Tuesday, December 25, 2012

ማቅ የቤተክህነቱ እዳ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም እዳ ነው!!!

ከዚህ በፊት አንድ አንጋፋ ፖለቲከኛ፣ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባለው ድርጅትየቤተ ክህነቱ እዳ ነውበማለታቸው በማቅ መንደር አቧራው ጨሰ ማሰኘቱ  አይዘነጋም። ቹ ጠቅላይ ሚኒስትርም “ማቅ፣ሰለፊያ መሰል ማኅበር ነው” በማለታቸውም ብዙ ጊዜ የማኅበሩ ስውር ልሳኖች ወይም አፍቃሬ ማቅ እንደሆኑ ከሚታሙት የሀገር ቤት  መጽሔቶችና ጋዜጦች አንስቶ እስከ የመረጃ መረብ ድረ ገጾች ድረስ ማቅ እንዴት ተነክቶ? የሚል ጩኸት በአንድነት አስተጋብተው ነበር።  የማኅበሩ የጡት አባት የሆነው የሜሪላንዱ ሰውዬ ደግሞ እንባ ቀረሽ ጽሑፍ በማቅረብ የማኅበሩን ቅዱስ መሆን በመለፈፍ ለማሳመን ብዙ መጣሩን እናስታውሳለን። ማኅበሩ ያሰማራቸውና  በፍቅሩ የወደቁለት የጋሪ ፈረስ የመጦመሪያ ድረ ገጾችም ስለማኅበሩ ቅድስና በተጠራው  የምስክርነት ለቅሶ ላይ የቻሉትን ያህል የሀዘን እንባ ጽሁፍ በማቅረብ ትብብራቸውን አሳይተዋል። ማኅበሩ ከሰፈረበት የአሸባሪነት የመንግሥት /Black list/ ጥቁር መዝገብ ላይ ባያሰርዘውም ጊዜ ለመግዛትና መንግሥት ሊያፈርሰን ነው ከሚለው ፍርሃት ለጊዜውም ቢሆን መጽናኛ ሆኗቸው ማለፉ አይዘነጋም። የማቅ አልቃሾችን የአዞ እንባ ጽሑፍ ተከትሎ የማኅበሩን ዐመል በደንብ የመረመሩ  ጸሐፊያንምማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክህነቱ እዳበሚል ርእስ መጽሐፍ አሳትመው  ማኅበሩ ቅዱስ እንዳልሆነና በቅዱሳን ሽፋን ተሰባስቦ  የራሱን አጀንዳ  የሚያራምድ የእውነት ሁሉ እንቅፋት መሆኑን የሚያስረዳ  ጽሁፍ ለንባብ ማብቃት
 የተናጋሪ ፖለቲከኞችንም ይሁን የጸሐፊያኑን ማንነት ትተን በማቅ ዙሪያ የሚነገሩትን የተነገሩትን ልብ ብለን ብንመለከት ከማኅበሩ ጠባይ አንጻር የምንደርስባቸው እውነታዎች መኖራቸው  በምንም መልኩ የሚስተባበሉ አይደሉም።  ለመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ማነው?   የቅዱሳን ማኅበር የሚባለው የማኅበሩ አባላት ራሳቸው ናቸው ወይስ ስማቸው ያልተገለጸ ቅዱሳን? ከማኅበሩ ጠባያት አንጻር ብዙ ማለት የሚቻል ቢሆንም ስለ ቅድስናው ትተን ከዓላማው አንጻር ጥቂት አመክንዮታዊ ነጥቦችን እናንሳ።

የገጽታ ግንባታውን በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ መዘርጋት፣

1/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንበረ  ፓትርያርክ አንስቶ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ወጥ የሆነ መዋቅር እንዳላት ይታወቃል። ማኅበረ  ቅዱሳን ደግሞ በዚህ መዋቅር ውስጥ የታቀፈ ነገር ግን ራሱን የቻለ አንድ ተቋም ነው። ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ራሱን አክሎ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን መስሎ ተደራጅቷል። የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ለራሱ አባልነት ይመለምላል። ዐውደ ምሕረቷን ይጠቀማል። ከማእከል ወደ አጥቢያ የሚወርዱ መመሪያዎችን ያስተላልፋል፣ በማኅበሩ ንድፈ ሃሳብ /Theory/ የተጠመቁ ምልምል መምህራንን በስብከተ ወንጌል ስም ይልካል። በየአድባራቱ፣ ዩኒቨርሲቲውና ኮሌጆቹ ውስጥ የማኅበሩ ስም በወጣቱ ልብ ውስጥ እንዲሰርጽ አጥብቆ ይሰራል። ይህም ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተጠሪና ጠበቃ እንደሆነ ለማሳየት የሚከወን የመንፈሳዊነት የስም ግንባታ ሥራ መሆኑ ነው።

በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለ ሥልጣናት መጠቀም፣

2/ ራሱን አክሎና ቤተ ክርስቲያኒቱን መስሎ ለመንቀሳቀስ ይችል ዘንድ የጳጳሳቱን ማንነት ለራሱ ጥቅም በመጠምዘዝ፣ በመደለል፣እንዲሁም ቅዱስ በመምሰልና እውነተኛ እንደሆነ በውስጣቸው የማንነት ምስሉን በማስቀመጥ  ተቀባይነት እንዲኖረው የውዴታ መልካም ፈቃዳቸውን ይቀበላል። የማይቀበሉት ካሉ ደግሞ ራሱም ይሁን በአገልጋዮቹ በኩል ይዘምትባቸዋል።  በየደረሱበት ሁሉ ይቃወማቸዋል።/እንደ አቡነ ፋኑኤል ያሉትን፣ ከደቡበ ኢትዮጵያ ጀምሮ  እስከ አሜሪካ  እንዴት እግር በእግር እየተከታተለ ሲዋጋቸው መቆየቱን ልብ በሉ!!/     
በሚቀበሉት ጳጳሳትና የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች  የተነሳ ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለችበት ሁሉ ህልው ሆኖ ይንቀሳቀሳል።

የገንዘብ አቅሙን ማሳደግ፣

3/ “ገንዘብ ካለህ በሰማይ መንገድ አለ” በሚለው ብሂለ አበውና / GYM fitness makes you healthy man but  money GYM makes you powerful/  በሚለው ብሂለ  ፈረንጅ እየታገዘ የገንዘብ አቅሙን ለማዳበርና ፈርጣማ ክንድ እንዲኖረው ያለመታከት በመስራት ላይ ተጠምዶ የሚገኝ ሲሆን ይህንንም በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶችና በሲዲ ሽያጭ  እንዲሁም ሆቴሎችን በመክፈት፣ የንግድ ተቋማትን በመትከል፣ ህንጻ በመገንባት ላይ መሰማራቱ የ20 ዓመታት እውነታ  ነው። በዚህም የሚሊዮኖች ብር ባለሃብት ለመሆን አስችሎታል። ይህ ከበጎ አድራጊዎችና ከአባላት መዋጮ የሚያግበሰብሰውን ሳይጨምር ነው። ባለሃብት መሆን ክፋት ባይኖርውም የሰንበት ተማሪዎች ማኅበር ነኝ የሚል ማኅበር በዚህ ሁሉ የንግድ ዘርፍ ውስጥ መሰማራቱ ለስውር ዓላማው መሳካት የገንዘብን አስፈላጊነት ከማመን የተነሳ ካልሆነ በስተቀር እወክለዋለሁ ከሚለው ስም አንጻር የቀደሙት ቅዱሳን  በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ነበር የሚል ጽሁፍ እስካሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ አላቆየችንም።


ከፖለቲካው ንፋስ ጋር በጥበብ መንፈስ፣

4/ ማኅበሩ የ21ኛው ክ/ዘመን ወጣቶች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን የሀገሪቱን ሕይወትና የኑሮ  አየር ጸባይ ይከታተላል። አየሩ ሲሞቅ አብሮ ይሞቃል፣ ሲቀዘቅዝ ደግሞ አብሮ ይቀዘቅዛል። የማኅበሩ ሊቀመንበር የነበረው ሰው በአንድ ወቅት ማንም ሳይገርፈው ብዙዎቻቸን የኢህአዴግ አባላት ነን ማለቱም አይዘነጋም። ዳሩ ግን ማኅበሩ የኢህአዴግ አባል ይኖረው እንደሆን እንጂ ደጋፊ ሊሆን አይችልም።  አባል መሆን ለእስትራቴጂክ ጥቅም ሲሆን መደገፍ ደግሞ በአቋም እምነት ላይ የሚመሰረት ነውና በዚህ ዙሪያ  መንገዱ የተለየ ነው። ስለዚህ ማኅበሩ ከየትኛውም ወገን ሳይላተም ነፍሱን በማቆየት ለመዝለቅ ብቃት ያለውን እቅድ ይከተላል።

