«በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር…»!

የራስ ቅል ኮረብታ በ19ኛው ክ/ዘመን 

የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?» ገላ 3፤1
ኢየሱስ ክርስቶስ በየዓመቱ የሚከበርለትን የመታሰቢያ ትንሣኤ ሊመሠርት እንዳልመጣ እሙን ነው። የከበረ እንጂ የሚከብር፤ የሚፈጸም እንጂ የሚታሰብ ትንሣኤ ትቶልን አልሄደም። እንደዚያማ ከሆነ ከሕግ አገልግሎት ገና አልወጣንም ማለት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንደዚህ ያላቸው።

 «የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?»ብሎ ይጠይቃቸዋል።
 እውነት ነው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዕለት፤ ዕለት በዓይናችን ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ የሚታይ እንጂ በማስታወሻ መልክ በየዓመቱ «ዬ፤ዬ፤ዬ» እያልን የምናስበው የአንድ ሳምንት አጀንዳ አይደለም። የኦሪት ሕግ በዓላት በተወሰነላቸው ቀናት በየዓመቱ ይከበራሉ። ከዚያን ቀን ውጪ የሕጉ በዓላት በሰው ሕይወት ላይ የተደነገገላቸውን ኃይል ሊፈጽሙ ሥልጣን የላቸውም። አይሁድ ፋሲካቸውን  ከግብጽ ምድር የወጡበትን ዕለት በማሰብ በየዓመቱ ለአንድ ሳምንት በወርኀ ሚያዚያ ያከብራሉ። ያልቦካና እርሾ ያልገባበትን ኅብስት የሚመገቡት በፋሲካ ሳምንት ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ የፋሲካው የሕግ ሥልጣን ስለሚያበቃ ወደቀደመው አመጋገብና መደበኛ ኑሮ ይመለሳሉ። የክርስቲያኖች ፋሲካ ግን በአማኞች ሕይወት ላይ ያለምንም የብልጫ ቀናት ልዩነት በእምነት የሚፈጸምና ዓመቱን ሙሉ ኃይልና ሥልጣን ያለው አገልግሎት ነው። እንደገላትያ ክርስቲያኖች ወደ ሕግ ሥርዓት ተመልሰን በዓመት የምናስበውና የምንዘክረው እንዲሁም ከጥሉላት በስተቀር ሌላውን ገድፈንና የገደፍነውን መልሰን የምንረከብበት፣ እስከሆድ ድረስ የምግብ ዓይነት ነጻነታችንን የምናስከብርበት ዘመቻ ምግብ ፋሲካ አልተሰጠንም።  ፋሲካችን «እንኳን አደረሰህና እንኳን አደረሰሽ» በመባባል ያልደረስንበት የድነት ቀን ያለ ይመስል የሚታወስ የአንድ ሳምንት የስጦታ ካርድ መለዋወጫ በዓል በላይ የላቀ ሰማያዊ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው: «በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፤ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም"

«ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአል» ስንል እነዚህን የሥጋ ሥራዎች ሁሉ ከሕይወታችን አስወግደን በመንፈሱ ሥልጣን እየተመራን ነው ማለታችን ነው። እነዚህን ደግሞ የምናስወግደው በየዓመቱ በሚከበር ፋሲካ ሳይሆን ዕለት፤ ዕለት የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በፊታችን ተስሎ ሲገኝ ብቻ ነው። አለበለዚያ ከገላትያ ሰዎች የበዓል አከባበር አስተሳሰብ ገና አልወጣንም ማለት ነው። የገላትያ ሰዎች «አባ፤ አባት» ብሎ ለመጣራት የሚያበቃ የተሰጣቸውን የልጅነት ሥልጣን ትተው በባርነት ቀንበር ሥር ወደምትጥል ወደወር፤ ቀንና ዘመንን የማክበር ቁልቁለት ወርደው በተገኙ ጊዜ የተናገራቸው ቃል በዚህ ዘመንም ቦታ አግኝቶ መታየቱ ምን ዓይነት አዚም ቢወድቅብን የሚያሰኝ ነው።

«ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ» ገላ 4፤ 1-11

ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ፍለጋ የት መሄድ ይገባናል? የእግዚአብሔር መገኛው የት ይሆን? ከምድራዊት ቤተ መቅደስ? ከገሪዛን፤ ከጌባል? ወይስ በኢየሩሳሌም?
 አንዳንዶች ኢየሩሳሌምን የተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን ይሆናል ይላሉ። የቆረበ ደግሞ የበለጠ የ40 ቀን ሕጻን እንደሚሆንም ይሰበካል። ከተሳለመ የ40 ቀን ሕጻን በመሆንና ከቆረበ የ40 ቀን ሕጻን በመሆን መካከል ያለው ልዩነት አይገባኝም።  ኢትዮጵያ በመቁረብና ኢየሩሳሌም ከጎልጎታ ሄዶ በመቁረብ መካከልስ ያለው ልዩነት ምንድነው?  ሰዎች ክርስትናን እንደሕግ ሥርዓት ማክበር ሲጀምሩ የሕግ የብልጫ ልዩነት ክርስትናውን መውረስ ይጀምረዋል። ኢየሩሳሌም ሄዶ በመሳለም ወይም በመቁረብና ኢትዮጵያ በመቁረብ መካከል ልዩነት የሚመጣውም ለዚህ ነው። መቱ ባለች ቤተ ክርስቲያን ጓሮ በመቀበርና ደብረ ሊባኖስ በመቀበር መካከል ያለው የመብት ልዩነትም ውጤቱ የሕግ ተፋልሶ ክርስትናውን በመዋጡ የመጣ ነው። የወንጌል እውነት ግን ያንን እንድል አይነግረንም። እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቦታና በሥፍራ የሚወሰን አምላክ አይደለም። ስለዚህም እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በእምነትም፤ የመንፈስ  የሆነ ሥራ በሕይወታችን ላይ ሊገለጥ ይገባዋል። ያኔ ዲላ ሚካኤል ተቀበርን፤ ደብረ ሊባኖስ፤ ደሴ ቆረብን ሞቻ በማንነታችን ላይ ለውጥ የለውም። በሕይወቱ የክርስትና ማንነት የሌለው ሰው ደብረ ሊባኖስ ጓሮ መቀበሩ በፍርድ ወንበር ፊት ለውጥ አያመጣለትም። ሰው ሲሞት ይዞት የሚሄደው በምድር የነበረውን ሥራ እንጂ በሰማይ የሚፈጸም የክርክር ዳኝነት የለም። «እስመ አንተ ትፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ» እንዳለ ዳዊት በመዝሙር 62፤12
ስለዚህ እግዚአብሔር በመንፈስ ይመለካል፤ በመንፈስ ይሰገድለታል፤ በመንፈስ ይታመናል እንጂ በቦታና በሥፍራ አይደለም። እሱን ይይዝ ዘንድ የሚችል ምድራዊ መቅደስ የለንም። «ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ» የሐዋ 7፤50

«ወትቤሎ፤ አበዊነሰ በዝንቱ ደብር ሰገዱ፤ ወአንትሙሰ ትብሉ ከመ በኢየሩሳሌም መካን ውእቱ ኀበ ይሰግዱ። ወይቤላ ኢየሱስ፤ እመንኒ ብእሲቶ ከመ ትመጽእ ሰዓት አመ ኢበዝንቱ ደብር፤ ወኢበኢየሩሳሌም ዘይሰግዱ ለአብ፤ አንትሙሰ ትሰግዱ ለዘኢታአምሩ፤ ወንሕንሰ ንሰግድ ለዘናአምር፤ እስመ መድኃኒት እምነ አይሁድ ውእቱ። ወባሕቱ ትመጽእ ሰዓት፤ ወይእዜ ይእቲ፤ እመ እለ በርቱዕ በአማን ሰጋድያን፤ ይሰግዱ ለአብ በመንፈስ ወበጽድቅ እስመ አብኒ ዘከመዝ የኀሥሥ እለ ይሰግዱ ሎቱ። እስመ እግዚአብሔር መንፈስ ውእቱ፤ እለሂ ይሰግዱ ሎቱ በመንፈስ ወበጽድቅ ሀለዎሙ ይሰግዱ ሎቱ»

ትርጉም፤ 
«አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል» ዮሐ 4፤20-24

የኢየሱስ ስቅለት የሚታሰበው በመንፈስ መሆኑን ለማመልከት ጳውሎስ ለገላትያ  ሰዎች እንዲህ አላቸው። ኢየሱስ የተሰቀለው ኢየሩሳሌም እንጂ ገላትያ አለመሆኑን እያወቀ ለገላትያ ሰዎች ግን «በዓይናችሁ ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር» እያለ ይወቅሳቸዋል። ምክንያቱም ስቅለቱ በአማኞች ፊት የሚታየው በየዓመቱ ለሁለት ወር በሚደረግ ጾምና ለአንድ ሳምንት በሚታሰብ  የሕማማት ሳምንት ሳይሆን በየትኛውም ቦታ ብንሆን ያለምንም ዕረፍት በዘመናችን ሙሉ ነውና።
 የሕማማቱ ሳምንት ካለፈ በኋላስ? በዓለ ፍስሐ ወሀሴት፤ በዓለ ድግስ ወግብዣ፤ በዓለ ምግብ ወመጠጥ ነው? የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለሁለት ወር ከምግብ የመከልከል ማዕቀብና ለሁለት ወር ተከልክለው የነበሩ ምግቦች በተራቸው ድል የሚቀዳጁበት በዓል አይደለም። ዓመቱን ሙሉ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ የምናስብበት፤ በመንፈስና በእውነት የምንሰግድለት ቋሚ የሕይወታችን መርህ እንጂ በአርብ ቀን የወይራ ጥብጣብ የሚያበቃ ዓመታዊ ልምምድ ካደረግነው ከገላትያ ሰዎች በምን እንሻላለን? 

