Thursday, August 14, 2014

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሷል!

  • የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲፈራርስ ዝምታው እስከመቼ?
  •  
  •  ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ጉዳይ ምላሻቸው ምን ይሆን?

ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚለው ቃል ከወረቀት ባለፈ በመሬት ላይ ተፈሚነቱ የሚታየው በጣም በጥቂቱ ነው። በተለይም ቤተ ክርስቲያኒቱ አለኝ በምትለው ማእርገ ክህነት በኩል ዲቁና፤ ቅስና ( ምንኩስና) ቁምስና በሙሉ የሚሰጠው ለማንና መስፈርቱ ምን እንደሆነ በማይታወቅ መልኩ ሥርዓተ የለሽ ሆኖ ይታይበታል። እነ መቶ አለቃ ግርማ ወንድሙ ሳይቀሩ በር የሚዘጋ መስቀል ተሸክመው እያሳለሙ በአጥማቂነት ተሰማርተው ገንዘብ ይሰበስባሉ። ከዚህ በፊት ወደእስራኤል አቅንቶ የነበረው ግርማ ወንድሙ ገና ገንዘብ መሰብሰብ ሲጀምር አንዷን ሴት ሲያጠምቅ ጎረቤቷ ቡዳ ሆና በላቻት በማሰኘቱ፤ ቡዳ ናት የተባለችው ሴት ፍርድ ቤት በስም አጥፊነት ከሳው መጥሪያ ብታመጣበት ሌሊቱኑ ፈርጥጦ ወደኢትዮጵያ ማምለጡን ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ሰምተን ተገርመን ነበር። ባለቤት የሌላትን ቤተ ክርስቲያን እየተዘዋወረ በክፉ መንፈስ የሚበጠብጠው ግርማ አሁን ደግሞ ወደአውሮፓ ዘልቆ በጣሊያን የዘረፋውንና የቡዳ በላሽ ዜማውን እያስነካው ይገኛል። እነባህታዊ ገብረ መስቀል ማርያምን ተገለጸችልኝ እያሉ ህዝቡን ሲያጭበረብሩ እንዳልነበር ብህትውናውን እርግፍ አድርገው ቆንጆ መርጠው ሚስት አግብተው ልጆች ወልደው ማርያም ተገለጸችልኝ፤ ገብርኤልን አየሁት ከሚል ማደናገሪያ ነጻ ወጥተዋል። ከማጭበር በር ይህኛው የተሻለ አማራጭ ይመስለናል።
ይህ ማእርገ ክህነት የሚባለው ሹመት በአንዳንዶች ዘንድ የክብር ዶክትሬት ይመስል ከስም ባለፈና የሕዝቡን ግንባር ከሚገጩበት በስተቀር እንደማኅበረ ቅዱሳን ባሉ ማኅበራት ዘንድም የአገልግሎት ዋጋ የሌለው መሳሪያ ሆኖ ይገኛል። በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉበት አይታይም። የማዕረጉን ስም የሚፈልጉት ክህነት የላቸውም እንዳይባሉና በክህነት ሽፋን በሚገኘው ክብር የመበለቶችን ቤት ለመዝረፍ ስለሚረዳ እንጂ ከመጀመሪያው በድንግልና ጸንተው ለማዕርገ ዲቁና በቅተው «ተንሥኡ፤ ጸልዩ» እያሉ ሲያገለግሉበት ቆይተው፤ በኋላም በስርዓተ ቤተ ክርስቲያን በተክሊል በድንግልና የጸናች አግብተው አይደለም። ሲጀመር ጀምሮ ዲቁናም ይሁን ቅስና የተቀበሉት ሰዎች ድንግላቸው የፈረሰበትን ጊዜ ራሳቸው በትክክል አያውቁትም። ራሳቸው በድንግልና ሳይቆዩ፤ ድንግልና እንደፈንጣጣ በጠፋበት ዘመን ድንግል አግብተው አይቀስሱም።  በተለይ ወንዶቹ አጭበርባሪዎች፤ ቀሳጮችና መልቴዎች ናቸው። በዚህ ዙሪያ ሀገር ሰፈሩን ሲያዳርሱ የኖሩ የዘመኑ ቀሳውስትና መነኮሳት ነን ባዮች ቅስናን እንደማጭበርበሪያ ይጠቀሙበታል። ቅዱስ በተባለው መቅደስ ገብተው በርኩስናቸው ሕዝቡን ያታልሉበታል። ይህ ዐመፃና ማታለል በሀገር ላይ ጥፋትን፤ በሕዝብ ላይ ቁጣን ማምጣቱ አይቀርም። ማንም እመራበታለሁ ብሎ ላወጣው ለራሱ ሕግ የማይታዘዝ ከሆነ የሚጠፋው በዚያው በራሱ ሕግ ነው።
«ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል» ሮሜ 2፤12
ዛሬ ሁሉም ከዚህ ከራሳቸው የሕግ ክብር ስለወረዱ ማንም ምንንም አይቆጣጠርም። ሥርዓት ፈረሰ፤ ሕግ ተጣሰ የሚል አንድም ስንኳ የለም። «ኩሉ ዐረየ፤ ወኅቡረ ዐለወ» እንዳለው ዳዊት በመዝሙሩ ሁላቸውም ተሳስተዋል፤ ሁላቸውም በዐመጻ ስለተስተካከሉ ዲቁና ሰጪውም ተቀባዩም ከሥርዓት ውጪ ሆነዋል።  ከዚህ በታች የቀረበውም ጽሁፍ ይህንን መሠረት ያደረገ ነው።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን «እንበለ አሐዱ ኄር፤ ኢይኀድጋ ለሀገር» ለሀገር እንዲሉ አንድ ተቆርቋሪ ኤርትራዊ ቄስ ከሀገረ እስራኤል-ቴል አቪቭ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ለልዩ ልዩ ድረ ገጾች በግልባጭ ሲልክ ለእኛ የደረሰውን ጽሁፍ እንዳለ አቅርበነዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምን ሆነች?

በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከመለያየታቸው በስተቀር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ዛሬም ድረስ አንድ ነን። ሥርዓቱና ሕግጋቱ የተለያየ አይደለም። በማዕረገ ክህነት አሰጣጥ ልዩነት ያለን አይመስለንም።  ነገር ግን እጅግ አሳዝኝና አስገራሚ ነገር ስናይ የምንጠይቀው አጥተናል። በተደረገው ሁኔታ እኛ በእስራኤል የምንገኝ ኤርትራውያን በተደረገው አድራጎት ተጎድተናል። ይኸውም ለሰሚ የሚከብድና ከምናውቃት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህግጋት ውጪ ማዕረገ ክህነት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ሲሰጥ በማየታችን በጣም አዝነናል። ነገሩን በአጭሩ አስረዳለሁ።
ሰውየው በትግራይ ክፍለሀገር ሰንቃጣ እንደተወለደ አውቀነዋል። ስሙም ሓጎስ አስገዶም ይባላል። በትግራይ ክፍለ ሀገር ይህ ሓጎስ አስገዶም የተባለ ሰውዬ አባ ሰላማ የሚባል ማኅበር አቁሞ ህዝብ ለህዝብ ሲያጋጭ ተይዞ ሶስት አመት ወኅኒ ታስሮ ነበር። በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ማኅበሩ በትእዛዝ ፈረሰ። በሲኖዶስም ተወሰነበት። ተስፋ ያልቆረጠው ይህ ሓጎስ አሰገዶም የተባለ ሰውዬው ወደ ሽመልባ የኤትራውያን ስደተኛ ካምፖ በመግባት ባሕታዊ ወልደ ሥላሴ እባለሎህ በማለት ማደናገር ጀመረ።
ባህታዊ ነኝ የሚለው ሓጎስ አስገዶም

በዚያም በእሱ የተጀመረ ረብሻ በሽመልባ ባሉ የኤርትራ ቤተክርስቲያን በመበራከቱ ጥቂት ተከታዮች አስከትሎ በሱዳን አድርጎ ሊቢያ ገባ። ሊቢያ ሲገባም አባ ሰላማ መልዕክት ነግረውኛል ከዛሬ ጀምሮ አንተ ሞኖክሴ ነህ ብለውኛል ብሎ አባ ሳሙኤል ነኝ አለ። ከዚያም ይህ ሓጎስ አስገዶም ከሊቢያ ወደእስራኤል ሀገር ከኤርትራውያን ጋር ገብቶ ኤርትራዊ ነኝ ብሎ የስደተኛ ወረቀት ከወሰደ በኋላ ሳይሞኖክስ አባ ሳሙኤል ተብሎ እየተጠራ ቆየ። አጠምቃለሁ እያለ ሲያታልል፤ ህዝብ ሲያሳብድ፤ ገንዘብ ሲሰበስብ ቆይቶ ብዙ ኤትራውያን ደግሞ አንተ ሞኖክሴ አይደለህም፤ ለምን አባ ትባላለህ። ክህነት የለህም ለምን ታሳልማለህ።  ንስሀ ለምን ትሰጣለህ ስንለው የእኔ ክህነት በአባ ሰላማ ፍሬምናጦስ አማላጅነት ከሰማይ ነው የተሰጠኝ፤ የእናንተ ክህነት ግን ከኃጢአተኛ ጳጳስ እጅ የተሰጠ ነው እያለ ሲሳደብ በማየታችን ህዝቡ በዚህ አታላይ ሰው እንዳይታለል ስናስተምር ተናዶ ወደኢየሩሳሌም በመሄድ ከኢትዮጵያ ሊቀጳጳስና አንዳንድ መነኮሳት ጋር በስውር መገናኘቱን ቀጠለ።
ባህታዊ ወልደ ሥላሴ ነኝ እያለ በሽመልባ ሲያታልል

 ከዚያም ከሊቀ ጳጳሱ አባ ዳንኤል ዘንድ ዲቁና ተቀበልኩ አለና በአስማቱ ለሚያታልላቸው ደጋፊዎቹ  ማዕረጉ ሲሰጠው የሚያሳይ ፎቶና ፊልም አሳየ። ትንሽ ቆይቶ ሞኖኮስኩኝ ብሎ እንደቦብ ማርሊ ያሳደገውን ጸጉሩን ቆርጦ ጥቁር ቆብና ቀሚስ አድርጎ መጣ። አንተን አመነኮሰች ቤተ ክርስቲያን? ብለን አዘንን። አለቀስን።
በአባ ሳሙኤል ስም ቄስና መነኩሴ ነኝ አለን ደግሞ

ከሱ ጋር የነበሩና ስናስተምራቸው የተመለሱ ሁለት ዲያቆናት ለመመንኮስ 50 ሺህ ሼቄል ከፍሏል አሉን። ለሊቀ ጳጳሱና ከመነኮሳቱ መካከል አባ ፍስሐና አባ ብርሃና መስቀል የተባሉም ገንዘብ መቀበላቸውን አሁንም ይመሰክራሉ። የሰው ማስረጃ አለን። ሌሎችም መነኮሳት የተቀበሉ አሉ። ይህ አታላይ አባ ሳሙኤል የተባለው ትንሽ ቆይቶ የቅስና ማዕረግ ከአባ ዳንኤል ተሰጠኝ ብሎ በደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሥርዓት በቢዲዮና በፎቶ  ቴልአቪቭ አምጥቶ ለተከታዮቹ አሳየ። ይህ ሁሉ ማስረጃ በእጃችን ይገኛል።
ምንም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሙያ ለሌለው፤ ዲቁና ሳይኖረው  ለሓገስ አስገዶም ቅስና ሲሰጡት አቡነ ዳንኤል ናቸው

