Saturday, March 29, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን የሚፈርሰው በራሱ ተግባር ነው፤ ኢሕአዴግ ላለፉት 22 ዓመታት መቼ ነካው?



ይህ ህንጻ የማነው? የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን? የመንበረ ፓትርያርክ? የኢንቨስተር? የነጋዴ? የአስመጪና ላኪ?

የሀገሬ ሰው «ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል» ይላል። ይህ አባባል ለሰሞነኛው የማኅበረ ቅዱሳን የጅቡ በላኝ ጩኸት ይስማማል። ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ነው ሲል በየግል ጋዜጣው ማስወራቱ 22 ዓመታት ኢህአዴግ በሚመራት ሀገር ውስጥ ያልነበረ ይመስላል። ሲነግድ፤ ሲያስነግድ፤ ሲሸጥ ሲለውጥ፤ከግብርና ታክስ ተከልሎ በሚሊዮኖች ብር ህንጻ ሲገነባ በሀገሪቱ ኢህአዴግ ያላየው ወይም የማያውቀው ይመስላል። ኢህአዴግ ማኅበረ ቅዱሳንን በአስማት ይሁን በምትሃት እስከዛሬ ሳያየው ቆይቶ አሁን ለማየት ዓይኑን ሲከፍት ማኅበረ ቅዱሳንን አገኘውና ሊበላው ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ኢህአዴግ ሊያጠፋኝ ለምን ፈለገ ሲል ለመጠየቅ የተገደደ ይመስላል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለው ተግባሬ ከማኅበረ ካህናቱ ጋር አጋጨኝ፤ በማያገባኝ አስተዳደር ውስጥ እጄን ሳስገባ ተገኘሁ እንዳይል ከመሬት ተነስቶ ኢህአዴግ ሊውጠኝ ነው ወደሚል ቅስቀሳ መግባቱን  ከመምረጡ በስተቀር በምድር ላይ ያለው እውነታ ግን የምርጫ ዘጠና ሰባት ውጤትና ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ስንቱን ፓርቲና የተቃዋሚ መሪዎች እየደፈጠጠ ሲያልፍ ማኅበረ ቅዱሳን ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታዛ ተጠልሎ አልፏል። ኢህአዴግ ቢያጠፋው ኖሮ ያኔ ባጠፋው ነበር።
ከዚህ በፊት ማኅበሩ እንደጥራጊ አውጥቶ የጣለው ዳንኤል ክብረት ይህን ኢህአዴግ ሊበላኝ ነው የሚለውን የማኅበረ ቅዱሳንን ዘፈን እንዲህ ሲል በደጀሰላም ብሎግ ላይ አውጥቶ ነበር።
«እኔ እንደምገምተው የማኅበሩ አባላት መንግሥትን እንዲፈሩ እና እንዲጠሉ የሚፈልጉ አካላት በአመራሩ ውስጥ ሳይኖሩ አይ ቀርም፡፡ ምንጊዜም አንዳች ከባድ ነገር ሲነሣ መንግሥት እንዲህ ብሎናል፣ በዚህ ስብሰባው እንዲህ ብሏል፣ ሊዘጋን ነው፣ ሊያስረን ነው፣ ሊጨርሰን ነው ከማለት ያለፈ አንድም ቀን በጎ ነገር ስለ መንግሥት የማያነሡ አካላት አሉ»
 ስለዚህ ከዚህ አባባል ተነስተን ልንል የምንችለው ነገር ይህ መንግሥት ሊበላን ነው የሚለው ዜማ እንደስልት የተያዘና መንግሥት በአባላቱ ዘንድ እንዲጠላ የተዘየደ መሆኑ ነው። ከዚያም ባሻገር መሰሪ ስራውን ለመደበቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ለመሳል የታቀደ ጥበብ ሲሆን ጻድቁ ማኅበረ ቅዱሳንን ኢህአዴግ ሊያጠፋው ስለሆነ ኦርቶዶክሳውያን የሆናችሁ ሁሉ የዚህን መንግሥት መሠሪነት ተመልከቱ ብሎ ክፉ ስዕል ለመስጠት የተፈለገ ብልጠት ነው።
