Sunday, December 15, 2013

የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ለውጥ ከላዕላይ መዋቅር ይመነጫል እንጂ ለአንድ ሀ/ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ቢሮ አይደለም!


  • የማኅበረ ቅዱሳን ሩጫ ሀገረ ስብከት የመቆጣጠር ስልት እንጂ ዘረፈ ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለመፍታት አያገለግልም።
  • ማኅበረ ካህናቱ ከማኅበረ ቅዱሳን አፈናና ስለላ ለመዳን መታገል ያለባቸው ዛሬ ነው!
  • ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ ተቋማዊ ለውጥ የሚያስፈልገው ድርጅት ነው!
   ከዚህ ቀደም እንዳልነው ተቋማዊ ህዳሴና አስተዳደራዊ ለውጥ የሚያስፈልገው ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን  መነሻ ባደረገ መልኩ መሆን አለበት የሚለው ሃሳብ በመጀመሪያ ረድፍ የሚቀመጥ አጀንዳ ነው። ከላዕላይ መዋቅሩ ወይም ከዋልታው የለውጥ ተሐድሶ ባልተጀመረበትና ፈጽሞ ባልታሰበበት ሁኔታ በተናጠል የአንዱ ሀገረ ስብከት አጀንዳ እንደሆነ በመቁጠር በዚያ ዙሪያ መኮልኮል ውጤታማ ፍጻሜ ሊኖረው በፍጹም አይችልም።

 በተለይም ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን በተባለ አንጃ ተጠንስሶና የዲስኩር ውሃ ተሞልቶ ካህናቱ እንዲጠጡ በተዘጋጀው የስልጠና ወሬ የተነሳ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለውጥ ይመጣል ማለት ዘበት ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ ተቋማዊ ለውጥ የሚያስፈልገው አፈንጋጭ ድርጅት ሆኖ ሳለ የሀገረ ስብከቱ እቅድ ነዳፊ፤ አሰልጣኝና «የያብባል ገና» ዜማ ደርዳሪ ሆኖ መሰየሙ አስገራሚ ነው። እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ላይከዱት በልጆቻቸው ስም ቃለ መሃላ የገቡለት ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ «ተቀመጥ በወንበሬ፤ ተናገር በከንፈሬ» ብለው ለማኅበሩ ያስረከቡትን ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናቱ አሜን ይሁን፤ ይደረግልን ብለው መቀበላቸው ያሳዝናል። በጣፈጠና በለሰለሰ አማርኛ ነገ ብርሃን ሊወጣልህ ነው እያሉ በማደንዘዝ ላይ የተጠመዱት የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች የአዲስ አበባን ችግር ከአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር በተለየ የመፍታት ምትሃታዊ ኃይል ስላላቸው ሳይሆን ማኅበረ ካህናቱ ማቅ የተባለውን ድርጅት ውስጣችን አናስገባም ብለው ለ21 ዓመት የታገሉትን ለመቋቋም ይቻለው ዘንድ ገሚሱን የስልጠናው ደጋፊና ገሚሱን የስልጠናው ተቃዋሚ አድርጎ ከፋፍሎ በመምታት እግሩን በመሃከል አደላድሎ ለመትከል ያለመ መሆኑን ሊጤን ይገባል።
  ማኅበረ ካህናቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲመጣ ካስፈለገ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንትና ምሁራን እንጂ ይህ ገንዘቡን በጓሮ እያደለበ፤ ስንት እንደነገደና ስንት እንዳተረፈ ካዝናው የማይታወቅ የመሰሪዎች ስብስብ ማኅበር በሚያረቀውና በሚያቀርበው የስልጠና መርሃ ግብር መሆን እንደሌለበት ማኅበረ ካህናቱ ሊገነዘብ ይገባል። የራሱን በጉያ ደብቆ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ካዝና ለመቆጣጠር እቅድና ትልም ማውጣቱ ድፍረት ብቻ ሳይሆን ጳጳሳቱ እስከደገፉት የሚከለክለው እንደሌለ ያሳየበት አጋጣሚ ነው።
  መዋቅራዊውን ለውጥ ከግቡ ለማድረስ አቅሙና እውቀቱ ካላቸው ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከቅዱስ ሲኖዶስ መመንጨት አለበት። ከዚያም በተረፈ ቤተ ክርስቲያን ብትጠራቸው ይህንን ለመስራት ማገዝ የሚችሉ ቅን፤ የቤተ ክርስቲያናቸው ጉዳይ ግድ የሚላቸው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት የአስተዳደር ጉድለት ዘወትር የሚያንገበግባቸው ኦርቶዶክሳውያን ምሁራን ሞልተዋል። ስለዚህ ነጋዴ የወጣቶች መንጋ ስኬት ያገኘ ስለመሰለው ብቻ ሀገረ ስብከቱን ልዘዘው፤ ልናዘው ብሎ ስለጠየቀ ሊፈቀድለት አይገባም። ደረጃውም፤ አቅሙም ስላይደለ ሀይ ሊባል የሚገባው ሰዓት ቢኖር አሁን ነው።