 የዚህ ሁሉ አስተባባሪ አባ ፍስሐ ይባላሉ። አባ ብርሃነ መስቀል የተባሉት፤ አባ ተወልደ የተባሉትም አብረውት አሉ። ገንዘብ የተቀበሉ መኖክሴዎች ዝርዝር በእጃችን አለ። በቁጥር ትንሾች ቢሆኑም የቤተ ክርስቲያን ስርዓት ጠፋ ብለው የተናገሩ ቢኖሩም የሰማቸው የለም።  ገንዘብ የሁሉንም አፍ ዝም አሰኝቷል።



 እኛ የምናዝነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ሹማምንት በገንዘብ ስልጣነ ክህነት እየሰጡ ለምን ቤተ ክርስቲያንን ያሰድባሉ? የኢየሩሳሌም ገዳም ሞኖክሴዎችስ ለምን በገንዘብ ይደለላሉ? ክህነት እንደዚህ ነው? ሙንኩስናስ እንደዚህ ነው? በበኩላችን ይህን ሰውዬ ያለአግባብ እያታለለ ከኤርትራውያን እጅ የወሰደውን በብዙ መቶ ሺህ ሼቄል ለማስመለስና በህግ ፊት ለማቆም ማስረጃዎቻችንን ይዘናል። እናንተ በሰጣችሁት ክህነት አንታለልም። አንታወክም። ለነገሩ ቤተ ክርስቲያንን አዋርዳችሁታል። ሓጎስ አስገዶም ቄስ ሆነ? ሚስቱንም አምጥቶ አመነኮሰ። አንድ ቤት አንድ ላይ ይኖራሉ። አይ ኦርቶዶክስ፤ እንደዚህ መሆና ያሳዝናል። ሕግ ካለ፤ ዳኛ ካለ ኢየሩሳሌም ያሉ ሞነኮሳትን ከገዳሙ ማባረር ነበር። ለሓጎስ አስገዶም ቅስና የሰጡ ሊቀጳጳሱም መቀጣት ነበረባቸው።
ያሳዝናል። ያሳዝናል። በትክክልም ዘመኑ ተጨርሷል። ክህነትና ሙንኩስና  በገንዘብ ሆነ። ኤሎሄ ኤሎሄ ይባላል።

ለምእመን በገንዘብ ክህነት እንዲያገኝ ያደረጉ አባ ብርሃነ መስቀል የሚባሉት በቀኙ፤ አባ ፍስሐ የሚባሉት አባ ፍስሐ የሚባሉት በግራ በመሀል አቡነ ዳንኤልና ሲሆኑ በደብረ ገነት ቤተመቅደስ ውስጥ ሓጎስ አስገዶም ፤ ወልደሥላሴና አባ ሳሙኤል የተባለው ቅስና ሲቀበል የሚያሳይ ፎቶ። የዚህ ሥርዓት ሙሉ ቪዲዮ በእጃችን አለን።
             
                     ፍትዊ አንገሶም ቴልአቪቭ

Monday, August 11, 2014

ትክክለኛው ሃይማኖት የቱ ነው?



 ቀልጣፋ ሬስቶራንቶች በቀላሉ የሚስቡን የፈለግነውን ምግብ በምንወደው መንገድ እንድናዝ መንገድ ስለሚከፍቱልን ነው። ጥቂት ካፌዎች ደግሞ ከመቶ በላይ የተለያዩ የቡና ጣዕም እንደሚያቀርቡ በጉራ ይናገራሉ። መኖሪያ ቤቶችና መኪናዎችን ስንገዛ እንኳ የምንፈልገው ምርጫ እንዲያሟላ እንሻለን። በቼኮላት፣ በቫኒላና በእንጆሪ ዓለም ታጥረን መኖር አንፈልግም። ፍላጎት ንጉሥ ነው! እንደግላዊ ፍላጎትህና ምርጫህ የምታገኝበት ሁሉ የተሟላበት ዘመን ነው።
ለአንተ ብቻ ትክክለኛ ሃይማኖት የማግኘቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል? ወቀሳ አልባ፣ ብዙ ጫና የሌለውና ይህንን አድርግ አታድርግ እያለ የማያስቸግር ሐይማኖት ብታገኝስ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ያውና እዚያ አለ ነገር ግን ሃይማኖት እንደሚወዱት አይስክሬም የሚመረጥ ነው እንዴ?
ትኩረታችንን ለመሳብ የሚሻሙ በርካታ ድምፆች ስላሉ ለምን ብሎ ነው አንድ ሰው ኢየሱስን ከሌሎች ማለትም ከመሐመድ ወይም ከኮንፊሸየስ፣ ከቡድሐ ወይም ቻርለስ ቴዝ ራስል ወይም ከጆሴፍ እስሚዝ አስበልጦ የሚመርጠው? ዞሮ ዞሮ ሁሉም መንገዶች የሚያደርሱት ወደ መንግስተ ሰማይ አይደለም እንዴ? በመሰረቱ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉም እንዴ? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መንግስተ ሰማይ አያመሩም። ሁሉም መንገዶች ወደ ኢንዲያና መቼም አያደርሱም።
ኢየሱስ ብቻውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ይናገራል።
1/  ምክንያቱም ኢየሱስ ብቻ ነው ሞትን ያሸነፈው። እስካሁን ድረስ መሐመድ፣ ኮንፊሸየስና ሌሎች በመቃብር በስብሰው ይገኛሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በራሱ ስልጣን በጨካኙ የሮማውያን መስቀል ከሞተና ከተቀበረ ከሦስት ቀን በኋለ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቶአል። በሞት ላይ ስልጣን ያለው ማንኛውም ሰው ትኩረታችን ሊስብ ግድ ይላል። ማንም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ግለሰብ ሲናገር ልናደምጠው አስፈላጊ ነው። ሞትን ማሸነፍ የቻለ ከፍጥረታት መካከል ማንም የለም። ከሰማይ የመጣው ብቻ ሞትን አሸንፎ ወደሰማይ ወጥቷል።ስለዚህ እንዲህ ያለው አሸናፊ የተናገረው የእምነት መሠረት መሆን አለበት። ሰው ሟች መሆኑን ያውቃል። ሟች ደግሞ ከሞት ለማምለጥ የሚችለው በሞት ላይ ባለሙሉ ሥልጣን በሆነ ክንድ ላይ ሲያርፍ ነውና ኢየሱስን ማመን የግድ ይለዋል። ሌላ ማንም አዳኝ የለም።
2/ የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣዔ ምስክር ያለውና እውነት ነው።  የኢየሱስን ትንሣዔ የሚደግፈው መረጃ የሚያጥለቀልቅ ነው።   ሮማውያንና ሰቃልያኑ ካህናት የኢየሱስን መቃብር ማስጠበቅ ያስፈለጋቸው «በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ» ያለውን ቃሉን ይዘው እንጂ የሞተ ሰው መቃብር ስለሚጠበቅ አልነበረም።  አዎ ትንሣዔውን ለመከላከል ወታደሮች ከመቃብሩ ማንም እንዳይወጣ፤ ወደመቃብሩም ማንም እንዳይደርስ አድርገው አስጠብቀው ነበር። ነገር ግን የመቃብሩ ቦታ ባዶ ሆኗል!  እንደተናገረው አልተነሳም እንዳይሉ የኢየሱስ ጠላቶች ያን ሁሉ ስለትንሣዔው የተነዛውን ወሬ ለማክሸፍ የበሰበሰውን አካሉን በማቅረብ በቀላሉ ያስታግሱት ነበር። ግን አልቻሉም፤ መላው ሲጠፋባቸው ደቀመዛሙርቱ ሬሳውን ሰርቀውት ይሆን? አሉ።  ከሐዋርያቱ መካከል ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ የሸሹት በጊዜ ነው። የሸሹ ሰዎች ተመልሰው ከሮማ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ሰረቁት ማለት የማይመስል ነገር ነው። ቀላሉ ሃቅ ግን የኢየሱስ ትንሳኤ እንዲሁ ተነግሮ ተገልፆ የሚያልቅ መች ሆነና! ትንሣዔውን ያለምስክር ያልተወ ኢየሱስ ግን በአንድና በሁለት ሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በአምስት መቶ ሰዎች ፊት ትንሣዔውን አስመስክሯል።

«መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ» 1ኛ ቆሮ 15፤4-8

ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማመን የሚያስችላቸው በቂ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደኢየሱስ ሞትን ያሸነፈ፤ ትንሣዔውን በምስክር ያረጋገጠ ማንም የለም። ስለዚህ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም ሰው ሊደመጥ ይገባል። ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን አረጋግጧል። ስለዚህ የሚናገረውን መስማት ይገባናል። ለድነት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን ራሱ ይናገራል።(ዮሐንስ 14፡ 6)። ካሉትም ብዙ መንገዶች አንዱ አይደለም። ኢየሱስ ብቸኛ የድነት መንገድ ነው። ሌላ መንገድ ሁሉ በትንሣዔና በሕይወት ላይ ሥልጣን የሌለው የሞት መንገድ ነው።
3/ ኢየሱስ ከሸክም ያሳርፋል። በዚህ ምድር ላይ ከሸክም አሳርፋችኋለሁ ብሎ ቃል የገባ አንድም ሥጋ ለባሽ የለም። ይህ ብቸኛ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች፤ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡ 28)። ሕይወትም አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ደምተናል፣ ቆስለናል፣ ጦርነትንም እንፈራለን። ዓለምም አስጨናቂ እየሆነች ነው። ስለዚህ የሚያሳርፈንን ብንፈልግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከኢየሱስ በቀር ሸክም የከበዳችሁ ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ማንም ሌላ የለም። በትንሣዔውና በሕይወቱ የታመነ ኢየሱስ ይህንን የማለት ብቃት ስላለው በእርሱ ላይ ማረፍ ከአስጨናቂው ዓለም ለመዳናችን ዋስትናችን ነው።
ስለዚህ ምን ትፈልጋላችሁ? ከኃጢአት፤ ከድካም፤ ከተስፋ መቁረጥ በንስሐ መታደስ ወይስ  የአንዱ ሃይማኖት አባል በመሆን ብቻ መኖር? ሕያው የሆነ አዳኝ ወይስ “ከሞቱት በርካታ ነቢያት ወይም ጻድቅ” አንዱን ተስፋ ማድረግ? ትርጉም ያለው ግንኙነት ወይስ ተራ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት መከተል?
ኢየሱስ አማራጭ ሳይሆን ምርጫ ነው! ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈሳዊ ድርጅት ወይም የአንዱ ተቋም ስያሜና የዚያ አባል ሆኖ መኖር ማለት አይደለም።  ከእግዚአብሔር  አብ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ትፈልግ እንደሆን ሃይማኖትህ ኢየሱስን ማመን ነው። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው»  ይላል መጽሐፍ። (ዮሐንስ 3፡ 36) አንዳንዶች ይህንንማ እናምናለን ነገር ግን ትክክለኛው እምነት ያለው በኛ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ አባል ሁነን ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በማኅበር ስለመጸለይ ይነግረናል እንጂ ኢየሱስን ለማመን የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተቋም አባል ሁን የሚል ትዕዛዝ የለውም። ኢየሱስ በሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ የሃይማኖት ድርጅት ሊመሠረት አልመጣም።

«የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን» 1ኛ ዮሐ 5፤15

(www.Gotquestions.org)ተሻሽሎ የተወሰደ

Friday, August 1, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

(ዘርዓ ያዕቆብ ፈላስፋ) ክፍል ሁለት

የሰው  ፍጥረት  ታካችና  ደካማ  መሰለኝ፡፡ ሰው  ግን ፍቅርን  ቢወዳትና  በጣም  ቢያፈቅራት  የተሸሸገውንም  ፍጥረትን  ቢያውቅ ይወዳል፡፡ ይህም  ነገር  እጅግ  ጥልቅ  ነውና  በትልቅ  ድካምና  ትዕግስት  ካልሆነ  በስተቀር  አይገኝም፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን፡ “ከፀሐይ  በታች  ስለተደረገው  ሁሉ  ጥበብን  ለመፈለግና  ለመመርመር  ልቤን  ሰጠሁ፡፡  እግዚአብሔር  ለሰው  ልጆች  እንዲደክሙበት የሰጣቸውን  ክፉ  ስራ  አየሁ”ይላል፡፡

   ስለዚህ  ሰዎች  ሊመረምሩት  አይፈልጉም፡፡  ሳይመረምሩ  ከአባቶቻቸው  የሰሙትን  ማመን  ይመርጣሉ፡፡  ነገር  ግን እግዚአብሔር  ሰውን  የምግባሩ  ጌታ  ክፉ  ወይም  መልካም  የፈለገውን  እንዲሆን  ፈጠረው፡፡  ሰውም  ክፉና  ዋሾ  መሆንን  ቢመርጥ ለክፋቱ የሚገባውን  ቅጣት  እስኪያገኝ  ድረስ  ይችላል፡፡ ነገር  ግን  ሰው ሥጋዊ  ነውና  ለሥጋው  የሚመቸውን  ይወዳል፡፡ ክፉ  ይሁን  መልካም  ለስጋው  ፍላጎት የሚያገኝበትን  መንገድ  ሁሉ  ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር  ሰው  የፈለገውን  እንዲሆን  ለመምረጥ  መብት  ሰጠው  እንጂ  ለክፋት  አልፈጠረውም፡፡ ስለዚህ  መምረጥ  ክፉ  ቢሆን  ለቅጣት  መልካም  ቢሆን  ደግሞ  የመልካምነት  ዋጋ  ለመቀበል  የተዘጋጀ  እንዲሆን  እድል  ሰጠው፡፡

  በሕዝብ  ዘንድ  ክብርና  ገንዘብ  ለማግኝት  የሚፈልግ  ዋሾ  ሰው  ነው፡፡  ዋሾ  ሰው  ይህን  በሐሰተኛ  መንገድ  ሲያገኝ  እዉነት አስመስሎ ሀሰት  ይናገራል፡፡ ሊመረምሩ  የማይፈልጉ  ሰዎች  እውነት  ይመስላቸውና  በእርሱ  በጽኑ  ሃይማኖት  ያምናሉ፡፡ እስኪ  ሕዝባችን  በስንት  ውሸት  ያምናል?  በጽኑ  ሃይማኖት  ያምናል፡፡  በሃሳበ  ከዋክብትና  በሌላም  አስማት፣  አጋንንት  በመሳብና በመርጨት፣ አስማት በማድረግ፣ በጥንቆላ  ሁሉ  ያምናሉ፡፡ ይህንን  ሁሉ  መርምረው  እውነቱን  አግኝተው  አያምኑም፡፡ ነገር  ግን  ከአባቶቻቸው  ሰምተው ያምናሉ፡፡ እነዚያስ  የፊተኞቹ  ገንዘብና  ክብር ለማግኝት  ካልሆነ በቀር ስለምን  ዋሹ?  እንዲሁ  ህዝብን  ሊገዙ  የሚፈልጉ  ሁሉ  እውነት  እንነግራቸኋለን  እግዚአብሔር  ወደናንተ  ላከን  ይሏቸዋል፡፡  ሕዝቡም  ያምናሉ፡፡
ከነርሱም  በኋላ  የመጡት  እነርሱ  ሳይመረምሩ  የተቀበሏትን  የአባቶቻቸውን  እምነት  አልመረመሩም፡፡  ከዚያ  ይልቅ  ለእውነትና ለሃይማኖታቸው  ማስረጃ  ታሪክን፣ ምልክቶችን ፣ ተዓምራትን  እየጨመሩ እውነት  አስመስለው  አጸኑት፡፡  በነገሩ ሁሉ እግዚአብሔርን  ስም ጨመሩ።  እግዚአብሔርንም የሐሰኞች ተካፋይና  የሐሰት  ምስክር  አደረጉት፡፡

  ጥልቅ   ምርመራ  ስለ  ሙሴና  መሐመድ  ሕግጋት

 ለሚመረምር  ግን  እውነት  ቶሎ  ይገለፃል፡፡  ፈጣሪ  በሰው  ልብ  ያስገባውን  ንጹህ  ልቦና  የፍጥረት  ሕግጋትና  ስርዓትን  ተመልክቶ የሚመረምር  እርሱ  እውነትን  ያገኛል፡፡ ሙሴ  ፈቃዱንና  ሕጉን  ልነግራችሁ  ከእግዚአብሔር  ዘንድ  ተልኬ  መጣሁ  ይላል፡፡ ከሆነ ታዲያ «ሴት በወር አበባ ወቅት የረከሰች ናት» ለምን ይላል? የሙሴ  መጽሐፍ  ከፍጥረት  ሕግ  ሥርዓትና  ከፈጣሪ  ጥበብ  ጋር  አይስማማም፡፡  ከውስጡ  የተሳሳተ  ጥበብ  ይገኛል፡፡ ለሚመረምር  ግን  እውነት  አይመስለውም፡፡  በፈጣሪ  ፈቃድና  በፍጥረት  ህግ  የሰው  ልጅ  እንዳይጠፋ  ልጆችን  ለመውለድ  ወንድና  ሴት  በፍትወተ  ሥጋ  እንዲገናኙ  ታዟል፡፡  ይህም  ግንኙነት  እግዚአብሔር  ለሰው  በሕገ  ተፈጥሮ  የሰጠው  ነው፡፡ እግዚአብሔርም  የእጁን  ሥራ  አያረክስም፡፡ እግዚአብሔር  ዘንድ  እርኩሰት  ሊገኝ  አይችልም፡፡  ፈጣሪ የፈጠረውን መልሶ አያረክሰውም እላለሁ። 

