ቀልጣፋ ሬስቶራንቶች በቀላሉ የሚስቡን የፈለግነውን ምግብ በምንወደው መንገድ እንድናዝ መንገድ ስለሚከፍቱልን ነው። ጥቂት ካፌዎች ደግሞ ከመቶ በላይ የተለያዩ የቡና ጣዕም እንደሚያቀርቡ በጉራ ይናገራሉ። መኖሪያ ቤቶችና መኪናዎችን ስንገዛ እንኳ የምንፈልገው ምርጫ እንዲያሟላ እንሻለን። በቼኮላት፣ በቫኒላና በእንጆሪ ዓለም ታጥረን መኖር አንፈልግም። ፍላጎት ንጉሥ ነው! እንደግላዊ ፍላጎትህና ምርጫህ የምታገኝበት ሁሉ የተሟላበት ዘመን ነው። የዓይን አምሮትና ፍላጎትን የሚያሟላው ዓለም የእምነት መንገድንም ለዘላለማዊ ሕይወት ይበጃል ያለውን በአማራጭ አቅርቧል።
ታዲያ ለአንተ /ለአንቺ/ ትክክለኛ እምነት የማግኘቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ወቀሳ አልባ፣ ብዙ ጫና የሌለውና ይህንን አድርግ አታድርግ እያለ የማያስቸግር ሐይማኖት ብታገኝስ? ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ያውና እዚያ አለ እንደሚሉት ነገር፣ ሃይማኖት እንደሚወዱት አይስክሬም የሚመረጥ ነው እንዴ?
እድሜው፣ ሥርዓቱና ደንቡ ስለሚስብህ ይሆን? ወይስ በባለብዙ መንገድ የሕይወትህ ቤዛ ቃል ስለተገባልህ በአንዱ ላይ ተስፋህን ለማኖር?
ትኩረታችንን ለመሳብ የሚሻሙ በርካታ ድምፆች ስላሉ ለምን? ብሎ ነው አንድ ሰው ኢየሱስን ከሌሎች ማለትም ከመሐመድ ወይም ከኮንፊሸየስ፣ ከቡድሐ ወይም ቻርለስ ቴዝ ራስል ወይም ከጆሴፍ እስሚዝ አስበልጦ የሚመርጠው? ዞሮ ዞሮ ሁሉም መንገዶች የሚያደርሱት ወደ መንግስተ ሰማይ አይደለም እንዴ?
“በኢየሱስ እናምናለን” የሚሉቱ ራሳቸው የማዳኑን ተስፋ የሚገልጡበት መንገድ የተለያየ ስለሆነ እንደገበያ ላይ ሸቀጥ ገብተን ድነትን የምንሸምትባቸው አይደሉም።
በመሰረቱ ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉምና። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ መንግስተ ሰማይ አያመሩም። ሁሉም መንገዶች ወደ ኢንዲያና መቼም አያደርሱም። የእምነት ድርጅቶች ሳይሆኑ ወደመንግሥቱ የሚያስገባው ላመኑበት ሁሉ “ኢየሱስ ብቻ ነው” የምንለው ማለት ስለፈለግን ሳይሆን እንድንል የሚያስገድደን እውነት ያለው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ስለተፈፀመ ነው።
ኢየሱስ ብቻውን በእግዚአብሔር ሥልጣን ይናገራል።
1/ ምክንያቱም ኢየሱስ ብቻ ነው ሞትን ያሸነፈው። እስካሁን ድረስ መሐመድ፣ ኮንፊሸየስና ሌሎች በመቃብር በስብሰው ይገኛሉ። ነገር ግን ኢየሱስ በራሱ ስልጣን በጨካኙ የሮማውያን መስቀል ከሞተና ከተቀበረ ከሦስት ቀን በኋለ መቃብሩን ፈንቅሎ ተነስቶአል። በሞት ላይ ስልጣን ያለው ማንኛውም ሰው ትኩረታችን ሊስብ ግድ ይላል። ማንም በሞት ላይ ስልጣን ያለው ግለሰብ ሲናገር ልናደምጠው አስፈላጊ ነው። ሞትን ማሸነፍ የቻለ ከፍጥረታት መካከል ማንም የለም። ከሰማይ የመጣው ብቻ ሞትን አሸንፎ ወደሰማይ ወጥቷል።ስለዚህ እንዲህ ያለው አሸናፊ የተናገረው የእምነት መሠረት መሆን አለበት። ሰው ሟች መሆኑን ያውቃል። ሟች ደግሞ ከሞት ለማምለጥ የሚችለው በሞት ላይ ባለሙሉ ሥልጣን በሆነ ክንድ ላይ ሲያርፍ ነውና ኢየሱስን ማመን የግድ ይለዋል። በሞት ላይ ሥልጣን ያለው፣ ለሞታችን ብቸኛ ዋስትና የመሆን ብቃት አለው። ሌላ መንገድ፣ ሌላ ቃል ኪዳን፣ ሌላ አዳኝ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም የለም። ይህንን እውነት ያለምንም ድርድር ማወጅ ያልቻለ እምነት፣ ምድራዊ የሃይማኖት ድርጅት እንጂ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ምስክር አይደለም።
