Thursday, December 20, 2012

ጳጳሳቱንም ሆነ መንግሥትን በፓትርያርክ ምርጫ ላይ ስህተት እንዳይፈጽሙ እናሳሰባለን!

አባ ጎርጎርዮስ ፓትርያርክ ለመሆን የጓጓ ይመስላል።
Ø መንግሥትም እሱን የፈለገ ቢመስልም ምርጫው ከምራጭ ላይ የወደቀ ነው!!
Ø አባ ጎርጎርዮስ ምርጫው በእጣ ሳይሆን በካርድ ይሁን ሲል ውሏል። ለምን ይሆን?
Ø የውጭ ዜግነት ያላቸው ጳጳሳት ከጫወታው ውጪ ስለተደረጉ ሸክሙ ቀሎላቸው ይሆን?
ከአሜሪካው ሲኖዶስ ጋር ሲደረግ የቆየውና እርቅ ይሁን የሥልጣን ሼር /አክሲዮን/ መሆኑ ያልታወቀው ጉዳይ ያበቃለት ይመስላል። ይህም የምርጫ ህግና አስመራጭ በመምረጥ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ  ስለምርጫው አይቀሬነት እቅጩን ተናግሯል። ሥልጣን፣ ሥልጣን ከሚል ጩኽት ባሻገር መንፈሳዊ እርቅ ፈጽሞ የማይታይበትን ጉዞ በወጪና በኪሳራ ከማጀብ ይልቅ አዲስ ምርጫ አድርጎ  ሁለቱም ወገን ቁርጣቸውን አውቀው በያዙት ተግባር ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረጉ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለን። ዋናው ነገር የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስ እንደሚወደው አድርጎ ከመምራቱ ላይ እንደነበር ያኔም ይሁን ዛሬ ሁላችንም ችግሩን ስለምናውቀው ስለ ሥልጣን ሼር በመጨቃጨቅ ጊዜ ማጥፋት የለብንም። ሁሉም ባለበት የሐዋርያነትን ሥራ ይሥራ!!!
ይልቅስ አፋችንን ከፍተን ውጪ ውጪውን ስናማትር ብልጦች ተሽቀዳድመው ለቀም ሳያደርጉ የሀገር ቤቱን ሹመት ነቅተን መከታተሉ ጠቃሚ ነው።
የምርጫ ህጉ ከጸደቀ በኋላ ምርጫው በእጣ እንዳይሆንና እንደ ቀበሌ ሊቀመንበር ምርጫ በካርድ እንዲሆን ብዙ እንደተከራከረ የሚነገርለት አባ ጎርጎርዮስ፣ የውጭ ዜግነት ያላቸውን በህግ ሽፋን ለምርጫ እንዳይቀርቡ ካስወገደ በኋላ ራሱን ለፓትርያርክነት ማዘጋጀቱን ይነገራል። ላለፉት 20 ዓመታት በምሥራቅ ሸዋ / ስብከት ተቀምጦ ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ሳያሳይ ይህችን ቀን ሲጠባበቅ የቆየው ጳጳስ፣ ዛሬ ፓትርያርክ ለመሆን ሲሯሯጥ እጅግ ያስገርማል። ከዝዋይ ገዳም የአትክልት ሽያጭ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር እንደሰበሰበ የውስጥ አዋቂ መረጃዎቻችን  ከመጠቆማቸውም  ከዚያም ባሻገር በጆሮ ለመስማት በሚቀፍ ግብር ላይ የሚጠረጠር ሰው ዓይኑን በጨው ታጥቦ ቢቀርብ ቤተክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ፓትርያርክ አድርጋ ልትሸከም መዘጋጀት አይገባትም። የውስጥ ጉዳችንን ለማን እንነግራለን ብለው እንጂ ይህንን መጥፎ ግብሩን ጳጳሳትም ሳይቀሩ ያውቁታል። መንግሥትም ቢሆን በህዝቡ ዘንድ የጠራ ስምና ግብር የሌለውን እንደዚህ ዓይነቱን ሰው ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በማድረግ በራሱ ላይ እሳት ሲያነድ መኖር የለበትም እንላለን።  መንግሥት ለዚህ ሰው ውስጥ ውስጡን ድጋፍ ለማድረግ የወደደው በምን መለኪያ ይሆን?
