Thursday, August 28, 2014

«ፍትሕን ለግል ስሜት መወጫ ማድረግ የቱን ያህል ለትውልድ መተዛዘቢያ ሆኖ የተሰወረ ሊሆን አይችልም» አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ለአፄ ኃ/ሥላሴ በ1957 ዓ/ም ከጻፉት ደብዳቤ







ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

አዲስ አበባ

ግርማዊ ሆይ፣

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሕይወት የሚታየውን ምሬትና ግፍ፣ የፍትሕም መጓደል ምክንያት በማድረግ ወደ አገሬ ለመግባት ያለኝን አሳብ ማቆየት ግድ እንደሆነብኝ ለግርማዊነትዎ መግለጥ አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚታረምበትን በኅብረት ለመሥራት ባንሞክር ታላቅ ብጥብጥ እንደሚያስከትልብን ከታሪክ መማር ካልቻልን፣ ከተከታዩ መቅሰፍት የምናመልጥበትና የምንከለልበት ሰው ሠራሽ ዘዴ ይገኝለታል ብሎ ራስን መደለል በሕልም ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደ መፈተን ይቆጠራል፡፡
ከዚህም በቀር ለተተኪው ትውልድ አቋም ይሆናሉ ብለን ተከባክበን ልናሳድጋቸው አላፊነት ያለብንን ሕፃናትና ውለታ ትተው ለማለፍ የተደራጁትን ሽማግሎቻችንንም ደህና ዕረፍት እንዳያገኙ ከአገሪቱ በተፈጥሮ ያገኙትን ዕድል መንፈግ ያሰኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በፈጸምነው ስህተት ታሪክ ምሕረት ሊያደርግልን በፍጹም አይችልም፡፡
ይህን የመሳሰለው ሁኔታ በብርቱ የሚያሳስበን መሆኑን ስንገልጥ ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ‹‹አንተ ምን አገባህ?›› በማለት በጉዳዩ ባለቤትነት ክፍያ ድርሻችንን ለማሳነስ ቢሞክሩም በኢትዮጵያዊነት ትክለኛ መብት ላይ አጥብበው ያሰመሩትን የወሰን ክልል አሜን ብሎ ለመቀበል ከቶ ስለሚያስቸግር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አላፊነቱን የማስወረድ ተግባር እንዳለበት አይካድም፡፡ እኔም ይህን ምክንያት አድርጌ በአሁኑ የመንግሥት አስተዳደር የደረሰውን ሕገ ወጥ አፈጻጸም ሁሉ ለማረምና ፍትሕን ለማደላደል የሚቻልበትን አሳብ በነፃ ለመግለጥ ስል እውጭ አገር መቆየትን መረጥሁ፡፡
በአሁኑ አያያዝ እንዲቀጥል የተተወ እንደሆነ በኢትዮጵያ የወገን መለያየትና የደም መፍሰስ እንደሚያሠጋ የመላው ኢትዮጵያውያን ግምት የወደቀበት ነው፡፡ ዋናው አላማ ይህ እልቂት የሚወገድበት መድኃኒቱ ምንድነው? ለተባለው ጥያቄ ለመመለስ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ መቸም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚመስለውና በሚያምንበት ረገድ መልሱን ለመስጠት ሞክሯል፡፡ አሁን የጐደለ መስሎ የሚታየው ከዙፋኑ በኩል የሚጠበቀው ይሁንታ ብቻ ነው፡፡ ነገሩን በመጠኑ ለማብራራት ያህል በሚከተሉት መስመሮች አስተያየቴን ለመግለጥ እሰነዝራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዙፋኑ የሰጠው ልባዊ አክብሮት ዘላቂ ሆኖ በታሪካዊ ቅርስነት እንዲጠበቅ በቤተ መንግሥቱ በኩል አልታሰበበትም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ባለፈው ‹‹መለኮታዊ መብት›› የተባለው የዘውድ ቴዎሪ የተሳሳተ መሆኑን ቢረዳውም፣ ሕዝቡ፣ ዘውዱን ታሪካዊ ሲምቦል ወይም ምሳሌ አድርጐ በክብር ሊያኖረው ሲፈቅድ ወደ መለኮታዊ መብት አስተያየት እንደገና እንዲመለስና ጣኦታዊ ስግደት እንዲያደርግ ማስገደድ፣ በእልህ ዘውዱን ለማስረገጥ ካልሆነ በቀር ለሌላ አያገለግልም፡፡
ጃንሆይ፣ ባለዘውድ፣ አስተዳዳሪ፣ ሕግ አውጭ፣ ዳኛ፣ ምስለኔ፣ ፖሊስ፣ ጭቃ ሹም ሆኜ ልሥራ ሲሉ፣ በ፳ኛው [20ኛው] ክፍለ ዘመን የሚገኝ ሕዝብ ይህን መብት አጠቃሎ በፈቃዱ ለዘውዱ ብቻ ይለቃል ማለት የማይታመን ነው፡፡ መቸም እየተደጋገመ የሚሰጠው ምክንያት ‹‹ሕዝቡ ኃላፊነትን ለመቀበል አልደረሰም›› የሚል መሆኑን በየጊዜው ሰምተናል፡፡ በውነቱ ከአፍሪካና ከኤሻ ሕዝብ መካከል አልደረሰም ተብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ መፍረድ ይገባልን? ደግሞስ ያለመድረስ ትርጓሜው ምንድነው? ምናልባት የማሰብ፣ የመምረጥ፣ የማመዛዘን፣ የመፍረድ ሴንስ አልተፈጠረለትም ማለት ነው? እንደዚህማ ከሆነ በ፫ሺሕ [በ3 ሺሕ] ዘመን ውስጥ ለዚህ ሕዝብ ጭንቅላት ሆኖ ያሰበለት፣ ዓይን ሆኖ ያየለት፣ ጆሮ ሆኖ የሰማለት የዛሬው ዘውድ ነው ማለት ነዋ! የሚፈተነው ይህን የመሰለ አስተያየት ለማቅረብ እንደሆነ ምሕረት የሌለው በደል ነው፡፡
ይልቁንስ ጃንሆይ የሕግ ጠባቂነትን ልብስ ተጐናጽፈው በዚህ መንፈስ ፍትሕን ከሚያጓድሉ፣ ሥልጣኑን ለሕዝብዎ ሰጥተው እርሱ ቢጨነቅበት እንደሚሻል ጥርጥር የለውም፡፡ ያለዚያ ከዚህ ማስታወሻዬ ውስጥ ለስማቸው እንኳ ሥፍራ ለመስጠት ዋጋ የሌላቸውና ሕሊና ቢሶች የሚያቀርቡልዎትን ‹‹ደህና ታይቷል›› እያሉ ፍትሕን ለግል ስሜት መወጫ ማድረግ የቱን ያህል ለትውልድ መተዛዘቢያ ሆኖ እንደሚኖር የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡
ይህን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ለማሻሻል የሚቻለው ጃንሆይ ዘውዱን ለራስዎ አስቀርተው አስተዳደሩን ለሕዝብ በመስጠትና የዴሞክራሲን መንፈስ በማስገባት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አስተያየት ለግርማዊነትዎ ሰውነት አለርጂ ሆኖ ቢያስቸግርም እንኳ ሌላ ማማረጫ ይኖራል፡፡ ይኸውም ዘውዱን ለልዑል አልጋ ወራሽ ማስተላለፍና አብዲኬት ማድረግ ነው፡፡ እርሳቸው ሕገ መንግሥት ጠብቀው ለመኖር ፈቃደኛ እንደሆኑ አያሌ ሰዎች ሲመሰክሩላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ያለዚያ ተከታዩ ትርምስና ደም መፋሰስ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
ይህ አቤቱታ ከኔ ብቻ የቀረበ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርኃት ታፍኖ ነጋም መሸም የሚያጕተመትመው ይህንኑ ነው፡፡ ድምፁን ከፍ ለማድረግ ግን አካባቢው አልፈቀደለትም፡፡ እኔም ከርሱ የተለየሁ መስዬ ታይቼ እንደሆነ ያጋጣሚ ነገር ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ የታፈንኩትን ያህል እዚህ ከተነፈስሁ በኋላ ወደ አገሬ እንድመለስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምናልባት ይህን አቤቱታ በመጻፌ እወነጀል ይሆናል፡፡ ግድ የለም፡፡ የሆነ ሆኖ በትእዛዝ ሳይሆን በነፃ የሚፈርድና በግልጽ የሚያስችል ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ራሴን በሕጋዊ ጠበቃ አማካይነት ለመከላከል ጃንሆይ የሚፈቅዱልኝ ከሆነ በአገሬ ውስጥ ለመተንፈስ ዕድል ተሰጠኝ ማለት ነው፡፡