እውነቱ ግን ማኅበረ ቅዱሳን ነጋዴ ድርጅት መሆኑ ማንም ያውቃል። የግል ይሁን የአክሲዮን ማኅበር መሆኑ ያልታወቀና የራሱን ሀብት የፈጠረ ተቋም ስለመሆኑም ስራው ምስክር ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከንግድ ተቋማቱና ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮቹ ባሻገር የራሱ የሆኑ አባላት ያሉትና የአባልነት መዋጮ የሚሰበስብ ድርጅት ነው። ከዋናው ማዕከል ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁመት የራሱ የሆነ መዋቅርና  ራሱን የቻለ አደረጃጀት ያለው ነገር ግን አደረጃጀቱ በየትኛው የሀገሪቱ  የአደረጃጀት ፈቃድ ላይ እንደቆመ ያልታወቀ መሆኑም እርግጥ ነው። ይህንን የራሱ ተቋማዊ ኅልውና ያለውን ማኅበር በሀብቱ፤ በንግድ ተቋማቱ፤ በመዋቅራዊ አካላቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቆጣጠርና የማዘዝ ምንም ሥልጣን የላትም።  በአንጻሩም ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስር ተሸፋፍኖ እንደመጠለሉ መጠን ቤተ ክርስቲያኒቱ በማኅበሩ ላይ የመቆጣጠርና የማዘዝ ሥልጣን እንዳላት ግምት ያለው በመሆኑ መንግሥት ይህን ድርጅት ነክቶት አያውቅም። ስለዚህ ይህንን ማኅበር ቤተ ክርስቲያኒቱም፤ መንግሥትም ሳይመለከቱት ከሁለት ወገን ቁጥጥር ነጻ ሆኖ 22 ዓመት ዘልቋል።
 «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንዲሉ ሆኖ ማኅበሩን ማነህ? ምንድነህ? የት ነህ? ምን አለህ? ምን አገባህ? የሚሉ ካህናትና የአመራር አካላት ተባብረው በመነሳት መጠየቅ ሲጀምሩ ጥቂት ሟሳኞችና አሟሳኞች ወደሚል ሃሳብ ለመውረድ ተገዷል።  በምንም ደረጃ ያሉ ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳንን መክሰስ መቻላቸው የማኅበሩን ማንነት ማሳያው ተግባሩ እንጂ ክሱ አይደለም።  እየተከሰሰ ያለው ማኅበር በተግባሩ ያልታወቀ ማኅበር ባለመሆኑ በሟሳኞችና አሟሳኞች የቃላት ጫወታ እየፈጸመ የቆየውን ሸፍጥ ሸፍኖ ማስቀረት አይቻልም።
ማኅበረ ቅዱሳን በተግባር በሌለው ሥልጣንና መብት መናፍቃን ናቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን በራሱ ጥቁር መዝገብ አስፍሮ አስደብድቧል፤ ሰልሏል፤ ስም አጥፍቷል፤ አስፈራርቷል፤ እንዲሰደዱ አድርጓል። ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያኒቱ ስም መጽሔትና መጻሕፍትን፤ ካሴትና ቪዲዮ፤ አልባሳትና ንዋየ ቅድሳትን ከታክስና ከቀረጥ ነጻ ሆኖ ነግዷል። የማኅበረ ቅዱሳን አቋም የሚቃወሙ ሁሉ ጠላቶቹ ናቸው። የሚደግፉት ደግሞ ጳጳሳቱ ሳይቀሩ ወንጀል ቢኖርባቸው እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ታማኝ አገልጋይ ተደርገው ዜና ይሰራላቸዋል፤ ሙገሳ ይሰጣቸዋል። አባ እስጢፋኖስን ማንሳት ይቻላል። ጠላቶቼ ከሚላቸውና ስማቸውን ሌሊትና ቀን ሲያጠፋቸው ከቆዩት ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ደግሞ የጥላቻ የአፍ መፍቻው ናቸው። ሌሎቹም ፈርተው አንገታቸውን ደፍተውለታል። የተገዳደረውን አንገት ያስደፋል፤ አለያም ቀና ካለ አንገቱን ይሰብራል።  