Friday, December 21, 2012

ቤተ ክርስቲያኒቱ የወንበዴዎች ዋሻ፣ ንስሐ የማይገቡ ሌቦች መሸሺያ ሆናለች!!


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሰይጣን እንደ ስንዴ  ሊያበጥራት እግዚአብሔርን የለመነ ይመስላል። ልክ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በጭንቅ ይፈትናቸው ዘንድ እንደለመነው ማለት ነው።

ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነሉቃ 22  እንዳለው።

ከዚህ ፈተና ቤተ ክርስቲያኒቱ ትወጣ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አጥብቆ የሚጸልይ ኤልያሳዊ ማንነት  ያለው አንድም ሰው ጠፍቷል። ገዳማቱን የዐመጻ ሰዎች ሞልተውበታል። ዋልድባን በመሳሰሉ ትላልቅ ገዳማት ሳይቀር ቀጣፊዎች እርስ በእርስ በመነቃቀፍና  የሀሰት ስም በመለጣጠፍ፣ ስለሃይማኖት ልዩነት በማውራትና በማስወራት የሰይጣንን አገልግሎት በተገቢው እየፈጸሙ መገኘታቸው  በጸሎታቸው እንኳን ለዓለሙ ሊተርፉ የራሳቸውን ይዞታ ከስኳር ልማት ለማስጠበቅ የማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ የተቃውሞ ሰልፍ አስፈልጓቸዋል። አብዛኛዎቹ ገዳማትም የመርበብተ ሰሎሞን፣ የመድፍነ ጸር፣ የዐቃቤ ርእስና የገድላ ገድል መፈልፈያዎች ከመሆን አልፈው የሀገሪቱን ችግር ማቃለል የሚችል የጸሎት መልስ የሚገኝባቸው ናቸው ብሎ መጠበቁ ከቀረ ዓመታት አልፈዋል። ደብረ ሊባኖስን ያየ ዓለም እንዴት ሰነበትሽ? ማለቱ እንደማይቀር  ጥርጥር የለንም።  ያላየም ሄዶ በማየት እውነታውን ሊያረጋግጥ ይችላል።

አዲስ አበባ ላይ ማጅራት መቺዎችና ኪስ አውላቂዎች ንስሐ ሳይገቡ አስተዳዳሪዎች፣ጸሐፊዎችና ገንዘብ ያዥዎች ሆነው አብያተ ክርስቲያናቱ የደም እንባ እያለቀሱ ይገኛሉ። ሰሞኑን በልደታ ቤተ ክርስቲያን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ሲዘርፉ የተደረሰባቸው የቢሮ ሠራተኞች ተጠቃሾች ናቸው። ቤሳ ቤስቲን የሌላቸው ሹመኞች ሚሊየነሮች ሆነዋል። ኑሮ በከበደበት ሀገር የቤተ ክህነቱ ሰዎች ቱጃሮች ለመሆን መቻላቸው ያስገርማል። ለሌቦቹ ካህናት ቤት መገንባትና መኪና መግዛት ቀላል ነገር ነው። እንደ እነ ቄስ ኃይሌ ዓይነቶቹ ዓይን አውጣዎች ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና ወደ መግዛት ተሸጋግረዋል። በብሔረ ጽጌ /ማርያም ቤተ ክርስቲያን የራያ ሰዎች መፈልፈያ ያደረገ ዘረኛ መሆኑም አንዱ የአሳዛኝ  ግብሩ ማሳያ ነው። እነ ኃይለ መለኮት በጎፋ ገብርኤል የኪስ ማደለቢያ ኢንቨስትመንት ከፍተው ያጋብሳሉ። የሰዋስወ ብርሃኑ ቤተ ክርስቲያን  አስተዳዳሪ ደግሞ ከእነ መሐመድ ጋር በድለላ ሥራ ተሰማርቶ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጊዜ የለሽ ሆኗል።

