Wednesday, September 6, 2017

«አማለደ» ያለው አማለደ ለማለት ሳይሆን . . . » ለቀሲስ ደጀኔ የተሰጠ መልስ ( ሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል )





Kesis Melaku Terefe

መነሻው እንደጰላድዮስ በጥያቄ፥ እንደንስጥሮስ በክርክር ቢሆንም፥ ለተነሡት ጥያቄዎችና ክርክሮች መልስ እንዲሆን ቅዱሳን አባቶቻችን ጽፈውልን የተዉልን ጦማሮችና ድርሳናት ፥ ዛሬ በጨለማ እንዳንዳክር መንገድ ጠቋሚዎች ሆነው፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ እንድንመረምርባቸው ረድተውናል። ዛሬም በስሕተት ጎዳና ካሉት ጋር የምናደርገውን ክርክር የምንመራው ፥ እነዚህ አባቶቻችን የቀደዱልንን ፈር በመከተል ነው። ምስክራችን ቅዱሳን ሐዋርያት፥ ሐዋርያውያን አበው፥ የኋላ ሊቃውንት እና ሲኖዶሶቻቸው ነው። ከሳሾቻችን ክርክሩን ለማሸነፍ እየሞከሩ ያሉት፥ በቃላት ስንጠቃና በብልጣ ብልጥነት ነው። ቢታጣ ቢታጣ፥ የግእዙንም ሆነ የአማርኛውን ሰዋስው ተጠያቂ የሆኑትንና በዚህም የኢትዮጵያውያን ሁሉ ባለውለታ የሆኑትን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌንና ደስታ ተክለ ወልድን ለአማርኛ ቃል ክርክር ምስክር ስላደረግናቸው፥ የቦሩ ሜዳውን ክርክር ወደኛ ለማምጣት እየሞከሩት ነው። ትንሽ ቆይተው ደግሞ ኪዳነ ወልድ የተረጎሙት ሕዝቅኤል ይቃጠልልን ብለው ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ አቧራ እንደሚያስነሱ እንጠብቃለን። ለነገሩ ይህን የሚያውቁት አይመስለንም። አለቃ ግን  አፉ ያልተገራ ጨዋ እንዲህ ሲሰድባቸው ቢሰሙ ኖሮ በአጭሬ ግጥማቸው ያቀምሱት ነበር። ግን ምን ያደርጋል!
እኛ ግን የተዋህዶ ማኅተም እየተባለ የሚጠራው፥ የእስንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ቄርሎስ፥ « ከመ አሐዱ ክርስቶስ» የተሰኘውን ተዋህዶን ያመሠጠረበትን ድንቅና ታላቁን ድርሰቱን ሲጀምር፥ « ለትምህርተ ቅዱሳት መጻሕፍት አልቦ ዘይጸግቦን ግሙራ ወኢመኑሂ፤ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርት ማንም ማን አይሰለችም።» በማለት እንደተናገረው ያለ መሰልቸት፥ ከአበው የተማርነውን እንጽፋለን እንናገራለን። የእግዚአብሔር ቃልን ከመናገር ቸል አንልም አንሰለችም። ይኸው ሃይማኖቱ የቀና ( ኦርቶዶክሳዊ) አባት፥ « ሲሲተ ልብ ቃላቲሁ ለእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ቃል የልቡና ምግብ ነው» እንዳለው፥ በዚህም ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንደሚመግቡ ተስፋ እናደርጋለን።
ወንድሜ ቀሲስ ደጀኔ፥ ባለፈው በክፍል ሁለት ጽሑፋችን አራት ዋና ዋና ነገሮችን አንሥተናል፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናትነት ፍጹም ሰው በመሆኑ እንደሆነ፤ ሊቀ ካህናትነቱ በሹመት እንደሆነ፥ ሊቀ ካህንነቱ ለማስታረቅ እንደሆነ፥ በመጨረሻም ሊቀ ካህናትነቱ እንደ መልከ ጼዴቅ እንደሆነ ተመልክተናል። በዚህ ክፍል ሦስት ጽሑፋችን ደግሞ የአውጣኪን የስህተት ጎዳና በመከተል፥ የክርስቶስን የሊቀ ካህናትነቱን የማስታረቅ አገልግሎት የካድክባቸውን ነጥቦች በማንሳት፥ አንድ በአንድ መልስ እንሰጣለን።
ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ፦ «ከዚህም አያይዞ፡-“እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚ ችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤”ብሎአል። የቅዱስ ጳውሎስ የትርጓሜ መጽሐፍ፡-ይኸንን ገጸ ንባብ ሲያብራራው፡-“ወእመ ሀሎ በመዋ ዕለ ሥጋሁ፥ ጸሎተ ወስኢለ አብአ፥ በዐቢይ ገዓር ወአንብዕ።ይኸውም ሊታወቅ ሰው ኾኖ የሰውነትን ሥራ በሠራበት ወራት (ከቤተል ሔም እስከ ቀራንዮ ባደረገው የማዳን ጉዞ) ጸሎ ትን፡-እንደ ላም፥ምልጃን(ልመናን)፡-እንደ በግ አድ ርጎ፥በፍጹም ሐዘንና በብዙ ዕንባ አቀረበ ፤”ብሎአል።ምክንያቱም፡-የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ለል መና እና ለምልጃ የሚያቀርቡት የበግ እና የላም መሥዋዕት ነበር።በመሆኑም፡-በንባቡ ጸሎትና ምልጃ የተባለው፡-“አማለደ፤” ለማለት ሳይሆን፥እንደ ላምና እንደ በግ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን እንደሆነ ማስተ ዋል ይገባል » ብለህ ነበር።
ይህ ጽሑፍህ  ከእግዚአብሔር ቃልና ከአባቶች ትርጓሜ ጋር ሙግት የያዘ ነው። አንደኛ፥ ጸሎት እና ምልጃ ተብሎ የተጻፈውን  ጸሎትና ምልጃ ብላችሁ አታንብቡ ትለናለህ። የእግዚአብሔርን ቃል ታጣምም ዘንድ እንዴት ደፈርህ። በዚህ አላበቃህም።  ሁለተኛ፥ አባቶች « ጸሎትን እንደ ላም ምልጃን እንደ በግ አድርጎ አቀረበ» ብለው የተረጎሙት፥ ጸሎትና ምልጃ ለማለት አይደለም  በማለት ምልጃና ጸሎት ተብሎ የቀረበው ሥጋው ነው በማለት ነበር ያስቀመጠው። ይህ ሁሉ ግን ፥ ክርስቶስ በሊቀ ካህንነቱ አልማለደም አልጸለየም ለማለት ነው።  ያንተን ትርጓሜ የማንቀበልበትን በዝርዝር እናስረዳ፤