ሌላው ቀርቶ ሲያመሰግናቸው የነበሩትን አዲሱን ፓትርያርክ ጠላቶቼ የሚላቸውን ሰዎች ሲቀጣ በቆየበት መልኩ በስም ማጥፋት ቅጣት ናዳውን እያወረደባቸው ይገኛል። ለራሱ ኅልውና ብቻ የሚጨነቅ፤ ካልመሰለው ደግሞ ሲያወድሳቸው ለነበሩት ሳይቀር ግድ የሌለው ማኅበር ስለመሆኑ ከድርጊቱ ተነስቶ መናገር ይቻላል።  ወትሮውንም ሸፋጭ ነጋዴ ገንዘቡን እንጂ ወዳጅና እውነት በእሱ ዘንድ ዋጋ የሌላቸው ስለሆኑ የሚያስበው ጊዜያዊ ትርፉን ብቻ ነው። በዚህ ዙሪያ ማኅበሩ አሸንቅጥሮ የጣለውና ለተቀበለው የእጅ መንሻ በውጪ እንዳለ የሚለፈልፈው ዳንኤል ክብረት ማኅበሩ ስለግለሰቦችና ስለቤተ ክርስቲያኒቱ ደንታ ቢስ እንደሆነ ያጋለጠው እንዲህ ሲል ነበር።
«ዲያቆን በጋሻው ማስተማር የጀመረው መቼ ነው? ማኅበሩ በነዲያቆን በጋሻው ላይ ሃሳብ ዛሬ መሠንዘር ለምን ጀመረ? በጋሻው ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው ብሎ ስላሰበ አይደለም፡፡ በጋሻው ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ስለ ተናገረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ምንም ያልተናገረው ማኅበር ስሙ ሲነሣ ቤተ ክርስቲያን ተነካች ብሎ ተነሣ፡፡ ማኅበሩ አቡነ ጳውሎስን በተመለከተ የተለየ አቋም መያዝ የጀመረው መቼ ነው? «እርሳቸው ማኅበሩን ሊያፈርሱ ነው» ብሎ መሥጋት ከጀመረ በኋላ፡፡ አባ ሠረቀንም ቢሆ ንኮ ዛሬ ዛሬ በእምነት ችግር ይከሳቸዋል እንጂ፣ ከእርሳቸው ጋር ያለው ዋናው ችግሩ ማኅበሩ መነካቱ ነው፡፡ አባ ሠረቀ ማኅበረ ቅዱሳንን ሳይነኩ የፈለጉትን ቢሆኑ ኖሮ አይናገራቸውም ነበር፡፡ ባለፈው ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ችግር ሲፈጠር፣ ዝምታን መርጦ የነበረው አመራር የመንግሥት አካላት ከቤተ ክህነቱ ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ስለ ማኅበሩ ሲያወያዩት ግን አገር ይያዝልኝ አለ፡፡ የአዋሳ ምእመናንን ችግር በዝምታ ያለፈው አመራር አባ ሠረቀ አንዳች ነገር ተናገሩ ብሎ ድምፁን አሰምቶ ተናገረ፡፡ እነዚህ እና መሰል ሁኔታዎች አመራሩ የሚቆረቁረው ማኅበሩ ሲነካ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትነካ አለመሆኑን ያመለክታሉ» ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን ከራሱ በላይ ማንንም እንደማይወድ እርግጥ ነው።
