Saturday, September 30, 2017

ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ምንድነው?



ከማኅበረ ቅዱሳን መሥራቾች አንዱ እንደሆነ የሚናገረው የሜሪላንዱ ኤፍሬም እሸቴ  ስለማቅ ጥንስስ እንደተረከው ብላቴ ጦር ካምፕ ውስጥ ተቀፍቅፈን፤ ዝዋይ ላይ በመፈልፈልና አዲስ አበባ ላይ ኅልውና አግኝተን ሕይወት ዘራን ሲል ይተርክልናል። የኅልውናቸውን መስራቾችና ፈልፋዮች ማንነት ኤፍሬም ዘለግ አድርጎ ሲገልፅ በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ በመንደር ምሥረታ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሰዎች ሲሆኑ እነሱ ባሉበት የዳቦ ስም ወጥቶላቸው «ማኅበረ ቅዱሳን» እንደተባሉ «አደባባይ» በተሰኘው መካነ ጦማሩ በአንድ ፅሁፉ አውግቶናል። ለጠቅ አድርጎ: «ተማሪው በጋምቤላ፣ በመተከል፣ በወለጋ … ጎጆ ቤት ሲሠራ፣ ተፈናቃዩን ሲያቋቁም ቆይቶ ተመለሰ። በደህና ወጥቶ ለመመለስ ያልቀናውም ነበር። እነዚያ መንደር ሊመሠርቱ የወጡት ታላላቅ ወንድሞቻችን በየዛፉ ሥር፣ በየመንገዳቸው ጸሎተ ማርያም ማድረሳቸውን፣ ሲችሉም ተገናኝተው ቃለ እግዚአብሔር መስማታቸውን እንዳላስታጎሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እኛን ቃለ እግዚአብሔር ያስተማሩን የዚያ “መንደር መሥራች ትውልድ” አካላት የሆኑ ወንድሞች ናቸው። ወደ ዝዋይም የላኩን እነርሱ ናቸው። እኛ እና እነርሱ በአንድ ላይ ስንሆን ጊዜ በጋራ “ማቅ” ተባልን» ይለናል።
  በእርግጥ የዚያን ዘመን መንደር መሥራችና ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት እነማን መሆናቸውን ባናውቅም ረጅም ህልም የነበራቸው: በእውቀትና በሥልጣን ትላልቅ ሰዎች እንደነበሩ መገመት ይቻላል። ለኤፍሬም ሆነ ለማቅ አባላት ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት የማኅበሩ ፈጣሪዎችን ረጅም ዓላማ በግልጽ ያውቁት እንዳልነበር እርግጥ ቢሆንም አብዛኛው የማኅበሩን አባላት ያሰባሰባቸው ግን እምነታቸው ስለመሆኑ ከጥርጣሬ ላይ የሚወድቅ አይደለም። ብዙዎቹን የማኅበሩ ተከታይ ያደረጋቸው የቤተ ክርስቲያናቸው ቅናት ብቻ ነበር። ሲመሰረትም የወንድሞች ማኅበር «ማኅበረ ቅዱሳን» ከዚያ ከትንሹ ጅምር ተነስቶ ይህንን ያህል በመግዘፍ ሀገራዊ ማኅበርና የሲኖዶስ ጉባዔ የየዓመቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ ይሆናል ብሎ የገመተ አይኖርም። ምናልባት ትላልቅ ወንድሞች የተባሉት እግር በእግር እየተከታተሉና እየኮተኮቱ ያሳደጉበትን  ኅቡእ አጀንዳ ራሳቸው ያውቁ እንደሆን እንጂ ዛሬም ድረስ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው የማኅበሩ አባላት እያገለገሉ ያሉት ቤተ ክርስቲያናቸውን እንደሆነ ያስባሉ።
 ነገር ግን ከአባላቱ መካከል በተለየ ተልእኮ ተመልምለው ረጅም አላማና ግቡን እንዲጨብጡ የተደረጉ አመራሮች በሂደት አልተፈጠሩም ማለት የማይቻልበት ምክንያት አንድ ተራ የፅዋ ማኅበር ከብላቴና ከዝዋይ ተነስቶና ግዝፈቱ እውን እየሆነ ሄዶ የጳጳሳቱን ጉባዔ ሲኖዶሱን ማነቃነቅና ለህልውናው ዘላቂነት እንዲቆሙ የማድረግ አቅም መጨበጥ መቻሉ ከበቂ በላይ አስረጂ ነው። ከዚህ ደረጃ ላይ  መድረሱ  እንዲደርስ የተፈለገበት ረጅም ህልምና ራእይ የለውም ማለት ጅልነት ነው። ኅልውናውን የሚያስጠብቅበትን የሕግ ማዕቀፍ በመጎናጸፍ፤ ማኅበሩን ለማሳደግ የሰው ኃይል በማደራጀት፤ የገንዘብ አቅሙን በማጎልበት፤ በአሰራር ውስጥ ጠልቆ በመግባት ራሱን የሚያስጠብቅበት ቅርጽና መዋቅር ቤተክርስቲያኒቱን መስሎና አኅሎ እየያዘ እንደመጣ እርምጃዎቹ ዋቢዎቻችን ናቸው። ዓላማና ግብ ሳይኖረው ኅልውናውን ማስጠበቅ እንደማያስፈልገው ይታወቃል።  እዚህ ይደርሳል ብለው ያልገመቱ ቢገኙም ሂደት ራሱ በሚፈጥረው ስኬት ከተነሳበት ሃሳብ ወጣ ባለ መልኩ ወደሚፈልግበት አዲስ ግብ ለመድረስ  ስትራቴጂ የለውም ማለት ሞኝነት ነው።  ታዲያ የት ሊደርስ ነው? ማኅበረ ቅዱሳን ተሰኝቶ እየደረጀ የሚሄደው?