 ስለሆነም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ማኅበረ ካህናት የሆናችሁ ሁላችሁም ይህ ካዝናውን በጓሮ የደበቀ ማኅበር የናንተን የአገልግሎት ካዝና እንዲቆጣጠር ልትፈቅዱለት አይገባም። እርግጥ ነው፤ የብዙ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳደሮች ጉድለት፤ ብክነትና ምዝበራ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። በእኛ እምነት ይህ ችግር የሚቀረፈው የቤተ ክርስቲያኒቱ ላዕላይ መዋቅር የችግሩን አንገብጋቢነትና ስፋት በጥልቀት ተመልክቶ በቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራንና ሊቃውንት አስጠንቶ አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ እንደሆነ እናምናለን። ከዚህ ውጪ አንዱን ጫፍ ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ በመስጠት ለውጥ ሊመጣ ስለማይችል ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ማሻሻል ጉዳይ እንዲወጣ መታገል ወቅቱ ዛሬ ነው።
በውስጥ ጉዳያችን ማኅበረ ቅዱሳን መግባት የለበትም ለማለት የማኅበረ ካህናቱ ድምጽ መሰማት ያለበት ዛሬ ነው።

Thursday, December 12, 2013

የማኅበረ ቅዱሳን መግነንና ብቀላ መሳ ለመሳ ናቸው፤ እንደጠዋት ጤዛም ቀትር ላይ ይጠፋሉ!


ነፍሳቸውን በአጸደ ቅዱሳን ያሳርፍልንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ያለውልና ፊርማ ተረክቧት እያስተዳደረ ይገኛል። አቡነ ጳውሎስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህንን መሠሪ ማኅበር ከመነሻው የደገፉት ሲሆን ውሎ አድሮ አካሄዱን አይተው የእድሜ ዘመኑን ለማሳጠር ብዙ ቢጥሩም ማኅበሩ ስር ሰዶ፤ የራሱን ጳጳሳት በመመልመል የሲኖዶሱን እኩሌታ መቆጣጠር የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ጥቂት ከማንገዳገድ ውጪ ሊጥሉት ሳይችሉ ቀርተው ወደማይቀረው ሞት ሄደዋል።
  አበው «የጠሉት ይወርሳል፤ የፈሩት ይደርሳል» እንዲሉ ይህንን ማኅበር የጠላነውን ያህል ሳይዳከም፤ የፈራነው ቤተ ክርስቲያኒቱን የመረከብ የረጅም ጊዜ ህልሙ እውን እያደረገ መገኘቱን ስንመለከት መጨረሻውስ? ብለን እስክንጠይቅ ድረስ መደመማችን አልቀረም። ምናልባት ቤተ ክህነቱን እንደወረሰ ቤተ መንግሥቱንም ይረከብ ይሆን? ይህንንም እንጠይቃለን። ማኅበሩን ስለመጥላት ስንናገር ሰውኛ ጥላቻ ሳይሆን  እንዴት አንድ ተራ ማኅበር፤ ለዚያውም በጦር ካምፕና በዝሙት መስዋእት ተመስርቶ ሁለት ሺህ ዘመን የዘለቀችውን ቤተ ክርስቲያን ተረክቦ በእጁ ያደርጋታል ከሚል መንፈሳዊ ቁጭትና መሸሻውም ይሁን መገኛው ከንስሐ ሥፍራ መሆን ሲገባው ዐመጽ ወልዶት፤ ዐመጽ ያሳደገው ማኅበር እዚህ መድረሱ አስገራሚም አስደማሚም ከመሆኑ የተነሳ ነው። አንዳንዶች ይህ ማኅበር እንደቴዎዳስ ዘግብጽ ቶሎ ያልጠፋው እግዚአብሔር ስለተከለው ነው በማለት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር በማስተሳሰር ሊያሳምኑን ይከጅላሉ። ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አጥፍቶ፤ ሕዝቡን 70 ዘመን በባርነት የገዛው ናቡከደነጾር እግዚአብሔርን ያመልክ ስለነበር ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለው እስራኤል ከእግዚአብሔር አምልኮ ስላፈነገጠ መሆኑም እንዳይዘነጋ ማስረጃ እናቀርብላቸዋለን። ማኅበረ ቅዱሳን 21 ዓመት የመቆየቱ ምስጢርና ቤተ ክርስቲያኒቱን እስከማዘዝ የመድረሱ ነገር በቅድስናው ልክ እግዚአብሔር በመደሰቱ ነው ብለን አናስብም። በዚህ ርዕስ የማኅበረ ቅዱሳንን አነሳስ ትተን አሁን ያለበትን መንፈሳዊ መሰል ሕይወቱን ብንዘረዝር ውሎ ያሳድረናል። ሌላው ቀርቶ የማይታዘዙለትን ጳጳሳት እንዴት እንደሚያበሻቅጥና ሰጥ ለጥ ብለው የሚታዘዙለትን ደግሞ የቱንም ያህል አስነዋሪ ገመና ቢኖራቸው ምን ያህል እንደሚያንቆለጳጵሳቸው በመመልከት ስለማኅበሩ መናገር ይቻላል። «ከእነማን ጋር እንደምትውል ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ» ይባል የለ!