ማኅበረ ቅዱሳን በፖለቲካው ዙሪያ ከምርጫ 97 በፊትም ሆነ በኋላ ስላለው ሁኔታ መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው ይሰማል። በዚህ ዙሪያ መንግሥት ያለውን መረጃ እስኪያወጣ ድረስ የምንለው ነገር የለም። ነገር ግን ማኅበሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያምሳት መቆየቱን፤ እጁን እያስገባ ሲኖዶሱን ሳይቀር እንደሚጠመዝዝ እናውቃለን። ማኅበሩ ደፋርና የልብ ልብ የተሰማው አንዳንድ የሲኖዶስ አባላት ተጠግቶ የጉባዔ ሃሳብ በራሱ መንገድ እስከመጠምዘዝ የመድረሱን አቅም እየለካ በመሄዱ ነው። ዛሬ ላይ ያ ነገር የለም። ፓትርያርክ ማትያስ ለዚህ የማኅበሩ ሃሳብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ከኢህአዴግ ጋር ተመሳጥረው ሊያጠፉኝ ነው እያለ ስም ወደማጥፋት ወርዷል። በተቃራኒው ደግሞ ማንም እንደማያጠፋው በሚገልጽ ጀብደኝነቱ ፓትርያርክ ጳውሎስም እንደዚሁ ሊያጠፉኝ ሞክረው እንደማያዋጣቸው አውቀው አጃቸውን ከእኔ ላይ ለማንሳት ተገደዋል በማለት ለፓትርያርክ ማትያስ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ እየሰራ ይገኛል። እጅዎን ከእኔ ላይ የማንሳትን ጉዳይ ችላ ሳይሉ ከቀድሞው ፓትርያርክ ትምህርት ውሰዱ በማለት ማሳሰቢያ እየሰጠ መሆኑ ነው። የሚፈራው ከተገኘ ጥሩ ጀብደኝነት ነው፤ ነገር ግን ባለቀ ጊዜ ማላዘን ዋጋ የለውም። ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያኒቱ ስንት ችግር ባለባት ሰዓት ራሱ ችግር ፈጣሪ ሆኖ ካለቦታው የተገኘ ማኅበር ስለሆነ ተገቢ ቦታውን መያዝ ካለበት ሰዓቱ አሁን ነው። ማኅበረ ካህናቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር አባላት ጠንክሮ መታገል የሚገባችሁ ወቅት ቢኖር ዛሬ ነው። ማኅበሩ ቁጭ ብሎ አዋጭ የሆነውን መንገድ መቅረጽ ካለበት ቶሎ ብሎ ይህንኑ እንዲፈጽም ምክር እንለግሰዋለን። የአክሲዮን ማኅበር፤ የሃይማኖት ተቋም፤ በጎ አድራጊ ድርጅት ወይም የተሻለ ነው ብሎ የደረሰበትን ውሳኔ ወደተግባር መቀየር ካለበት ቀኑ ሳይመሽ በብርሃኑ ይሆን ዘንድ ልናሳስበው እንወዳለን። ሲሆን ዘንድሮ፤ ካልሆነም በቀጣዩ ዓመት፤ ቢረዝም፤ ቢረዝም አንድ ቀን ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጉያ እንደመዥገር የተጣበቀበት ቀን እንደሚያበቃ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ማኅበሩና ተግባሩ፤ ካህናቱና አስተዳደሩ መቼም ቢሆን አሁን ባለው መንገድ አብረው መጓዝ አይችሉምና ነው።  ከዚህ ሁሉ ፓትርያርኩም፤ ካህናቱም፤ አመራሮችም፤ መንግሥትም ይህንን ማኅበር ቦታ የማስያዙን ጉዳይ ችላ ሊሉት አይገባም። ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖር ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ ማኅበረ ቅዱሳን ሳይኖርም ትኖራለች!!!  «ማኅበረ ቅዱሳን ከሌለ ቤተ ክርስቲያን ትጠፋለች» የሚለው ራሱ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ነው።