የውጭ ዜግነት ያላቸው ጳጳሳት በምርጫ የመወዳደር ፋይል በምርጫ ህጉ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመልሷል። በዚያ ላይ ምርጫው በእጣ ሆኖ እግዚአብሔር የወደደው ይሁን እንዳንል እነ አባ ጎርጎርዮስ በካርድ ሽፋን ሥልጣን እጃችው ሊያስገቡ እጣ የሚባል ነገር መነሳት የለበትም በማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የምርጫ ሥርዓትን ሲቃወሙ ይገኛሉ።

Wednesday, December 19, 2012

በእጃቸው ካደጉ ልጆቻቸው አንዱ ነኝ

    ለደጀ ብርሃን
    “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ገንዘብን የሚወዱ ትምክህተኞች፤ትዕቢተኞች፤ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፤ የማያመሰግኑ፤ ቅድስና የሌላቸው፤ፍቅር የሌላቸው፤ዕርቅን የማይሰሙ ሃሜተኞች፤ ራሳቸውን የማይገዙ፤ጨካኞች መልካም የሆነውን የማይወዱ ከዳተኞች፤ ችኩሎች፤ በትዕቢት የተነፉ.....ይሆናሉ።”
(2ኛ ጢሞ. ምዕ. 3 ቁጥ.1-5)
Ø ለደጀ ብርሃን ማህበራዊ ድረ ገጽ ብሎገሮች /አምደኞች፤
በዚሁ ብሎጋችሁ የታላቁን ገዳምና መንፈሳዊ ማሰልጠኛ ዝዋይ ገዳም፤ እንዲሁም የመናኙን አባት ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ስም አንስታችሁ የጻፋችሁትን አሳዛኝና ህሊናዊ ሚዛን አልባ መረጃ ተመልክተናል።
እናንተ ማስተዋልን በተቀማ፤ የህሊና ፍርድ ለመስጠትም ማገናዘብ ባልቻለ ጭፍን ሀሳብና ክፉ ልብ፤ እንዲሁም የሚዲያን ባለሙያ ስነ ምግባር ባልጠበቀ ማንነት የጻፋችሁትን ይህንን የአንድ በስርቆትና የስነ ምግባር ጉድለት የተከሰሰና በህግ የተፈረደበት(እናንተው ራሳችሁ በጽሁፋችሁ እንደገለጻችሁት ማለት ነው)ግለ ሰብ ወሬ አይተን ዝም ብንል የእውነት አምላክ እውነቱን በሚያውቀው ህሊናችን ላይ ይፈርድብናልና የሚሰማ ልብና የሚያስተውል አእምሮ ቢኖራችሁም ባይኖራችሁም እውነቱን ልንነግራችሁ ግድ ነው።
ከሁሉ አስቀድመን ከላይ በመግቢያው የተጠቀሰውን የቅዱስ ጳውሎስን ህያው ቃል አንባቢ ሁሉ እንዲያስተውለው እንመክራለን። ምክንያቱም የተነሳንበትን ርዕሰ ጉዳይ የተመለከተ ሁሉ ምን አይነት ዘመን ላይ እንደ ደረስን ይገነዘብ ዘንድ ነው።
ይህ ዘመን የሀሰት አባት ዲያብሎስ በአንድም በሌላም መንገድ ውጊያውን ያጠነከረበት፤ በሀሰተኛ መረጃዎችም የዓማኙን ሁሉ ልብ ለስህተት ይማርክ ዘንድና በእውነተኛይቱ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንና መንፈሳውያን መሪዎችዋ ላይ በክፋት ያዘምት ዘንድ አበክሮ የሚሰራበት ክፉ ወቅት ነው። በእርግጥም ይህን የክፋትና የዓመጽ ዘመን መጨረሻ ምንነት አስቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ ያየው ታላቁ ሀዋርያ በዚሁ የስህተት ዘመን የሚነሱትን የሀሰት መልዕክተኞች ማንነት ሲገልጽ፦
“አእምሮአቸው የጠፋባቸው፤ ስለ እውነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው እውነትን ይቃወማሉ” ካለ በኋላ የክፋት አሰራራቸው የትም እንደማይደርስ ሲያረጋግጥ ደግሞ፦
“ዳሩ ግን የእነዚህ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም” ይላል። (2ኛ ጢሞ. ምዕ. 3 ቁ. 8—10)።
ስለሆነም የእውነት አምላክ ሁላችንንም ከስህተት ይጠብቀን ዘንድ እየጸለይን እንቀጥላለን።
ለመሆኑ እንዲህ በክፋት የዘመታችሁበት ታላቅ ገዳም ታሪክ እውነታና እንዲህ በክፉ ስም የኮነናችኋቸው ብጹዕ አባት ማንነት ምን ይሆን?