የታላላቅ ወንድሞች ህልም ማኅበሩን ቅርፅና መልክ እየሰጡ ከትንሹ ትንሳዔው አንስቶ ያሳደጉት ስኬትን እያጎናፀፉ መድረስ ከሚፈልጉት ስውር ግብ ለማድረስ እንጂ በጽዋ ማኅበር ስር ታጥሮ እንዲቀር እንዳልነበር አሁን የደረሰበት ስኬት ያረጋግጥልናል። ዛሬ ከሲኖዶሱ ይልቅ ማኅበሩ ኃይል አለው። ከወዳጆቹ ጳጳሳት ተጠግቶ የበላቸውን እያከከ:ባልመሰላቸው ነገር ደግሞ እያስፈራራ ወይም በተአቅቦ አፋቸውን አስለጉሞ ማንም የማይደፍረውና የቤተ ክርስቲያኒቱ ያልታጠቀ ልዩ ኃይል መሆን ችሏል።
ማኅበረ ቅዱሳን በጥቂቶች አስተሳሰብ በእቅድ የተመሠረተ፤ በተራው አባል ግን በአጋጣሚ እግዚአብሔር ፈቅዶ የተቋቋመ ያህል የሚታሰብ ድርጅት መሆኑን ቢታሰብም እውነታው ግን ቤተ ክርስቲያንን ራሱ መውረስ ነው። መንግሥታዊ መንበሩንም አይመኝም ማለት የዋህነት ነው። አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን ማኅበሩን እንገምግም!

1/ማኅበረ ካኅናቱ ማቅን እንዴት ያየዋል?

ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበረ ካህናቱ ዘንድ የሚታየው በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሽብልቅ የገባ ዘመን አመጣሽ የጭዋ ማኅበር: ሰላይ: ነጋዴ: ስም አጥፊና የኃጢአት ጸሐፊ ዐቃቤ መልአክ ተደርጎ ነው። ይህ የአደባባይ ምስጢር ነው።  ማኅበሩ በቀጥታ ከማኅበረ ካህናቱ ጋር መጋጨት የማይፈልገው ምእመናኑ በአጠቃላይ የተያዙት በካህናቱ አባትነት ስለሆነ. ከስልታዊ አዋጭነቱ አንፃር ጉዳት የሚያስከትልበት መሆኑን በመገምገም ሲሆን በሂደት ግን ጉልበት ለማግኘትና ማኅበረ ካህናቱን ለመናድ በህግ ማሻሻያ ሰበብ በደንብና በመመሪያ. ሽፋን በአባ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀ/ ስብከት ዘመነ ጵጵስና ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ጊዜ ለመግዛት ካልሆነ በስተቀር ነገ ያንኑ  በሲኖዶስ አስፀድቆ ካህናቱን ለመበታተን ዳግመኛ አይመለስም ማለት የዋህነት ይሆናል። በጥቅሉ ማኅበረ ቅዱሳንና ካህናቱ ዓይንና ናጫ ናቸው።