፩ኛ. ንባቡ የሚለው « ጸሎትንና ምልጃን» አቀረበ ነው።
« እርሱም ሥጋ ለብሶ በዚህ ዓለም በነበረበት ጊዜ፥ በታላቅ ጩኸትና እንባ ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ ጽድቁንም ሰማው» ነው የሚለው። በዚህ ንባብ ውስጥ ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮች በግልጥ ተቀምጠዋል። ጩኸት ( ገዓር) እና እንባ (አንብእ) ጸሎት እና ምልጃ ተነግረዋል።  ምንም እንኳ ሙሉ በሙሉ ወልድ በሥጋው ወራት ወደ አባቱ እንደጸለየ ብትክድም፥ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ይህን በግልጥ ያስቀምጣሉ።

ስለ ጸሎቱ ለምሳሌ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታ በጌቴሴማኒ ሲጸልይ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጥ እንዲህ ይላል። የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው። ፈራ መላልሶም ጸለየ ላቡም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆነ» ይላል፤ ሉቃስ ፳፫፥፵፬። እዚህ ላይ ከመጸለይ ባሻገር፥ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ « ፈራ» ብሎ ሲናገር እናያለን። ቀሲስ ደጀኔ ባንተ አተረጓጎም ከሄድን « ፈራ ሲል ፈራ ማለት አይደለም» ብለን የፈጠራ ትርጉም መስጠት እንችል ነበር። ግን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲህ በማድረግ አናጣምም። ፈራ ሲል ፈራ ነው። አማለደ ሲል አማለደ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የእግዚአብሔር ልጅ እንዴት ፈራ ይባላል፥ አባቶች በሚገባ መልሰውታል። « በሰው ልማድ ፈራ፤» አሉ፤ ትርጓሜ ወንጌልን ተመልከት። ማለትም በእውነት ፍጹም ሰው ስለሆነ ማናቸውም ሰው እንደሚፈራው ነው የፈራው። ከኃጢአት በቀር እንደኛ የሆነ ሰው ነውና። ነገር ግን ከዚያ በላይ ታላቅ የሆነ መልእክት አለ። ለምን ፈራ? እኛን ሆኖ፥ ስለ እኛ ብሎ ስለሆነ የወደቀውና የተነሣው፥ የፈራውም የእኛን ፍርሃት ነው። በእውነት እኛን ሆኖ የእኛን ፍርሃት ፈራ። « ሶበሰ ኢፈርሃ እምኢሰሰለ ፍሃት እምኔነ፤ ባይፈራ ኖሮ ( የምትሃት ቢሆን ኖሮ፥ ወይም በእውነት ሳይፈራ ለትምህርት ብቻ ያሳየው ቴያትር ቢሆን ኖሮ) ፍርሃት ከእኛ ባልተወገደ ነበር።»  የጸለየውም መላልሶ ነው። አባቶች እንዳስቀመጡት፥ « ወጸርሐ ኀበ አቡሁ ከመ ትምጽኦ ረድኤቱ፤ ረድኤቱ ትመጣለት ዘንድ ወደ አባቱ ጮኸ፤» እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ ቢባል በለበሰው ሥጋ።
ይህ የአባቶች ትርጓሜ፥ ከነባቤ መለኮት ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ትምህርት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። አቡልናርዮስ ጌታ ነፍስን አልነሣም ብሎ የኑፋቄ ትምህርቱን ይዞ ሲነሣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የሰጠው መልስ «What has not been assumed has not been healed; it is what is united to his divinity that is saved. ያልነሣውን አልፈወሰውም፤ ከመለኮትነቱ ጋር የተዋሃደውን ያንን  ነው የዳነው» ነበር ያለው። ይህ የነባቤ መለኮት ጎርጎርዮስ አባባል የሚያስረግጥልን፥ ጌታ የኛን ባሕርይ የተዋሃደው ሊያድነን ነው።
ያዳነን የተዋሃደውን ባሕርይ ነው። ከኃጢአት በቀር፥ የሚዝል፥ የሚደክም የሚፈራ፥ የሚራብ የእኛን ባሕርይ ነው የተዋሃደው። በእውነት የሰውን ባሕርይ ገንዘብ አድርጎአልና።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ይህን የቅዱስ ሉቃስን ንባብ ሲተረጉመው እንዲህ አለ። « እርሱ እንደፈራ በተናገረ ጊዜ ጌታ የተዋሐደውን የሰውን ባሕርይ አስረዳ፤ እውነተኛ ሰው እንደሆነም አስረዳ። በዚህም ጌታ የተዋሐደው ኃጢአት የሌለበትን የሥጋን ሥራ ሰው መሆኑንም አስረዳ፤ ፍርሃት ከመለኮት ባሕርይ አይደለም። ወዙ እንደ ደም ነጠብጣብ በዝቶ እስኪወርድ ድረስ አለ፤ ደም መስሎ መውረድም የሥጋ ገንዘብ ነውና። የሚያጽናናው የእግዚአብሔር መልአክም ከወደ ሰማይ መጣ አለ።» ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ም. ፶፮. ክፍል ፫ ቍ. ፵፪- ፵፫
፪ኛ. የአባቶች ትርጓሜም ትኩረት የሚያደርገው  « ጸሎትንና ምልጃን» ነው።  
