Thursday, April 14, 2016

ውስጤ መኖር ያለበት ቃና ቲቪ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ነው!!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከወዳጅ ጓደኞቼ ጋር በተገናኘን ቁጥር የመወያያ አጀንዳችን የሆነው ጉዳይ የዛሬውን ፅሁፍ እንድፅፍ አስገደደኝ፡፡ ዋና መቀመጫውን በዱባይ አድርጎ በቅርብ ጊዜ በሀገራቸን ስርጭቱን የጀመረው ቃና ቴሌቪዥን በአማረኛ እየተረጎመ (dubbing) በሚያቀርባቸው የቱርክ፣ የጣሊያን፣ የህንድ፣ የጃፓን እና የመሳሰሉት ሀገሮች ተከታታይ ፊልሞቹ የበርካታ ሰወችን ቀልብ እንደገዛ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ በእጅጉ የሚገርመው ደግሞ በዙሪያየ ያሉና የማውቃቸው በርካታ ክርስቲያኖች ጭምር ለእነዚህ የባህር ማዶ ፊልሞች እጅ ሰጥተው በጉጉትና በከፍተኛ ናፍቆት ሲጠብቁ ማየት ነው፡፡ የቃና ቲቪ ፊልሞች የሚታዩበት ሰዓት ደግሞ ወላጆች ከስራ፣ ልጆች ከትምምርት ቤት፣ ወጣቶችም ከሚውሉበት ስፍራ በቤት በሚሰበሰቡበት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በሚያጠኑበት፣ በጋራ በሚፀልዩበት ሰዓት ነው፡፡ እውነትም በስጋ አይን ለተመለከታቸው ፊልሞቹ በከፍተኛ ሁኔታ የሰውን ቀልብ የመግዛት አቅም እንዲኖራቸው ሆነው ተሰርተዋል፡፡ አንደኛው ፊልም ሲያልቅ በቅፅበት ሌላው ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከምሽት 12፡00 ሰዓት የተቀመጠ ሰው እስከ ምሽት 4፡00 ሰዓት ሌላ ስራ ሳይሰራ ያለምንም እንቅስቃሴ ይቀመጥ ዘንድ ግድ ይለዋል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ልብ እንበል የተቀማነው ወትሮ ለፀሎትና ለእግዚአብሔር ቃል ጥናት በእጅጉ ይመቸን የነበረውን ሰዓት ነው፡፡ ከዛም ደክሞን እንተኛለን፡፡ እዚህ ጋር ግን እንደመንፈሳዊ ሰው ልንነቃ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ሰባት በየቀኑ ለየአንድ አንድ አዓት የሚታዩ መሳጭ የባህር ማዶ ፊልሞች እቤታችን ድረስ መጥተው በራሳችን ቋንቋ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ቀድሞ ለጌታ የምንሰጠውን ሰዓት እየተውን፣ በፀሎት የምናሳልፈውን ጊዜ እየሸረሸርን ከክርስትና በእጅጉ የራቁ ሐገሮች ሰርተው በሚልኩልን ነገር ስንጠመድ የእነሱን ባዕድ፣ አምልኮ ኢ-ክርስትናዊ ነገሮች በሙሉ ወደ ውስጣችን እየሰገሰግን ነው፡፡ ልጆቻችንም ከክርስትና በእጅጉ ያፈነገጠ ነገር በየቀኑ እየተመለከቱ እንዲያድጉ እየተፈረደባቸው ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን በቆላስይስ 2፥8 ላይ ‹‹ እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ›› ብሎ በዓለማዊ ነገር እንዳንጠመድ ያስጠነቅቀናል፡፡ ኢየሱስም በማርቆስ ወንጌል 4፥24 ‹‹ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ›› ብሎ ከምንሰማውና ከምናየው እንድንጠበቅ ያዘናል፡፡ ዓለማችን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ስለመጨረሻው ዘመን የተናገራቸውን የዘመን መጨረሻ ምልክቶች አንድ በአንድ አስተናግዳ ወደ ማገባደደዱ ትገኛለች፡፡ ብዙ ነገሮች ሆነዋል ብዙ ነገሮች ተፈፅመዋል፡፡ ባጠቃላይ ሰይጣን ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው አውቆ ከመቸውም ጊዜ በላይ በኃይለኛ ቁጣ እየተጋ ያለበት ዘመን ነው፡፡ ዲያብሎስ በዚህ ዘመን በተለይም ወጣቱን ክፍል ከቤተክርስቲያን ለማራቅ ወደ እግዚአብሔር ቃል ትኩረት እንዳያደርግ ከሚጠቀምባቸው ዋና ነገሮች መሀል የፊልምና የሙዚቃው ኢንደስትሪ እጅግ ወሳኙን ድርሻ ይዟል፡፡በዘመናችን የሚሰሩ ፊልሞች በአብዛኞቹ ሰወችን ለዓለማዊ ምኞትና ለርኩሰት አብዝተው የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች እንንቃ። ሰይጣን በረቀቀ መንገድ በእኛ ላይ እንዲሰለጥን እድል አንስጠው፤ የቱርክና የህንድ ፊልሞችን እያሳየ ከእግዚአብሔር መንግስት የሚለየን ጣቢያ ውስጣችን "ቃና ውስጤ ነው" እያልን ውስጣችን ሊሆንብን አይገባም፡፡ ምክንያቱም እኛ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነን፡፡ ውስጣችን እሱ ብቻ ነው መኖር ያለበት። ብናምንም ባናምንም ዘመኑ የመጨረሻ ነው፡፡ ያኛው መንግስት እኛን በመዝናኛ ነገር ጠምዶ ከጌታ መንግስት ሊለየን እየተጋ ነው። እኛ ታዲያ ነቅተን ብዙ ምርኮ ልንበዘበዝ ሲገባን በወጥመዱ ከገባንለት እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ ስለዚህም እንንቃ በኢንተርቴመንት ስም ውድ ጊዜያችንን እንዳናስበላ፤ ይልቀንስ የእግዚአብሔርን ዓለምን በልጁ የመጠቅለል አላማ ለማሳካት አብሮ ሰራተኞች እንሁን!ስለወንጌል ግድ ይበለን፡፡
እኛ "መንፈስ ቅዱስ ውስጣችን ነው!"