  እንደገናም  የክርስቲያን  ሕግ  ለማስረጃዋ  ተአምራቶች ተገኝተዋልና  ከእግዚአብሔር  ናት  ይላሉ፡፡  ነገር  ግን  የወሲብ  ሥርዓት  የተፈጥሮ  ሥርዓት  እንደሆነ  ምንኩስና  ግን  ልጆች ከመውለድ  ከልክሎ  የሰውን  ፍጥረት  አጥፍቶ  የፈጣሪን  ጥበብ  የሚያጠፋ  እነደሆነ  ልቦናችን  ይነግረናልና  ያስረዳናል፡፡ የክርስቲያን  ሕግ  ምንኩስና  ከወሲብ  ይበልጣል  ብትል  ሐሰት  ትናገራለችና  ከእግዚአብሔር  አይደለችም፡፡  የፈጣሪን  ሕግ  የሚያፈርስ  እንዴት  ከጥበብ በለጠ ?  ወይስ  የእግዚአብሔርን  ስራ  የሰው  ምስክር ሊያስተካክለው ይቻለዋልን ? ሰዎች ግን ሳይመረምሩ ምንኩስና ከጋብቻ ትበልጣለች ይላሉ። ዘርን የሰጠ ፈጣሪ ዘር አያስፈልግም አይልም። ቀጣፊዎች በእግዚአብሔር ስም  እውነት አስመሰሉት እንጂ።

እንዲሁም  መሐመድ  የማዛችሁ  ከእግዚአብሔር  የተቀበልኩትን  ነው  ይላል፡፡  መሐመድን  መቀበል  የሚያስረዱ  የተዓምራት  ፀሐፊዎች  አልጠፉምና  ከሱም  አመኑ፡፡ እኛ  ግን  የመሐመድ  ትምህርት  ከእግዚአብሔር  ሊሆን  እንደማይችል  እናውቃለን፡፡ የሚወለዱ  ሰዎች  ወንድና  ሴት  ቁጥራቸው  ትክክል  ነው፡፡ በአንድ  ሰፊ  ቦታ  የሚኖሩ  ወንድ  ሴት ብንቆጥር  ለእያንዳንዱ  ወንድ አንዲት  ሴት  ትገኛለች  እንጂ  ለአንድ  ወንድ  ስምንት  ወይም  ዐሥር  ሴቶች  አይገኙም፡፡ የተፈጥሮ  ህግም  አንዱ  ከአንዲት  ጋር እንዲጋቡ  አዟል፡፡ አንድ  ወንድ  ዐሥር  ሴት  ቢያገባ  ግን  ዘጠኝ  ወንዶች  ሴት  የሌላቸው  ይቀራሉ፡፡ ይህም  የፈጣሪን  ስርዓትና  ሕገ ተፈጥሮን  የጋብቻንም  ጥቅም  ያጠፋል፡፡ አንድ  ወንድ ብዙ ሴቶች ሊያገባ  ይገባዋል  ብሎ  በእግዚአብሔር  ስም  ያስተማረ  መሐመድ  ግን  ትክክል  ነው አልልም፡፡ ከእግዚአብሔር  ዘንድ  አልተላከም፡፡  ጥቂት  ስለጋብቻ  ሕግ  መረመርኩ  ፡፡ ከመጀመሪያም  ለአዳም አንድ ሴት ከመፍጠር ይልቅ ዐሥር ሴት ያልፈጠረለት ለምንድነው? ይህን የፈጣሪ ሕግ  ሳይመረምሩ የመሐመድን  ሕግ መቀበል ስህተት ነው። ከእግዚአብሔር እንደተገኘ  ብመረምርም  በህገ  ኦሪትና  በክርስትናና  በእስልምና  ሕግ  ፈጣሪ  በልቦናችን  ከሚገልጽልን  እውነት  እና  እምነት ጋር የማይስማማ ብዙ ነገር አለ  አልኩ።

    ፈጣሪ  ለሰው  ልጅ  ክፉና  መልካም  የሚለይበት  ልቦና  ሰጥቶታል፡፡  «በብርሃንህ  ብርሃንን  እናያለን»  እንደተባለውም  የሚገባውን  የማይገባውን  ሊያውቅ፣  እውነትን  ከሐሰት እንዲለይ ነው፡፡ ስለዚህ የልቦናችን  ብርሃን  እንደሚገባ  በእርሱ  ብናይበት  ሊታይልን አይችልም፡፡ ፈጣሪያችን ይሄን ብርሃን  የሰጠን  በርሱ  እንድንድን  ነው እንጂ  እንድንጠፋ  አይደለም። የልቦናችን  ብርሃን  የሚያሳየን  ሁሉም  ከእውነት  ምንጭ  ነው፡፡ ሰዎች  ከሐሰት  ምንጭ  ነው  ቢሉን ግን  ሁሉን  የሰራ  ፈጣሪ  ቅን እንደሆነ  ልቦናችን  ያስረዳናል፡፡ ፈጣሪ  በመልካም ጥበቡ  ከሴት  ልጅ  ማህጸን  በየወሩ  ደም  እንዲፈስ አዟል፡፡  ሙሴና  ክርስቲያኖች  ግን  ይህን የፈጣሪ  ጥበብ  እርኩስ  አደረጉት፡፡
እንደገና  ሙሴ  እንዲህ  ያለችው  ሴት ከተቀመጠችበት የተቀመጠውንም፤ የተገናኛትንም  ያረክሳል፡፡  ይህም  የሙሴ  ህግ  የሴትን  ኑሮ  በሙሉና  ጋብቻዋን  ከባድ አድርጎታል፡፡ የመራባትንም  ህግ  አጥፍቷል፡፡ ልጆችንም  ከማሳደግ  ከልክሎ  ፍቅርንም  ያፈርሳል፡፡ ስለዚህ ይህ  የሙሴ  ሕግ  ሴትን  ከፈጠረ  ሊሆን  አይችልም  እላለሁ፡፡ «ሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል » የምትለው የሙሴ ሕግ ሞትን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር አይደለችም። እንደገናም  የሞቱትን  ወንድሞቻችንን  ልንቀብራቸው  ተገቢ መሆኑን ልቦናችን  ይነግረናል፡፡ በድኖቻቸውም  በሙሴ  ጥበብ  ካልሆነ  በስተቀር  ከመሬት  የተፈጠርንበት  ወደ መሬትም  ልንገባበት  በፈጣሪያችን  ጥበብ  እርኩሳን  አይደሉም፡፡ ነገር  ግን  ለፍጥረት  ሁሉ  እንደሚገባ  በትልቅ  ጥበብ  የሰራ  እግዚአብሔር ሥርዓቱን  አያረክሳውም፡፡ ሰው  ግን  የሐሰትን  ቃል  እንዲያከብር  ብሎ  ሊያረክሰው ይፈልጋል፡፡