በግልጽና በስውር የወሳኝነት ድርሻውን መወጣት፣

5/ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ  ሲኖዶስ  ውስጥ በተወሰነ  መልኩ “አሜን”  ብለው በተገዙለት ጳጳሳት በኩል ገብቷል።  በተለይም  ለልቡ መሻት መላወሻ አሳጥተውት ከነበሩት ከአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት በኋላ የቀድሞ ተቃዋሚ ጳጳሳቱን በመጠቀም እነ ያረጋልና ባያብልን  በመሳሰሉት በኩል አጀንዳ ከማስቀረጽ አንስቶ  የሕግ ማርቀቅ ኮሚቴ አባል እስከመሆን ደርሷል። ስድስተኛው ፓትርያርክ ከሚመረጥበት  የምርጫ ህግ አንዱ ተሳታፊ መሆኑ እየታወቀ ለጉዳዩ እንግዳ የሆነ ለማስመሰል ቢሞክርም ስውር እጁን መጋረድ አልቻለም።  የስድስተኛውን ፓትርያርክ ምርጫ እቃወማለሁ የሚል ጩኸት የሚያሰማው  ከልቡ ስለሚቃወም ሳይሆን በዚህ ጩኸት ሽፋን ከሚያጃጅላቸው ደጋፊዎቹ ጋር ሳይጋጭ ራሱ ያጨውን ጳጳስ፣ ፓትርያርክ አድርጎ ለማስቀመጥ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ጠባብ ወቅት ስለቤተ ክርስቲያን አንድነት አጥብቆ መጮህ የሚያስገኘውን ጥቅም አሳምሮ ያውቃልና አጥብቆ መጮህን መርጧል።  ስለ አቡነ ሳሙኤል ፓትርያርክ መሆን እያስወራ ከመገኘት ጀምሮ  በስውር እጁ ደግሞ አባ ማቴዎስን እስከ ማጨት  እየሰራ እንዳለ  የመረጃ ምንጮቻችን ቢጠቁሙንም ማኅበሩ የሚመቸውን ሰው ለመሰየም እንጂ በእርቅ ጉዳይ ለመስራት የሚያስችል ማንነት እንደሌለው ግን እርግጠኞች ነን።  ምክንያቱም  ከውጭው ሲኖዶስ አባቶች ጋር ስምምነት እንደሌለው በግልጽ ይታወቃልና ነው። በተለይም ከአቡነ መልከ ጼዴቅ ጋር!!
ስለሆነም ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን አመራር በተወሰነ ደረጃ የተቆጣጠረ  በመሆኑ በስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫም ይሁን የእርቁ ሂደት በተገቢው መንገድ እንዳይሄድ በወዲህና በወዲያ ሁለት ስልቶችን ይዞ እየተጓዘ ይገኛል። 

ራሱን ለማቆየት ሁሉንም አማራጭ መጠቀም፣

7/  መንግሥት የዚህን ማኅበር ማንነት አሳምሮ የሚያውቀውና ጳጳሳቱም ቁጭ ብለው እንደሰቀሉት ቆመው ማውረድ እንዳቃታቸው ቢረዳም ነገሩን በትእግስት ለመከታተል እንደፈለገ እንረዳለን።  ማኅበረ ቅዱሳን  ከሰንበት ት/ቤቶች የማኅበር አቅም ጋር ከሚነጻጸርበት ደረጃ  ከፍ ያለና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሽፋን ራሱን የቻለ ተቋም ወደመሆን የተሸጋገረ  እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደተነገረበት ሰለፊያነቱን ለማስታገስ የሌሎቹን አሸባሪ ሰለፊያዎችን ፋይል እስኪዘጋ መታገስ አስፈልጓል ብለን እንገምታለን።  የግለሰቦችን ሰብእና በመግፋት ከማውገዝና ከማስወገዝ አንስቶ በስኳር ልማት የተቃውሞ ሰልፍ እስከመጥራት  የሄደበት ረጅም መንገድ ከወጋገን ባንክ ጋር በመወዳጀቱ  የሚሰረይ ሳይሆን የተቆረጠለት ቀን ባለመድረሱ ብቻ ነው።