2/ የኢየሱስ ሕይወትና ትንሣዔ ምስክር ያለውና እውነት ነው።
የኢየሱስን ትንሣዔ የሚደግፈው መረጃ የሚያጥለቀልቅ ነው። ሮማውያንና ሰቃልያኑ ካህናት የኢየሱስን መቃብር ማስጠበቅ ያስፈለጋቸው «በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ» ያለውን ቃሉን ይዘው እንጂ የሞተ ሰው መቃብር ስለሚጠበቅ አልነበረም። አዎ ትንሣኤውን ለመከላከል ወታደሮች ከመቃብሩ ማንም እንዳይወጣ፤ ወደመቃብሩም ማንም እንዳይደርስ አድርገው አስጠብቀው ነበር። ነገር ግን የመቃብሩ ቦታ ባዶ ሆኗል! እንደተናገረው አልተነሳም እንዳይሉ የኢየሱስ ጠላቶች ያን ሁሉ ስለትንሣኤው የተነዛውን ወሬ ለማክሸፍ የበሰበሰውን አካሉን በማቅረብ በቀላሉ ያስታግሱት ነበር። ግን አልቻሉም፤ መላው ሲጠፋባቸው ደቀመዛሙርቱ ሬሳውን ሰርቀውት ይሆን? አሉ። ከሐዋርያቱ መካከል ከዮሐንስ በስተቀር ሌሎቹ የሸሹት በጊዜ ነው። የሸሹ ሰዎች ተመልሰው ከሮማ ወታደሮች ጋር ተዋግተው ሰረቁት ማለት የማይመስል ነገር ነው። የመቃብሩ ባዶ መሆን ሳያንስ ሞቶ የተቀበረ ሰው ዳግም ተነስቶ በሰዎች ፊት ራሱን በመግለጥ ያረጋገጠ በታሪክ ማንም የለም። ኢየሱስ ብቻ ይህን ማድረግ ችሏል።
ትንሣዔውን ያለምስክር ያልተወ ኢየሱስ ግን በአንድና በሁለት ሰዎች ፊት ብቻ ሳይሆን በአምስት መቶ ሰዎች ፊት ትንሣዔውን አስመስክሯል።
«መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ» 1ኛ ቆሮ 15፤4-8
ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለማመን የሚያስችላቸው በቂ የእምነት ማስረጃ ስላላቸው ነው። በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደኢየሱስ ሞትን ያሸነፈ፤ ትንሣኤውን በምስክር ያረጋገጠ ማንም የለም። ስለዚህ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ማንም ሰው ሊደመጥ ይገባል። ኢየሱስ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን አረጋግጧል። ስለዚህ የሚናገረውን መስማት ይገባናል። ለድነት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ መሆኑን ራሱ ይናገራል።(ዮሐንስ 14፡ 6)። ኢየሱስ ክርስቶስ ካሉትም ብዙ መንገዶች አንዱ አይደለም። ኢየሱስ ብቸኛ የድነት መንገድ ነው። ሌላ መንገድ ሁሉ በትንሣኤና በሕይወት ላይ ሥልጣን የሌለው የሞት መንገድ ነው። በሞትና በትንሣኤ ላይ ሥልጣን በሌለው ማንኛውም የመዳን ተስፋ ቃል ላይ አትታመኑ። እውነት የምትመስል ነገር ግን የጥፋት መንገድ ናት። “በዚህና በዚያም ትድናላችሁ” የሚሉ ድምጾች መጨረሻቸው ሞት ነው። ሟች ለሟች የተስፋ መንገድ መሆን አይችልም።
3/ ኢየሱስ ከሸክም ያሳርፋል።