ይህን እንደገና አባቶች በትርጓሜያቸው እንዴት እንዳስቀመጡት እንመለከት፦  « ሰው ኾኖ የስውነት ሥራ በሠራበት ወራት፤ጸሎትን እንደላም ስኢልን እንደበግ አድርጎ አቀረበ።በፍጹም ኀዘን በብዙ ዕንባ አቀረበ። የልቡና ነውና፥ ግዳጅ ይፈጽማልና፥ አንድ ጊዜ ነውና በታላቅ ጩኸት ( ኀዘን) እና በእንባ አለ። ከሞት ሊያድነው ወደሚቻለው ወደ አብ አቀረበ። የምእመናንን ድኅነት ለራሱ አድርጎ፥አንድም ምእመናንን ከሞት ሊያድንለት ወደሚቻለው ወደ አብ አቀረበ። ቁርጥ ልመናውንም ሰማው። የባሕርይ ልጅ ሲሆን፥ ታዞ መከራ ስለተቀበለ፥ መታዘዝን አመለከተ ( ዐወቀ)። ትንቢተ ነቢያትን፥ ዘመንን፥ ቀጠሮን፥ አሥሩ ቃላትን፥ ሕማማተ መስቀልን ፈጽሞ፥ ለሚያምኑበት ኹሉ ሕይወትን የሚያድል ኾነ። የዘላለም ሕይወት ሆነ»
በግዴለሽነት የአባቶችን ትርጓሜ « ለማቃናት » የጮሌነት አካሄድ ብትሄድም፥ ትርጓሜው አይሰድህም። « « ጸሎትን እንደላም ስኢልን እንደ በግ አድርጎ አቀረበ» ሲል ላምና በግ ስለተጠቀሰ « ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን የሚያመለክት ነው» ያልከው መሥዋዕት ያለ ምልጃና ያለጸሎት እንደማይቀርብ ባለማስተዋልህ ነው። ያው የአባቶች ትርጓሜ ትኩረቱ ምን ላይ እንደሆነ፥ በጥንቃቄ ትረዳው ነበር። ለምሳሌ « በፍጹም ኀዘን በብዙ ዕንባ አቀረበ» የሚለውን ሲተረጉሙ የሚያሳየው ይህን እውነት ነው። እነርሱ ያሉት « የልቡና ነውና፥» ማለት የመታየት፥ የምትሃት አይደለም፤ « ግዳጅ ይፈጽማል » ማለት የቤዛነት ሥርየተ ኃጢአትን የሚያሰጥ ነው ል  « አንድ ጊዜ ነው» አንድ ጊዜ ለዘላለም የከናወነው ነው የሚል ነው። ይህ ብቻ አይደለም ። « ወሰምዖ ጽድቆ፥ ጽድቁ ተሰማለት» የሚለውን « ቁርጥ ልመናውንም ሰማው» ብለው ነበር የተረጐሙት። ንባቡ ልመናው ስለመሰማቱ ፥ ስለመታዘዙ ነው የሚናገረው። እንህ   « ቁርጥ ልመናውን ሰማው ማለት፥ ቁርጥ ልመናውን ሰማው ለማለት አይደለም» ካላልክ በስተቀር፥ የቀረበffው ቁርጥ ልመና ነው፤ የቀረበው ምልጃ ነው።

፫ኛ. ዓለም የታረቀው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው ጸሎትና ምልጃ ነው።
ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የጸለየው ጸሎት የምልጃ ጸሎት ነው። ይህን በተለይ ዮሐንስ 17 በግልጥ ያሳየናል። በዚያ ጸሎት ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ለነበሩት ደቀመዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ ነበር የጸለየው። በመስቀል ላይ የነበረው ጩኸቱም በመስቀል ላይ የቀረበ የምልጃ ጩኸት ነው። ይህን ከእኔ ይልቅ አለቃ አያሌው ውበት ባለው አገላለጥ አስቀምጠውታል። አስተውል አለቃ እንዴት አድርገው ይህን የቤዛነት ሥራ እንደገለጡት በጥንቃቄ ተከታተለው።
አለቃ አያሌው እንዲህ ይላሉ፦ « በዕለተ ስቅለት በካህኑ ፋንታ ሆኖ « እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም፤ ስለሰጠኸኝ እንጂ፡ የአንተ ናቸውና የእኔም የሆነ ሁሉ ያንተ ነው። የአንተውም የእኔ ነው። እኔም ስለእነርሱ ከብሬአለሁ፤ ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም። . . . ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑትም ደግሞ እንጂ ስለእነዚህ ብቻ አልለምንም» ብሏል። ( ዮሐ ፲፯፥፱-፳) ስለጠቅላላ ምእመንን ባቀረበው ጸሎትም በመስቀል ላይ ሳለ አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» « አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ» ብሎ በመናገር፥ « ራሴን ስለበጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ እሺ በጄ ብዬ መጣሁ ብሎ የተናገረው ቃል ሲፈጸም « አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ እሰጣለሁ ብሎ ነፍሱን ከሥጋው በመለየቱ፥ ከአሮን ክህነት በላቀና በረቀቀ የክህነት ሥርዓት ካህን፥ አስታራቂ መታረቂያ መሥዋዕት ሆኖ በፈጸመው በሞቱ የሰውና የእግዚአብሔር እርቅ ከፍጻሜ ደረሰ። ከአብ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም ይቅር ባይ፥ ታራቂ፥ መስዋዕት ተቀባይ ፥ ሕይወትን አዳይ ዋጋ ከፋይ በመሆኑ በኃጢአት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የሰውና የእግዚአብሔር አንድነት በተዘምዶውና ( ሰው በመሆኑንና) በቤዛነቱ ታደሰ። » ( ምልጃ እርቅና ሰላም፤ ገጽ ፳፩- ፳፪) ይህ የአለቃ አገላለጥ ሰፊ ትንታኔ የሚያስፈልገው ብቻ ሳይሆን፥ በዝምታ ( በጽሞና) ልናሰላስለው የሚገባን ድንቅ የመዳናችን ምሥጢር ነው።