  አብዛኛዎቹ ጳጳሳትም ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ይህንን ማኅበር ቆመው ማውረድ እስኪያቅታቸው ድረስ በተዘዋዋሪ መንገድ ለዚህ ማኅበር የምርኮኝነት እጃቸውን ሰጥተዋል። በየሄዱበት ሀገረ ስብከት ወንበራቸውን ከኋላ የሚሾፍረው ይህ ማኅበር ሲሆን በተለይም ከአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ በተጠናና በታወቀ ስልት እያደባ፤ ካህናቱንም ሳያስደነግጥ፤ በረቀቀ መንገድ አስተዳደሩን ተረክቦ የሁለት ተቋም አስተዳዳሪ ሆኖ ይገኛል። አንዱ  ቅዱስ የተባለው የሲኖዶስ መንበር ሲሆን ሁለተኛው በግልጽ የሚጠራበት የራሱ ማኅበር ተቋማዊ የንግድ አስተዳደር ነው። ለረጅም ጊዜ ባካበተው የስለላ ልምዱ መረጃዎችን ወደአንድ ቋት በመሰብሰብ እቅድና ትግበራውን በግልጽም በስውርም ያካሂዳል። ለዚህም ተጠቃሹ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዱ ነው።
  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሙስና፤ በአስተዳደር ብልሹነትና በንቅዘት ግንባር ቀደም ሀገረ ስብከት የመሆኑን ያህል ከፍተኛ የለውጥ እርምጃ የሚያስፈልገው ስለመሆኑ አያጠያይቅም።  እጃቸው በተጠመዘዘና በማኅበረ ቅዱሳን ሳንባ በሚተነፍሱት በአባ እስጢፋኖስ በኩል ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ግን «ላሞች ባልዋልሉበት ኩበት ለቀማ» ከመሆን የዘለለ ውጤት አይኖረውም ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን አናት ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ የመስጠት ሂደት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
  «የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በለውጥና ህዳሴ ጎዳና፤ ያብባል ገና» በሚለው የማኅበረ ቅዱሳን መፈክር ስር የተጠለለው የአስተዳደር ማሻሻል ትግበራ ሂደት ጥናቱ፤ እቅዱና አፈጻጸሙ ሙሉ በሙሉ እየተከናወነ ያለው በማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በኩል ስለመሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ዞሮ ዞሮ ሀገረ ስብከቱን ለማኅበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴ አመቺ በሆነ መልኩ ማዋቀርና ሊመጣ የሚችልበትን ግልጽና ስውር ተቃውሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዝጋት «ማኅበረ ቅዱሳን፤ ማኅበረ ቅዱሳን» የሚል ድምጸትን የሚያስተጋባ አስተዳደርን መመስረት ዋነኛ ግቡ ስለመሆኑ የምንሰማቸው አቤቱታዎችና እንቅስቃሴዎች አመላካች ናቸው። በቅርቡ እንዳየነው ለማኅበረ ቅዱሳን በጎ አመለካከት የላቸውም የተባሉ ካህናትና ሰራተኞች በስመ ዝውውርና ሽግሽግ ሰበብ ዱላ እያረፈባቸው መገኘቱ አንዱ አስረጂ ነው። ለወደፊቱም በፍጥነት ሳያስደነግጡና ሳያስደነብሩ በማለሳለስ ተመሳሳዩን የበቀል ዱላ እያሳረፉ ለአዲሱ ለውጥና ህዳሴ ስለሆነ ሁላችሁም «ያብባል ገና»  በሚለው ዝማሬ ስር ተሰባሰቡ ማለቱን ይቀጥላል። አባ እስጢፋኖስ ከማኅበረ ቅዱሳን ጉያ ለመውጣት አቅሙም፤ ብቃቱም፤ ሞራሉም የላቸውም፤ ስለዚህ በቦታው እስካሉ ድረስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጓሮ አስተዳዳሪ ማኅበረ ቅዱሳን ሆኖ መቀጠሉም አይቀሬ ነው። በባላ የተደገፈ ቤት ለጊዜው እንጂ በቀጣይነት ሊቆም አይችልም። የአባ እስጢፋኖስ የማኅበረ ቅዱሳን መዋቅራዊ ማሻሻያም የዚያው ተመሳሳይ ውጤት ከመሆን አይዘልም።  ምናልባትም የማኅበረ ቅዱሳን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የማቡካት የመጋገር ጅማሮ የማኅበሩን ዕድሜ ቀጣይነት ወሳኝ ምዕራፍ ከፋች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በሂደት የምናየውም ይሆናል።

