Friday, August 22, 2014

ሐተታ ዘርዓ ያዕቆብ

 (ዘርዓ ያዕቆብ ፈላስፋ

ስለ አምላክ  ሕግና ስለ ሰው ሕግ

እግዚአብሔር  የገዛ  ሕዝቡን  እንዲያስቷቸው  ስለምን  ዋሾ  ሰዎችን  ይተዋል  ብዬ  አሰብኩ፡፡  እግዚአብሔር  ግን  ለሁሉም
ለእያንዳንዱ  እውነትንና  ሐሰትን  እንዲያውቅ  ልቦና  ሰጥቶናል፡፡  እውነት  ወይም  ሐሰት እንደፈቃዱ  የሚመርጥበት
መምረጫም ሰጠው፡፡ እውነትን ብንወድ ለፍጥረት ሁሉ አስፈላጊና ተገቢ የሆነውን እርሱም እንድናይበት እግዚአብሔር
በሰጠን ልቦናችን ውስጥ እንፈልጋት፡፡ ሰው ሁሉ ዋሾ ነውና እውነትንም በሰዎች ትምህርት አታገኟትም፡፡ ከእውነት ይልቅ
ሐሰትን ብንመርጥ ስለዚህ እኛ በስህተታችን እንጠፋለን እንጂ ለፍጥረት ሁሉ የተሰራው የፈጣሪ ሥርዓትና ሕግ አይጠፋም፡፡
እግዚአብሔር ማንንም በሠራው ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ከሰው ሥራ ግን የእግዚአብሔር ሥራ ይጸናል፡፡ የሰው ሥራ ሊያጠፋው
አይችልም።  ስለዚህም  ከጋብቻ  ይልቅ  ምንኩስናን  ይበልጣል  ብለው  የሚያምኑ  እነርሱ  በፈጣሪ  ሥራ  ጽናት  ወደ  ጋብቻ
ይሳባሉ፡፡ ፆም ነፍስን እንደሚያፀድቅ የሚያምኑ እነርሱ ደግሞ ረሃብ በበዛባቸው  ጊዜ ይበላሉ፡፡ ገንዘቡን የተወ ፍፁም
እንዲሆን  የሚያምኑ በገንዘብ  ለሚያገኙት   ጥቅም  ወደ  ገንዘብ  መፈለግ  ይሳባሉ፡፡  ብዙዎች  የሀገራችን  መነኩሴዎችም
እንደሚደርጉት ከተዉት በኋላ እንደገና ይፈልጉታል፡፡ እንደዚሁ ዋሾዎች ሁላቸው የተፈጥሮን ሥራ ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ፡፡
ነገር ግን ደካማነታቸውን ያሳያሉ እንጂ አይችሉም፡፡ ፈጣሪም ይስቅባቸዋል፡፡ የፍጥረት ጌታም በላያቸው ይሳለቅባቸዋል፡፡
እግዚአብሔር የእግዚአብሔርን ፍርድ ማድረግ ያውቃልና ኃጥአንም በእጁ ሥራ ወጥመድ  ተጠመደ፡፡ ስለዚህም የጋብቻን
ሥርዓት የሚያስነውር መነኩሴ በክፉ በሽታና ፍጥረቱ ባልሆነ በሌላ የሴት አበሳ በዝሙት ተጽዕኖ ይጠመዳል፡፡ ገንዘባቸውን
የሚንቁ  ገንዘብ  እንዲያገኙ  በሀብታሞችና  በነገሥታት  ዘንድ  ግብዞች  ይሆናሉ፡፡  ለእግዚአብሔር  ብለው  ዘመዶቻቸውንም
በሽምግልናቸውና በችግራቸውም ረዳት ባጡ ጊዜ የተዉ በነሱ ሽምግልና ጊዜ ሰውና እግዚአብሔርን ወደ ማማት፤ መሳደብ
ይደርሳሉ፡፡  እንደዚሁም  የፈጣሪን  ሥርዓት   የሚያፈርሱ  ሁሉ  በእጃቸው  በሰሩት  ወጥመድ  ይወድቃሉ፡፡  እንደገናም
እግዚአብሔር  ክፋትን፤ ስህተትን  በሰው  መካከል  ይተዋል፡፡  ነፍሶቻችን  በዚህ  ዓለም  የእግዚአብሔር ጥበብ  የፈጠረውን
የፈተና ቀን ይኖራሉ፡፡

ጠቢቡ ሰለሞን

"እግዚአብሔር  ፃድቃንን  ፈተናቸው፡፡  ወርቅ  በእሳት  እንደሚፈተን  ይፈትናቸዋል፡፡  ለእርሱ  የተዘጋጁ  ሆነውም
አግኝቷቸዋልና፡፡ እንደተወደደ ዕጣን መዐዛም ይቀበላቸዋል" ይላል፡፡
ከሞታችን በኋላም ቢሆን ወደፈጣሪያችን በገባን ጊዜ እግዚአብሔር በእውነትና በትልቅ በጥበብ ከሠራው ሁሉ እውነትና ቅን
የሆነውን መንገድ ሁሉ እንለያለን፡፡ ነፍሳችንም ከሥጋዊ ሞታችን በኋላ እንደምትድን ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓለም ውዴታችን
አይፈፀምምና የሌላቸው ይፈልጋሉ፤ ያላቸው ባላቸው ላይ እንደገና ሊጨምሩ ይፈልጋሉ፡፡ሰው በዚህ ዓለም ያለው ሁሉ
እንኳን  ቢኖረው  እንደገና  ይወዳል  እንጅ  አይጠግብም፡፡  ይህም  የፍጥረታችን  ጠባይ  ለሚመጣው  ንብረት  እንጂ  ለዚህ
ዓለም ንብረት ብቻ እንዳልተፈጠርን ያመለክታል፡፡ በዚያውም የፈጣሪያቸውን ፈቃድ የፈፀሙ ነፍሳት ፍፁም ይጠግባሉ
እንጂ ከእንግዲህ ሌላ አይወዱም፡፡ አለዚያ ግን የሰው ፍጥረት አስፈላጊውን ሁሉ አላገኝምና ጎዶሎ በሆነ ነበር፡፡ እንደገናም
ነፍሳችን  እግዚአብሔርን  ማሠብ  ትችላለችና  በሃሳቧም  ታየዋለች፡፡  እንደገናም  ለዘላለም  መኖር  ማሰብ  ትችላለች፡፡
እግዚአብሔርም ይህን ማሰብ በከንቱ አልሰጣትም፡፡ ነገር ግን እንደሰጣት ልታስብና  እንድታገኝም ሰጣት፡፡ ደግሞ በዚህ
ዓለም ፅድቅ ሁሉ አይፈፀምም፡፡ ክፉ ሰዎች ከዚህ ዓለም መልካም ይጠግባሉ፡፡ ደጋጎች ይራባሉ፡፡ የሚደሰት ክፉ አለ፣
የሚያዝን ደግ አለ፣ የሚደሰት ዐመፀኛ አለ፣ የሚያለቅስ ፃድቅም አለ፣ ስለዚህም  ከሞታችን በኋላ ለሁሉ እንደየምግባሩ
የሚከፍለው  ሌላ  ኑሮና  ፍፁም  ፅድቅ  ያስፈልጋል፡፡  በብርሃን  ልቦናችን  ተገለፀላቸው፡፡  የፈጣሪን  ፈቃድ  የፈፀሙና
በተፈጥሯቸውም ፀባያዊ ህጉን የጠበቁ ዋጋቸው ይከፈላቸዋል፡፡ የተፈጥሮን ሕግ ከመረመርን የተረጋገጠ መሆኑን ልቦናችን
በግልፅ  ይነግረናል፡፡  ነገር  ግን ሰዎች  ሊመረምሩ  አልፈለጉምና  የፈጣሪያቸውን  ፈቃድ በእውነት  ከመፈለግ  የሰዎችን  ቃል
ማመን መረጡ፡፡

 ስለ ባህሪያዊ ዕውቀት

የፈጣሪ ፈቃድ ግን ለእግዚአብሔር ለፈጣሪህ ስገድ ፣ ሰውንም ሁሉ እንደነፍስህ አፍቅር ይላል፡፡ ይህ በልቦናችን እውነት
መሆኑ  ይታወቃል፡፡  እንደገናም  በልቦናችን  እውነትነቱ  የሚታወቅ  ሌላ  እውነት  "ሊያደርጉብህ  የማትፈልገውን  በሰው
አታድርግ፡፡  ላንተ  ሊያደርጉልህ  የምትፈልገውን  አድርግላቸው"  ይላል፡፡  የሰንበትን  ማክበር  የሚለው  ካልሆነ  በቀር  ዐሥሩ
የኦሪት  ትዕዛዛት  የፈጣሪ  ናቸው፡፡  ሰንበትን  ለማክበር  ግን  ልቦናችን  ዝም  ይላል፡፡ ልንገድልና  ልንሰርቅ፣  ልንዋሽና  የሰው
ሚስት  ልንሰርቅ  ይህን  የሚመስለውን  ልናደርግ  እንደማይገባን  ልቦናችን  ይነግረናል፡፡ እንዲሁ  ስድስቱ  የወንጌል  ቃላት
የፈጣሪ  ፈቃዶች  ናቸው፡፡  እኛ  ይህን  የምህረት  ሥራ  ሊያደርጉልን  እንፈልጋለን፡፡  በሚቻለን  ለሌሎች  ልናደርግላቸው
ይገባናል፡፡ ደግሞም በዚህ ዓለም ሕይወታችን፣ ንብረታችን እንድንጠብቅ የፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ ከፈጣሪ ፈቃድ ወጥተን
በዚህ ሕይወት እንኖራለን፡፡ በተቀደሰ ፈቃዱ ካልሆነ በቀር ልንተወው አይገባንም፡፡እርሱ ፈጣሪያችን ለሁሉ ልቦናና ችሎታ
ስለሰጠ ኑሯችንን በዕውቀትና በሥራ እንድናሳምረው ይፈቅድልናል፡፡ ይህ ካልሆነ በቀር የሕይወታችን ፍላጎት አይገኝም፡፡
እንዲሁ  አንዱ  ካንዷ  ጋር  መጋባትና  ልጆች  ማሳደግን  ፈቅዷል፡፡  ደግሞም  ከልቦናችን  ጋር  የሚስማማ  ለህይወታችንም
ለሁሉም  የሰው  ልጆች  ኑሮ  የሚያስፈልጉ  ሌሎች  ብዙ  ሥራዎች  አሉና  የፈጣሪ  ፈቃድም  እንዲሁ  ስለሆነ  ልንጠብቀው
ይገባናል፡፡ እግዚያብሔር ፍፁማን አድርጎ እንዳልፈጠረን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ለመፈፀማችን የተዘጋጀን አዋቂዎችና በዚህም
ዓለም  እስካለን  ድረስ  እንድንፈፅምና  ፈጣሪያችን  በጥበቡ  ላዘጋጀልን  ዋጋ  የተዘጋጀን እንድንሆን  አድርጎ  ፈጠረን፡፡  በዚህ
ምድር ፍፁማንና ብፁዓን አድርጎ ሊፈጥረን ለእግዚአብሔር ይቻለው ነበር፡፡ ነገር ግን ለመፈፀማችን የምንዘጋጅ አድርጎ
ፈጠረን እንጅ እንዲሁ ሊፈጥረን አልፈቀደም፡፡ ከሞታችን በኋላ ፈጣሪያችን ለሚሰጠን ዋጋ የተዘጋጀን ፍፁማን እንድንሆን
በዚህ የፈተና ዓለም መካከል አኖረን፡፡ በዚህ ዓለም እስካለንም ወደ እርሱ እስኪወስደን ድረስ እየታገስን ፈቃዱን እየፈፀምን
ፈጣሪያችን  ልናመሰግነው  ይገባል፡፡  የፈተናችንንም  ጊዜያቶች  እንዲያቀልልን  ባለማወቃችን  ሠራነውን  የእብደት  አበሳ
እንዲተውልን የተፈጥሮ ሕግጋትን አውቀን እንድንጠብቃቸው ልቦና እንዲሰጠን ወደቸርነቱ እንለምን፡፡ ፀሎት ደግሞ ላዋቂ
ነፍስ  አስፈላጊ  ነውና  ዘወትር  ልንፀልይ  ይገባናል፡፡  አዋቂ  ነፍስ  ሁሉን  የሚያውቅና ሁሉን  የሚጠብቅ  ሁሉን  የሚገዛ
እግዚአብሔር እንዳለ ታውቃለች፡፡ ወደ እርሱ እንድትፀልይም ከእርሱ መልካም እንድትለምን፣ ከክፉ እንድትድንና ሁሉን
ወደሚችል እጅ እንድትማፀን ወደ እርሱ ትሳባለች፡፡ እግዚአብሔር ምሁርና ትልቅ ነው፡፡ የሚሳነውም የለም፡፡ ከበታቹ
ያለውን ያያል፣ ሁሉንም ይይዛል፣ ሁሉን ያውቃል ፣ ሁሉን ይመራል፣ ሁሉን ያስተምራል አባታችን ፈጣሪያችን ጠባቂያችን
ነው፡፡  የነፍሳችን  ዋጋ  ቸርና  ይቅር  ባይ  ችግራችንን  ሁሉ  የሚያውቅ  ነው፡፡  ለሕይወት  እንጂ  ለጥፋት  አልፈጠረንም፡፡
በትዕግስታችን ይደሰታል፡