  እንደዚሁም  እግዚአብሔር  የከንቱ  ነገር  አያዝም፡፡  «ጥረህ ግረህ በላብህ ወዝ ብላ» ያለው አምላክ ይህን  ብላ፣ ይህን  አትብላ፣ ዛሬ ብላ፣ ነገ  አትብላ  አይልም፡፡ ለክርስቲያኖች  እንደሚመስላቸውና  የጾም  ሕግጋት  እንደሚጠብቁ  ሥጋን  ዛሬ  ብላ፤  ነገ  አትብላ  አይልም፡፡  ለክርስቲያኖች እንደሚመስላቸውና  የጾም  ሕግጋት  እንደሚጠብቁ  ሥጋን  ዛሬ ብላ ነገ ግን  አትብላ  አይልም፡፡  እስላሞችንም  እግዚአብሔር  ለሊት  ብሉ  ቀን  አትብሉ  ብሎ  ይሄንና  የመሳሰሉትን  አይላቸውም፡፡ የፍጥረታችንን  ጤና  የማያውክ ነገር ሁሉ  ልንበላ  እንደሰለጠንን  ልቦናችን  ያስተምረናል።  አንድ  የመብል ቀን፤ አንድ  የጾም  ቀን ግን  ጤናን  ያውካል፡፡ የጾም ህግ መብላትን  ለሰው  ሕይወት  ከፈጠረና  ልንበላቸው  ከፈቀደ  ፈጣሪ የወጣ  አይደለም፡፡ በልተን ልናመሰግነው  እንጂ  በረከቱን  ልናርም አይገባንም፡፡ ሕገ  ፆም  የሥጋን  ፍትወት ለመግደል  የተሰራ  ነው  የሚሉም  ቢኖሩ  ፍትወተ  ሥጋ  ወንድ  ወደ ሴት  ሊሳብ  ሴትም ወደ  ወንድ  ልትሳብ  የፈጣሪ ጥበብ  ነውና  እርሱ  ፈጣሪ  በሰራው  በታወቀ  ማጥፋት  አይገባም  እላለሁ፡፡  ፈጣሪያችን  ይህን ፍትወት ለሰው፤  ለእንስሳት  ሁሉ  በከንቱ  አልሰጠም፡፡ ነገር ግን  ለዚህ  ዓለም  ሕይወትና  ለፍጥረት  የተሰራለት  መንገድ  ሁሉ  መሠረቱ  ሆኖ እንዲቆይ  ይህ  ፍትወት  ለሰው  ልጅ  ተሰጠ፡፡ አስፈላጊያችንን ልንበላ  ይገባናል፡፡ በእሁድ  ቀንና  በበዓል  ቀናት  በአስፈላጊው  ልክ  የበላ  እንዳልበደለ  እንዲሁ  በአርብ  ቀንና  ከፋሲካ  በፊት  ባሉት  ቀናት  ለክቶ  የሚበላ  አልበደለም፡፡  እግዚአብሔር  ሰውን  በሁሉ  ቀንና  በሁሉ  ወራት  ካስፈላጊ  ምግብ  ጋር  አስተካክሎ  ፈጥሮታል፡፡  አይሁድ፣  ክርስቲያንና  እስላም  ግን  የፆምን  ሕግ  ባወጡ  ጊዜ ይህን  የእግዚአብሔር  ሥራ  ልብ  አላሉም፡፡ እግዚአብሔር  ፆምን  ሰራልን፤  እንዳንበላም  ከለከለን  እያሉ ይዋሻሉ፡፡ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን  ነው፡፡ ግን  የምንበላውን  ምግባችንን   እንድንመገበው ሰጠን  እንጂ  እርሱን  ልናርም  አይደለም፡፡  በሚያስተውል ልቡናችን  ለክተን  መኖር የኛ ፈንታ ነው።