በዚህ ምድር ላይ ከሸክም አሳርፋችኋለሁ ብሎ ቃል የገባ አንድም ሥጋ ለባሽ የለም። ይህ ብቸኛ ኢየሱስ እንዲህ ይላል “እናንተ ደካሞች፤ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11፡ 28)። ሕይወትም አስቸጋሪ ነው። ብዙዎቻችን ደምተናል፣ ቆስለናል፣ ጦርነትንም እንፈራለን። ዓለምም አስጨናቂ እየሆነች ነው። ስለዚህ የሚያሳርፈንን ብንፈልግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ከኢየሱስ በቀር ሸክም የከበዳችሁ ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ ያለ ማንም ሌላ የለም። በትንሣኤውና በሕይወቱ የታመነ ኢየሱስ ይህንን የማለት ብቃት ስላለው በእርሱ ላይ ማረፍ ከአስጨናቂው ዓለም ለመዳናችን ዋስትናችን ነው። ከድካማችሁ በማያሳርፉ በማንም ላይ አትታመኑ። ትድኑበት ዘንድ ብቸኛው ቃል ኪዳን ኢየሱስ ለመሆኑ “ወደእኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” የሚል ቃል ነግሮናልና ነው። በዚህ ተራራ ወይም በዚያ ሸለቆ የሚያሳርፍ ቃል የለም። ቃል፣ ቀራንዮ ላይ ስለእኛ አንድ ጊዜ ተሰጥቷል። በሞቱ ሞታችንን ሽሮ፣ በትንሣኤው ሕይወት በሰጠን በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ብቻ እንድንታመን የሚያስፈልገን የሚያስተማምን ምስክርነት ስለተወልን ነው።
ስለዚህ ምን ትፈልጋላችሁ? ከኃጢአት፤ ከድካም፤ ከተስፋ መቁረጥ በንስሐ መታደስ ወይስ የአንዱ ሃይማኖት አባል በመሆን ብቻ መኖር? ሕያው የሆነ አዳኝ ወይስ “ከሞቱት በርካታ ነቢያት ወይም ጻድቅ” አንዱን ተስፋ ማድረግ? ትርጉም ያለው ግንኙነት ወይስ ተራ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት መከተል?
4/ ኢየሱስ አማራጭ ሳይሆን ምርጫ ነው!
ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈሳዊ ድርጅት ወይም የአንዱ ተቋም ስያሜና የዚያ አባል ሆኖ መኖር ማለት አይደለም። ከእግዚአብሔር አብ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት ትፈልግ እንደሆን ሃይማኖትህ ኢየሱስን ማመን ነው። «በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው» ይላል መጽሐፍ። (ዮሐንስ 3፡ 36) አንዳንዶች ይህንንማ እናምናለን ነገር ግን ትክክለኛው እምነት ያለው በኛ ሃይማኖት ውስጥ ስለሆነ አባል ሁነን ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በማኅበር ስለመጸለይ ይነግረናል እንጂ ኢየሱስን ለማመን የዚህ ወይም የዚያ ሃይማኖት ተቋም አባል የመሆን ትዕዛዝ የለውም። ኢየሱስ በሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዲድኑ እንጂ የሃይማኖት ድርጅት ሊመሠረት አልመጣም። ለጸሎት በኅብረት መሆን ቢያስፈልግ መጀመሪያውም መጨረሻውም የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ የሚከብርበት እንጂ ሰው፣ ሰው የሚሸትበት፣ ብቃትና የሰዎች ማንነት የሚደሰኮርበት ከሆነ ድርጅትን ማምለክ ይሆናል። በዚህ ዘመን ብዙዎች ተሰነካክለዋል።
በራሱ ሥልጣን ከሙታን የተነሳ ማን አለ? ወይም በዓለም ላይ ካሉ የተለያዩ የሃይማኖት ድርጅቶች መካከል ለሰው ልጆች ዘላለማዊ የሕይወት ተስፋ ለመስጠት አስተማማኝ ማን አለ? መሐመድ፣ ኮንፊሽየስ፣ ራስል፣ ስሚዝ፣ ሉተር፣ ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንት ወዘተ ማንም ቢሆን ይህን ማድረግ አይችሉም።
እምነት ከሞት በላይ በሆነ በትንሣኤው ምስክርነት ላይ ይታመናል። ሕይወት ከድርጅት ሥልጣንም ባለፈ ብቸኛ የድነት መንገድ በሆነው ኢየሱስ ላይ ይጸናል።
“እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” ዮሐ 6:47 ያለን ኢየሱስ ብቻ ነው።