Friday, December 21, 2012

ቤተ ክርስቲያኒቱ የወንበዴዎች ዋሻ፣ ንስሐ የማይገቡ ሌቦች መሸሺያ ሆናለች!!


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሰይጣን እንደ ስንዴ  ሊያበጥራት እግዚአብሔርን የለመነ ይመስላል። ልክ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በጭንቅ ይፈትናቸው ዘንድ እንደለመነው ማለት ነው።

ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነሉቃ 22  እንዳለው።

ከዚህ ፈተና ቤተ ክርስቲያኒቱ ትወጣ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አጥብቆ የሚጸልይ ኤልያሳዊ ማንነት  ያለው አንድም ሰው ጠፍቷል። ገዳማቱን የዐመጻ ሰዎች ሞልተውበታል። ዋልድባን በመሳሰሉ ትላልቅ ገዳማት ሳይቀር ቀጣፊዎች እርስ በእርስ በመነቃቀፍና  የሀሰት ስም በመለጣጠፍ፣ ስለሃይማኖት ልዩነት በማውራትና በማስወራት የሰይጣንን አገልግሎት በተገቢው እየፈጸሙ መገኘታቸው  በጸሎታቸው እንኳን ለዓለሙ ሊተርፉ የራሳቸውን ይዞታ ከስኳር ልማት ለማስጠበቅ የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ የተቃውሞ ሰልፍ አስፈልጓቸዋል። አብዛኛዎቹ ገዳማትም የመርበብተ ሰሎሞን፣ የመድፍነ ጸር፣ የዐቃቤ ርእስና የገድላ ገድል መፈልፈያዎች ከመሆን አልፈው የሀገሪቱን ችግር ማቃለል የሚችል የጸሎት መልስ የሚገኝባቸው ናቸው ብሎ መጠበቁ ከቀረ ዓመታት አልፈዋል። ደብረ ሊባኖስን ያየ ዓለም እንዴት ሰነበትሽ? ማለቱ እንደማይቀር  ጥርጥር የለንም።  ያላየም ሄዶ በማየት እውነታውን ሊያረጋግጥ ይችላል።

አዲስ አበባ ላይ ማጅራት መቺዎችና ኪስ አውላቂዎች ንስሐ ሳይገቡ አስተዳዳሪዎች፣ጸሐፊዎችና ገንዘብ ያዥዎች ሆነው አብያተ ክርስቲያናቱ የደም እንባ እያለቀሱ ይገኛሉ። ሰሞኑን በልደታ ቤተ ክርስቲያን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ሲዘርፉ የተደረሰባቸው የቢሮ ሠራተኞች ተጠቃሾች ናቸው። ቤሳ ቤስቲን የሌላቸው ሹመኞች ሚሊየነሮች ሆነዋል። ኑሮ በከበደበት ሀገር የቤተ ክህነቱ ሰዎች ቱጃሮች ለመሆን መቻላቸው ያስገርማል። ለሌቦቹ ካህናት ቤት መገንባትና መኪና መግዛት ቀላል ነገር ነው። እንደ እነ ቄስ ኃይሌ ዓይነቶቹ ዓይን አውጣዎች ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና ወደ መግዛት ተሸጋግረዋል። በብሔረ ጽጌ /ማርያም ቤተ ክርስቲያን የራያ ሰዎች መፈልፈያ ያደረገ ዘረኛ መሆኑም አንዱ የአሳዛኝ  ግብሩ ማሳያ ነው። እነ ኃይለ መለኮት በጎፋ ገብርኤል የኪስ ማደለቢያ ኢንቨስትመንት ከፍተው ያጋብሳሉ። የሰዋስወ ብርሃኑ ቤተ ክርስቲያን  አስተዳዳሪ ደግሞ ከእነ መሐመድ ጋር በድለላ ሥራ ተሰማርቶ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጊዜ የለሽ ሆኗል።