ይህ በክፋት ወሬ ስሙን ልታጎድፉት የምትጥሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተስፋና አለኝታ የሆነው ታላቅ ገዳምና የካህናት ማሰልጠኛ ዝዋይ ገዳም በቀደሙትና የቤተ ክርስቲያን ብርሃን በነበሩት የህያው ታሪክ ባለቤትና ጻድቅ አባት አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ መንፈሳዊ ራዕይ የተመሰረተና ከእርሳቸው ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አለኝታ የሆኑና በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ቤተ ክርስቲያኒቱን በቅንነት የሚያገለግሉ ደቀመዛሙርትን በመንፈሳዊ ህይወትና በመልካም ስነ ምግባር አንጾ ከማፍራቱ በላይ አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን በጵጵስና ማዕረግ በአባትነት የሚመሩ ብዙ ብጹአን አባቶችን ያስገኘ፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን የነገ ተስፋ የሚሆኑ እጓለማውታ ህጻናት በቃለ እግዚአብሄር ተኮትኩተውና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ታንጸው የሚያድጉበት መንፈሳዊ የበረከት ስፍራ እንጂ በእናንተ አፍ እንደተባለው የጥፋትና የርኩሰት ቦታ አይደለም።

Wednesday, November 7, 2012

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እንዲሰነጣጠቅ ሲኖዶስ የወሰነው ለምንድነው?

ጀ ብርሃን ብሎግ የዘንድሮውን የሲኖዶስ ጉባዔ በቅርበት እየተከታተለች ከመዘገብ የተቆጠበችው፤ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው ጉባዔ እንደመሆኑ መጠን በፓትርያርኩና በጽንፈኛ ጳጳሳቱ በኩል የሁለት ወገን መሳሳብ፤ እንዲሁም የኃይል ሚዛን መጠባበቅ ጉዳይ ያከተመለት በመሆኑ የነጠረ ወይም የከረረ ጉባዔ ሊኖር እንደማይችል በማመናችን ነበር። ይልቁንም በፓትርያርኩ ሞት የተነሳ የተገኘውን ክፍተት በማኅበረ ቅዱሳን የመሞላትና ታዛዥ ጳጳሳቱና ማኅበሩ በጋራ በሚቀርጹት አጀንዳ ይወሰን ዘንድ በሚፈልጉት ሃሳቦች ዙሪያ በጋራ ምክክር የሚፈጸም  እንደሆነ በማመናችንም ነበር።
 በእርግጥም ከጥቂት ተንፈራጋጮች በስተቀር በአብዛኛው እየሆነ ያለውና የሆነውም ይኸው ያለአቡነ ጳውሎስ መኖር ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ጉባዔ ላይ የጎደለውን በሞላው ማኅበርና እንዳሻቸው ለመናገር ክፍተት ባገኙ ጳጳሳት ፍላጎት የተደመደመ ሆኖ አልፏል። በአቡነ ፋኑኤል ሀ/ስብከት ጣልቃ በመግባት ማኅበሩን ለማስደሰት የተኬደው ረጅም ክርክር በአባ አብርሃምና በአባ ኤልያስ በኩል የተደመጠው ጫጫታ ክፍቱን ባገኙት ጉባዔ ላይ እድለኛ ተናጋሪዎች ሲያደርጋቸው ሰምተን ታዝበናል። ስለጳጳሳት ሀብት ማፍራት ተራ ዲስኩርና ባእዳዊ ዜጋ የመሆን ጉዳይ ከወሬ የማያልፍ መቀበጣጠርም መደመጡ እንደዚህም ብለን ሀቀኛ ለመምሰል ሞክረን ነበር ከማለት ያላለፈ እንደሆነ እንገነዘባለን። ከዚህ በፊት ስንለው እንደቆየነው ሁሉ ከእርቁ በፊት ስለስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዝግጅት ሸብ ረብ ዜማ ሲናፈስ መስማታችን እርቁን ከወዲሁ የመገፍተር ሁኔታና የውጭው ሲኖዶስ ራሱን ለምን ሕጋዊ ሲኖዶስ ይላል? የሚለውም ተልካሻ ክስ እርቁን የማጥላላት አንድ አካል እንደነበርም  አስተውለናል።