ለዚህም ነው፤ ብዙ ክርስቲያኖች ከነገሠባቸው የሥጋ ሥራ ሳይላቀቁ ፋሲካን እያከበሩ ዘመናቸውን ሁሉ የሚፈጽሙት። ጋብ ብሎ የነበረው የሥጋ ሥራ ከፋሲካ በዓል በኋላ ይደራል። ዝሙቱ፤ ውሸቱ፤ ስርቆቱ፤ ማጭበርበሩ፤ ሃሜትና ነቀፋው ያለማንነት ለውጥ እንደነበረው ይቀጥላል። ዓመቱን ሙሉ ያጠራቅሙትን ኃጢአት የፋሲካ ጾም ሲመጣ ለማራገፍ እንደሚቻልበት አመቺ ጊዜ ጠብቀው ብዙ ሰዎች ጥሬና ቆሎ ቋጥረው በየዋሻውና ፍርክታው ልክ እንደሽኮኮ ይመሽጋሉ። ሀብት ያላቸው ኢየሩሳሌም ሄደው ለመሳምና ለመቁረብ ገንዘባቸውን በየዓመቱ ይከሰክሳሉ። የክፉ ቃል ምንጭ የሆነውን አንደበቱን ሳይዘጋ ሥጋ መሸጫ ቤቱን የሚዘጋ የት የለሌ ነው። ከተማውን ሁሉ የወረረው የሚዛን መሥፈሪያ በፈሪሃ እግዚአብሔርና ያለማጭበርበር ሳይሰሩበት ጾም የሚሉትን ፈሊጥ የሚጠብቁት ለምንድነው?   አቤት! የዘንድሮ ሚዛን የሚባለው የድሮና የዚህ ዘመን ሚዛን ልኬታ የተለየ ሆኖ ይሆን?

የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሚዘርፉ የሕግ ፋሲከኞች ቁጥራቸው ብዙ ነው። የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል የሚከንፉ ነገር ግን የቤታቸውን የፍቅርና የሰላም ደወል የተነጠቁ ቤቱ ይቁጥራቸው። ሠራተኞቻቸውን የሚያስጨንቁ፤ በፍትህ አደባባይ ፍርድን የሚጨፈልቁ፤ በመማለጃም የእንባን ዋንጫ የሚጎነጩ የሁለት ወር ጸዋሚዎችና ተሃ ራሚዎች አያሌ ናቸው። የልምድ ክርስቲያኖች የሕይወት ምስክርነት በሥራቸው ሊታይባቸው አይችልም።  ስለዚህም ይመስለኛል፤ በክርስቲያን ቁጥር ብዙ ሆነን በበረከት መትረፍረፍ አቅቶን እድሜ ልካችንን ከእምነት የለሾች ምጽዋት ጠባቂ ሆነን የቀረነው። እንደእምነት የለሾቹ፤ እምነት የለሾች ብንሆን ያለእምነት ስለሚፈረድብን በሥጋ ረሃብ ባልተገፋንም ነበር። እግዚአብሔርን እየጠራን፤ እንደፈቃዱ ለመኖር ባለመቻላችን በራሳችን የእምነት ጉድለት በሥጋችን እንቀጣለን።  ብዙ ባወቅህ ቁጥር ብዙ ሥራ ይጠበቅብሃል። ካልሰራኸው ግን ባታውቅ ቢቀርብህ ይሻልህ ነበር። ስለዚህ ማወቅህ ለመዳንህ ዋስትና የሆነውን ነገር ካላትርፈረፈልህ ክርስትናህ ምንድነው? ኢየሱስ በባዶ ተስፋ አልተወንም። እኛ ግን አስሮ በያዘን በገላትያውያን አዚም ፈዘን ሳለ ስለገላትያ አዚም እናስተምራለን።

  የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለትና ትንሣኤ በየዓመቱ እየዞረ የሚመጣ በዓል ሳይሆን ዕለት፤ ዕለት በፊታችን ተስሎ የሚታየን የሕይወታችን አካል ነው መሆን ያለበት። በቦታ፤ በሥፍራና በጉዞ ብዛት የሚከበር ሳይሆን በእውነትና በመንፈስ እንድናመልከው የተደረገልን የማዳን ሥራ ነው። በአዲስ ሰውነት ለውጥ እንጂ በሕግ ሥነ ሥርዓት ልናሳልፈው አይገባም።  ሰላምና እርጋታ በውስጡ መኖሩን መንፈስ ቅዱስ የሚመሰክርለት አማኝ ሀገር ለሀገር፤ ተራራ ለተራራ ትንሣኤውን ፍለጋ ሲዞር አይገኝም። ምክንያቱም፤ ሁል ጊዜ በዓይኑ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታየዋልና»! ከተያዝንበት አዚም ተላቀን በልባችን የተሳለውን ትንሣኤ፤ በኑሮአችን ፍሬ የሚታይበት እንዲሆን እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን።
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 2 የተሰጡ አስተያየቶች

May 2, 2016 at 11:22 AM

እግዚአብሔር ይባርክህ።

June 7, 2016 at 7:19 PM

Amen..Egezihabeher yibarkeh!

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger