬ ከሲኖዶሱ ይልቅ ማኅበሩ ኃይል አለው። ከወዳጆቹ ጳጳሳት ተጠግቶ የበላቸውን እያከከ:ባልመሰላቸው ነገር ደግሞ እያስፈራራ ወይም በተአቅቦ አፋቸውን አስለጉሞ ማንም የማይደፍረውና የቤተ ክርስቲያኒቱ ያልታጠቀ ልዩ ኃይል መሆን ችሏል።
ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂቶች አስተሳሰብ በእቅድ የተመሠረተ፤ በተራው አባል ግን በአጋጣሚ እግዚአብሔር ፈቅዶ የተቋቋመ ያህል የሚታሰብ ድርጅት መሆኑን ቢታሰብም እውነታው ግን ቤተ ክርስቲያንን ራሱ መውረስ ነው። መንግሥታዊ መንበሩንም አይመኝም ማለት የዋህነት ነው። አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን ማኅበሩን እንገምግም!

1/ማኅበረ ካኅናቱ ማቅን እንዴት ያየዋል?

ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበረ ካህናቱ ዘንድ የሚታየው በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሽብልቅ የገባ ዘመን አመጣሽ የጭዋ ማኅበር: ሰላይ: ነጋዴ: ስም አጥፊና የኃጢአት ጸሐፊ ዐቃቤ መልአክ ተደርጎ ነው። ይህ የአደባባይ ምስጢር ነው።  ማኅበሩ በቀጥታ ከማኅበረ ካህናቱ ጋር መጋጨት የማይፈልገው ምእመናኑ በአጠቃላይ የተያዙት በካህናቱ አባትነት ስለሆነ. ከስልታዊ አዋጭነቱ አንፃር ጉዳት የሚያስከትልበት መሆኑን በመገምገም ሲሆን በሂደት ግን ጉልበት ለማግኘትና ማኅበረ ካህናቱን ለመናድ በህግ ማሻሻያ ሰበብ በደንብና በመመሪያ. ሽፋን በአባ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀ/ ስብከት ዘመነ ጵጵስና ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ጊዜ ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ነገ ያንኑ  በሲኖዶስ አስፀድቆ ካህናቱን ለመበታተን ዳግመኛ አይመለስም ማለት የዋህነት ይሆናል። በጥቅሉ ማኅበረ ቅዱሳንና ካህናቱ ዓይንና ናጫ ናቸው።

2/ ማኅበረ ቅዱሳንና የሰንበት ት/ ቤት ወጣቶች:

ወጣቶች ከእድሜአቸው አንፃር ነገሮችን የሚመለከቱበት መነፅር በአንድ አቅጣጫ የተወሰነ ነው። በተለይ ደግሞ ከእምነት አንፃር በሚገባቸው  ስስ ስሜት በኩል በወጣት ቋንቋ የሚነግራቸውን ቶሎ ይቀበሉታል። አሁን ባለው ሁኔታ ነጠላን በመስቀልኛ አጣፍቶ የራሱን ስብከት ለነገራቸው ማቅ ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው።  የማኅበሩ ያልታጠቀ ኃይል የሰንበት ት/ቤት ወጣት ነው። ይህንን ኃይል መያዝ ማለት በየአጥቢያው ለማኅበሩ ህልውናና ስርፀት አስፈላጊ በር ለማስከፈት ጠቃሚ መሆኑን አሳምሮ ያውቃል። በዚያ ላይ ለማኅበሩ ህልውና አደጋ የሚፈጥር የአጥቢያ አስተዳዳሪ ወይም ማኅበረ ካህናት የማስወገጂያ ጦር ሆኖ ያገለግላል። በተለይ ደግሞ ሙሰኛና ነውር የተገኘበት ከሆነ ግፋ በለው የሚል አዋጅ የሚታወጀው በሰንበት ት/ ቤት ወጣት በኩል ነው። ስለሆነም የወጣቶቹን የሰንበት ት/ቤት ኃይል መቆጣጠር ማለት አጥቢያውን መቆጣጠር ማለት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለጥምቀት በዓል አስፋልት በመጥረግ: ቄጠማ በመጎዝጎዝና ምንጣፍ በማንጠፍ መንፈሳዊ ቅናት መሰል ቅንቅን የወረሳቸውን የበጎ ፈቃድ ወጣቶችን ማኅበሩ "የጥምቀት ተመላሾች ማኅበር" በሚል ስም አዋቅሯቸው በራሱ መረብ ስር አስገብቷቸዋል። ነገር መፈለጊያ ጥቅስ በማልበስ "አንዲት ሃይማኖት: አንዲት ጥምቀት" የሚል ቲሸርት አስለብሶም በአደባባይ ጠብ ያለሽ በዳቦ ሲያሰኝም ነበር።  በሌላ በኩልም በአባልነት የያዛቸው የየአጥቢያውን ሰንበት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን "ግቢ ጉባዔ" በሚል ሽፋን ለራሱ ዓላማ ስርፀት ከሚደክምባቸው ኃይሎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ነገ በሚሰማሩበት የሥራና የሥልጣን ወንበር የማኅበሩ ወኪል የሚሆኑበትን መደላድል ዩኒቨርሲቲ ድረስ ገብቶ ይፈጥራል። ሌላው መረሳት የሌለበት ነገር ማኅበሩ የፖለቲካ ድርጅት የሆነ ያህል አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሚጠሉ ፖለቲከኞች ሁሉ እንደ አንድ አስፈላጊ አካል ሆኖ የመቆጠሩ ጉዳይ
መዘንጋት የለበትም። ለምን? ብሎ መጠየም ተገቢ ጉዳይ ነው።
እነዚህ አብሮነት ያገናኛቸው የእምነት ስምምነት ውል መኖሩ ሳይሆን የሚያቀራርባቸው ፖለቲካዊ ስልት መሆኑን ለማወቅ ብዙም ምርምር አይጠይቅም።

ማኅበሩ ከላይ ከፍተኛው የሥልጣን አካል የሆነውን ሲኖዶሱን ይዟል። ከታች አብዛኛውን የገንዘብ ምንጭና የጉልበት ኃይል የሆነውን ወጣቱን አቅፏል። በመካከል ያለው የካህናቱ ኃይል የሚደመጥበትና ማኅበሩን የሚቋቋምበት አቅም ስለሌለው አንገቱን ደፍቶ ቀርቷል።

3// ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ያበረከተው ምንድነው?

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ መቅደሱ የክህነት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ባለመሆኑ ለምዕመናኑ ከካህናቱ በተሻለ የሚሰጠው አገልግሎት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሳትሰጥ የቀረችውና ማኅበሩ ሊያሟላው የሚችለው አንዳችም ነገር የለም።
 በየአድባራቱ ወይም በየገዳማቱ ከምዕመናን አባላቱና ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ጋር ያለውን ቅርርብ በመጠቀም ዓላማና ግቡን ለማስረጽ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ከካህናቱ በኩል ያለውን  ተቃውሞ ለመከላከል ሲል ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆር በመምሰል ስም በማጥፋት፤ በአድማና በህውከት ከቦታቸው እንዲነሱ፤ እንዲጠሉ በማስደረግ ወይም ዝም ጭጭ ብለው፤ አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ በሚያደርገው ተግባሩ ያተረፈው ነገር ቢኖር የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ወደሌሎች ቤተ እምነቶች መኮብለል ብቻ ነው። በሐረር፤ በድሬዳዋ፤ በደቡብ፤ በምዕራብና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እንደጎርፍ ቤተ ክርስቲያኒቱን ትተው የኮበሉለት ማኅበረ ቅዱሳን በየቦታው በፈጠው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ ነው።

   በእርግጥ አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ባሉበት መርጋት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ቢሉም ተረትና እንቆቅልሽ ለማስተማር ካልሆነ በስተቀር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን የመተካት አንዳችም አቅም የሌለው ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ1960 ዓ/ም በፊት ከ1% በታች የነበሩት የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች እስከ 1984 ዓ/ም ድረስ 5.5% የደረሱ ሲሆን እስከ 1994 ዓ/ም ድረስ በዐሥር ዓመት ውስጥ ብቻ 10.2% ለመድረስ በቅተዋል። አሁን ባለው ስታስትስቲክ የፕሮቴስታንቱ ቁጥር ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ 18.6% ሲደርስ በተቃራኒው ደግሞ ከሀገሪቱ ሕዝብ 60% ገደማ የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት ተከታይ የነበረው ቁጥር በአስደንጋጭ መጠን ወደ 43.5% ያሽቆለቆለው ባለፉት ዐሥርተ አመታት ውስጥ መሆኑ የሚያሳየን ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን የስብከትና እንቅስቃሴ ምዕመናኑን ከመበተን ይልቅ በቤታቸው የማቆየት አቅም እንዳልነበረው አረጋጋጭ ነው። ውግዘትና ሁከት እንደውጤት ከተቆጠረ ማቅ በተገቢው ሰርቷል።   አንዳንዶች እንደሚያስወሩት ሰዎች ከነባር ቤተ እምነታቸው የኮበለሉት በስንዴና በአቡጀዲ ተገዝተው ሳይሆን መሬት ያለው እውነታ የሚነግረን ጊዜውን የሚመጥን አስተዳደርና ዘመኑን የሚዋጅ የወንጌል ቃል ትምህርት ስለሌለ ብቻ ነው። ለመሆኑ "ድንጋይ ዳቦ ነበረ" ከሚል ስብከት ያልተላቀቀው ማቅ ሁከትና ብጥብጥ ጨምሮበት ማን ባለበት ቆሞ ሕይወቱን በከንቱ ይገብራል?
ወደፕሮቴስታንቱ ጎራ ከኮበለለው 17% ገደማ የሚሆነው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወጣ እንጂ በዳንጎቴ ፋብሪካ የተመረተ የሰው ሲሚንቶ አይደለም። ማቅ እንኳን ከሌላ ቤተ እምነት ሰብኮና አሳምኖ ሊያመጣ ይቅርና ያሉት ተረጋግተው እንዳይኖሩ ሲሰራ የቆየ መሆኑ አይታበልም። የማኅበረ ቅዱሳን የተረትና እንቆቅልሽ አስተምህሮ ማንንም ሰብኮ መመለስ አይችልም።  ለጠያቂ ትውልድ የሚመጥን መልስ ሳይኖር ስመ ተሐድሶን መለጠፍና የስንዴ ሃይማኖት በማለት ማጣጣል ኩብለላውን ማስቆም አይቻልም። "አንድ ሳር ቢመዘዝ"  በሚል የሞኝ ተረት እያቅራሩ መኮፈስ የትም አያደርስም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሥግው ቃል የሆነበት ምስጢር አንድ ሰው ፍለጋ ነው። ማቅና ደጋፊ ጳጳሳቱ ከአፋቸው የማይጠፋው ነገር በሰው ቁጥር መመካታቸው ቢሆንም ሳሩ ተመዞ ተመዞ እያለቀ መሆኑን አላቆመም።  ማኅበረ ቅዱሳን ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ከተጠቀመችው ይልቅ ማኅበሩ በየቦታው በሚፈጥረው ሁከትና ግርግር የተጎዳችበት ይልቃል።
4// ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያበረከተው አገልግሎት እውነት እንደሚወራው ነው?

ሲጀመር ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን የካዝና ቋቱንና ኪሱን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አያሳይም። በሞዴላ ሞዴል ተጠቀም! ሂሳብህን አስመርምር! በምትሰራው ነገር ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ጠይቅ! መባሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የመሆኑ ማረጋገጫ  ካልሆነ በስተቀር ሀብትና ንብረቱን ስለመውረስ የሚያውጅ ድርጊት አልነበረም።  ቀደም ሲል ከእነአባ ሠረቀ ብርሃን ጋር ያጋጫቸው ይኸው ዘራፍ ባይነቱና ዘራፊነቱ ነበር።  ማኅበሩ የትኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁጥጥር መቀበል አይፈልግም። ለምን?

   ማኅበሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ የሚያመለክተው ቢኖር አንድም ራሱ ብቻ አዋቂ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን አሠራር ይንቃል፤ አለያም ምን እየሰራ እንዳለ እንዲታወቅበት አይፈልግም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን  አበረከትኩት የሚለው አገልግሎት የስም፤ የዝናና ራሱን በማሳደግ የሚጠቅምበት ስልታዊ እንቅስቃሴ ከመሆን የዘለለ አልነበረም ማለት ነው።
ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ በመንገድ ሥራ፤ በውሃ ቧንቧ ግንባታ፤ በመብራት ዝርጋታ ላይ ተሰማርታ ነበር። ኢጣሊያ ያንን ማድረጓ ወረራዋን ፍትሃዊ ሊያሰኘው እንደማይችለው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን ፈጸምኳቸው የሚላቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች  የማኅበሩን ኢፍትሃዊ እርምጃዎችን ፍትሃዊ ሊያሰኙት በጭራሽ አይችሉም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ተመስርቶ ከተከናወኑት ሥራዎች ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ የደረሰባት ወከባና ሁከት ዐሥር እጅ ይልቃል። ደግሞስ በ25 ዓመት ዓመት እድሜው «ጧፍና ሻማ ረዳሁ» ከሚል በስተቀር የጧፍና ሻማ ማምረቻ ገነባሁ ሲል አልሰማንም። እንዲያውም ይህንን መንግሥት ለማጃጃል ካለው ገንዘብ ቀንሶ ቦንድ ገዛበት ሲባል ነበር።  በተዘዋዋሪ መንገድ ትመረመራለህ ከምትለው ቤተ ክርስቲያን ያለውን ገንዘብ የመደበቅ ባንዳነት ነው ። ለአብነት ት/ቤቶችና ለመምህራን ሠራሁ የሚለውም ቢሆን በአካፋ ከዛቀው በማንኪያ እያካፈለ ላለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባደረገችው ምርመራ አልመሰከረችለትም።   በአጠቃላይ ማቅ በመኖሩ ቤተ ክርስቲያን ከኪሳራ በቀር ያተረፈችው ነገር የለም።

5/ከማኅበረ ቅዱሳን ጥፋት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ደጋፊ ጳጳሳቱ ናቸው!

በማኅበሩ ሁሉን አቀፍ ጥፋት ዋነኛ ባለእዳዎች ደጋፊ ጳጳሳቱ ናቸው። ይልቁንም የአማራ ጳጳሳት: በይበልጥም ሸዌ ጳጳሳት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። በቅርቡ ባየሁት አንድ የፌስቡክ ገጽ ላይ አባ ቀውስጦስ የአዞ እንባ ሲያፈሱ ነበር።  ማኅበሩ ከሌለ እኛ የለንም የሚሉና ቤተክርስቲያኒቱን መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ማኅበሩ የሚጠብቃት አድርገው የደመደሙ አስመሳይ ጳጳስ ናቸው። ብዙዎቹ ጳጳሳት በዐውደ ምሕረት ስለቅድስና ይስበኩ እንጂ ቀርቦ ገመናቸውን ለመረመረ የሚሰቀጥጥ ነገር ይሰማል። ይህንን ገመና ለመሸፈን ለማኅበሩ "ተናገር በከንፈሬ ተቀመጥ በወንበሬ" ብለው እሱ እነሱን አስቀምጦ ሀገረ ስብከታቸውን ያስተዳድርላቸዋል። ከዚያም በላይ ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አስቀርጾ ለሚያስገባ ማኅበር ጥብቅና የሚቆሙ: የራሳቸው ኅልውና ለማኅበሩ አሳልፈው የሰጡ ጳጳሳት ለቤተ ክርስቲያን መዳከም ተጠያቂዎች ናቸው። ፓትርያርኩን በህገ ቤተ ክርስቲያን ተጣሰ ሽፋን እጅ ከወርች አስረው አላሰራ እያሉ ያሉት ሞቴን ከማኅበሩ በፊት ያድርገው የሚሉ የክርስቶስን ሞት በማኅበሩ ጉልበት የተኩ
ጳጳሳት ናቸው። እነዚህ ሥጋውያንእንጂ መንፈሳውያን አይደሉም። ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን ነው ተጠብቃ ያለችው ከማለት ሌላ ሞት አለ?
ከዚያም ባሻገር ጵጵስና ማዕርግ እንጂ ከኃጢአት የመንጻት የመጨረሻ ማረጋገጫ አይደለም።  በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ቪላ የሚገነቡ፤  ከደሃይቱ ቤተ ክርስቲያን በሚወጣ ገንዘብ እንደውሃ በሚፈስ መኪና የሚሄዱት: ገንዘባቸው ባንክን ማጨናነቁ በሚነገርበት ሁኔታ ዓለም በቃኝ ብለዋል ብሎ ስለብቃት በመናገር ማንንም ማታለል አይቻልም። እንኳን በፈጣሪ ፊት በካህናቱ ዓይን ብዙው ገመና እየታወቀ በብፅእና ማዕርግ ተቀብሎ መኖሩ  የራስ ገመና ለማን ይነገራል? ተብሎ እንጂ የተከደነ: ያልተገለጠ: የተሰወረ : ያልታወቀ ኖሮ አይደለም። የዘር ቆጠራውና የወንዜ ልጅ ዜማው የሚገነው በነዚሁ በጳጳሳቱ ላይ ነው። ዘመድ ከመቅጠርና የዓይኑ ቀለም ያላማራቸውን ሰው ከማባረር ባሻገር ለህዝባቸው አገልግሎት የሚውል  ጤና ጣቢያ: የውሃ ቧንቧና ለልጆቻቸው ት/ቤት ሰርተዋል ተብሎ ዜና በማይነገርበት የልማት ዘመን ለከንቱ ማኅበር መቆም ለኦርቶዶክስ የቆሙ ያህል ከማሰብ የበለጠ ከንቱነት ሊኖር አይችልም።
ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በማሳደግ፤ በማግነን አሁን ላለበት ደረጃ በማድረስ በኩል ጳጳሳቱ ኃላፊነት አለባቸው። የትውልድም፤ የታሪክም ተጠያቂነት እንዲሁም በሆነውና በሚሆነው ነገር ሁሉ በእግአብሔር ፊት ባለእዳዎች ናቸው።
ጳጳሳቱ በተቀመጡበት የቤተ ክርስቲያን አመራር ወንበር ላይ መንፈሳዊ ይሁን ቁሳዊ ልማት የማምጣት፤ ሕዝቡን ወደ እድገትና ራስን ወደመቻል የሥራ አቅም የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ይህንን ሲያደርጉ አይታዩም። ከዚህ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን ባላ እየተደገፉ ስሙን ጳጳሳቱ ተሸክመው ሥራውን ለማኅበሩ በመስጠት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከነበረችበት ፈቀቅ እንዳትል አድርገዋታል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ካሏት ሁለት ኮሌጆች በስተቀር በሀገረ ስብከት ደረጃ አንድም ጳጳስ ኮሌጅ ወይም ሴሚናሪ ት/ቤት ከፍቶ ማኅበረ ካህናቱን በሙያ: በክህሎት: በትምህርትና ዘመኑ ከደረሰበት የእውቀት መር አስተዳደር እያደረሱ እንዳልሆነ እናውቃለን።
 ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት የተከፈለችውም ይሁን ክፍፍሉ ባለበት ቦታ ሁሉ ውስጧ የሚታወከው በጳጳሳቱ በራሳቸው መሆኑን ያየናቸው ተሞክሮዎች ያስረዱናል። መንፈሳዊነታቸውን ያሸነፈ ሥጋዊ ጳጳስነት ባያይል ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት አትከፈልም ነበር። ተከፍላም አትቀርም ነበር።