   እነ ተክለማርያም፣ ነአኩቶ ለአብ፣እነ እዝራ  ኧረ  ስንቱ ተቆጥሮ!!!  አብዱልቃድርና አሕመድም በስመ /ማርያም  ተሸሽጎ የማይጠፋ የሚመስለው ጭካኔ የተሞላበቱ ዘረፋና ዘረኝቱ ሲታይ ነው። ግራኝ አህመድስ ከዚህ ወዲያ ምን  አደረገ?  የአብያተ ክርስቲያኒቱ ዘረፋና ዘረኝነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ  መግነኑ ያንን ያሳያል።  ቤተ ክርስቲያኒቱ መሪና ተመሪ የሌላት የባለጊዜዎች መፈንጫ ሆናለች። በግብራቸው  እነ አቡነ ኢብራሂም፣ እነ አቡነ ኢሊያስ፣እነ አቡነ ጅብሪል፣እነ አቡነ ጊርጊስ  የሚመሯት፣ እነ የሃዘን ልብሱ (ማቅ) የሚያሾሯት ቤተ ክርስቲያን የወንበዴዎች ዋሻ፣ ንስሐ የማይገቡ ሌቦች መሸሸጊያ መሆኗ እውነት ነው። ጳጳሳቱ ሚሊየነሮችና G+ ባለህንጻዎች፣ ማኅበራቱ የሚሸጡባትና የሚሸቅጡባት የእርግብ ለዋጮች ሜዳ ካደረጓት ውሎ አድሯል።  በዚህም መሃከል ግን ብዙዎች ምስኪናን ቀሳውስትና  ዲያቆናት የበይ ተመልካች ሆነው በኑሮ እሳት ይጠበሳሉ።

Thursday, December 20, 2012

ጳጳሳቱንም ሆነ መንግሥትን በፓትርያርክ ምርጫ ላይ ስህተት እንዳይፈጽሙ እናሳሰባለን!