መንግሥት አካላት መጠቀም፣

8/ ማቅ ብልጥ በመሆኑ ከተራ ፖሊስ አንስቶ እስከ ከፍተኛ  የመንግሥት ባለሥልጣናት በአባልነት አቅፎ ይዟል። ግለሰቦቹ ቤተ ክርስቲያኒቷ ከምትሰጣቸው መንፈሳዊ አገልግሎት በተለየ መልኩ ከማቅ የሚዘንብላቸው የቅድስና ማእበል ባይኖርም በአባልነት ታቅፈው በታማኝነት ያገለግሉታል። ተራ ፖሊሶቹ በማቅ የሚፈለግን ሰው አስሮ ከመደብደብ አንስቶ በሃስት ምስክር ክስ እስከ መመስረት ድረስ ሲያገለግሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ደግሞ ከመንግሥት የሚመጣው ምስጢራዊ ጫና እንዲረግብ የቅድመ ጥንቃቄ መረጃ ክፍል ሆኖ በመስራትና  በድልድይነት የገጽ ግንባታ ክፍል ሆነው አገልግሎታቸውን ያበረክታሉ።  በአንድ ወቅት ዲ/ን ሙሉጌታ ወ/ገብርኤል የማቅን ማንነት ገልጾ በመጽሐፍ በማውጣቱ ብቻ ፣ ለጽሁፉ ምላሽ ከመስጠት ወይም የተጣሰ መብታቸውን በሕግ ከማስከበር ይልቅ የማቅ አገልጋይ የመንግሥት አካላት ከወከባ እስከ ድብደባና እስር ድረስ የዘለቀ እርምጃ መውሰዳቸው ይታወቃል። በኋላም ወደ ግድያ የተሻገረ እንቅስቃሴ በመከተሉ መንግሥት ባለበት ሀገር ትንሹን መንግሥት፣ ማቅን በመሸሽ ወደ ኬንያ ብሎም ወደ አሜሪካ ለመኮብለል መገደዱን የምናውቅ እናውቃለን። ስለማቅ ገመና በመረጃ የተደገፈ መጽሐፍ መጻፍ እየተቻለ የሲሲሊው ማፊያ ማኅበር፣ የመንግሥት አባላት ሹመኞችን እርምጃ በመፍራት ቁም ሣጥናቸው ውስጥ ቆልፈው ለማስቀመጥ የተገደዱ አሉ። ከማኅበሩ ብቃት አንዱ በመንግሥት አካላት ሥልጣን መጠቀም የመቻሉ እውነት ነው።

ስናጠቃልል ማቅ የቤተ ክህነቱ እዳ ብቻ አለመሆኑን ማስመር እንፈልጋለን። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ማቅ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አቅም በላይ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ስለዚህ ማኅበር ማንነት ደፍረው ለመናገር ከማይችሉበት የፍርሃት ድባብ ሥር ወድቀዋል። በአጭር ቃል ማቅ፣ የቤተ ክህነቱ መንግሥት ሆኗል።  ይርቡም፣አይርቡም የሀገሪቱ የመንግሥት ተቃዋሚዎች እንኳን የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ ይደመጣል። በማቅ የቤተ ክህነቱ መንግሥት ግን ይህ መብት የለም። እንደቤተ ክህነት አባልነት ባይሆንና እንደሀገሪቱ የዜጋ መብት የአንድ ካህን ድምጽ በማኅበረ ቅዱሳን ክንድ የሚዳፈነው በየትኛው ሕገ መንግሥት ደጋፍ ነው? ቤተ ክርስቲያኒቱ ከላይ እስከ ታች በማኅበሩ መዳፍ ሥር ወድቃለች። እንደ እኛ እምነት ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ እዳ ከመሆን አልፎ የመንግሥትም እዳ ወደ መሆን ተሸጋግሯል እንላለን። መንግሥትን የምንጠይቀው ይህ ኃይል  በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያገለግለኛል የሚል ከሆነ ቁርጡን ይንገረንና የመንግሥት አንድ  ክንፍ አድርገን እንቁጠረው፣ አለበለዚያም በሁለት መንግሥት ለመተዳደር ይከብደናልና የቤተ ክህነቱን መንግሥት ማቅን ያይዝልን!! 

ውሎ አድሮ ማቅ የቤተ ክህነቱ እዳ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም እዳ መሆኑ እርግጥ ነው!!!!