6/ ማኅበረ ቅዱሳንና የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አይገናኙም!

ቤተክርስቲያን በመዋቅር የሊቃውንት ጉባዔ እንዳላት ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ የሊቃውንት ጉባዔ የቤተ ክርስቲያኒቱን በዘመኑ ያሉ አስተምህሮዎች እየመረመረ ስህተቶችን እየለየ፤ በሐዋርያት መሠረት ላይ ያሉትን እያጸና እውነታኛውንና የቀደምት አበውን ትምህርት ሕዝቡን መመገብ ሲገባው እስከመኖሩ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መገኘቱ ያሳዝናል። ዛሬ ላይ የሊቃውንት ጉባዔውን ጉባዔ በአጅ አዙር በመረከብ በመመርመር ለስደትና ለውግዘት ተሰልፎ የሚገኘው ይህ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ያልተማረው ሊቃውንት ጉባዔ ነው። በዚህ ማኅበር የተነሳ እውነት ተደፍቆ ተቀብሯል። ሊቃውንት ተሰደዋል። እነ "ሆድ አምላኩና እነልጆቼን ላሳድግበት" ብቻ ወንበር ይዘው ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ድርጊት መቀጠሉ መልስ ያልተገኘላቸውን ጥያቄዎች ማስቀረት አይችልም። የተለመደው ባህላዊ እምነት ሳይነካ ባለበት ተሸፍኖ እንዲቀመጥ ማድረጉ ኩብለላውን አያቆምም። ትውልዱ የሚነገረውን ብቻ እየሰማ የሚነዳ ሳይሆን የሚጠይቅም በመሆኑ ከፊት እየሄደ የሚመራ ሊቃውንት ጉባዔ ያስፈልግ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ይህ አልሆነም። አሁን በሚታየው ሁኔታም መቼም ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በዚህ ላይ የተረት አባትና የአፄው ዘውግ አንጋች ማኅበረ ቅዱሳንና ጳጳሳቱ እያሉ የወንጌል እውነት ተገልጦ፤ የአበው አስተምህሮ አደባባይ ላይ ይነገራል ማለት ዘበት ነው። ተረትና እንቆቅልሽ፤ ባህልና ወግ እንደእምነት ተቀላቅሎ መኖራቸው ያበቃል ተብሎ አይታሰብም። ተኀድሶ የባህሪው የሆነው እግዚአብሔር ነገሮችን በሆነ መንገድ ይለውጥ እንደሆነ ወደሰማይ ማንጋገጥ የወቅቱ አማራጭ ሆኗል። በአጠቃላይ ሲታይ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይፈለግ የተገኘ፤ ሳይወደድ የቆየ፤ እየተጠላ ለመኖር የሚታገል በጥቂት አንጃ ጳጳሳት የሚደገፍና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሸክም የሆነ ድርጅት ነው።

"እርሱም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ። ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም። "
(ትንቢተ አሞጽ 8: 2)



Sunday, September 10, 2017

በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ!



እኛ ነን ወደአዲሱ ዓመት የደረስነው ወይስ ዘመኑም እንደእኛው እየሄደ ነው?

  ቆሞ የሚጠብቅ ዘመን የለም። ዘመኑም እኛም በዘመኑ ውስጥ እየሄድን ነው። እግዚአብሔር በዓመት፤ በዓመቱ የሚሰራው አዲስ ዘመን የለም። እግዚአብሔር ዘመናትን የሠራው አንድ ጊዜ ነው።  በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተሠራው ዘመን በራሳችን እድሜ ላይ ሲቆጠር «አዲስ ዘመን» ከማለታችን በስተቀር ዘመኑም ለማለቅ ራሱ ወደእርጅና እየተጓዘ ነው።  ሰውም ዘመናትም የማለቂያ እድሜ አላቸው። ዘመናት የተሠሩት፤ ለሰው ልጆች አገልግሎትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀው መልካሙን ሁሉ ይሠሩባቸው ዘንድ ነው። እንኳን «ለአዲሱ ዘመን አደረሰን!» ስንል እኛ በዘመን ውስጥ መታደሳችንንና መለወጣችንን መናገራችን ነው። እንደዚያ ካልሆነማ ዘመናት የተሠጣቸውን ግዳጅ እየፈጸሙ ወደተሰጣቸው እርጅና እየሄዱ እንጂ መቼ ቆመው ይጠብቁናል? ክረምትና በጋ፤ ብርሃንና ጨለማ፣ ዘርና ማዕረርን ዘመናት ከመስጠት አለማቆማቸውና በዘመን ስሌት መፈራረቃቸው እስከጊዜው የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል። እድሜአቸው አልቆ እስኪጠቀለሉም ይህንኑ ግዳጃቸውን ይወጣሉ።

  መዝ 102፤25-26 «አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል»

ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልዕክቱ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደምንጠባበቅ መናገሩ አሁን ያለን ሰማይና የምንኖርባት ምድር አርጅተው እንደሚለወጡ በግልጽ ያስረዳናል።

2ኛ ጴጥ 3፥13 «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን»

 ስለዚህ በዘመን ውስጥ በእድሜ ጣሪያ የምንጓዝ እኛ የሰው ልጆች ምን ማድረግ ይገባናል?
በጎ መመኘት በጎ ነው። በጎ መመኘት ብቻውን በጎ ነገር አያመጣም። የተመኘነውን በጎ ነገር ለመሥራት በጎ ጥረት ያስፈልገናል። አዲስነት ከእኛነታችን ውጪ የሚገኝ አይደለም። ዘመን በተቆጠረ ቁጥር «እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ» መባባሉ ጥሩ ቢሆንም ባልተለወጠ ማንነታችን ውስጥ ምን አዲስ ለውጥ አይመጣም። መታደስ፤ መለወጥ ለሰው ልጆች ማንነት ልዩ ግኝት ስለሆነ መለወጥ ያለብን እኛ ነን።

 ቁጡና ቂመኛ ሆነን ስለአዲሱ ዘመን ማውራት ምን ይጠቅማል? በውሸትና በቅድስና ጉድለት እየኖርን ከጉዞው ጨብጠን ልናስቀረው ስለማንችለው አዲስ ዘመን መልካምነት መመኘት በራሱ የሚጨምርልን አንዳች ነገር የለም።
ይልቁንስ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውንና ሁልጊዜ እያነበብን ለመተግበር የተቸገርነውን በጎ ነገር እየፈጸምን ስለአዲስ ዘመን በጎ ምኞት እናስብ።

 «በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ»  ኤፌ 4፤21-32

አለበለዚያ ዘመን ካልሰራንበት «እንኳን አደረሳችሁ ሲባባሉብኝ ጊዜያቸውን በከንቱ ፈጸሙ\ ብሎ በኋለኛው ቀን እንዳልሰራንበት ይመሰክራል።
«ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» ስለዚህ ንስሐ እንግባ፤ በልባችንም መታደስ እንለወጥ! ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!