2/ ማኅበረ ቅዱሳንና የሰንበት ት/ ቤት ወጣቶች:

ወጣቶች ከእድሜአቸው አንፃር ነገሮችን የሚመለከቱበት መነፅር በአንድ አቅጣጫ የተወሰነ ነው። በተለይ ደግሞ ከእምነት አንፃር በሚገባቸው  ስስ ስሜት በኩል በወጣት ቋንቋ የሚነግራቸውን ቶሎ ይቀበሉታል። አሁን ባለው ሁኔታ ነጠላን በመስቀልኛ አጣፍቶ የራሱን ስብከት ለነገራቸው ማቅ ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው።  የማኅበሩ ያልታጠቀ ኃይል የሰንበት ት/ቤት ወጣት ነው። ይህንን ኃይል መያዝ ማለት በየአጥቢያው ለማኅበሩ ህልውናና ስርፀት አስፈላጊ በር ለማስከፈት ጠቃሚ መሆኑን አሳምሮ ያውቃል። በዚያ ላይ ለማኅበሩ ህልውና አደጋ የሚፈጥር የአጥቢያ አስተዳዳሪ ወይም ማኅበረ ካህናት የማስወገጂያ ጦር ሆኖ ያገለግላል። በተለይ ደግሞ ሙሰኛና ነውር የተገኘበት ከሆነ ግፋ በለው የሚል አዋጅ የሚታወጀው በሰንበት ት/ ቤት ወጣት በኩል ነው። ስለሆነም የወጣቶቹን የሰንበት ት/ቤት ኃይል መቆጣጠር ማለት አጥቢያውን መቆጣጠር ማለት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለጥምቀት በዓል አስፋልት በመጥረግ: ቄጠማ በመጎዝጎዝና ምንጣፍ በማንጠፍ መንፈሳዊ ቅናት መሰል ቅንቅን የወረሳቸውን የበጎ ፈቃድ ወጣቶችን ማኅበሩ "የጥምቀት ተመላሾች ማኅበር" በሚል ስም አዋቅሯቸው በራሱ መረብ ስር አስገብቷቸዋል። ነገር መፈለጊያ ጥቅስ በማልበስ "አንዲት ሃይማኖት: አንዲት ጥምቀት" የሚል ቲሸርት አስለብሶም በአደባባይ ጠብ ያለሽ በዳቦ ሲያሰኝም ነበር።  በሌላ በኩልም በአባልነት የያዛቸው የየአጥቢያውን ሰንበት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን "ግቢ ጉባዔ" በሚል ሽፋን ለራሱ ዓላማ ስርፀት ከሚደክምባቸው ኃይሎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ነገ በሚሰማሩበት የሥራና የሥልጣን ወንበር የማኅበሩ ወኪል የሚሆኑበትን መደላድል ዩኒቨርሲቲ ድረስ ገብቶ ይፈጥራል። ሌላው መረሳት የሌለበት ነገር ማኅበሩ የፖለቲካ ድርጅት የሆነ ያህል አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሚጠሉ ፖለቲከኞች ሁሉ እንደ አንድ አስፈላጊ አካል ሆኖ የመቆጠሩ ጉዳይ
መዘንጋት የለበትም። ለምን? ብሎ መጠየም ተገቢ ጉዳይ ነው።
እነዚህ አብሮነት ያገናኛቸው የእምነት ስምምነት ውል መኖሩ ሳይሆን የሚያቀራርባቸው ፖለቲካዊ ስልት መሆኑን ለማወቅ ብዙም ምርምር አይጠይቅም።

ማኅበሩ ከላይ ከፍተኛው የሥልጣን አካል የሆነውን ሲኖዶሱን ይዟል። ከታች አብዛኛውን የገንዘብ ምንጭና የጉልበት ኃይል የሆነውን ወጣቱን አቅፏል። በመካከል ያለው የካህናቱ ኃይል የሚደመጥበትና ማኅበሩን የሚቋቋምበት አቅም ስለሌለው አንገቱን ደፍቶ ቀርቷል።

3// ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ያበረከተው ምንድነው?