 የቤተክርስቲያኒቱ የዘመኑ ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ በመፈተሽ፤ የቤተክርስቲያኒቱ ድርሻ በመንፈሳዊ ፤ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያለችበትን ደረጃ በመገምገም የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመቀየስ ቀጣይ እርምጃዎችን የሚያመላክት ውሳኔ የሚያስፈልግበት አሳሳቢ ምዕራፍ ላይ ብትገኝም ለዚህ የተዘጋጀ አቅምና ችሎታ የሌለው ሲኖዶስ መያዢያ መጨበጫ በሌላቸውና እንቶ ፈንቶ በሆኑ ጉዳዮች ላይ 10 ቀናትን ማሳለፉ በእርግጥም መጪው ጊዜ የበለጠ ጨለማ ለመሆኑ አመላካች ነው።
ከፊት ለፊት ያለውን ያገጠጠ እውነት ወደጎን በመግፋት የአንድ ሳር ቢመዘዝ ….ዜማ ዛሬም ሳይለወጥ እየኮበለለ ያለውን ወጣት ባለበት ማቆየት ያልተቻለበትን ምክንያት መርምሮ መፍትሄ በመፈለግ፤ ቤተክርስቲያኒቱ ምእመናኖቿን ገንዘብ አምጡ ከምትለው ባሻገር በሰበሰበችው ገንዘብ መልሳ የልማት ስራ በመስራት ደራሽነቷን ማሳየት ሲገባት ሎሌቹ የሥራ ድራሻዋን ተረክበው በደን ልማት፤ በንጹህ የመጠጥ ውሃ፤ በጤና ልማትና በማኅበራዊ ተቋማት ግንባታ ላይ ተሰማርተው ወንጌሉን በተጓዳኝ እያካፈሉ ዛሬ ወደ 18 ሚሊዮን የደረሱት ባለፉት 20 ዓመት ውስጥ መሆኑ ስንመለከት፤ 2000 ዘመን ያስቆጠረችው ቤተክርስቲያን ግማሽ ያህል መድረሳቸው የማይቆጠቁጠው ሲኖዶስ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ያለውን ርዕይ ሳናይለት በመጠናቀቁ በአግራሞት ከመደመም ባሻገር ኅሊናቸው እንደፎጣቸው ከሽፍንፍን ተገልጦ የቤተክርስቲያኒቱን ችግር ለማየት ገና ብዙ ዘመን እንደሚቀረው ያስገነዘበን ሆኗል።
ሲኖዶሱ በየሁለት ዓመቱ የራሱን ደመወዝ እየጨመረ ከመበተን፤ ይልቁንም ከልመናና ከኃጢአት ሥርየት ገንዘብ በላተኝነት ራሱን ነጻ የሚያወጣበትን መንገድ ከመፈልግና ቤተክርስቲያኒቱ የሀብትና ንብረት ዘረፋ ባለሙያዎች የተሰማሩባት እስኪመስል ድረስ  ያለችበትን ተግዳሮት መከላከል ባለመቻል ሲንጫጫ ሰንብቶ መበተኑ እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን ያሳያል።
የሌለውን ስእል በመሳል ሐዋርያዊት፤ ጥንታዊት፤ብሔራዊት ወዘተ የሚል ራስን መሸንገያ ቃላትን በመደርደር ልክ በእውነተኛ መንፈሳዊ ማንነት ውስጥ ያሉ ለማስመሰል መሞከር እግዚአብሔርን ለማታለል ከመሞከር ከንቱነት ባለፈ የምንኖርበትን በእግዚአብሔር ፊት የተገለጠውን ማንነት አይሸፍነውም። መጥፎ ግብራችንን ያደበዝዘው እንደሆን እንጂ ትክክለኛውን መንገድ እየሄድን እንደሆነ አያረጋግጥም። እግዚአብሔር እንድንሆንለት የሚፈልገውን ስንሆንለት እንጂ በነበርነው ማንነት ላይ እየተመካን ግን ለመኖር ባልቻልንበት የአሁን ማንነታችን እየለካ ለራሳችንን የምንሰጠውን ውዳሴ የሚመዝን እንዳልሆነ ለማወቅ ከኤፌሶን፤ ከፊላዴልፊያና ከሰርምኔስ አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ መማር ያልቻለ ሲኖዶስ እየወሰደን የት ያደርሰን ይሆን? የሚለውንም ጥያቄ ብናነሳ ተገቢነቱ አያጠያይቅም ።