ቤተ ክርስቲያን ስቅለቱን በየዓመቱ ስታከብር፥ የስቅለቱን ንባብ ካህኑ ካነበበ በኋላ ባለው የወንጌል መርገፍ ላይ « ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት ገዓረ ኢየሱስ በቃሉ ወወጽአት መንፈሱ ሶቤሃ፤ በዘጠኝ ሰዓት ኢየሱስ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፤ ያን ጊዜም ነፍሱም ወጣች» ብሎ አሰምቶ በዜማ ይናገራል። ይህም ከማር ፲፭፥፴፯ ላይ ያለው ነው። ይህ ጩኸት የህመም ጩኸት ነው። ይህ ጩኸት የተራ እሩቅ ብእሲ ( ተራ ሰው) ጩኸት ስላይደለ ግን አባቶች እንደሚሉት፥ « ግዳጅ የሚፈጽም» ለቤዛነት የሆነ፥ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ ለዘላለም የሆነ ጩኸት ነው።
፬ኛ. የሰውነቱንና የአምላክነቱን ሥራዎች እንዴት እንደምንናገር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሰጠን ምክር
እዚህ ላይ፥ ቀሲስ ደጀኔ ትልቁ ስህተትህ መለኮት ገንዘብ ያደረጋቸውን የትስብእትን ሥራ በሚገባ ለይተህ ለመዘርዘር አለመቻልህ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የትስብእቱን ሥራ መካድህ እንደሆነ ደጋግሜ ተናግሬአለሁ ። ይህም አውጣኪን ወደ ስህተት የወሰደ መንገድ ዛሬም አንተን ወደ ከባድ ስህተት እየወሰደህ ነው።
በሰውነቱ የሠራቸውን ሥራዎች፥ በአምላክነቱ የሠራቸውን ሥራዎች እንዴት መናገር እንችላለን? እዚህ ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዕብ ፭፥፭ንና የመሳሰሉትን ኃይለ ቃላት በእንዴት ያለ መንገድ መተርጎም እንዳለብን የሰጠውን ምክር፥ ማለትም የቅዱስ ጳውሎስን አካሄድ በጥንቃቄ ያብራራበትን ብትይዝ ኖሮ ወደ ብዙ ስህተት አትገባም ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ቅዱስ ጳውሎስ አጻጻፍ ሲናገር እንዲህ ይላል ፦ « የጳውሎስ ልማድ አንድም ትምህርቱ እንዲህ ነው። የጌታን ልዕልናውን አንድም የአምላክነቱን ነገር ልናገር ባለ ጊዜ፥ (ይመጽእ ለኰንኖ ዓለመ) በዓለም ላይ ለመፍረድ ይመጣል አለ። ትህትናውን አንድም የሰውነቱን ነገር ልናገር ባለ ጊዜ ፥ (አብአ ጸሎተ ወስኢለ) ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤(ወሰምዖ ጽድቆ) ቁርጥ ልመናው ተሰማለት፤ ( ወሰመዮ ሊቀ ካህናት) ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾመው፥ ( ወፈጺሞ ኮነ ዐሣዬ ሕይወት) ሁሉን ከፈጸመ በኋላ ሕይወትን የሚያድል፥ የዘላለም ሕይወት ሆነ አለ።»  ይህን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን የአተረጓጎም ስልት ብትይዝ ለወደፊቱም ከብዙ ስህተት ትድናለህ።


፭ኛ. አማለደ . . . ይማልዳል ስንል ምን ማለታችን ነው?
ስለ ክርስቶስ ምልጃ ስንነጋር ብዙ ጊዜ ከቅዱሳን ጸሎትና ልመና ጋር ስለሚያያዝ ልዩነቱን በግልጥ ለማስቀመጥ የሚከተሉትን ነጥቦች ማስቀመጥ አለብን። የክርስቶስን የማስታረቅ አገልግሎት የምንጠቅሰው የቅዱሳንን ጸሎትና በረከት ለመካድ ከሆነ እንግዲያውስ የክርስቶስን የማስታረቅ አገልግሎት ፈጽሞ አልተረዳንም። እንዲሁ፥ የክርስቶስን የማስታረቅ አገልግሎት የምንክደው የቅዱሳንን ክብር ያጎላን መስሎን ከሆነ ከባድ የሆነ ስህተት ውስጥ ወድቀናል። ሁለቱ ፈጽሞ የተለያዩ ናቸውና ። የሚከተሉትን ነጥቦች በጥንቃቄ ተመልከት።
አንደኛ፥ የክርስቶስ ምልጃ፥ ክርስቶስ የእኛ ሊቀ ካህናት በመሆኑ የሚያከናውነው ነው። በሌላ አነጋገር ማላጅነቱ የትስብእቱ ( የሰውነቱ) ሥራ ነው።  እርሱ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ ነው።መካከለኛነቱም ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑ ነው። የቅዱሳን ጸሎት፥ ከቅዱሳን ጋር ካለን ሕብረት ( communion of saints) የሚመነጭ ነው። በሰማያት ያለችው ድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን እና በምድር ያለችው አንድ ናትና። አባቶቻችን « እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አእጹቂሃ» እንዳሉ።
ሁለተኛ፥ የክርስቶስ ምልጃ በደም የሆነ ነው። ማለትም ክርስቶስ ጸሎቱንና ምልጃውን ያቀረበው ራሱን መሥዋእት አድርጎ በማቅረብ ነው። ዓለምን ለማዳን የፈሰሰ ደም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። የእሩቅ ብእሲ ( የሰው ብቻ ደም) ዓለምን ስለማያድን፥ የፈሰሰው ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ከአቤል ጀምሮ እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ድረስ የፈሰሰው ደም አለምን አልጠቀመም። ዓለምን ያስታረቀው የምልጃ ደም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ሰማዕታት ደማቸውን ቢያፈሱ ለምስክርነት ነው። « ሰማዕታት ከዓዉ ደሞሙ በእንቲአሁ፤ ሰማዕታት ስለእርሱ [ ምስክርነት] ደማቸውን አፈሰሱ» እንደተባለ። የእርሱ ግን የመሥዋዕትነት ነው። የመታረቂያ ነው።