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ መቅደሱ የክህነት አገልግሎት ላይ የተሰማራ ባለመሆኑ ለምዕመናኑ ከካህናቱ በተሻለ የሚሰጠው አገልግሎት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሳትሰጥ የቀረችውና ማኅበሩ ሊያሟላው የሚችለው አንዳችም ነገር የለም።
 በየአድባራቱ ወይም በየገዳማቱ ከምዕመናን አባላቱና ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ጋር ያለውን ቅርርብ በመጠቀም ዓላማና ግቡን ለማስረጽ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ከካህናቱ በኩል ያለውን  ተቃውሞ ለመከላከል ሲል ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆር በመምሰል ስም በማጥፋት፤ በአድማና በህውከት ከቦታቸው እንዲነሱ፤ እንዲጠሉ በማስደረግ ወይም ዝም ጭጭ ብለው፤ አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ በሚያደርገው ተግባሩ ያተረፈው ነገር ቢኖር የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ወደሌሎች ቤተ እምነቶች መኮብለል ብቻ ነው። በሐረር፤ በድሬዳዋ፤ በደቡብ፤ በምዕራብና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እንደጎርፍ ቤተ ክርስቲያኒቱን ትተው የኮበሉለት ማኅበረ ቅዱሳን በየቦታው በፈጠው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ ነው።

   በእርግጥ አንዳንዶች ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ባሉበት መርጋት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ቢሉም ተረትና እንቆቅልሽ ለማስተማር ካልሆነ በስተቀር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን የመተካት አንዳችም አቅም የሌለው ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ1960 ዓ/ም በፊት ከ1% በታች የነበሩት የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች እስከ 1984 ዓ/ም ድረስ 5.5% የደረሱ ሲሆን እስከ 1994 ዓ/ም ድረስ በዐሥር ዓመት ውስጥ ብቻ 10.2% ለመድረስ በቅተዋል። አሁን ባለው ስታስትስቲክ የፕሮቴስታንቱ ቁጥር ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ 18.6% ሲደርስ በተቃራኒው ደግሞ ከሀገሪቱ ሕዝብ 60% ገደማ የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት ተከታይ የነበረው ቁጥር በአስደንጋጭ መጠን ወደ 43.5% ያሽቆለቆለው ባለፉት ዐሥርተ አመታት ውስጥ መሆኑ የሚያሳየን ነገር የማኅበረ ቅዱሳንን የስብከትና እንቅስቃሴ ምዕመናኑን ከመበተን ይልቅ በቤታቸው የማቆየት አቅም እንዳልነበረው አረጋጋጭ ነው። ውግዘትና ሁከት እንደውጤት ከተቆጠረ ማቅ በተገቢው ሰርቷል።   አንዳንዶች እንደሚያስወሩት ሰዎች ከነባር ቤተ እምነታቸው የኮበለሉት በስንዴና በአቡጀዲ ተገዝተው ሳይሆን መሬት ያለው እውነታ የሚነግረን ጊዜውን የሚመጥን አስተዳደርና ዘመኑን የሚዋጅ የወንጌል ቃል ትምህርት ስለሌለ ብቻ ነው። ለመሆኑ "ድንጋይ ዳቦ ነበረ" ከሚል ስብከት ያልተላቀቀው ማቅ ሁከትና ብጥብጥ ጨምሮበት ማን ባለበት ቆሞ ሕይወቱን በከንቱ ይገብራል?
ወደፕሮቴስታንቱ ጎራ ከኮበለለው 17% ገደማ የሚሆነው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወጣ እንጂ በዳንጎቴ ፋብሪካ የተመረተ የሰው ሲሚንቶ አይደለም። ማቅ እንኳን ከሌላ ቤተ እምነት ሰብኮና አሳምኖ ሊያመጣ ይቅርና ያሉት ተረጋግተው እንዳይኖሩ ሲሰራ የቆየ መሆኑ አይታበልም። የማኅበረ ቅዱሳን የተረትና እንቆቅልሽ አስተምህሮ ማንንም ሰብኮ መመለስ አይችልም።  ለጠያቂ ትውልድ የሚመጥን መልስ ሳይኖር ስመ ተሐድሶን መለጠፍና የስንዴ ሃይማኖት በማለት ማጣጣል ኩብለላውን ማስቆም አይቻልም። "አንድ ሳር ቢመዘዝ"  በሚል የሞኝ ተረት እያቅራሩ መኮፈስ የትም አያደርስም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሥግው ቃል የሆነበት ምስጢር አንድ ሰው ፍለጋ ነው። ማቅና ደጋፊ ጳጳሳቱ ከአፋቸው የማይጠፋው ነገር በሰው ቁጥር መመካታቸው ቢሆንም ሳሩ ተመዞ ተመዞ እያለቀ መሆኑን አላቆመም።  ማኅበረ ቅዱሳን ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ከተጠቀመችው ይልቅ ማኅበሩ በየቦታው በሚፈጥረው ሁከትና ግርግር የተጎዳችበት ይልቃል።
4// ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያበረከተው አገልግሎት እውነት እንደሚወራው ነው?

