- የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲፈራርስ ዝምታው እስከመቼ?
- ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ጉዳይ ምላሻቸው ምን ይሆን?
ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚለው ቃል ከወረቀት ባለፈ በመሬት ላይ ተፈሚነቱ የሚታየው በጣም በጥቂቱ ነው። በተለይም ቤተ ክርስቲያኒቱ አለኝ በምትለው ማእርገ ክህነት በኩል ዲቁና፤ ቅስና ( ምንኩስና) ቁምስና በሙሉ የሚሰጠው ለማንና መስፈርቱ ምን እንደሆነ በማይታወቅ መልኩ ሥርዓተ የለሽ ሆኖ ይታይበታል። እነ መቶ አለቃ ግርማ ወንድሙ ሳይቀሩ በር የሚዘጋ መስቀል ተሸክመው እያሳለሙ በአጥማቂነት ተሰማርተው ገንዘብ ይሰበስባሉ። ከዚህ በፊት ወደእስራኤል አቅንቶ የነበረው ግርማ ወንድሙ ገና ገንዘብ መሰብሰብ ሲጀምር አንዷን ሴት ሲያጠምቅ ጎረቤቷ ቡዳ ሆና በላቻት በማሰኘቱ፤ ቡዳ ናት የተባለችው ሴት ፍርድ ቤት በስም አጥፊነት ከሳው መጥሪያ ብታመጣበት ሌሊቱኑ ፈርጥጦ ወደኢትዮጵያ ማምለጡን ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ሰምተን ተገርመን ነበር። ባለቤት የሌላትን ቤተ ክርስቲያን እየተዘዋወረ በክፉ መንፈስ የሚበጠብጠው ግርማ አሁን ደግሞ ወደአውሮፓ ዘልቆ በጣሊያን የዘረፋውንና የቡዳ በላሽ ዜማውን እያስነካው ይገኛል። እነባህታዊ ገብረ መስቀል ማርያምን ተገለጸችልኝ እያሉ ህዝቡን ሲያጭበረብሩ እንዳልነበር ብህትውናውን እርግፍ አድርገው ቆንጆ መርጠው ሚስት አግብተው ልጆች ወልደው ማርያም ተገለጸችልኝ፤ ገብርኤልን አየሁት ከሚል ማደናገሪያ ነጻ ወጥተዋል። ከማጭበር በር ይህኛው የተሻለ አማራጭ ይመስለናል።
ይህ ማእርገ ክህነት የሚባለው ሹመት በአንዳንዶች ዘንድ የክብር ዶክትሬት ይመስል ከስም ባለፈና የሕዝቡን ግንባር ከሚገጩበት በስተቀር እንደማኅበረ ቅዱሳን ባሉ ማኅበራት ዘንድም የአገልግሎት ዋጋ የሌለው መሳሪያ ሆኖ ይገኛል። በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉበት አይታይም። የማዕረጉን ስም የሚፈልጉት ክህነት የላቸውም እንዳይባሉና በክህነት ሽፋን በሚገኘው ክብር የመበለቶችን ቤት ለመዝረፍ ስለሚረዳ እንጂ ከመጀመሪያው በድንግልና ጸንተው ለማዕርገ ዲቁና በቅተው «ተንሥኡ፤ ጸልዩ» እያሉ ሲያገለግሉበት ቆይተው፤ በኋላም በስርዓተ ቤተ ክርስቲያን በተክሊል በድንግልና የጸናች አግብተው አይደለም። ሲጀመር ጀምሮ ዲቁናም ይሁን ቅስና የተቀበሉት ሰዎች ድንግላቸው የፈረሰበትን ጊዜ ራሳቸው በትክክል አያውቁትም። ራሳቸው በድንግልና ሳይቆዩ፤ ድንግልና እንደፈንጣጣ በጠፋበት ዘመን ድንግል አግብተው አይቀስሱም። በተለይ ወንዶቹ አጭበርባሪዎች፤ ቀሳጮችና መልቴዎች ናቸው። በዚህ ዙሪያ ሀገር ሰፈሩን ሲያዳርሱ የኖሩ የዘመኑ ቀሳውስትና መነኮሳት ነን ባዮች ቅስናን እንደማጭበርበሪያ ይጠቀሙበታል። ቅዱስ በተባለው መቅደስ ገብተው በርኩስናቸው ሕዝቡን ያታልሉበታል። ይህ ዐመፃና ማታለል በሀገር ላይ ጥፋትን፤ በሕዝብ ላይ ቁጣን ማምጣቱ አይቀርም። ማንም እመራበታለሁ ብሎ ላወጣው ለራሱ ሕግ የማይታዘዝ ከሆነ የሚጠፋው በዚያው በራሱ ሕግ ነው።
«ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል» ሮሜ 2፤12
ዛሬ ሁሉም ከዚህ ከራሳቸው የሕግ ክብር ስለወረዱ ማንም ምንንም አይቆጣጠርም። ሥርዓት ፈረሰ፤ ሕግ ተጣሰ የሚል አንድም ስንኳ የለም። «ኩሉ ዐረየ፤ ወኅቡረ ዐለወ» እንዳለው ዳዊት በመዝሙሩ ሁላቸውም ተሳስተዋል፤ ሁላቸውም በዐመጻ ስለተስተካከሉ ዲቁና ሰጪውም ተቀባዩም ከሥርዓት ውጪ ሆነዋል። ከዚህ በታች የቀረበውም ጽሁፍ ይህንን መሠረት ያደረገ ነው።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነን «እንበለ አሐዱ ኄር፤ ኢይኀድጋ ለሀገር» ለሀገር እንዲሉ አንድ ተቆርቋሪ ኤርትራዊ ቄስ ከሀገረ እስራኤል-ቴል አቪቭ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ለልዩ ልዩ ድረ ገጾች በግልባጭ ሲልክ ለእኛ የደረሰውን ጽሁፍ እንዳለ አቅርበነዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምን ሆነች?
በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከመለያየታቸው በስተቀር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ዛሬም ድረስ አንድ ነን። ሥርዓቱና ሕግጋቱ የተለያየ አይደለም። በማዕረገ ክህነት አሰጣጥ ልዩነት ያለን አይመስለንም። ነገር ግን እጅግ አሳዝኝና አስገራሚ ነገር ስናይ የምንጠይቀው አጥተናል። በተደረገው ሁኔታ እኛ በእስራኤል የምንገኝ ኤርትራውያን በተደረገው አድራጎት ተጎድተናል። ይኸውም ለሰሚ የሚከብድና ከምናውቃት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ህግጋት ውጪ ማዕረገ ክህነት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ሲሰጥ በማየታችን በጣም አዝነናል። ነገሩን በአጭሩ አስረዳለሁ።
ሰውየው በትግራይ ክፍለሀገር ሰንቃጣ እንደተወለደ አውቀነዋል። ስሙም ሓጎስ አስገዶም ይባላል። በትግራይ ክፍለ ሀገር ይህ ሓጎስ አስገዶም የተባለ ሰውዬ አባ ሰላማ የሚባል ማኅበር አቁሞ ህዝብ ለህዝብ ሲያጋጭ ተይዞ ሶስት አመት ወኅኒ ታስሮ ነበር። በአቡነ መርሐ ክርስቶስ ማኅበሩ በትእዛዝ ፈረሰ። በሲኖዶስም ተወሰነበት። ተስፋ ያልቆረጠው ይህ ሓጎስ አሰገዶም የተባለ ሰውዬው ወደ ሽመልባ የኤትራውያን ስደተኛ ካምፖ በመግባት ባሕታዊ ወልደ ሥላሴ እባለሎህ በማለት ማደናገር ጀመረ።
ባህታዊ ነኝ የሚለው ሓጎስ አስገዶም |
በዚያም በእሱ የተጀመረ ረብሻ በሽመልባ ባሉ የኤርትራ ቤተክርስቲያን በመበራከቱ ጥቂት ተከታዮች አስከትሎ በሱዳን አድርጎ ሊቢያ ገባ። ሊቢያ ሲገባም አባ ሰላማ መልዕክት ነግረውኛል ከዛሬ ጀምሮ አንተ ሞኖክሴ ነህ ብለውኛል ብሎ አባ ሳሙኤል ነኝ አለ። ከዚያም ይህ ሓጎስ አስገዶም ከሊቢያ ወደእስራኤል ሀገር ከኤርትራውያን ጋር ገብቶ ኤርትራዊ ነኝ ብሎ የስደተኛ ወረቀት ከወሰደ በኋላ ሳይሞኖክስ አባ ሳሙኤል ተብሎ እየተጠራ ቆየ። አጠምቃለሁ እያለ ሲያታልል፤ ህዝብ ሲያሳብድ፤ ገንዘብ ሲሰበስብ ቆይቶ ብዙ ኤትራውያን ደግሞ አንተ ሞኖክሴ አይደለህም፤ ለምን አባ ትባላለህ። ክህነት የለህም ለምን ታሳልማለህ። ንስሀ ለምን ትሰጣለህ ስንለው የእኔ ክህነት በአባ ሰላማ ፍሬምናጦስ አማላጅነት ከሰማይ ነው የተሰጠኝ፤ የእናንተ ክህነት ግን ከኃጢአተኛ ጳጳስ እጅ የተሰጠ ነው እያለ ሲሳደብ በማየታችን ህዝቡ በዚህ አታላይ ሰው እንዳይታለል ስናስተምር ተናዶ ወደኢየሩሳሌም በመሄድ ከኢትዮጵያ ሊቀጳጳስና አንዳንድ መነኮሳት ጋር በስውር መገናኘቱን ቀጠለ።
ባህታዊ ወልደ ሥላሴ ነኝ እያለ በሽመልባ ሲያታልል |
ከዚያም ከሊቀ ጳጳሱ አባ ዳንኤል ዘንድ ዲቁና ተቀበልኩ አለና በአስማቱ ለሚያታልላቸው ደጋፊዎቹ ማዕረጉ ሲሰጠው የሚያሳይ ፎቶና ፊልም አሳየ። ትንሽ ቆይቶ ሞኖኮስኩኝ ብሎ እንደቦብ ማርሊ ያሳደገውን ጸጉሩን ቆርጦ ጥቁር ቆብና ቀሚስ አድርጎ መጣ። አንተን አመነኮሰች ቤተ ክርስቲያን? ብለን አዘንን። አለቀስን።
በአባ ሳሙኤል ስም ቄስና መነኩሴ ነኝ አለን ደግሞ |
ከሱ ጋር የነበሩና ስናስተምራቸው የተመለሱ ሁለት ዲያቆናት ለመመንኮስ 50 ሺህ ሼቄል ከፍሏል አሉን። ለሊቀ ጳጳሱና ከመነኮሳቱ መካከል አባ ፍስሐና አባ ብርሃና መስቀል የተባሉም ገንዘብ መቀበላቸውን አሁንም ይመሰክራሉ። የሰው ማስረጃ አለን። ሌሎችም መነኮሳት የተቀበሉ አሉ። ይህ አታላይ አባ ሳሙኤል የተባለው ትንሽ ቆይቶ የቅስና ማዕረግ ከአባ ዳንኤል ተሰጠኝ ብሎ በደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን ሥርዓት በቢዲዮና በፎቶ ቴልአቪቭ አምጥቶ ለተከታዮቹ አሳየ። ይህ ሁሉ ማስረጃ በእጃችን ይገኛል።
ምንም የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሙያ ለሌለው፤ ዲቁና ሳይኖረው ለሓገስ አስገዶም ቅስና ሲሰጡት አቡነ ዳንኤል ናቸው |
የዚህ ሁሉ አስተባባሪ አባ ፍስሐ ይባላሉ። አባ ብርሃነ መስቀል የተባሉት፤ አባ ተወልደ የተባሉትም አብረውት አሉ። ገንዘብ የተቀበሉ መኖክሴዎች ዝርዝር በእጃችን አለ። በቁጥር ትንሾች ቢሆኑም የቤተ ክርስቲያን ስርዓት ጠፋ ብለው የተናገሩ ቢኖሩም የሰማቸው የለም። ገንዘብ የሁሉንም አፍ ዝም አሰኝቷል።
እኛ የምናዝነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሹማምንት በገንዘብ ስልጣነ ክህነት እየሰጡ ለምን ቤተ ክርስቲያንን ያሰድባሉ? የኢየሩሳሌም ገዳም ሞኖክሴዎችስ ለምን በገንዘብ ይደለላሉ? ክህነት እንደዚህ ነው? ሙንኩስናስ እንደዚህ ነው? በበኩላችን ይህን ሰውዬ ያለአግባብ እያታለለ ከኤርትራውያን እጅ የወሰደውን በብዙ መቶ ሺህ ሼቄል ለማስመለስና በህግ ፊት ለማቆም ማስረጃዎቻችንን ይዘናል። እናንተ በሰጣችሁት ክህነት አንታለልም። አንታወክም። ለነገሩ ቤተ ክርስቲያንን አዋርዳችሁታል። ሓጎስ አስገዶም ቄስ ሆነ? ሚስቱንም አምጥቶ አመነኮሰ። አንድ ቤት አንድ ላይ ይኖራሉ። አይ ኦርቶዶክስ፤ እንደዚህ መሆና ያሳዝናል። ሕግ ካለ፤ ዳኛ ካለ ኢየሩሳሌም ያሉ ሞነኮሳትን ከገዳሙ ማባረር ነበር። ለሓጎስ አስገዶም ቅስና የሰጡ ሊቀጳጳሱም መቀጣት ነበረባቸው።
ያሳዝናል። ያሳዝናል። በትክክልም ዘመኑ ተጨርሷል። ክህነትና ሙንኩስና በገንዘብ ሆነ። ኤሎሄ ኤሎሄ ይባላል።
ለምእመን በገንዘብ ክህነት እንዲያገኝ ያደረጉ አባ ብርሃነ መስቀል የሚባሉት በቀኙ፤ አባ ፍስሐ የሚባሉት አባ ፍስሐ የሚባሉት በግራ በመሀል አቡነ ዳንኤልና ሲሆኑ በደብረ ገነት ቤተመቅደስ ውስጥ ሓጎስ አስገዶም ፤ ወልደሥላሴና አባ ሳሙኤል የተባለው ቅስና ሲቀበል የሚያሳይ ፎቶ። የዚህ ሥርዓት ሙሉ ቪዲዮ በእጃችን አለን።
ፍትዊ አንገሶም ቴልአቪቭ