   እነ ተክለማርያም፣ ነአኩቶ ለአብ፣እነ እዝራ  ኧረ  ስንቱ ተቆጥሮ!!!  አብዱልቃድርና አሕመድም በስመ /ማርያም  ተሸሽጎ የማይጠፋ የሚመስለው ጭካኔ የተሞላበቱ ዘረፋና ዘረኝቱ ሲታይ ነው። ግራኝ አህመድስ ከዚህ ወዲያ ምን  አደረገ?  የአብያተ ክርስቲያኒቱ ዘረፋና ዘረኝነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ  መግነኑ ያንን ያሳያል።  ቤተ ክርስቲያኒቱ መሪና ተመሪ የሌላት የባለጊዜዎች መፈንጫ ሆናለች። በግብራቸው  እነ አቡነ ኢብራሂም፣ እነ አቡነ ኢሊያስ፣እነ አቡነ ጅብሪል፣እነ አቡነ ጊርጊስ  የሚመሯት፣ እነ የሃዘን ልብሱ (ማቅ) የሚያሾሯት ቤተ ክርስቲያን የወንበዴዎች ዋሻ፣ ንስሐ የማይገቡ ሌቦች መሸሸጊያ መሆኗ እውነት ነው። ጳጳሳቱ ሚሊየነሮችና G+ ባለህንጻዎች፣ ማኅበራቱ የሚሸጡባትና የሚሸቅጡባት የእርግብ ለዋጮች ሜዳ ካደረጓት ውሎ አድሯል።  በዚህም መሃከል ግን ብዙዎች ምስኪናን ቀሳውስትና  ዲያቆናት የበይ ተመልካች ሆነው በኑሮ እሳት ይጠበሳሉ።


   የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘመናትን አቋርጣ እዚህ የደረሰችው እንዲህ በቀላሉ አልነበረም። ብዙ ጦርና ሰይፍ አልፎባታል። ብዙ ልጆቿን በባእድ እጅ ለሞት ከፍላለች። ቅርስ፣ ታሪክና ሀገር ያቆየችው ዛሬ ከሜዳ ተነስተው እንደሚፈነጩባት የዘመኑ ዲስኩረኞች ወሬ ሳይሆን በመከራ ውስጥ አልፋ ነው። አዎ! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እስከነ ድክመትዋ ኢትዮጵያ ለምትባለው ሀገር መኖር ዋጋ የማይተምነው ባለውለታዋ ነች። የሚሳዝነው ነገር አመድ አፋሽ ሆና መቅረትዋ ነው እንጂ!!  የወላድ መካን ሆና ሥነ ምግባራቸው የቆሸሸ ጳጳሳት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት ተፈልፍለውባት ለሥልጣን ሲሉ የሚገዳደሉባት፡የሚወጋገዙባት፣ ራሳቸውን የሚያጩባት፣ ሀብቷን፡ንብረቷን የሚዘርፉባት፣ ዘረኝነቱን የሚያስፋፉባት፣ ሁሉም ጥርሱን የነከሰባት ሆና መገኘትዋ ያሳዝናል፣ ያስለቅሳልም።  ቤተ ክርስቲያኒቷ ከውስጥም ከውጭም የስንግ ተይዛለች። ድክመትዋን፣ ጉድፏንና ተግዳሮቶችዋን ከወዲሁ አርማ ካልተነሳችና ንስሃ ካልገባች መጪው ጊዜ አስፈሪ ነው።  መጽሐፉ እንደሚለው ዘመንን የሚሰጠው ለንስሐና ለበጎ ፍሬ ነውና።

እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁራዕይ 25

ከመቼውም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመከራ ወጀብ እየተናጠች ትገኛለች። ልብ ብሎ ያስተዋለው ካልሆነ በስተቀር ቀኑ መሽቶ በመንጋቱ ብቻ ነገሮች ሁሉ እንደ ወትሮ እየሄዱ ያለ የሚመስለው ጥቂት አይደለም። በምድር ላይ ያለው እውነታ ግን ያንን የሚያሳይ አይደለም።  በነነዌ ዘመን ውስጥ እያለፍን እንዳለን ይሰማኛል። አምላክ ሆይ አንዱን ዮናስ ላክና ከዚህ ዐመጻ እንድን ዘንድ የንስሐን እድል ስጠን! የርግብ ሻጮቹንና የገንዘብ ለዋጮቹን ጠረጴዛ ገልብጠህ እውነተኛ ቃልህ በደጅህ የሚታወጅበትን ቀን አምጣልን!!

ቤተ ክርስቲያኒቱ በሰይጣን ፈተና እንደ ስንዴ እየተበጠረች ነውና ስለእምነታችን አንተ ማልድ! አንተው ይቅር በል!! አሜን!