ሲጀመር ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን የካዝና ቋቱንና ኪሱን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አያሳይም። በሞዴላ ሞዴል ተጠቀም! ሂሳብህን አስመርምር! በምትሰራው ነገር ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ጠይቅ! መባሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የመሆኑ ማረጋገጫ  ካልሆነ በስተቀር ሀብትና ንብረቱን ስለመውረስ የሚያውጅ ድርጊት አልነበረም።  ቀደም ሲል ከእነአባ ሠረቀ ብርሃን ጋር ያጋጫቸው ይኸው ዘራፍ ባይነቱና ዘራፊነቱ ነበር።  ማኅበሩ የትኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁጥጥር መቀበል አይፈልግም። ለምን?

   ማኅበሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ የሚያመለክተው ቢኖር አንድም ራሱ ብቻ አዋቂ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን አሠራር ይንቃል፤ አለያም ምን እየሰራ እንዳለ እንዲታወቅበት አይፈልግም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን  አበረከትኩት የሚለው አገልግሎት የስም፤ የዝናና ራሱን በማሳደግ የሚጠቅምበት ስልታዊ እንቅስቃሴ ከመሆን የዘለለ አልነበረም ማለት ነው።
ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ በመንገድ ሥራ፤ በውሃ ቧንቧ ግንባታ፤ በመብራት ዝርጋታ ላይ ተሰማርታ ነበር። ኢጣሊያ ያንን ማድረጓ ወረራዋን ፍትሃዊ ሊያሰኘው እንደማይችለው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን ፈጸምኳቸው የሚላቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች  የማኅበሩን ኢፍትሃዊ እርምጃዎችን ፍትሃዊ ሊያሰኙት በጭራሽ አይችሉም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ተመስርቶ ከተከናወኑት ሥራዎች ይልቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ የደረሰባት ወከባና ሁከት ዐሥር እጅ ይልቃል። ደግሞስ በ25 ዓመት ዓመት እድሜው «ጧፍና ሻማ ረዳሁ» ከሚል በስተቀር የጧፍና ሻማ ማምረቻ ገነባሁ ሲል አልሰማንም። እንዲያውም ይህንን መንግሥት ለማጃጃል ካለው ገንዘብ ቀንሶ ቦንድ ገዛበት ሲባል ነበር።  በተዘዋዋሪ መንገድ ትመረመራለህ ከምትለው ቤተ ክርስቲያን ያለውን ገንዘብ የመደበቅ ባንዳነት ነው ። ለአብነት ት/ቤቶችና ለመምህራን ሠራሁ የሚለውም ቢሆን በአካፋ ከዛቀው በማንኪያ እያካፈለ ላለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባደረገችው ምርመራ አልመሰከረችለትም።   በአጠቃላይ ማቅ በመኖሩ ቤተ ክርስቲያን ከኪሳራ በቀር ያተረፈችው ነገር የለም።

5/ከማኅበረ ቅዱሳን ጥፋት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ደጋፊ ጳጳሳቱ ናቸው!