አባ ጎርጎርዮስ ፓትርያርክ ለመሆን የጓጓ ይመስላል።
Ø መንግሥትም እሱን የፈለገ ቢመስልም ምርጫው ከምራጭ ላይ የወደቀ ነው!!
Ø አባ ጎርጎርዮስ ምርጫው በእጣ ሳይሆን በካርድ ይሁን ሲል ውሏል። ለምን ይሆን?
Ø የውጭ ዜግነት ያላቸው ጳጳሳት ከጫወታው ውጪ ስለተደረጉ ሸክሙ ቀሎላቸው ይሆን?
ከአሜሪካው ሲኖዶስ ጋር ሲደረግ የቆየውና እርቅ ይሁን የሥልጣን ሼር /አክሲዮን/ መሆኑ ያልታወቀው ጉዳይ ያበቃለት ይመስላል። ይህም የምርጫ ህግና አስመራጭ በመምረጥ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ  ስለምርጫው አይቀሬነት እቅጩን ተናግሯል። ሥልጣን፣ ሥልጣን ከሚል ጩኽት ባሻገር መንፈሳዊ እርቅ ፈጽሞ የማይታይበትን ጉዞ በወጪና በኪሳራ ከማጀብ ይልቅ አዲስ ምርጫ አድርጎ  ሁለቱም ወገን ቁርጣቸውን አውቀው በያዙት ተግባር ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረጉ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለን። ዋናው ነገር የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስ እንደሚወደው አድርጎ ከመምራቱ ላይ እንደነበር ያኔም ይሁን ዛሬ ሁላችንም ችግሩን ስለምናውቀው ስለ ሥልጣን ሼር በመጨቃጨቅ ጊዜ ማጥፋት የለብንም። ሁሉም ባለበት የሐዋርያነትን ሥራ ይሥራ!!!
ይልቅስ አፋችንን ከፍተን ውጪ ውጪውን ስናማትር ብልጦች ተሽቀዳድመው ለቀም ሳያደርጉ የሀገር ቤቱን ሹመት ነቅተን መከታተሉ ጠቃሚ ነው።
የምርጫ ህጉ ከጸደቀ በኋላ ምርጫው በእጣ እንዳይሆንና እንደ ቀበሌ ሊቀመንበር ምርጫ በካርድ እንዲሆን ብዙ እንደተከራከረ የሚነገርለት አባ ጎርጎርዮስ፣ የውጭ ዜግነት ያላቸውን በህግ ሽፋን ለምርጫ እንዳይቀርቡ ካስወገደ በኋላ ራሱን ለፓትርያርክነት ማዘጋጀቱን ይነገራል። ላለፉት 20 ዓመታት በምሥራቅ ሸዋ / ስብከት ተቀምጦ ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ሳያሳይ ይህችን ቀን ሲጠባበቅ የቆየው ጳጳስ፣ ዛሬ ፓትርያርክ ለመሆን ሲሯሯጥ እጅግ ያስገርማል። ከዝዋይ ገዳም የአትክልት ሽያጭ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር እንደሰበሰበ የውስጥ አዋቂ መረጃዎቻችን  ከመጠቆማቸውም  ከዚያም ባሻገር በጆሮ ለመስማት በሚቀፍ ግብር ላይ የሚጠረጠር ሰው ዓይኑን በጨው ታጥቦ ቢቀርብ ቤተክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ፓትርያርክ አድርጋ ልትሸከም መዘጋጀት አይገባትም። የውስጥ ጉዳችንን ለማን እንነግራለን ብለው እንጂ ይህንን መጥፎ ግብሩን ጳጳሳትም ሳይቀሩ ያውቁታል። መንግሥትም ቢሆን በህዝቡ ዘንድ የጠራ ስምና ግብር የሌለውን እንደዚህ ዓይነቱን ሰው ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በማድረግ በራሱ ላይ እሳት ሲያነድ መኖር የለበትም እንላለን።  መንግሥት ለዚህ ሰው ውስጥ ውስጡን ድጋፍ ለማድረግ የወደደው በምን መለኪያ ይሆን?
የውጭ ዜግነት ያላቸው ጳጳሳት በምርጫ የመወዳደር ፋይል በምርጫ ህጉ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል። በዚያ ላይ ምርጫው በእጣ ሆኖ እግዚአብሔር የወደደው ይሁን እንዳንል እነ አባ ጎርጎርዮስ በካርድ ሽፋን ሥልጣን እጃችው ሊያስገቡ እጣ የሚባል ነገር መነሳት የለበትም በማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የምርጫ ሥርዓትን ሲቃወሙ ይገኛሉ።

