በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተለመደ የመጣ ችግር አለ። በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በሁለትና ሦስት ጎራ ተከፋፍሎ የመጣላት፤ የመደባደብና ፍርድ ቤት ድረስ የመካሰስ አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰፋ መጥቷል። መሠረታዊው የግጭቱ ምክንያት ሲገመገም በሁለት ነጥቦች ላይ ያጠነጥናል።
የሴራው መነሻ፤
1/ በተለያየ መንገድ ገንዘብ ለመዝረፍ እና
2/ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የማይነቃነቅ ባለሥልጣን ለመሆን ነው።
የሴራው ተሳታፊዎች፤
የተወሰኑ ምዕመናንና ምዕመናት ግን በሴራው ተዋናዮች ዓላማ ተጠልፈው በቅንነት ቤተ ክርስቲያናቸውን ከአደጋ ለመከላከል ሲሉ ወደጦርነቱ ይገባሉ። የፖለቲካ ክፍፍሉም የራሱ ሚና ይኖረዋል። የሁለት ጎራ ሴረኞች ሕዝቡን የሚቀሰቅሱት ለቤተክርስቲያን ያለነሱ የተሻለ አሳቢ የሌለ በማስመሰል እንጂ ሁለቱም ጎራዎች ድብቅ ዓላማቸው አንዱ አንዱን በመንቀል በቦታው ላይ ራሳቸውን ለመትከል ነው። ይህ ሲባል በቅን አስተሳሰብ የተነሱ የለም ማለት አይደለም። ነገር ግን ቅኖቹ «ከነገሩ ጦም እደሩ» ብለው ራሳቸውን ስለሚያገሉ በመፍትሄው ላይ ተሳታፊ አይደሉም። ሁከቱና ብጥብጡ በውጪው ዓለም ባሉ አብያተክርስቲያናት ማለትም በለንደን፤ በሮም፤ በደቡብ አፍሪካ፤ በሰሜን አሜሪካ እየከፋ ሄዷል።
የሴራው ተዋናዮች
የሴራው ተዋናዮች ዓይነት ደግሞ የተለያዩ ናቸው። በአብዛኛው በየአኅጉረ ስብከቱ የሴራው ባለቤቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሲሆኑ በየአድባራቱ ደግሞ አስተዳዳሪዎች፤ ቦርዶች፤ የሰበካ ጉባዔ አባላትና ማኅበረ ቅዱሳን ናቸው። ከታች የተመለከተው ቪዲዮ ጦርነቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲካሄድ ያሳያል።
«ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ» ገላ 5፤15