ከዚህም ሁሉ ጋር ላስታውሰው የምፈቅደው፣ ይህን ማስታወሻ በመጻፌ ተቀይመው የእኔን ሕይወት ለማስጠፋት በሺሕ የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም፡፡ አዝናለሁ፡፡ እኔ ለሞት የተዘጋጀሁ ስለሆነ ገንዘቡ ባይባክንና ለነፍሰ ገዳይ በመስጠት ፈንታ ለጦም አዳሪ ችግረኛ ቢውል የበለጠ እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም፡፡ በበኩሌ በአገራችን ሬሾሉሽን እንዲነሣና የማንም ደም እንዲፈስ አልፈቅድም፡፡ በዚህ ባቤቱታዬ የምወተውተውም ሰላማዊ ለውጥ እንዲሆንና የምንፈራው ደም መፋሰስ እንዳይደርስ ስለሆነ ጃንሆይ አንድ ቀን ‹‹ለካ ብርሃኑ ውነቱ ኖሯል!›› ሳይሉ አይቀርም፡፡
እንኳን ዘውድ የጫነ ሰውነትንና ማናቸውንም ሰው የማክበር ልምድ ስላለኝ፣ ይህ አቀራረቤ ክብርን ለመድፈር እንደማያስቆጥርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ውነት ሁል ጊዜ መራራ ናት፡፡ የመድኃኒት ፈውሱ እንጂ ምሬቱ አይታሰብም እንደተባለው ይህ በቅን ልቡና የቀረበው ውነተኛ አቤቱታዬ የግርማዊነትዎን ልብ አራርቶ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሕይወት አንድ ፈውስ እንዲያመጣለት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ጃንሆይ! በኢትዮጵያ ወጣቱ ሽማግሌው ሴቱ ወንዱ የአኗኗሩ ዘዴ ውሉ ተዘባርቆበታል፡፡ አምላካችን፣ ፈጣሪያችን እያለ ቢደልልዎት አይመኑት፡፡ ጨንቆት ነው፡፡ ከልብ የሚመርቅዎት ግን ራስህን አስተዳድር ብለው አርነት ሲያወጡትና ወደ ዴሞክራሲ ሲመሩት ነው፡፡ ይህንንም ስል ሕዝብ በራሱ ሲተዳደር ችግር አይገጥመውም ማለቴ አይደለም፡፡ እስከዚህ አልሳሳትም፡፡ ነገር ግን ሌላው ለፍቶ ከሚጥለውና ላንሣህ ከሚለው፣ ራሱ ወድቆ በራሱ መነሣትን ይመርጣል፡፡ ይኽም በሥሕተት መማር ይባላል፡፡ ስለዚህ ጃንሆይም ተሳሳቱ እያለ ከሚከስዎት እርሱ ለሥሕተት እንዲጸጸትና እንዲማር ቢያደርጉት ትልቅ ውለታ ይቆጠራል፡፡
የዛሬው ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስገንባት የሚረዳ ካለመሆኑም በላይ ያንኑም ቅሉ አክብሮ ለመጠበቅ በአንቀጽ ፳፩ [21] እንደተመለከተው ከንጉሠ ነገሥቱ በመሐላ የተሰጠው ቃል ፈርሷል እያሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን እንደሚያማርሩ ግርማዊነትዎ ሳይሰማው አይቀርም፡፡ መቸም ሕገ መንግሥቱን፣ ለመጣስ አንድ የጽሕፈት ሚኒስቴር ደብዳቤ ይበቃል፡፡ እንግዴህ ሕዝቡ ወይም ሹማምቱ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ ነኝ እያሉ ቢምሉም፣ ንጉሠ ነገሥቱ በበኩሉ መሐላውን የሚጠብቅ ካልሆነ በመሐላቸው ታስረው እንደማይኖሩ በልጅ ኢያሱ ጊዜ የደረሰው ሁኔታ ምሳሌ ሊሆን ይችል ይመስለኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የገጠመንን ፕሮብሌም እንደ መጠኑ ለመግለጥ ‹‹በግርማዊነታቸው መንግሥት ያገኘሁት ኤክስፔሪያንስ›› የሚለው መጽሐፌ በሙሉ ታትሞ እስከወጣ ድረስ ፲፪ኛውን [12ኛውን] ምዕራፍ ከዚህ ጋር አያይዤ ለግርማዊነትዎ በትህትና አቀርባለሁ፡፡

                          ዋሽንግተን ግንቦት ፳፭/፶፯ [ግንቦት 25/57]
                                ከታላቅ አክብሮታዊ ፍርሐት ጋራ
                                          ብርሃኑ ድንቄ