ሦስተኛ ፥ የክርስቶስ ምልጃ ለቤዛነት ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀበትና የሚታረቅበት ነው። ዛሬም በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ነው። ቤዛ ማለት «ለውጥ፥ ምትክ» ማለት ነው። በእኛ ፈንታ ገብቶ የእኛን ጩኸት የጮኸልን ክርስቶስ ነው። የቅዱሳን ምልጃ ግን ወደ ክርስቶስ የሚደረግ ልመና ነው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ እንደተናገሩት « The intercessions of the saints for us are merely praying for us; ቅዱሳን ስለ እኛ የሚማልዱት ስለ እኛ የሚጸልዩት ነው። they are of the pleading type, which is completely different to Christ’s atoning mediation» ይህ የቅዱሳን ጸሎት የልመና ዓይነት ሲሆን፥ ለኃጢአት ሥርየት ከሆነው የክርስቶስ መካከለኛነት ፈጽሞ የተለየ ነው» ይሉናል።
አራተኛ፥ የክርስቶስ ምልጃ እምቢ ያልተባለ አዎን አሜን የሆነ ነው። ክርስቶስ ያማረ ሽቱ አድርጎ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ አባቱ በደስታ ተቀብሎታል። ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ ስምን ተቀብሎአል።
አምስተኛ የክርስቶስ ምልጃ አንድ ጊዜ ለዘላለም የሆነ ነው። በዕለተ አርብ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባከናወነው እርቅ፥ ለዘላለም መታረቂያ ሆኖልናል። ዛሬ እንደገና ክርክር፥ ዛሬ እንደገና መውደቅና መነሣት አያስፈልገውም። መሥዋዕቱ ሞቶ የቀረ አይደለም። ሊቀ ካህናቱ ሞት የገደበው አይደለም። የታረደው በግ ዛሬም ሕያው ስለሆነ፥ ሊቀ ካህናቱም ለዘላለም በሕይወት ስለሚኖር፥ ወደ እርሱ የሚመጡትን ፈጽሞ የሚያድናቸው ነው።
አለቃ አያሌው የተናገሩትን እዚህ ላይ እንደገና መድገሙ መልካም ነው። « እኔ ስለ እነሱ እለምናለሁ» ያለው ቃሉ ጊዜ የሚወስነው ሳይሆን እስከ አለም ፍጻሜ የሚሠራ ነው። ይህንንም « እኔ የምለምንህ ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም። በቃላቸው ስለሚያምኑብኝም ጭምር ነው እንጂ ያለው ቃሉ ያጸናዋል። ዓለምን ሲፈጥር የተናገረው ቃሉ እስከ ዛሬ በመሥራት ላይ እንዳለ፥ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሲሰራ እንደሚኖር፥ ይህም « እኔ ስለ እነሱ እለምናለሁ» ያለው ቃሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሲሰራ ይኖራል። እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ « እርሱ ቢያጸድቅ የሚኮንን ማነው? ሞቶ የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በአብ ቀኝ ተቀምጦአል። ስለ እኛ ይከራከራል» ይላል። ( ሮሜ 8፥34) እንዲሁም « እነዚያን ብዙዎቹን ካህናት ሞት ይሽራቸዋልና ( ያልፋሉና) ለዘለዓለም አይኖሩም። እኔ ሕያው ነኝ ያለ እሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል። ክህነቱም አይሻርም። ፈጽሞ ሕያው ነውና ያስታርቃቸውማልና። በሱ አስታራቂነትም ወደ እግዚአብሔር ለሚቀርቡት ሁሉ ፍጹም ድኅነትን ሊሰጣቸው ይችላል። እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል። እውነተኛ የዋህ ከኃጢአት ሁሉ የራቀ፥ ንጹሕ ከሰማየ ሰማያት የመጠቀ» ያለ ስለዚህ ነው። እስከ ዓለም ፍጻሜ በመሥዋዕትነት በሚቀርብባት በቤተ ክርስቲያን ሲሠራ የሚኖር የማያቋርጥ ኃይል ነውና። ዕብ 7፥23_26) እንግዲህ ጌታ « አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ህልቀተ ዓለም፤ እስከ ዓለም ፍጻሜ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ» ( ማቴ 28፥20) ሲል በተናገረው ቃል መሠረት ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በምታስተምርበት መልእክቱን በምታስተላልፍበት ጊዜና ሥፍራ ሁሉ የሚረዳት፥ በልዩ ልዩ አደባባይም የሚከራከርላት መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ በጻፈው መእክቱ « ይትዋቀስ በእንቲአነ» ስለ እኛ ይከራከራል ብሎ እንደጻፈ፥ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር አምላኪየ ናሁ ወልድከ መሥዋዕት ዘያሰምረከ ወበዝንቱ አናህሲ ሊተ ኵሎ ኃጢአትየ» እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ አንተን ደስ የሚያሰኝህ መሥዋዕት ልጅህ እነሆ፤ በዚህም ኃጢአቴን አስተስርይልኝ» እያለች መሥዋዕቷን በምታቀርብበት ጊዜ ሁሉ « ወአንሰ በእንቲአሆሙ እስዕል» ያለው ቃሉ ስለሚረዳቸው ለዘለዓለም ሕያው ነውና ይማልድላቸዋል» ብሎ ጻፈ።»