 ስለ  ሃይማኖቶች    መለያየት

 ሌላ ትልቅ  ምርመራ  አለ፡፡ ሰዎች  ሁሉ  በእግዚአብሔር  ዘንድ  ትክክል  ናቸው፡፡ እርሱም  አንድ  ሕዝብ ለሕይወት፤  አንድ  ሕዝብ ለሞት፤  አንድም  ለምህረት፤  አንድም  ለኩነኔ  አልፈጠረም፡፡  ይህም  አድሎ  በስራው  ሁሉ  ጻድቅ  በሆነ  በእግዚአብሔር  ዘንድ እንደማይገኝ  ልቦናችን  ያስተምረናል፡፡ ሙሴ  ግን  አይሁድን  ለብቻቸው  እንዲያስተምራቸው  ተላከ፡፡ ለሌሎች  ሕዝቦች  ፍርዱ አልተነገረም፡፡  እግዚአብሔር  ስለምን  ለአንድ  ሕዝብ  ፍርድ  ሲነግር  ለሌላው  አልነገረም፡፡  በዚህም  ጊዜ  ክርስቲያኖች  የእግዚአብሔር  ትምህርት  ከኛ  ጋር  ካልሆነ  በስተቀር  አይገኝም  ይላሉ፡፡ አይሁድና  እስላም  የህንድ  ሰዎችም  ሌሎችም  ሁሉ እንደነሱ  ይላሉ፡፡ እንዲሁ  ደግሞ  ክርስቲያኖች  እርስ  በርሳቸው  አይስማሙም፡፡ ካቶሊኮች  እግዚአብሔር  ከኛ  ጋር  ነው  ያለው እንጂ ከናንተ  ጋር አይደለም  ይሉናል፡፡ እኛም  እንዲሁ  እንላቸዋለን፡፡ ሰዎች  እንደምንሰማቸው  ግን  የእግዚአብሔር  ትምህርት  እጅግ  ጥቂቶች  ወደ ሆኑት  እንጂ  ለብዙዎቹ  አልደረሰም፡፡  ከእነዚህ  ሁሉ  ደግሞ  ወደ  ማን  እንደደረሰ  አናውቅም፡፡ እግዚአብሔር  ከፈቀደ ቃሉን  በሰው  ዘንድ  ማጽናት ተስኖት  ነውን?  ሆኖም  ግን  የእግዚአብሔር  ጥበብ  በመልካም  ምክር  ይህ  ነገር  እውነት እንዳይመስላቸው  ሰዎች  በሐሰት  ሊስማሙ  አልተወም፡፡ ሰዎች  ሁሉ  በአንድ  ነገር  በተስማሙ  ጊዜ  ይህ  ነገር እውነት ይመስላል፡፡ ሰዎች  ሁሉ  በሃይማኖታቸው  ምንም  እንደማይስማሙ  በሃሳብም  ሊስማሙ  አይችሉም፡፡
    እስኪ  እናስብ  ሰዎች  ሁሉ  ሁሉን  የፈጠረ  እግዚአብሔር  አለ  በማለታቸው  ስለምን  ይስማማሉ?  ፍጡር  ያለ  ፈጣሪ  ሊገኝ  እንደማይችል፤ ስለዚህም  ፈጣሪ  እንዳለ እውነት  ነውና  ነው፡፡ ይህ  የምናየው  ሁሉ  ፍጡር  እንደሆነ  የሰው  ሁሉ   ልቦና  ያውቃል ፡፡ ሰዎች ሁሉ በዚህ  ይስማማሉ፡፡  ነገር  ግን  ሰዎች  ያስተማሩትን  ሃይማኖት  በመረመርን  ጊዜ  በውስጡ  ሐሰት  ከእውነት  ጋር  ተቀላቅሎበታል፡፡  ስለዚህ  እርስ  በርሱ አይስማማም፡፡ ሰዎች  እርስ በርሳቸው  አንዱ  ይህ  እውነት  ነው ሲል፤ ሁለተኛው  አይደለም፤  ሐሰት  ነው  ሲል  ይጣላሉ፡፡ ሁሉም  የእግዚአብሔርን  ቃል  የሰው  ቃል  እያደረጉ  ይዋሻሉ፡፡  እንደገናም  የሰው  ሃይማኖት  ከእግዚአብሔር  ብትሆን  ክፉዎችን   ክፉ  እንዲያደርጉ  እያስፈራራች  መልካም  እንዳያደርጉ ትፈቅድላቸው  ነበር፡፡ ደጎችንም በትዕግስታቸው ታጸናቸው ነበር፡፡

  ለኔም እንዲህ ያለው  ሃይማኖት  ባሏ  ሳያውቅ  በምንዝርና  የወለደች ሴትን ትመስለኛለች፡፡ ባሏ ግን  ስለመሰለው  በሕፃኑ  ይደሰታል፡፡ እናቲቱንም ይወዳታል፡፡ በዝሙት  እንደወለደችው  ባወቀ  ጊዜ  ግን  ያዝናል፡፡ ሚስቱንም  ልጅዋንም  ያባርራል፡፡ እንዲሁም  እኔም  ሀይማኖቴን አመንዝራና  ዋሾ  መሆኑዋን  ካወኩ  በኋላ  ስለርሷ  በዝሙት  ስለተወለዱ   ልጆቿ አዘንኩ ፡፡ እነሱ  በጠብ፣ በማሳደድ፣ በመማታት፣ በማሰር፣ በመግደል  ወደዚህ  ዋሻ  ያባረሩኝ  ናቸው፡፡  ከውሸታቸው ጋር ስላልተባበርኩ ጠሉኝ። ነገር  ግን  የክርስቲያን  ሃይማኖት  ሀሰት  ናት እንዳልል  በዘመነ  ወንጌል  እንደተሰራ  ክፉ  አልሆነችም፡፡  የምህረትን  ሥራ  በሙሉ  እርስ   በርስ መፋቀርን ታዛለች፡፡  እነሱ ግን ፍቅርን ፈጽሞ አያውቋትም። በዚህ ዘመን  ግን  የሀገራችን  ሰዎች  የወንጌልን  ፍቅር  ወደ ጠብና  ኃይል  ወደ  ምድራዊ  መርዝ  ለወጡት፡፡  ሃይማኖታቸውን  ከመሰረቱ  ዐመጻ  እየሰሩ  ከንቱ  ያስተምራሉ፡፡  በሐሰትም  ክርስቲያኖች ይባላሉ፡፡