Wednesday, December 19, 2012

በእጃቸው ካደጉ ልጆቻቸው አንዱ ነኝ

    ለደጀ ብርሃን
    “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ገንዘብን የሚወዱ ትምክህተኞች፤ትዕቢተኞች፤ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፤ የማያመሰግኑ፤ ቅድስና የሌላቸው፤ፍቅር የሌላቸው፤ዕርቅን የማይሰሙ ሃሜተኞች፤ ራሳቸውን የማይገዙ፤ጨካኞች መልካም የሆነውን የማይወዱ ከዳተኞች፤ ችኩሎች፤ በትዕቢት የተነፉ.....ይሆናሉ።”
(2ኛ ጢሞ. ምዕ. 3 ቁጥ.1-5)
Ø ለደጀ ብርሃን ማህበራዊ ድረ ገጽ ብሎገሮች /አምደኞች፤
በዚሁ ብሎጋችሁ የታላቁን ገዳምና መንፈሳዊ ማሰልጠኛ ዝዋይ ገዳም፤ እንዲሁም የመናኙን አባት ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ስም አንስታችሁ የጻፋችሁትን አሳዛኝና ህሊናዊ ሚዛን አልባ መረጃ ተመልክተናል።
እናንተ ማስተዋልን በተቀማ፤ የህሊና ፍርድ ለመስጠትም ማገናዘብ ባልቻለ ጭፍን ሀሳብና ክፉ ልብ፤ እንዲሁም የሚዲያን ባለሙያ ስነ ምግባር ባልጠበቀ ማንነት የጻፋችሁትን ይህንን የአንድ በስርቆትና የስነ ምግባር ጉድለት የተከሰሰና በህግ የተፈረደበት(እናንተው ራሳችሁ በጽሁፋችሁ እንደገለጻችሁት ማለት ነው)ግለ ሰብ ወሬ አይተን ዝም ብንል የእውነት አምላክ እውነቱን በሚያውቀው ህሊናችን ላይ ይፈርድብናልና የሚሰማ ልብና የሚያስተውል አእምሮ ቢኖራችሁም ባይኖራችሁም እውነቱን ልንነግራችሁ ግድ ነው።
ከሁሉ አስቀድመን ከላይ በመግቢያው የተጠቀሰውን የቅዱስ ጳውሎስን ህያው ቃል አንባቢ ሁሉ እንዲያስተውለው እንመክራለን። ምክንያቱም የተነሳንበትን ርዕሰ ጉዳይ የተመለከተ ሁሉ ምን አይነት ዘመን ላይ እንደ ደረስን ይገነዘብ ዘንድ ነው።
ይህ ዘመን የሀሰት አባት ዲያብሎስ በአንድም በሌላም መንገድ ውጊያውን ያጠነከረበት፤ በሀሰተኛ መረጃዎችም የዓማኙን ሁሉ ልብ ለስህተት ይማርክ ዘንድና በእውነተኛይቱ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንና መንፈሳውያን መሪዎችዋ ላይ በክፋት ያዘምት ዘንድ አበክሮ የሚሰራበት ክፉ ወቅት ነው። በእርግጥም ይህን የክፋትና የዓመጽ ዘመን መጨረሻ ምንነት አስቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ ያየው ታላቁ ሀዋርያ በዚሁ የስህተት ዘመን የሚነሱትን የሀሰት መልዕክተኞች ማንነት ሲገልጽ፦
“አእምሮአቸው የጠፋባቸው፤ ስለ እውነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ” ካለ በኋላ የክፋት አሰራራቸው የትም እንደማይደርስ ሲያረጋግጥ ደግሞ፦
“ዳሩ ግን የእነዚህ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም” ይላል። (2ኛ ጢሞ. ምዕ. 3 ቁ. 8—10)።
ስለሆነም የእውነት አምላክ ሁላችንንም ከስህተት ይጠብቀን ዘንድ እየጸለይን እንቀጥላለን።
ለመሆኑ እንዲህ በክፋት የዘመታችሁበት ታላቅ ገዳም ታሪክ እውነታና እንዲህ በክፉ ስም የኮነናችኋቸው ብጹዕ አባት ማንነት ምን ይሆን?
ይህ በክፋት ወሬ ስሙን ልታጎድፉት የምትጥሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተስፋና አለኝታ የሆነው ታላቅ ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ዝዋይ ገዳም በቀደሙትና የቤተ ክርስቲያን ብርሃን በነበሩት የህያው ታሪክ ባለቤትና ጻድቅ አባት አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ መንፈሳዊ ራዕይ የተመሰረተና ከእርሳቸው ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አለኝታ የሆኑና በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ቤተ ክርስቲያኒቱን በቅንነት የሚያገለግሉ ደቀመዛሙርትን በመንፈሳዊ ህይወትና በመልካም ስነ ምግባር አንጾ ከማፍራቱ በላይ አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን በጵጵስና ማዕረግ በአባትነት የሚመሩ ብዙ ብጹአን አባቶችን ያስገኘ፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን የነገ ተስፋ የሚሆኑ እጓለማውታ ህጻናት በቃለ እግዚአብሄር ተኮትኩተውና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ታንጸው የሚያድጉበት መንፈሳዊ የበረከት ስፍራ እንጂ በእናንተ አፍ እንደተባለው የጥፋትና የርኩሰት ቦታ አይደለም።