ከዚህ ውስጥ ዋነኛውና አስደናቂው ውሳኔ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ሰነጣጥቆ የማጠናቀቁ ሂደት አንዱ ነበር።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሲኖዶስ አባል የለም። ጳጳሳቱ የተመደቡባቸውን ሀ/ስብከቶች ለሥራ አስኪያጆቻቸው አስረክበው ሁለትና ሦስት ወራት ከአዲስ አበባ ቤቶቻቸው መሽገው ወለተ ማርያምንና ገ/ማርያምን እያሳለሙ እንደሚቀመጡ ይታወቃል። ግድ እየሆነባቸው እንጂ ሐዋርያዊ ተልእኰ ለመፈጸም ዝግጁዎቹ ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ አብዛኛዎቹ ጳጳሳት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመመደብ ያላቸው ፍላጎት ጫን ያለ ነው። ይህንኑ ጽኑ ምኞት ለመተግበር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ከፓትርያርክ ጳውሎስ ልዩ ሀ/ስብከትነት  በማላቀቅ 4 ቦታ እንዲከፈልና 4 ሊቃነ ጳጳሳት ሊመደቡበት ይታገሉ እንደነበር ያለፉት ጉባዔያቶቻቸው ያስረዱናል። ተፈላጊው ነገር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ችግሮች ምን እንደሆኑ በማወቅ መፍትሄ ለማምጣት ሳይሆን የአቡነ ጳውሎስን ስልጣን ከሀ/ስብከቱ ላይ በመቀማት 4 ጳጳሳት ተመድበውበት የሞቀ የደመቀውን በማግኘት ከክፍለ ሀገር ሀሩርና አቧራ ለመገላገል ብቻ ነበር። የሚገርመው ነገር ዛሬ አቡነ ጳውሎስ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መቻላቸው ሳይሆን ለምን? እንዲከፈል እንደተፈለገ አለማወቃቸው ነው። ምክንያቱም ሀ/ስብከቱን እንደዓይናቸው አምሮት ከመሰነጣጠቃቸው በቀር ለምን መሰነጣጠቅ እንዳስፈለገ የተናገሩት አሳማኝና ጥናታዊ መረጃ ያለውን ዝርዝር ነገር ሲነግሩን አለመደመጡ ነው። እንደ ደጀብርሃን ብሎግ እምነት የአዲስ አበባ ሀስብከት መሰንጠቅ የተፈለገው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ከፍላጎቶቻቸውና ከዓላማዎቻቸው አንጻር እንረዳለን።
1/ ከሚመጣው ፓትርያርክ ልዩ ሀ/ስብከትነት ነጻ በማውጣት ለሚመደቡ ጳጳሳት ልዩ የደስታ ግዛት ለመፍጠር፤
2/ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአንድ ሰው ግዛት አድርጎ ከማቆየት ይልቅ ከፋፍሎ ለሌሎችም ቶሎ እንዲዳረስ ለማስቻል ነው ብለን እንገምታለን። ምክንያቱም መሰነጣጠቅ ያስፈለገው ምን ለማምጣት እንደሆነ አሳማኝ ነገር አለመቅረቡ ነው።
በኛ እምነት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መሰንጠቅ ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔና የሀ/ስብከቱን ችግር ያልተመለከተ ስሜታዊ ውሳኔ ነው እንላለን። ምክንያቶቻችንም ለሀ/ስብከቱ የተሻለ መንገድ መኖሩን በማመላከት ይሆናል።
1/ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሀገሪቱና የአፍሪቃ ዋና ከተማ ከመሆኑም ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱ ማእከላዊ ሀ/ስብከት  በመሆኑ ሁኔታዎችን የገመገመ ልዩ መተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው ነበር።
2/ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አወቃቀር የመንግሥትንና ዓለምአቀፍ ተቋማትን ደረጃ ያገናዘበ ዘመናዊ፤ ሙያዊና ችሎታን የተመረኮዘ የአስተዳደር መዋቅር  የያዘ መሆን ነበረበት።
3/ አሁን ያሉትን አራት ሥራ ፈት የወረዳ ጽ/ቤቶችን ወደ ሁለት በማጠቃለል በአውራጃ ጽ/ቤት ደረጃ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሀ/ስብከቱ  ከፍሎ በመስጠት እንደአዲስ ቢደራጅ ስልጣን የተሰበሰበበትን የሀ/ስብከቱን  ማእከል ጫናና ድርሻ ከመቀነሱም በላይ ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማስፈን ይቻል ነበር።