ሌላው በተመሳሳይ መልኩ ማኅበረ ቅዱሳንን ካሰማሯቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል የሐዋሳው አቡነ ገብርኤል ተጠቃሽ ናቸው። እንዲያውም ማኅበሩ ራሱ በተደጋጋሚ እንደሚለፍፈው «ማኅበረ ቅዱሳን» ብለው የዳቦ ስሜን ያወጡልኝ አቡነ ገብርኤል ናቸው እያለ በሚጠራቸው የነፍስ አባቱ ቤትም ማዘዝ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በተዘዋዋሪም ተጠያቂነት ካለብኝም ይህንን ስም የሸለሙኝ ሊሆን ይገባል በሚል ድምጸት ማኅበሩ ስሙንና አቡነ ገብርኤል ለአፍታም ከአፉ አይነጥልም።

አቡነ ገብርኤል እድሜ ለንስሐ የሰጣቸውን አምላክ ከማመስገን ይልቅ ይህንን ማኅበር በጌታ ምትክ ዘወትር ሲያወድሱት ይታያሉ። በአሜሪካ አደባባይ «የፍየል ወጠጤ፤ ልቡ ያበጠበት…………» ከሚለው የጸረ ኢህአዴግ  ሰላማዊ ሰልፍ አንስቶ በይቅርታ ይሁን በንስሐ ከኢህአዴግ ጋር የታረቁበት መንገድ ለጊዜው ባይታወቅም ሐዋሳ እስከደረሱበት ጊዜ ድረስ በየሄዱበት ሰላም አስፍነው እንደማያውቁ ግለ ታሪካቸው  ይናገራል። ሐዋሳ እንደገቡም የመጀመሪያ ስራቸው ምእመናኑን በመከፋፈል ገሚሱን በማስደንበር የማባረር ስራ አሐዱ ብለው የጀመሩ ሲሆን ከዚህ ጀርባም ያ ቁጭ ብለው የሰቀሉትና ቆመው ማውረድ ያቃታቸው የነፍስ ልጃቸው ማኅበሩ አብሯቸው ነበር።
  እነመጋቤ ሐዲስ በጋሻውን፤ ቀሲስ ትዝታውንና ሌሎቹንም ዘማርያን ነክሶ የያዘውን ማኅበር ደስ ለማሰኘት አባ ገብርኤል እስከመጨረሻው ድረስ ለማሳደድ አላቅማሙም። ደም እስኪፈስና አካል እስኪጎድል ድረስ ሐዋሳን የጦርነት አውድማ ለማድረግም ወደኋላ አላሉም። ማኅበሩ ካዘዘ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥም ከመግባት እንደማይመለሱ ይታወቃል። እንዲያው ተሸፋፍኖ ይቅር ብለን እንጂ አባ ገብርኤል ምን የማያደርጉት ነገር አለ? ከዚህ በደል ለመገላገል ደግሞ ያላቸው ብቸኛው አማራጭ ንስሐ መግባት ሳይሆን ያንን ከነከሰ የማይለቅ ማኅበር እስከመጨረሻው ማገልገል ብቻ ነው። ሰሞኑን በእርቅ ሰበብ ከተጣሏቸው ምእመናን ጋር በመታረቅ አቡነ ገብርኤል ተስማምተውና አካባቢውን መስለው ለማደር ቢፈልጉም ያ ማኅበር ከኋላቸው ሆኖ «አይሆንም፤ አይደረግም» እያለ ሰቅዞ ይዟቸዋል። በተለይም የጥሉ አስኳል ተደርገው በማኅበሩ የብቀላ መዝገብ ላይ የሰፈሩት እነ በጋሻው ይቅርታ ይደረግልን የሚል ማመልከቻ ያቅርቡ እያለ መገኘቱ የሁከቱ ባለቤት ማን እንደነበረ በግልጽ እያሳየ ይገኛል። በዳይና ተበዳይ ማን እንደሆነ የመመርመር ሳይሆን ጉዳዩን በእርቅ የመፍታት ጥረት ላይ ነገሩን ለማደፍረስ የሚደረገው የማኅበሩ ሩጫ አስገራሚም አሳዛኝም ያደርገዋል።  በጋሻው «የበደላችሁኝን ሁሉ ይቅር ብያለው» ማለቱ ሲሰማ ማኅበሩ በተገላቢጦሽ «በድያችኋለሁና ይቅር በሉኝ» ሊል ይገባል በማለት ላይ መጠመዱ ሳያንስ ማኅበሩ በዚህ መካከል የሚጨምረው የተንኮል ቅርቃር ደግሞ «በጋሻው ሃይማኖታዊ ሕጸጽ ስላለበት ጉዳዩ በይቅርታ አያልቅም» የሚል መሆኑ ነው።

«የበደሉንን ይቅር እንደምንል» ጌታ ያስተማረን ጸሎት ነው። በጋሻው ይህንን በማለቱ ተቀባይነት የለውም ማለት ምን ማለት ነው? በግልባጩ በጋሻው በድሎናል የሚል ካለም ይህንን ቃል መልሶ በመጠቀም «የበደሉንን ይቅር እንደምንል» ማለት በጋሻው በድሎናል፤ ግን ይቅር ብለነዋል ማለት የክርስትና መገለጫ እንጂ የትንሽነት ወይም የተጠቂነት ስሜት ማንጸባረቂያ አይደለም። ይሁን እንጂ ማኅበሩ « የበደልኩ እኔ ነኝ፤ ይቅር በሉኝ» የሚል ልመና ሊቀርብልን ይገባል ሲል ይደመጣል። እንዲያማ ቢሆን ኖሮ እኛ የሰው ልጆች  ወደ እግዚአብሔር የማቅረብ የበደለኛነት ጥያቄ እያለብን  የተበደለው አምላክ በደላችንን ይቅር ሊለን ሥጋ ለብሶ ባልመጣ ነበር እንደማለት ነው።  «ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን» ሮሜ 5፤10
ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት» ማር 11፤25
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ» ቆላስ 3፤13