ቀሲስ ደጀኔ ስትጽፍ፦ « ጌታችን አምላካችን መድኃኒ ታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-በመዋዕለ ሥጋዌው(በተዋህዶ ሰው በሆነበት ዘመን) ለአብነት(ምሳሌ ሊሆነን) ያደረገውንና ለድኅነታችን ብሎ የፈጸመውን መለ የት ያስፈልጋል። ብዙዎች እነዚህ ሁለት ነገሮች እየተደባለቁባቸው ነው፥“ዛሬም ያማልዳል፤” የሚሉት።ጌታችን አምላካ ችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-እከብር አይል ክቡር፥እጸ ድቅ አይል ጻድቅ ሲሆን፡-የጾመው፥የጸ ለየው፥የሰገደው፥ለእኛ፡-አብነት(ለበጎ ነገር ሁሉ አርአ ያና ምሳሌ) ሊሆነን ነው። ለምሳሌ፡-አልዓዛርን ከማ ስነሣቱ በፊት ወደ አብ ከጸለየ በኋላ፡-“ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤”ብሎአል። ከዚያ በፊት የኢያኢሮስን ልጅ፡-ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንዲት በሆነች ሥልጣኑ አስነሥቶአል። ጥምቀታችንን በጥምቀቱ ቀድሶ የሰጠን፥ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድንጠመቅም ያዘዘን፥ሕገ ወንጌልን የሠራልን፥ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት፣ደሙም ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆ ንበትን ሥርዓተ ቍርባን ሠርቶ ያሳየን ፥ምሥጢሩንም በመስቀል ላይ የፈጸመልን ለድኅነታ ችን ነው።» ብለሃል
ይህ ያስቀመጥከው ቃል በቤተ ክርስቲያናችን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ትምህርት ነው። የምትጽፋቸውን ጽሑፎች ስመለከት ሁለት አደገኛ የሆኑ ሐሰተኛ የመከራከሪያ መንገዶችን ትጠቀማለህ። የመጀመሪያው የማከፈለውን የማይለያየውን መለያየት ( false dichotomy) ነው። ሁለተኛው ደግሞ ፥ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያላሉትን እንዳሉ አድርጎ በማቅረብ ( false premise) ፥ በዚያ ላይ የቅዱሳት መጻሕፍትን ማስረጃ ማቅረብ ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ጌታ ከጽንስ እስከ እርገት ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ለቤዛነት ለደኅንነታችን ያደረጋቸው ሥራዎች ናቸው።  እነዚህ የቤዛነት ሥራዎች  ደግሞ አብነትም ሆነውናል።  ለምሳሌ ጾሙን፥ ጸሎቱን ስግደቱን ለአብነት እንደሆነ ተናግረህ፥ በመስቀሉ የተከናወነው ግን ለድኅነታችን እንደሆነ ተናግረሃል። ይህ ፍጹም ክህደት ነው። በመስቀሉ ላይ የተከናወነው ለደኅንነታችንም ለአብነታችንም መሆኑን ሲገልጥልህ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ « የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤» ብሎአል። ፩ ጴጥ ም. ፪፥፳፩
ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው፥ « የጾመው የጸለየው የሰገደው ለእኛ አብነት ነው» በማለት በጾሙና በጸሎቱ ውስጥ ያለውን  የቤዛነቱን ሥራ ሙሉ በሙሉ ወደጎን ማድረግህ ነው። ቅዱሳት መጻሕፍትም የአበው ትርጓሜዎችም የጸለየው ወደ አብ መሆኑን ተናግረዋል። በመስቀል ላይ « የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» ብሎ የጸለየው ለአብነት ለምሳሌ ብቻ ነውን? ይህን ከቶ ከየት አመጣኸው? በጾሙ ቢያስተምረንም፥ በዚያው በጾሙ ደግሞ ዲያብሎስን ድል ነስቶልናል። ጾሙ የምሳሌ ብቻ አይደለም። የቤዛነትም ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያከናወነው ሥራው ብቻ ሳይሆን፥ ቃሉም ትምህርቱም ሥራውም የቤዛነት እንደሆነ፥ ይህም እስከ አለም ፍጻሜ እንደሚሠራ፥ አለቃ አያሌው ሲናገሩ፥ « እኔ በምድር ላይ ልሠራው የሰጠኸን ሥራ ፈጽሜ አከበርኩህ አሁንም አንተ አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር ግለጠኝ» በማለት ጌታችን ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ አስቀድሞ ወደነበረበት ካረገ በኋላ ምእመናን ኃይሉን፥ ጌትነቱን፥ ምልዓቱን፥ ስፋቱን፥ ርቀቱን፥ ጥንታዊና ዘለዓለማዊነቱን ለማወቅ ችለዋል። ተአምራት ብቻውን አይረዳም፤ ኃይል ካልተሰጠው በቀር። ከሙሴ ጀምሮ ብዙ ነቢያት ተአምራት ሲያደርጉ ኖረው አልፈዋል። ሥራቸውም ታሪክ ሆኖአል። ሠርተዋል፥ ሠርተው ነበር በማለትም ተወስኖአል። የጌታ ሥራ ግን ቃሉም ሥራውም ለዘላለም እንዲሆን እስከ ዓለም ፍጻሜም እንዲሠራ የተነገረና የተደረገ በመሆኑ በመዋዕለ ስብከቱ ብቻ ታይቶ የቀረ፥ ተሰምቶ ያለፈ አይደለም።»  ካሉ በኋላ « ከዕለተ ጽንስ እስከ ዕለተ ዕርገት የፈጸመው የቤዛነት ሥራ በየጊዜው የተነሡ ምዕመናን ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባቸው  ፍጹም ድኅነት ሊሠጣቸው ይችላል።»
መደመደሚያ፤ ምልጃ ለምን አስቸጋሪ ሆነ?
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጽሑፎች ቀሲስ ደጀኔ የገባበትን ስህተቶች ለማሳየት ሞክሬአለሁ። በዚህም ውስጥ እግዚአብሔር ወልድ በሰውነቱ ያከናወናቸው ሥራዎች ለድኅነታችን ወሳኝ የሆኑ ሥራዎች ስለሆኑ ስለእነዚህ ነገሮች ስንናገር በግዴለሽነት ልንናገር እንደማይገባ አመልክቼአለሁ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እንደተናገሩት እኛ ክርስቶስን « አንድ ባሕርይ » ስንል የሚያስረዳው ፍጹም የሆነ ተዋህዶን ነው እንጂ የአምላክነትና የሰውነት መቀያየጥና መደባለቅ አይደለም። አምላክነቱ ወደ ሰውነቱ አልተለወጠም፤ ሰውነቱም ወደ አምላክነቱ አልተቀየረም። በኦርቶዶክሳውያኑ እና በአውጣኪ መካከል የነበረው ትልቅ ልዩነት ይህ ነው። አውጣኪ የቄርሎስ ጠበቃ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ቢያስቀምጥም፥ ለቄርሎስ « አንድ ባሕርይ» ማለትና ለአውጣኪ አንድ ባሕርይ ማለት የተለያየ ነበር። ለቄርሎስ አንድ ባሕርይ ማለት ክርስቶስ በፍጹም ተዋህዶ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ ነው። በዚህም ተዋህዶ ያለመቀላቀል እና ያለመደባለቅ የቃልና የትስብእት መገናዘብ ስላለ፥ መከፈልና መለየት የለም። ለአውጣኪ ግን እንዲህ « አንድ ባሕርይ ሲል ትስብእትንና መለኮትን አንድ ላይ አጣፍቶ ነው። በመሆኑም ለእርሱ የሰውነቱን ነገር ለመናገር ቋንቋ የለውም።




ይህን ባለፉት ሦስት ክፍሎች በተነተንነውና መልስ በሰጠንበት የቀሲስ ደጀኔ ጽሑፎች ውስጥ በግልጥ አይተነዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በላ፥ ጠጣ፥ ማለደ፥ ጸለየ ለቀሲስ ደጀኔ ስድብ ነው። ምክንያቱም እንዴት አምላክ በላ ይባላል። እንዴት አምላክ ጸለየ ይባላል። እውነቱን ነው። የረሳው ግን ያ አምላክ የእኛን ባሕርይ ገንዘብ አድርጎአል። በመሆኑም በልቷል፥ ማልዷል፥ ጸልዮአል። አንቀላፍቷል። ሞቶአል። በሰውነቱ።
በአሁኑ ወቅት ጥቂቶች ያይደሉ፥ ራሳቸውን ሰባኪና ሊቅ ያደረጉ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ሆነው የሚናገሩትና ትምህርት ብለው የሚያቀርቡት ነገር፥ አንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው ትርኪ ምርኪ ሲሆን ፥ አንዳንዱ ደግሞ የለየለት ፍጹም ክህደት ነው።
ለምሳሌ በቅርቡ አንዱ በአውደ ምሕረት ላይ ቆሞ በሥነ ሥርዓት የሰበከው እንዲህ ይላል። « ተአምረ ማርያም ከሌለ፥ ማርያም የለችም፥ ማርያም ከሌለች፥ ክርስቶስ የለም፥ ክርስቶስ ከሌለ ሥላሴ የለም፤ ሥላሴ ከሌለ እግዚአብሔር የለም።» ይላል። ይህ የኑፋቄ ሁሉ ኑፋቄ ነው። ይህ ሰባኪ እንዲህ ብሎ የሰበከው፥ ነገር አሳምራለሁ፥ የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት የማይቀበሉ ሰዎችን እቃወምበታለሁ ብሎ ነው።  ነገር ግን ያስተማረው ሀልዎተ እግዚአብሔርን ገደል የከተተ ትምህርት ነው።
ታዲያ ብዙዎቹ ወደዚህ ዓይነት ክህደት ውስጥ የሚገቡት ትምህርታቸውን ቤተ ክርስቲያኒቱ ባስቀመጠችው ቀዋሚ ትምህርት ላይ ስለማይመሠርቱና  ፕሮቴስታንቶችን ወይም ሌሎች የእምነት ድርጅቶችን በማየት እምነታቸውን ለመቅረጽ ስለሚሞክሩ ነው።
ለምሳሌ አንዳንድ ፕሮቴስታንቶች የቅዱሳንን ጸሎትና ምልጃ በመካድ የሚጠቅሱት ሮሜ 8፥34ን፥ ዮሐ 2፥1ን ነው። እነዚህ ንባቦች ክርስቶስ ለእኛ አስታራቂያችን፥ ተከራካሪያችን ጠበቃችን እንደሆነ የሚገልጡ ንባቦች ናቸው። ታዲያ ጥቂት ያይደሉ የኛዎቹ መልስ ሰጪዎች የሚያደርጉትና እያደረጉ ያሉት፥ አንደኛ ሙሉ በሙሉ የክርስቶስን ማስታረቅ፥ምልጃውን፥ ጠበቃነቱን መካድ፥ ከዚያ አልፎ ደግሞ እነዚህን ምንባቦች ለመቀየር ወይም ለማደብዘዝ መሞከር ነው። ይህ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚሠነዘር ወንጀል ነው።
ማድረግ ያለብን ምን ነበር ? ማድረግ ያለብን ፥ የክርስቶስን የማስታረቅ አገልግሎት፥ የክርስቶስን መካከለኛነት መካድ ሳይሆን በክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎት እና በቅዱሳን ጸሎት መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየት ነው፤   የክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎት መዳናችን የተመሠረተበት ታላቅ ምሥጢር ነው። በግዴለሽነት ወደጎን የምናደርገው አይደለም። ለድርድርም የሚቀርብ አይደለም።

የክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ ከፍጡራን የልመና ጸሎት ፍጹም የተለየ ነውና። ከዚህ በፊት በሌሎች ጽሑፎቻችን ላይ የጠቀስነው ቢሆንም ሊቀ ሊቃውንት አባ መልአኩ ታከለ የተናገሩትን እንደገና እንጥቀስ ፥ « ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅም፥ ጳውሎስን አራቂ ዘውእቱ አምሳሊሁ ለክርስቶስ፤ በክርስቶስ አምሳል አስታራቂ ( አማላጅ) ነው ብሏል የክርስቶስ አራቂነት በሞቱ ሲሆን የጳውሎስ ግን በጸሎቱና በትምህርቱ። ስያሜው በመገናኘቱ ምንም አያስደንቅም ተግባሩ የተለያየ ነውና ከዚህ የተነሳ ትምህርቱን መመለክቱ ተገቢ ነው። ይህን ለመረዳት የቤተክርስቲያንን ትምህርት ማወቅ ያስፈልጋል።» ብፁዕ አቡነ ሽኖዳ ያሉት ይህን ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳም ለፕሮቴስታንቶች በሰጡት መልስ የቅዱሳንን ምልጃ እና የክርስቶስን ምልጃ ለይተው በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ሲያብራሩ በመጥቀስ ጽሑፋችንን እንደምድም። በነገራችን ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሽኖዳ ከክርስቶስ ምልጃና መካከለኛነት ጋር አዛምደው የጠቀሱአቸውን ንባቦች በጥንቃቄ ተመልከቱ እና የዘመናችን አውጣኪዎች እንዴት እንደሚክዷቸውና ለመቀየር እንደሚሞክሩ አስተውሉ። ከ
The mediation of the Lord Jesus Christ is an atonement, which means that He mediates for the forgiveness of our sins, being the Atoner who paid our debts on our behalf. His mediation means that He says to the Father: “Do not count their transgressions because I have carried their iniquity” (Is.53: 6). Thus He stands as a Mediator between God and men; or rather, He is the only Mediator between God and men; He fulfilled God’s Divine Justice and granted people the forgiveness of sins, by dying for them.
የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ፥ ለኃጢአት ሥርየት ( atonement) ነው። ይህም ማለት፥ ስለ እኛ ዕዳችንን የከፈለ ማስተስረያ በመሆን፥ ለኃጢአታችን ይቅርታ መማለዱ ነው። የእርሱ ምልጃ ማለት፥ ለአባቱ « አባት ሆይ በደላቸውን አትቁጠርባቸው፤ ምክንያቱም በደላቸውን እኔ ተሸክሜአለሁ» ማለቱ ነው። ( ኢሳ ፶፫፥፮) በመሆኑም፥ እርሱ በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ ሆኖ ቆሞአል። ወይም በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ብቸኛው መካከለኛ ነው። እርሱ ስለ ሕዝቡ በመሞት፥ የእግዚአብሔርን ፍትሕ ያረካና ለሕዝቡ የኃጢአት ሥርየትን የሰጠ ነው። This is what St. John the Apostle mea
nt when he said: “And if anyone sins, we have an Advocate with the Father, Jesus Christ the righteous. And He Himself is the propitiation for our sins, and not for ours only but also for the whole world”(1John.2: 1,2). Here, the atoning mediation is very clear. It is a mediation for the sinner: “If anyone sins”, and this sinner needs atonement. The only One who offered this atonement was Jesus Christ the righteous. Hence He can mediate for us through His blood which was shed for us.
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ «ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።»  በማለት የተናገረው ይህን ነው ፩ ዮሐ ፪፥፩፡፪። በዚህ፥ የማስተሥረያ መካከለኛነቱ ግልጥ ነው። መካከለኛነቱ ለኃጢአተኛ ነው። « ማንም ኃጢአት ቢያደርግ»፤ ይህ  ኃጢአተኛ የኃጢአት ሥርየት ያስፈልገዋል። ይህን የኃጢአት ማስተስሪያ ማቅረብ የሚችል ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በመሆኑም እርሱ ስለ እኛ ባፈሰሰው በደሙ በኩል ይማልድልን ዘንድ ይችላል።

The same meaning is given in the words of St. Paul the Apostle about the Lord Jesus Christ being the only Mediator between God and men. He says: “For there is one God and one Mediator between God and men, the Man Christ Jesus, who gave Himself a ransom for all” (1Tim.2: 5,6). The Lord Jesus Christ mediates for us as the Redeemer who sacrificed Himself and paid the price of our sins. This type of mediation is utterly unquestionable. It is attributed to Christ only, whereas the intercessions of the saints has no connection with atonement or redemption. It is intercessions for us to the Lord Jesus Christ Himself.
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ብቸኛው መካከለኛ ስለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውም ተመሳሳይ ትርጕም አለው። «አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥» ፩ ጢሞ ፪፥፭፡፮። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ የሚሆንልን፥ ራሱን መስዋዕት ያደረገና የኃጢአታችን ዋጋ የከፈለልን ቤዛ ሆኖልን ነው። እንዲህ ዓይነቱ መካከለኛነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ነው። የሚሰጠውም ለክርስቶስ ብቻ ነው። የቅዱሳን ምልጃ በአንጻሩ፥ ከቤዛነት ( redemption) እና ከኃጢአት ማስተስሪያ ( atonement) ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የቅዱሳን ምልጃ ስለ እኛ ወደ ራሱ ወደ ጌታ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመለመን ነገር ነው።» በማለት አብራርተው ተናግረዋል።
እኛም በዚሁ ለቀሲስ ደጀኔ የሰጠነውን መልስ እንደመድማለን። ይህን እንድንጽፍና ስለ እምነታችን እንድንመሰክር አቅምና ጉልበት የሆነን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይክበር ይመስገን።