Tuesday, April 5, 2016

ደቀ መዝሙር ከፍያለው ቱፋ ወደኮሌጁ እንዲመለስ ተወሰነለት!



ሰበር ዜና
       ደቀመዝሙር፥ ዲያቆን፥ ዘማሪ፥ መምህር ከፍያለው ቱፋ ‹‹በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ›› በነጻነት እየወጣ እየገባ እንዲማር የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምድብ አንድ ፍ/ብሔር ችሎት ወሰነ!!
       የሞት ጣር የሚያቅረው ማህበረ ቅዱሳን የተባለ የባንዳ ስብስብ፥ ባሳለፍነው ሳምንት ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ከሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፥ ከትምህርት ገበታው እንዲነሳ በላካቸው ጀሌዎቹ በኩል ተሟግቶ ‹‹እንዲታገድ›› ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህችም እንደትልቅ ድል ተቆጥራ ‹‹ሐራ ዘተዋህዶ›› በተባለችው የደከመች ብሎጋቸው ላይ ሁለት ጊዜ ዜና ሰርተው ማናፈሳቸውም የሚታወስ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ደቀመዝሙሩ እንዲታገድ በተወሰነው ‹‹ውሳኔ›› ላይ የኮሌጁ የበላይ ኃላፊ ‹‹ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤልና የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኀሩያን ሰርጸና ብዛት ያላቸው የኮሌጁ አመራሮች›› አለመፈረማቸውን ሸሽገዋል፡፡ ያልፈረሙበት ምክንያት ደግሞ ደቀመዝሙሩን ከኮሌጁ የሚያስወጣ የሃይማኖት ሕጸጽ ባለማግኘታቸው ነው፡፡ የማህበሩ ጀሌዎች ግን ኃላፊነቱን በመውሰድ፥ ያልስልጣናቸው የኮሌጁን ማህተም ተጠቅመው፥ ደቀመዝሙሩን ያሰናበቱት፡፡ ይህ ደግሞ ወንጀል በመሆኑ ምክንያት ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ለሚመለከታቸው የቤተክርስቲያናችን አባቶች በማሳወቅ፥ ጉዳዩን ‹‹ወደ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምድብ አንድ ፍ/ብሔር ችሎት›› ለመውሰድ ተገድዷል፡፡
        ከታች ለማስረጃነት ያቀረብነው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ፥ በቀን 23/07/2008 ዓ/ም፥ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት/ኮ/ቀ ምድብ 1ኛ ፍ/ብሔር ችሎት፥ በቁጥር የኮ/መ/ቁ 50074 ያሳለፈው ውሳኔ ሲሆን፥ ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ላይ በኪራይ ሰብሳቢነት የማህበረ ቅዱሳን ጀሌዎች በኮሌጁ ስም ያሳለፉትን ውሳኔ፥ ከመሰረቱ ያፈረሰ ‹‹አጭርና ግልጽ›› ትዕዛዝ ነው፡፡ ትዕዛዙም እንዲህ የሚል ነው፡-
“ሌላ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ ተከሳሽ በከሳሽ ላይ ትምህርቱን እንዳይማር የሰጠው ውሳኔ እንዳይፈጸም ታዟል፡፡ ለሚመለከተው አካል ይጻፍ፡፡ ማለትም በደብዳቤ ቁጥር 399/2/233/08 በ19/07/2008 ዓም የተጻፈው እንዳይፈጸም ታዟል፡፡”
       እንግዲህ ሽንፈት ለማን ነው? ለጠላት፥ ለዲያብሎስ አይደለምን? አሸናፊውስ፥ የልባችን ንጉስ፥ ጌታችን ኢየሱስ አይደለምን? እነሆ መስፋትና ማሸነፍ ለእግዚአብሔር ልጆች ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ መክሰር ለዲያብሎስ ሆኗል!!
      ይህ በእንዲህ እንዳለ ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ከትምህርት ገበታው እንዲነሳ ውሳኔ በማሳለፍ ሥራ ላይ የተጠመደው፥ በሙስና የኮሌጁ ምክትል ዲን የሆነው አቶ ማሞ ከበደ፥ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አልፈጽምም በማለቱ ምክንያት እስራት ይጠብቀዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ ማሞ ከበደ በማህበሩ የተሰጠውን አጀንዳ ለማስፈጸም ሲል ብቻ፥ ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤልና የኮሌጁ ዋና ዲን የሆኑት ሊቀ ኀሩያን ሰርጸ ፊርማቸውን ሳያስቀምጡ፥ ካለስልጣኑ በኮሌጁ ስም በወሰነው ወንጀል ሌላ ዘብጥያ ይጠብቀዋል፡፡ ሲጀመር አቶ ማሞ ከበደ የኮሌጁ ሠራተኛ ነው እንጂ የሃይማኖት ህጸጽ መርማሪስ ማን አደረገው? የሃይማኖት ህጸጽ ቢኖር እንኳ ሊጠይቀው የሚገባው፥ ቤተክርስቲያን ሥልጣን የሰጠችው አካል የሊቃውንት ጉባኤ ነው እንጂ፥ አንድ ጤና የጎደለው ሠራተኛ አይደለም፡፡ ሲኖዶስ ያልወሰነውን፥ ሊቃውንት ጉባኤ ያልወሰነውን ግለሰቡ የማሕበረ ቅዱሳንን አጀንዳ ተሸክሞ ለማስፈጸም መድከሙ ነውረኛነቱን የሚሳይ ነው፡፡ ሲቀጥልም ግለሰቡ የሃይማኖት ሕጸጽ የመመርመር ሥልጣንም ይሁን ብቃት የለውም፡፡ በርግጥ አቶ ማሞ ከበደ በደቀመዝሙሩ ላይ የእግድ ደብዳቤ የጻፈው ‹‹የሃይማኖት ህጸጽ›› ተመልክቶ ሳይሆን፥ ከማኀበሩ በሚያገኘው የኪራይ ሰብሳቢነት ልክፈት በመለከፉ ምክንያት እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክሩለታል፡፡
ይህን ጉዳይ እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