ዳሩ ግን ይህ ተበቃይ ማኅበር የጠላቸው ሰዎች መንበርከካቸውንና እጃቸውን በመሸነፍ ስለማስረከባቸው የማረጋገጫ ቃል ካላገኘ በቀር «የበደሉንን ይቅር ብለናል« የሚለው ቃል አያረካኝም እያለ ይገኛል። የወንጌልን ቃል የማይቀበል ይህን መናፍቅ ማኅበር ደርሶ የወንጌል ቃል ተቆርቋሪ ሆኖ በመታየት ሌሎችን የሃይማኖት ሕጸጽ አለባቸው በማለት አለማፈሩ ያስገርማል። የእነ ደብተራ ገለፈትን መጽሐፍ እንጂ ማኅበረ ቅዱሳንና ወንጌል የትም እንደማይተዋወቁ እርግጥ ነው። መናፍቁና ጸረ ወንጌሉ ማኅበር ተግባር የሚመሰክርበትን የወንጌል ቃል ተቃርኖ እየተናገረ ስለወንጌል የመናገር ብቃቱም፤ እውቀቱም የለውም። ዳሩ ግን «ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል» እንዲሉ ባሰረጋቸው መነኮሳቱ በኩል ጳጳሳት ሆነው ስለተገኙ ብቻ  ቤተ ክርስቲያኒቱን በእነሱ እጅ በመጥፎ አጋጣሚ እያሾራት መገኘቱ ያሳዝናል። እነ አባ ሉቃስን በመሳሰሉ አድር ብዬዎች በኩል መለመላዋን የተገኘችውን ቤተ ክርስቲያን ለጊዜው ተረክቧት ማኅበሩ እያስተዳደረ ነው። «የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ሁሉ ይቅር በለን» ማለት የክርስትና ጸሎት ነበር። ይህንን ማለት ግን የአላዋቂዎች ጸሎት ተደርጎ ተቆጥሯል። ዳሩ ግን ሥልጣን እውቀትን በተካበት ዘመን ወንጌል ሥፍራ እንደሌለው እውነት ነው። ይሁን እንጂ የወንጌል እውነት በሥልጣንና በገንዘብ ተቀብሮ ሊቀር አይችልም። ከማኅበረ ቅዱሳን አገልጋይ ጳጳሳትና ከማኅበሩም በላይ ሥልጣንና ኃይል የነበራቸውም እንኳን በታሪክ ውስጥ የወንጌልን እውነት ቀብረው ሊያስቀሩ አልተቻላቸውም። ወንጌል በኃይልና በሥልጣን ሊነሳ ሲፈልግ ቦታውን ግሳንግስ ይወረዋል። በውሸት መካከል የወጣ እውነት ሕይወትን የመስጠት ኃይል የሚኖረው ያኔ ነውና።
  የማኅበሩ እንዲህ መገስገስና በየስፍራው  እያየነው የመንገስ ጉዳይ የጥዋት ጤዛን ያሳየናል። ፀሐይ ሲወጣ ጤዛ ባለበት አይገኝም። ዛሬ ለእግዚአብሔር ያለመመቸታችንና ስለኃጢአታችን በፊቱ ያለመውደቃችን ምክንያት እንጂ ንስሐ ገብተን፤ መልካሙን ዘመን እንዲያመጣልን ከልብ ከጸለይን ብላቴን ላይ የተፈለፈለው ማኅበር እንደጥዋት ጤዛ ቢያለጨልጭም ቀትር ላይ ተመልሰን እንደማናገኘው እርግጠኞች ነን። ለዚህ ጸሎት አንድ ኤልያስ በመካከላችን እንደማይጠፋም እናውቃለን። በሰው ላይ እየፈረደ፤ ራሱን ለንግድ አሳልፎ የሚሰጥ ለጊዜው እንጂ ከቆመበት መውደቁ አይቀርም። ይልቅ ራሱን ለንስሐ ቢያዘጋጅ ይበጀዋል።

«እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ። ኃጥአን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም። ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል» መዝ 37፤34-38

 

Tuesday, December 10, 2013

ራሺያ የአሸባሪዎች መመሪያ ብላ የሰየመችው «ቁርአንን» በሀገሯ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዳይገባ አገደች።


 
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ የራሺያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአሸባሪዎች የሽብር መመሪያ ነው ያለውን ቁርአን ወደሀገሩ እንዳይገባ የእግድ ውሳኔ አሳለፈ። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ እንዳመለከተው ፤ አንድ መጽሐፍ ወደራሺያ ከመግባቱ በፊት ማኅበራዊ ኑሮን፤ የራሺያን ባህልና ወግ የማይጻረር መሆኑ ሳይመረመር በፊት መግባት ስለማይችል፤ ቁርአን የተባለው መጽሐፍ በሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ በራሺያው ዜጋ ኤልሚር ኩልየቭ በኩል ተተርጉሞ በነጻ ከታተመ በኋላ  ኮፒውን መርምረናል ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ይህ መጽሐፍ እንደማንኛውም ሌሎች መጽሐፍ ውስጡ ተመርምሮ የተደረሰበት ጭብጥ እንደሚያስረዳው ትርጉሙ ወደራሺያ ምድር ቢገባ ሽብርን በማበረታታት፤ ጥላቻን በመዝራትና ባህልና ወጋችንን በማደፍረስ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ በማድረግ በኩል አሉታዊ ጎኑ የበረታ በመሆኑ እንዳይገባ የእግድ ውሳኔ አሳልፈንበታል ሲል በውሳኔው ላይ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
  በኤልሚር ኩልየቭ በኩል የተተረጎመው ይህ በስም «ቁርአን» የተባለው መጽሐፍ በፍርድ ቤቱ የታየው በየትኛውም የሃይማኖት መጽሐፍነቱ ሳይሆን እንደአንድ ተራ መጽሐፍ ሲሆን የተመረመረውም ይኸው መጽሐፍ ሊሰጥ እንደሚችለው ሀገራዊ ጠቀሜታ አንጻር መሆኑንም ፍርድ ቤቱ ሳይገልጽ አላለፈም።

 ስለሆነም መጽሐፉ ለሀገራቸው ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ውስጡ ሲመረመር ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ትርጉሙ ወደሀገር ውስጥ እንዳይገባ ያገደ ሲሆን ይህንን የፍርድ ቤት እግድ ተላልፎ የተገኘ ማንም ዜጋ ሽብርተኝነትን በማበረታታትና በማስፋፋት በሚያስጠይቀው የሀገሪቱ ሕግ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆንም ተገልጿል።
  ይህ «ቁርአን» የተባለው መጽሐፍ የዐረቢኛው ትርጉም በራሺያውያን ሙስሊሞች እጅ የሚገኝ ቢሆንም ከራሺያ ቋንቋ ውጭ ስላሉ ትርጉሞች የተባለ ነገር የለም።

የራሺያው ቋንቋ የቁርአን ትርጉም  በወደሀገሪቱ እንዳይገባ መታገዱን በመቃወም የራሺያው የሙስሊሞች ሙፍቲ ራቪል ጋይኑትዲን ለራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጻፉት ደብዳቤ እንዳመለከቱት «ይህ እውቀት የጎደለውና ጸብ አጫሪ ውሳኔ እንደገና መታየት አለበት»  በማለት በኃይለ ቃል መግለጻቸውን «ኸፍ ፖስት» ጋዜጣ ዘግቧል።
  ጠቅላይ ሙፍቲው እንዳሳሰቡት « በጥቁር ባህር ወደብ ላይ ወደራሺያ ሊገባ የተዘጋጀው ይህ የቁርአን ትርጉም በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው፤ የእስላሞች መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ውሳኔ አድርገን እንቆጥራለን» ሲሉ መናገራቸውም ተሰምቷል። አንድ ራሺያዊ ዜጋ ስለጉዳዩ በሰጠው አስተያየት እንደተናገረው « ራሺያ እስልምና ለሚፈልገው ማንኛውም ጉዳይ እንደውሻ ጭራዋን እየቆላች ለማስተናገድ የምትገደድበት ምክንያት የለም፤ እስልምና እዚያው ተፈጠርኩበት ካለው በሳዑዲ ምድር አርፎ ይቀመጥ፤ እንግድነት ከፈለገም እኛ ዜጎቹ በምንፈቅድለት መጠንና መንገድ ብቻ ሊስተናገድ ይገባዋል ሲል የገለጸ ሲሆን ምሬቱን በማከልም « ሳዑዲ ዐረቢያ ቁርአንን አሳትማ ወደራሺያ ስትልክ እንድንቀበልላት እንደምትፈልገው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በዐረብኛ ተርጉመን ወደሀገሯ እንድናስገባ በኦፊሴል ትፈቅድልናለች ወይ? ሲል ጠይቋል።

የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በተመለከተ ለሙፍቲው የሰጡት መልስ ምን እንደሆነ አልተዘገበም።