በማኅበሩ ሁሉን አቀፍ ጥፋት ዋነኛ ባለእዳዎች ደጋፊ ጳጳሳቱ ናቸው። ይልቁንም የአማራ ጳጳሳት: በይበልጥም ሸዌ ጳጳሳት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። በቅርቡ ባየሁት አንድ የፌስቡክ ገጽ ላይ አባ ቀውስጦስ የአዞ እንባ ሲያፈሱ ነበር።  ማኅበሩ ከሌለ እኛ የለንም የሚሉና ቤተክርስቲያኒቱን መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን ማኅበሩ የሚጠብቃት አድርገው የደመደሙ አስመሳይ ጳጳስ ናቸው። ብዙዎቹ ጳጳሳት በዐውደ ምሕረት ስለቅድስና ይስበኩ እንጂ ቀርቦ ገመናቸውን ለመረመረ የሚሰቀጥጥ ነገር ይሰማል። ይህንን ገመና ለመሸፈን ለማኅበሩ "ተናገር በከንፈሬ ተቀመጥ በወንበሬ" ብለው እሱ እነሱን አስቀምጦ ሀገረ ስብከታቸውን ያስተዳድርላቸዋል። ከዚያም በላይ ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ አስቀርጾ ለሚያስገባ ማኅበር ጥብቅና የሚቆሙ: የራሳቸው ኅልውና ለማኅበሩ አሳልፈው የሰጡ ጳጳሳት ለቤተ ክርስቲያን መዳከም ተጠያቂዎች ናቸው። ፓትርያርኩን በህገ ቤተ ክርስቲያን ተጣሰ ሽፋን እጅ ከወርች አስረው አላሰራ እያሉ ያሉት ሞቴን ከማኅበሩ በፊት ያድርገው የሚሉ የክርስቶስን ሞት በማኅበሩ ጉልበት የተኩ
ጳጳሳት ናቸው። እነዚህ ሥጋውያንእንጂ መንፈሳውያን አይደሉም። ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን ነው ተጠብቃ ያለችው ከማለት ሌላ ሞት አለ?
ከዚያም ባሻገር ጵጵስና ማዕርግ እንጂ ከኃጢአት የመንጻት የመጨረሻ ማረጋገጫ አይደለም።  በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ቪላ የሚገነቡ፤  ከደሃይቱ ቤተ ክርስቲያን በሚወጣ ገንዘብ እንደውሃ በሚፈስ መኪና የሚሄዱት: ገንዘባቸው ባንክን ማጨናነቁ በሚነገርበት ሁኔታ ዓለም በቃኝ ብለዋል ብሎ ስለብቃት በመናገር ማንንም ማታለል አይቻልም። እንኳን በፈጣሪ ፊት በካህናቱ ዓይን ብዙው ገመና እየታወቀ በብፅእና ማዕርግ ተቀብሎ መኖሩ  የራስ ገመና ለማን ይነገራል? ተብሎ እንጂ የተከደነ: ያልተገለጠ: የተሰወረ : ያልታወቀ ኖሮ አይደለም። የዘር ቆጠራውና የወንዜ ልጅ ዜማው የሚገነው በነዚሁ በጳጳሳቱ ላይ ነው። ዘመድ ከመቅጠርና የዓይኑ ቀለም ያላማራቸውን ሰው ከማባረር ባሻገር ለህዝባቸው አገልግሎት የሚውል  ጤና ጣቢያ: የውሃ ቧንቧና ለልጆቻቸው ት/ቤት ሰርተዋል ተብሎ ዜና በማይነገርበት የልማት ዘመን ለከንቱ ማኅበር መቆም ለኦርቶዶክስ የቆሙ ያህል ከማሰብ የበለጠ ከንቱነት ሊኖር አይችልም።
ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በማሳደግ፤ በማግነን አሁን ላለበት ደረጃ በማድረስ በኩል ጳጳሳቱ ኃላፊነት አለባቸው። የትውልድም፤ የታሪክም ተጠያቂነት እንዲሁም በሆነውና በሚሆነው ነገር ሁሉ በእግአብሔር ፊት ባለእዳዎች ናቸው።
ጳጳሳቱ በተቀመጡበት የቤተ ክርስቲያን አመራር ወንበር ላይ መንፈሳዊ ይሁን ቁሳዊ ልማት የማምጣት፤ ሕዝቡን ወደ እድገትና ራስን ወደመቻል የሥራ አቅም የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ቢሆንም ይህንን ሲያደርጉ አይታዩም። ከዚህ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን ባላ እየተደገፉ ስሙን ጳጳሳቱ ተሸክመው ሥራውን ለማኅበሩ በመስጠት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከነበረችበት ፈቀቅ እንዳትል አድርገዋታል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ካሏት ሁለት ኮሌጆች በስተቀር በሀገረ ስብከት ደረጃ አንድም ጳጳስ ኮሌጅ ወይም ሴሚናሪ ት/ቤት ከፍቶ ማኅበረ ካህናቱን በሙያ: በክህሎት: በትምህርትና ዘመኑ ከደረሰበት የእውቀት መር አስተዳደር እያደረሱ እንዳልሆነ እናውቃለን።
 ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት የተከፈለችውም ይሁን ክፍፍሉ ባለበት ቦታ ሁሉ ውስጧ የሚታወከው በጳጳሳቱ በራሳቸው መሆኑን ያየናቸው ተሞክሮዎች ያስረዱናል። መንፈሳዊነታቸውን ያሸነፈ ሥጋዊ ጳጳስነት ባያይል ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት አትከፈልም ነበር። ተከፍላም አትቀርም ነበር።

6/ ማኅበረ ቅዱሳንና የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አይገናኙም!

ቤተክርስቲያን በመዋቅር የሊቃውንት ጉባዔ እንዳላት ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህ የሊቃውንት ጉባዔ የቤተ ክርስቲያኒቱን በዘመኑ ያሉ አስተምህሮዎች እየመረመረ ስህተቶችን እየለየ፤ በሐዋርያት መሠረት ላይ ያሉትን እያጸና እውነታኛውንና የቀደምት አበውን ትምህርት ሕዝቡን መመገብ ሲገባው እስከመኖሩ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መገኘቱ ያሳዝናል። ዛሬ ላይ የሊቃውንት ጉባዔውን ጉባዔ በአጅ አዙር በመረከብ በመመርመር ለስደትና ለውግዘት ተሰልፎ የሚገኘው ይህ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ያልተማረው ሊቃውንት ጉባዔ ነው። በዚህ ማኅበር የተነሳ እውነት ተደፍቆ ተቀብሯል። ሊቃውንት ተሰደዋል። እነ "ሆድ አምላኩና እነልጆቼን ላሳድግበት" ብቻ ወንበር ይዘው ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ድርጊት መቀጠሉ መልስ ያልተገኘላቸውን ጥያቄዎች ማስቀረት አይችልም። የተለመደው ባህላዊ እምነት ሳይነካ ባለበት ተሸፍኖ እንዲቀመጥ ማድረጉ ኩብለላውን አያቆምም። ትውልዱ የሚነገረውን ብቻ እየሰማ የሚነዳ ሳይሆን የሚጠይቅም በመሆኑ ከፊት እየሄደ የሚመራ ሊቃውንት ጉባዔ ያስፈልግ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ይህ አልሆነም። አሁን በሚታየው ሁኔታም መቼም ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በዚህ ላይ የተረት አባትና የአፄው ዘውግ አንጋች ማኅበረ ቅዱሳንና ጳጳሳቱ እያሉ የወንጌል እውነት ተገልጦ፤ የአበው አስተምህሮ አደባባይ ላይ ይነገራል ማለት ዘበት ነው። ተረትና እንቆቅልሽ፤ ባህልና ወግ እንደእምነት ተቀላቅሎ መኖራቸው ያበቃል ተብሎ አይታሰብም። ተኀድሶ የባህሪው የሆነው እግዚአብሔር ነገሮችን በሆነ መንገድ ይለውጥ እንደሆነ ወደሰማይ ማንጋገጥ የወቅቱ አማራጭ ሆኗል። በአጠቃላይ ሲታይ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይፈለግ የተገኘ፤ ሳይወደድ የቆየ፤ እየተጠላ ለመኖር የሚታገል በጥቂት አንጃ ጳጳሳት የሚደገፍና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሸክም የሆነ ድርጅት ነው።

"እርሱም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ። ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም። "
(ትንቢተ አሞጽ 8: 2)